Saturday, 02 November 2013 12:14

ናይጄርያ 2:1 ኢትዮጵያ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(6 votes)

የፍፃሜው ጦርነት ነው
የኢትዮጵያ የዓለም ዋንጫ ህልም አላበቃለትም፡፡ 15 ቀናቶች አሉ፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላ ዋልያዎቹ ክሮስ ሪቨር በተባለው የናይጄርያ ግዛት በምትገኘው ካላባር ከተማ ንስሮቹን በዩጄኡስዋኔ ስታድዬም ይገጥማሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አባላት ከሜዳቸው ውጭ ዓለም ዋንጫን ከናይጄርያ የመንጠቅ እድል አላቸው፡፡ የመልሱ ጨዋታ የሚጀመረው በናይጄርያ 2ለ1 መሪነት ነው፡፡ በማንኛውም ውጤት ማሸነፍ ወይም አቻ መለያየት እንዲሁም በ1 ጎል ልዩነት ብቻ መሸነፍ ናይጄርያን ለ5ኛው የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ያበቃታል፡፡ ኢትዮጵያም አንድ እድል አላት፡፡ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በውድድሩ የተካፈለች የምስራቅ አፍሪካ አገር ልትሆን ትችላለች፡፡ የወቅቱን የአፍሪካ ሻምፒዮን ጥሎ በማለፍ አስደናቂ ስኬት ተብሎም በ20ኛው የዓለም ዋንጫ ታሪክ በወርቃማ ቀለም የምትሰፍርበት ይሆናል፡፡ በሁለት ንፁህ ጎሎች ማሸነፍ 2ለ0፤ 3ለ1፤ ከዚያም በላይ ኢትዮጵያን ወደ ዓለም ዋንጫ ያሳልፋታል። በመልሱ ጨዋታ የአቻነትድርማም ያጋጥም ይሆናል፡፡ በመደበኛው ጨዋታ ክፍለ ጊዜ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 2ለ1 መለያየት ከቻለ ትንቅንቁ በ30 ደቂቃ ተጨማሪ ሰዓት ይቀጥላል፡፡ ከዚያም በመለያ ምቶች ጥሎ የሚያልፈው የሚለይ ይሆናል፡፡ ለዋልያዎቹ ምርጥ አጨዋወት ያለውን አድናቆትና ለኢትዮጵያ ስፖርት አፍቃሪ የሚሰጠውን ክብር በተደጋጋሚ በተናገራቸው አስተያየቶች የገለፀው አሰልጣኝ ስቴፈን ኬሺ በካላባር የሚደረገውን የመልስ ጨዋታ እንደ የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ እቆጥረዋለሁ ብሏል። በርግጥም የመልሱ ጨዋታ የወቅቱ የአፍሪካ ሻምፒዮን የሆነችው ናይጄርያ እና የተረሳችው የአፍሪካ እግር ኳስ መስራች ኢትዮጵያ የሚገናኙበት የፍፃሜ ጦርነት ነው፡፡

ከሜዳ ውጭ የደጋፊ ጫና
ባይኖር ጎልስ የታለ?
