Saturday, 09 November 2013 10:14

ከዩኒቨርስቲው የ200ሺ ብር እቃ ወስደዋል የተባሉ ተከሰሱ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

                ከ10 ዓመት በላይ ስለሚያስቀጣ ዋስትና ተከልክለዋል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኤሌክትሪካል ዲፓርትመንት ፕሮጀክት መስሪያ ክፍል ውስጥ ከ199ሺ ብር በላይ የሚያወጡ የኮምፒውተር የውስጥ አካላትን ፈታተው በመመሳጠር ወስደዋል የተባሉት የኢንስቲትዩቱ ሶስት ሠራተኞች ሰሞኑን ክስ ተመሰረተባቸው፡፡ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቱ የንብረት እና ጠቅላላ አገልግሎት ሃላፊ አቶ መሰለ ጥላሁን፣ የጥበቃ ክፍል ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ገ/ማርያም እና የኮምፒውተር ጥገና ባለሙያው አቶ ብስራት አበበ፤ የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት በማሰብ በኤሌክትሪካል ዲፓርትመንቱ የፕሮጀክት መስሪያ ክፍል ውስጥ ከተቀመጡ 47 ኤችፒ ኮምፒውተሮች መካከል ከሃያ ሰባቱ ውስጥ የተለያየ ዋጋ ያላቸውን እቃዎች አውጥተው ወስደዋል በሚል ነው የተከሰሱት፡፡

ከመስከረም ወር ጀምሮ እስከ የካቲት19/2004 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ 1ኛ ተከሣሽ አቶ መሠለ ጥላሁን የ5 ኪሎ ካምፓስ የንብረት አስተዳደር እና ጠቅላላ አገልግሎት ሃላፊ ሆኖ ሲሰራ በእጁ የገባውን የኮምፒውተር ክፍል ቁልፍ ለጥበቃ ክፍል ሃላፊው ለአቶ ተስፋዬ ገ/ማርያም በመስጠት፣ እንዲሁም አቶ ተስፋዬ ለኮምፒውተር ጥገና ባለሙያው አቶ ብስራት አበበ ቁልፉን በማስተላለፍ እቃዎቹን እንዲሠረቁ አመቻችተዋል ይላል - የአቃቤ ህግ የክስ ዝርዝር፡፡ የኮምፒውተር ባለሙያው አቶ ብስራት እቃዎቹን ወስዶ ሲወጣ የጥበቃ ሃላፊው እንዳይፈተሽ ማድረጋቸውም በክሱ ላይ ተጠቅሷል፡፡

በዚህ መሠረት ከተፈቱት 27 ኮምፒውተሮች ውስጥ በጠቅላላው 9ሺ ብር ዋጋ ያላቸው 3 ማዘር ቦርድ ፤ ከ27 ኮምፒውተሮች በጠቅላላው 54ሺ ብር የሚያወጡ ማይክሮ ፕሮሰሰር ፤ ከ43 ሺ ብር በላይ የሚያወጡ የ27 ኮምፒውተሮች ሚሞሪ ካርዶች፣ ከ40ሺ ብር በላይ የሚያወጡ የ27 ኮምፒውተሮች ግራፊክ ካርዶች እንዲሁም ከሁለት ኮምፒውተሮች በጠቅላላው 1200 ብር የሚያወጡ ቪ ጂ አይ ካርዶች ፤በአጠቃላይ ከ199ሺህ ብር በላይ የሚገመት ንብረት በመውሰዳቸው ሁሉም በሙሉ ተሣታፊነት በፈፀሙት በስራ ላይ የመውሰድ እና የመሰወር የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡

ከትናንት በስቲያ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ተገኝተው ክሣቸውን በንባብ የሰሙት ተከሣሾቹ፤ የዋስትና ጥያቄ ያቀረቡ ቢሆንም አቃቤ ህግ የጠቀስኩባቸው የወንጀል አንቀጽ ከ10 አመት በላይ የሚያስቀጣ ነው በማለቱ፣ ፍ/ቤቱ የዋስትና ጥያቄያቸውን ውድቅ በማድረግ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ትዕዛዝ ሰጥቷል። የጉዳዩን ቀጣይ ሂደት ለማየትም ፍ/ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Read 2510 times