Saturday, 09 November 2013 10:06

ሰማያዊ ፓርቲ የስደተኛ ዜጐች እንግልት እንዲቆም ጠየቀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(8 votes)

                 ሰማያዊ ፓርቲ አረብ አገር በሚገኙ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለው እንግልትና ስቃይ በአስቸኳይ እንዲቆም ጠየቀ፡፡ ፓርቲው ትላንትና ረፋድ ላይ በጽ/ቤቱ “በመንግስት ቸልተኝነት በስደት ላይ ባሉ ዜጐች እየደረሰ ያለው ግፍና መከራ ይቁም” በሚል መርህ በሰጠው መግለጫ እንዳብራራው፤ ዜጐች በኢህአዴግ ዘመን በሚደርሱባቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጫናዎች በህጋዊና ህጋዊ ባልሆኑ መንገዶች ከሀገራቸው መሰደዳቸውንና ለእንግልት፣ ለሞትና ለስቃይ መዳረጋቸውን ጠቁሟል፡፡

“ፓርቲያችን የዜጐች ስደትና እንግልት ያሳስበዋል፤ መንግስት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥም ድምፃችንን እናሰማለን” ብለዋል፤ የፓርቲው አመራሮች፡፡ የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፣ የፓርቲው የወጣቶች ጉዳይ ሃላፊ ወጣት ዮናታን ተስፋዬ እና የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ወጣት ብርሃኑ ተክለ ያሬድ በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ዜጐች የሚሰደዱት በአገሪቱ ላይ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍትህ ባለመኖሩ ነው ያሉ ሲሆን በነዚህ ጫናዎች ምክንያት ዜጐች በየበረሃው በኮንቴይነር ታሽገው እየሞቱ፣ በባዕዳን ኩላሊታቸው እየተሸጠ፣ በባህር ላይ ሲያቋርጡ በባህር አውሬዎች እየተበሉ መሆኑን አብራርተዋል።

በተለይም ሰሞኑን በሳኡዲ አረቢያ የሚገኙ ዜጐች እየደረሰባቸው ያለውን አስከፊ እንግልትና ስቃይ አጥብቀው እንደሚያወግዙ ተናግረዋል፡፡ “ዜጐች በባዕድ አገር በሚደርስባቸው በደል የኢህአዴግ መንግስት ከዜጐች ጐን በመቆም ስቃያቸውና በደላቸው እንዲቆም በመጠየቅ አጋር መሆን ሲገባው፣ በአገር ውስጥ ባሉ ሚዲያዎች “ሀገሪቱ በልማት እያደገች ባለችበትና ስራአጥነት እየተቀረፈ ባለበት ወቅት ዜጐች ሀገር ለቀው መሰደዳቸው ስህተት ነው” በሚል በዜጐች ላይ ማላገጡን ያቁም ሲል ፓርቲው አሳስቧል፡፡ “በተለይ በሳውዲ አረቢያ በዜጐች ላይ እየደረሰ ስላለው እንግልት፣ የአለም ትልልቅ ሚዲያዎች አጀንዳ አድርገው እየተነጋገሩበት፣ የኢትዮጵያ መንግስት ቸልታ “ይህቺ አገር መንግስት የላትም ወይ’ ያስብላል” ያሉት ኢ/ር ይልቃል የኢትዮጵያ ሚዲያስ ይህን አጉልቶ ካላወጣና ከዜጐቹ ጐን ካልቆመ ፋይዳው ምንድን ነው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የስዊድን ጋዜጠኞች በህገ ወጥ መንገድ አገር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ እና ሲታሰሩ የአገራቸው መንግስት ጥፋተኛ ናቸው ብሎ ችላ ሳይል ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ተደራድሮ በአጭር ጊዜ እንዲፈቱ ማድረጉንና አገራቸውም ሲገቡ የጀግና አቀባበል እንደተደረገላቸው የገለፁት ሊቀመንበሩ የኢትዮጵያ መንግስት ዜጐቹ በግልጽ እየተሰደዱ እየተንገላቱና እየሞቱ እጁን አጣጥፎ መቀመጡ የሚያስተቻቸው እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ወጣት ብርሃኑ በበኩሉ፤ በእድሜና በእውቀት ያልበሰሉ ህፃናት በህጋዊና ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ከአገር እየወጡ ለስቃይ ሲዳረጉ፣ በኤጀንሲዎች እና በህገወጥ ደላሎች ላይ ጥብቅ እርምጃ መውሰድና ዜጐቹን በተለያየ መንገድ ማስገንዘብ ሲገባው፣ ጭራሽ በየክልላቸው ፓስፖርት እንዲያገኙ እያደረገ ማበረታታቱ እንደሚያሳዝነው ተናግሯል፡፡ “ኤጀንሲዎችን ማገድና ፓስፖርትና ቪዛ መከልከል አሁንም ትክክለኛ መፍትሔ አይደለም” ያለው ብርሃኑ፤ መንግስት ፖሊሲዎቹን ማሻሻልና ማስተካከል እንዳለበት አሳስቧል፡፡