አንዳንድ የዋልያዎቹ አባላት ቡድናቸው ከሜዳ ውጭ ሲጫወት ብዙ ጫና እንደማይኖርበት በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡ ጫና የተባለው በአዲስ አበባ ስታድዬም በደጋፊ ፊት ሲጫወቱ በተመልካች የዝምታ ድባብ የሚፈጠረው ነው፡፡ በርግጥ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለይ በዓለም ዋንጫ ማጣርያው ከሜዳ ውጭ ጥሩ የሚባል ውጤት አስመዝግቧል፡፡ ከቅድመ ማጣርያው አንስቶ እስከ ጥሎ ማለፉ የመጀመርያ ጨዋታ 9 ጨዋታዎችን፤ አምስቱን በሜዳ አራቱን ከሜዳ ውጭ አደረገ፡፡ ከዘጠኙ ጨዋታዎች አምስቱን ሲያሸንፍ አራቱን በአዲስ አበባ ስታድዬም ነበር፡፡ ምንም እንኳን የጨዋታው ውጤት ቢሰረዝም በዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ቦትስዋናን በጋብሮኒ 2ለ1 ያሸነፈበት እና ለጥሎ ማለፍ ሲበቃ በኮንጎ ብራዛቪል መካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክን 2ለ1 የረታበት ነበር፡፡ ከሜዳ ውጭ በሁለት ጨዋታዎችም አቻ ተለያይቷል፡፡ በቅድመ ማጣርያው ከሶማሊያ ጋር በጅቡቲ 0ለ0 የተለያየበትና በምድብ የማጣርያው የመጀመርያ ጨዋታ ከደቡብአፍሪካ ጋር በሩስተንበርግ 1ለ1 የወጣበት ናቸው፡፡
በዓለም ዋንጫው 9 የማጣርያ ግጥሚያዎችን ዋልያዎቹ 14 ጐል አግብተዋል፡፡ 8 አስተናግደዋል፡፡ የዋልያዎቹ 14 ጎሎች 11 በሜዳቸው 3 ብቻ ከሜዳ ውጭ የተመዘገቡ ናቸው፡፡ ከስምንቱ የተጋጣሚ ቡድን ጎሎች 3 በአዲስ አበባ ስታድዬም መረቦች ሲያርፉ አምስቱ ከሜዳ ውጭ የተቆጠሩባቸው ናቸው፡፡ በሶከርዌይ አሃዛዊ ስሌት መሰረት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሜዳውም ሆነ ከሜዳውውጭ በአንድ ጨዋታ በአማካይ 1.58 ጐል የማግባት እድል ሲኖረው 0.89 ይገባበታል፡፡ በተለይ ከሜዳው ውጭ 1.25 ጎሎችን የማስተናገድ እጣ ያለው የዋልያዎቹ ስብስብ የማስቆጠር እድሉም ተመሳሳይ ነው፡፡ ግን በሰው አገር የግብ መረቡን ሳያስደፍር መቆየት የሚችለው እስከ 50ኛው ደቂቃ ነው፡፡ በዓለም ዋንጫው ጥሎ ማለፍ የመጀመሪያው ጨዋታ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምርጥ አቋም እንደነበረው በርካታ መረጃዎች ቢገልፁም የአጨራረስ ችግር እንደነበረበት እና ከ60 ደቂቃዎች በላይ ጠንክሮ እንደማይጫወት ያብራሩም ነበሩ፡፡ በአዲስ አበባ ስታድዬም በተደረገው የመጀመርያ ጨዋታ በኳስ ቁጥጥር ዋልያዎቹ 61 በመቶ አንዲሁም የአፍሪካ ሻምፒዮኖቹ 31 በመቶ ነበሩ፡፡ የማጥቃት ሙከራዎች 45 በኢትዮጵያ 34 በናይጄርያ፤የግብ ሙከራዎች በኢትዮጵያ 9 በናይጄርያ 12፤ ከጨዋታ ውጭ የሆኑ ኳሶች የኢትዮጵያ 1 የናይጄርያ 2፤ ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች የኢትዮጵያ 8 የናይጄርያ 4፤ የኮርና ምት 6 የኢትዮጵያ 3 የናይጄርያ፤ ፋውሎች 16 የኢትዮጵያ የናይጄርያ 6 እንዲሁም ቅጣት ምቶች የኢትዮጵያ 18 የናይጄርያ ነበር፡፡ እነዚህ አሃዛዊ ስሌቶችን ስንገነዘብ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሁለት ሳምንት በኋላ ከናይጄርያ ጋር በሚያደርገው ፍልሚያ በታሪክ ትልቁን ውጤት ለማስመዝገብ ከባድ ፈተና አለበት፡፡ ዋልያዎቹ በዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያዎች ያስመዘገቡትን ስኬት እጥፍ የሚጠየቁበት የፍፃሜ ፍልሚያቸው ነው፡፡

ለዋልያዎቹ ጉዞው ጨርቅ አልነበረም
ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫው ጉዞው ጨርቅ አልነበረም፡፡ በብዙ እንቅፋቶች የተደነቃቀፈ ነበር፡፡ ቅዠት የሞላው የዓለም ዋንጫ ህልም ሆኖ ቆይቷል፡፡ ቡድኑ በዚህ ጉዞው አሁን የመጨረሻውን ምዕራፍ ለመዝጋት በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡ ዋልያዎቹ በጉዟቸው እንቅፋቶች በዝተውባቸውም አላፈገፈጉም፡፡ በደረጃቸው እኩያነት ባይሆንላቸውም አልተንገታገቱም፡፡ በባለፈው ፌደሬሽን በ11ኛው ሰዓት የጠፋው ጥፋት የመጀመርያው እና አስደንጋጩ እንቅፋት ነበር፡፡ በወቅቱ በነበረው አስተዳደር ብሄራዊ ቡድኑ ባጋጠመው የሁለት የቢጫ ካርድ መርሳት ቅሌት ከዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ መግባት ወደ መውጣት ቅዠትን የፈጠረ ነበር፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ለዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ የመጀመርያ ጨዋታ የምድብ ማጣርያው ሳይጠናቀቅ አንድ ጨዋታ ቀደም ብሎ ያለፈበትን እድል ያበላሸ ፤ ዋልያዎቹ ለጨዋታ ጫና የዳረገና የስፖርት አፍቃሪውን ደስታ የበረዘ እንቅፋት ነበር፡፡ የፌደሬሽን ዝርክርክ አሰራር የዋልያዎቹን ግስጋሴ ቢያዘገየውም አልገታውም። ብሄራዊ ቡድኑ በዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ምድብ 1ን በመሪነት አጠናቀቀ፡፡ በጥሎ ማለፍ የመጨረሻ የማጣርያ ምእራፍ በማለፍ ከአፍሪካ 10 ምርጥ ብሄራዊ ቡድኖች አንዱ ሆነ። የዋልያዎቹ ስብስብ የተደለደለው ከወቅቱ የአፍሪካ ሻምፒዮን ናይጄርያ ጋር ነበር፡፡ ዋልያዎቹ ከናይጄርያ ጋር በሜዳቸው ከመጫወታቸው በፊትም መደነቃቀፋቸው አልቀረም፡፡ ከናይጄርያ ጋር በአዲስ አበባ ከተደረገው የመጀመርያው ጨዋታ 3 ቀናት ቀደም ብሎ አሁንም ፌደሬሽኑ ባልተጠበቀ ቅዠት ውስጥ ገባ። የኢትዮጵያን እግር ኳስ ፌደሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ ነበር፡፡ ለሚቀጥሉት 4 ዓመታት የሚመራውን አመራር ለመምራት ምርጫ ተካሄደ፡፡ የፌደሬሽን አመራር የመምረጡ ሂደት እጅግ አስፈላጊውን ትኩረት ዋልያዎቹን ያስነፈገ ጉባዔ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ይህም ብቻ አልነበረም፡፡ ጎን ለጎን ብሄራዊ ቡድኑ ከናይጄርያ ጋር ለሚደረገው ጨዋታ ከወር በላይ ያደረገው ዝግጅትም በማይጨበጡ የወዳጅነት ጨዋታ ወሬዎች ሲታወክ ሰነበተ፡፡ ዋልያዎቹ አቋምቸውን መፈተሻ ግጥሚያ ማግኘታቸው ፍሬከርስኪ የሞላው ነበር፡፡ ትኩረት ካስነፈገው የፌደሬሽን ጠቅላላ ጉባዔና የወዳጅነት ጨዋታ ማጣት በኋላ ዋልያዎቹ በአጠያያቂ የአካል ብቃት ከ2ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ ስታድዬም ከናይጄርያ ጋር ለተደረገው የመጀመርያ ጨዋታ ደረሱ፡፡ በዚህ ጨዋታም ሁሉ ነገር እድል ቢስ በተለያዩ ምክንያቶች መረበሻቸው አልቀረም፡፡ ጨዋታውን የሚመሩት ዳኞች የተመደቡ ካሜሮናውያን ነበሩ፡፡ ካሜሮናዊው