የፓርቲው የወጣቶች ጉዳይ ሃላፊ ወጣት ዮናታን በበኩሉ፤ “ኢህአዴግ ለወጣቶች ስራ የሚሰጠውና የሚያደራጀው አባል እስከሆነ ድረስ ብቻ ነው” ካለ በኋላ፤ “አብረን ከዩኒቨርሲቲ የወጣን ሆነን አባል ስለሆኑ ብቻ ትልልቅ ስራና ሃላፊነት ላይ የተቀመጡ ወጣቶች አሉ፡፡ እነሱ በመኪና እኛ በእግር እንተላለፋለን” ሲል አማሯል፡፡ “ኢትዮጵያ ውስጥ ልማትና እድገት ካለ ዜጐች ለቅንጦት አይሰደዱም” ያሉት የፓርቲው አመራሮች፤ በመንግስት ቸልተኝነት በኢትዮጵያ የስራ አጥ ቁጥር 40 በመቶ መድረሱን ገልፀዋል - አለም አቀፍ መረጃ መሆኑን በመጥቀስ፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ አገር ብድር ከ12 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን፣ የአገር ውስጥ የብድር መጠን 80 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ ባለፉት 10 ዓመታት ከኢትዮጵያ 11.7 ቢሊዮን ዶላር በህገወጥ መንገድ መውጣቱን እና መሰል መረጃዎችን የገለፁት አመራሮች፤ እነዚህ መረጃዎች የአለም ባንክና የአይኤምኤፍ መሆናቸውን ገልፀው፤ “ይህ ባለበት ስራ አጥነት ተቀርፏል፤ ልማት አለ የሚባለው በህዝብ ላይ ማሾፍ ነው” ብለዋል፡፡

ፓርቲው ባወጣው ባለአምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ፤ የዜጐችን ህይወት ለመታደግ መንግስት በአስቸኳይ ከሳኡዲ መንግስት ጋር እንዲነጋገር፣ የሳኡዲ አረቢያ መንግስት በዜጐች ላይ እያደረሰ ያለው በደል የሰብአዊ መብት ጥሰት በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲያቆም፣ ዜጐችን ለስደትና ለስቃይ የሚዳርጉ የችግሩ መንስኤዎች፣ ድርጅቶችና ግለሰቦች ለፍርድ እንዲቀርቡ እና ዜጐች የሚሰደዱበትን ምክንያት በጥልቅ በመመርመር አስከፊውን ስደት ለማቆም መንግስት የፖሊሲ ማሻሻያ እንዲያደርግ… የሚሉት ይገኙበታል፡፡ ፓርቲው በቀጣይነት ጥናቶችንና መረጃዎችን በማሰባሰብ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልፆ፤ ለዚህ ስኬት ህብረተሰቡ፣ የሲቪክ ተቋማት፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አለም አቀፉ ማህበረሰብ ከጐኑ እንዲቆሙ ጥሪ አስተላልፏል፡፡

Read 2495 times