ዳኛ እንደተፈራው ከምእራብ አፍሪካ ለተወከለችው ናይጄርያ ያደሉ መሰለባቸው፡፡ መላው ኢትዮጵያዊ የዓለም ዋንጫ ህልሙ መረብ ባልነኩ ሁለት ኳሶች ተቀዣበረ፡፡ ዋልያዎቹ በሜዳቸው እና በደጋፊያቸው ፊት የመጀመርያውን ሠዋታ በናይጄርያ 2ለ1 ተሸነፉ፡፡ ከዚሁ ትንቅንቅ በኋላ ወሳኙ የመልስ ጨዋታ 1ወር ይቀረው ነበር፡፡ አሁን ከ15 ቀናት በኋላ ናይጄርያ በካላባር የምታስተናግደው ይሆናል። ባለፈው ሁለት ሳምንት ዋልያዎቹ ዝግጅት ያደረጉት በተለያዩ ጉዳዮች ትኩረት አጥተው ነበር፡፡ ለመልሱ ጨዋታ የሚደረግ የነበረው ዝግጅት ከአጀማመሩ የሚያረካ አልነበረም፡፡ ከክለቦች የሊግ ውድድር ፕሮግራም በተናኘ የተፈጠረው እሰጥ አገባ እና ከወዳጅነት ጨዋታ መገኘት በተያያዘ የተፈጠሩ አጀንዳዎች የዓለም ዋንጫ ህልምን የሚያደበዝዙ ነበር፡፡ የወዳጅነት ጨዋታ ችግርም አሁንም በፌደሬሽኑ አልተቀረፈም፡፡ በመጀመርያ በአንድ ጋዜጠኛ ጥረት ከካሜሮን ጋርየወዳጅነት ጨዋታ ሊደረግ ስምምነት ተደረገ ተብሎ ተወራ እና ተግባራዊ ሳይሆን ቀረ፡፡ በዚያው ሰሞን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከቡርኪናፋሶ ጋር ከሜዳ ውጭ ጨዋታ ሊያደርግ ይችላል ተባለ፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ላይ ተገናኝተው ቡርኪናፋሶ 4ለ0 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፏ አለመዘንጋቱ ጥሩ አቋም መፈተሻ ይሆናል ተብሎ ተስፋ ተደረገ፡፡ እንደ ሱፐር ስፖርት ከገባ በኋላም ዋንጫው ጥሎ ማለፍ የአልጀሪያ 2ኛውን በሜዳው 3ለ2 ያሸነፈው የቡርኪናፋሶ ቡድን ከኢትዮጵያ ጋር ለሚያደርገው የወዳጅነት ጨዋታ ያሳየውን ፍላጐት ውሉን በማፍረስ ተወው፡፡ ሁለቱም የወዳጅነት ጨዋታዎች ቅዠት ሆነው ቀሩ፡፡
በመጨረሻም በዓለም ዋንጫ የምድባ ጣርያዎች በዲስፕሊን ችግር የተፈጠረው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ስብስብ መቃወስ ይነሳል፡፡ ቡድኑበየጨዋታው የቢጫ ካርድ ሰለባ የመሆን እድሉ 70 በመቶ ሲሆን ነው፡፡ እስካሁን 18 ቢጫ ካርድ ቅጣት አለበት፡፡

የአፍሪካ ሻምፒዮን ነን ማን ይገረስሰናል?
ናይጄርያ ውስጥ በዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ የመጀመርያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ያሳየችው የጨዋታ ብልጫ በካላባር በሚደረገው የመልሱ ጨዋታ መደገም የለበትም እየተባለ ነው፡፡ ለዓለም ዋንጫ የማለፍ እድልን በቀና ስሜት የሚጠባበቀው አሰልጣኝ ስቴፈን ኬሺ ናይጄርያ ካላባር ላይ ኢትዮጵያን ማሸነፍ እንደምትችል ሙሉ እምነቱን ሰሞኑን ገልጿል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ የናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን ለቻን ውድድር በሚያደርገው ዝግጅት እና ከኢትዮጵያ ጋር ለሚደረገው የዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ጨዋታ መሟሟቂያ እንዲሆነው በአቡጃ ብሄራዊ ስታድዬም የአገሪቱ ፕሪሚዬር ሊግ ክለብ ከሆነው ሎቢ ስታርስ ጋር በመጫወት 1ለ0 አሸንፏል፡፡ ባለፈው ሰኞ ደግሞ በአገርውስጥ ተጨዋቾች ብቻ የተዋቀረው የናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን ከዮርዳኖስ ጋር ከሜዳው ውጭ አማን ላይ ባደርገው የወዳጅነት ጨዋታ 1ለ0 ተረትቷል፡፡ ለናይጄርያ ክለቦች የሚሰለፉ ተጨዋቾች ብቻ የተሰባሰቡበት ቡድን በአቡጃ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ዝግጅት አድርጓል፡፡ ይህ ዝግጅት ከመላውአውሮፓ የሚሰባሰቡትን ከ18 በላይ ፕሮፌሽናሎችን በመቀላቀል ለዓለም ዋንጫና ከኢትዮጵያ ጋር ለሚደረገው የመልስ ጨዋታ ዋና የብሄራዊቡድን ተጨዋቾችን ለመምረጥ ያግዛል ተብሏል፡፡ በተለያዩ የአውሮፓ አገራት በሚገኙ ክለቦች ውስጥ በፕሮፌሽናልነት የሚጫወቱ የናይጄርያ ተጨዋቾችም ጥሩ አቋም በማሳየት ላይ ናቸው፡፡ ቪንሰንት ኢኒዬማ በፈረንሳዩ ክለብ ሊል በሊግ ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርበት ከ7 ጨዋታዎች በላይ አሳልፏል። በኢትዮጵያ ላይ ሁለት ጎሎችን ያገባው ኤምኒኬ ለቱርኩ ክለብ ፌነርባቼ የማሸነፊያ ጎሎች በማግባት የሊጉ መሪ አድርጎታል፡፡ ቪክተር ሞሰስ ወደ እንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ተመልሶ ለሊቨርፑል ሲጫወት ወደ ጥሩ ብቃቱ እንደተመለሰ አሳይቷል፡፡
አንዳንድ የናይጄርያ ሚዲያዎች በካላባር ከኢትዮጵያ ጋር ስለሚደረገው የመልስ ጨዋታ ከማውራት ይልቅ በ20ኛው የዓለም ዋንጫ አገሪቱ ይዛ ስለምትቀርባቸው 23 ተጨዋቾች አመራረጥ በሚያነሷቸው ሃሳቦች ተጠምደዋል። ብዙዎቹም አሰልጣኝ ስቴፈን ኬሺ አንዳንድ ወሳኝ ተጨዋቾችን ወደ ብሄራዊ ቡድን እንዲቀላቅል ግፊት እያደረጉ ናቸው፡፡ ወደ ብሄራዊ ቡድኑ እንዲጠሩ ዘመቻ ከሚደረግላቸው ተጨዋቾች መካከል ታዬ ቲያዎ፤ ቪክቶር አንቼቤ፤ ጆኤል ኦቢ፤ፒተር ኢዲምንዉጌ እና የቀድሞው አምበል ጆሴፍ ዮቦ ይጠቀሳሉ፡፡ በንስሮቹ ወቅታዊ የቡድን ስብስብ መጠናከር የልብ ልብ የተሰማው አሰልጣኙ ስቴፈን ኬሺ አዲስ ተጨዋች ወደ ቡድኑ ለመቀላቀል በሩ ክፍት እንደሆነ ሲገልፅ በጣም የላቀ ብቃት የሚኖረው ተጨዋች ካልመጣ በቀር አዲስ ምልመላ ለማካሄድ ሃሳብ የለኝም ብሏል፡፡
ናይጄርያ ለብራዚሉ የዓለም ዋንጫ በማለፍ በውድድሩ ታሪክ አምስተኛውን ተሳትፎ እንደምታሳካ በሰፊው እየተነገረላትም ነው፡፡ በርካታ የስፖርት ተንታኞች ብራዚል ላይ በሚደረገው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ናይጄርያ ስትሳተፍ ካሜሮን በ1990፤ ሴኔጋል በ2002 እንዲሁም ጋና በ2010 እኤአ ላይ ለሩብ ፍፃሜ ምዕራፍ በመብቃት ያገኙትን ስኬት የምትደግም የወቅቱ የአፍሪካ ሻምፒዮን መሆን አለባት እያሉ ናቸው፡፡ ናይጄርያ አስቀድሞ በተሳተፈችባቸው 4 የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ወደ ጥሎ ማለፍ ምእራፍ በ1994 እና 1998 እኤአ ላይ የገባችው ትልቁ ውጤቷ ሲሆን በሁለት የዓለም ዋንጫዎች በመጀመርያው ዙር ተሰናብታለች። በቢልቸርስፖርት በተሰራ ቅድመ ትንበያ ናይጄርያ ለ20ኛው የዓለም ዋንጫ ካለፈች በምድብ 1 ከብራዚል ደቡብ ኮርያ እና ፖርቱጋል ጋር እንደምትመደብ ሲገልፅ ሌላ ትንበያ ደግሞ በምድብ 3 ከቤልጅዬም፤ ሆንዱራስ እና ሆላንድ ጋር ልትደለደል እንደምትችል ገምቷል፡፡ የዋልያዎቹአፍሪካ ሻምፒዮንን በመገርሰስ ለዓለም ዋንጫ ካለፉ ግምቱ በተገላቢጦሽ ለእነሱ ነው፡፡

20ኛው የዓለም ዋንጫ ለምን ይለያል?
ብራዚል የምታስተናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ከ9 ወር ያነሰ እድሜ ቀርቶታል፡፡ ከ3 ሳምንት በብራዚል የምናያቸው 32 ብሄራዊ ቡድኖች ሙሉ ለሙሉ ተለይተው ይታወቃሉ፡፡ ከ15 ቀናት በኋላ የማጣርያው የመጨረሻ የጥሎ ማለፍ ምዕራፍ ነው፡፡ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከቅድመ ማጣሪያው ጀምሮ በ6 የፊፋ ኮንፌዴሬሽኖች የሚገኙ 207 አገሮች ተካፍለውበት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ የሚያበቃው ከ816 ግጥሚያዎች በኋላ ነው፡፡ እስካሁን 21 ብሄራዊ ቡድኖች ማለፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡ የቀረው የተሳትፎ ኮታ የ11 ብሄራዊ ቡድኖች በማጣርያው የቀሩት የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች 17 ናቸው። አምስቱ ጨዋታዎች ከአፍሪካ አህጉር የሚጠበቁ ናቸው። ቀሪዎቹ 12 ጨዋታዎች በተለያዩ አህጉራት ይደረጋሉ። በእነዚህ ጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች አራት ብሄራዊ ቡድኖች በአውሮፓ በሚደረጉ ሁለት የደርሶ መልስ ጨዋታዎች የሚወሰኑ ሲሆን ሁለት ብሄራዊ በድኖች ደግሞ ከኤሽና ደቡብ አሜሪካ እንዲሁም ከመካከለኛው አሜሪካ ኮንፌደሬሽኖች ተወካዮች ይታወቃሉ፡፡ አንድ ማንኛውም ብሄራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ከሚሳተፉ 32 አገራት አንዱ በመሆኑ ብቻ ከፊፋ እስከ 14 ሚሊዮን ዶላር ይታሰብለታል፡፡ በብሄራዊ ቡድን የሚሰለፉ የዓለም ዋንጫ ተጨዋቾች እስከ 30 ፕርሰንት ድርሻ ለእያንዳንዳቸው ያገኙበታል፡፡ በዓለም አቀፍ የእግር ኳስ መልማዮች በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት የሚያገኙበትም መድረክ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ግን ቡድኑ በስፖንሰርሺፕ፤ በተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ገቢ ሊያገኝበት ይቻለዋል፡፡ ለስፔን እና እንግሊዝ ከ50 እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር ሊያስገኝ የሚችለው የዓለም ዋንጫ እንደ ኢትዮጵያ ላሉት አገራት ቢያንስ ግማሹን ሊያስገኝ ይችላል፡፡
መላው የዓለምን ህዝብ መነጋገሪያው በማድረግ ዓለም ዋንጫን የሚያህል የለም፡፡ ማንኛውም አገር በእኩልነት የሚሳተፍበት ታላቅ የስፖርት መድረክም ነው፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ መሳተፍ ለማንኛውም አገር ትልቅ የታሪክ ምእራፍ ከመሆኑም በላይ፤ የእድገት መገለጫ የሚሆንም ስኬት ነው፡፡ እያንዳንዱ የዓለም ዋንጫ ጨዋታ በአማካይ በስታድዬም እስከ40ሺ እንዲሁም እስከ 15 ሚሊዮን የቲቪ ተመልካች ይኖረዋል፡፡ ዓለም ዋንጫ በከፍተኛወጭ የሚዘጋጅ የውድድር መድረክምነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ 19ኛውን የዓለም ዋንጫ ለማስተናገድ ወጭ ያደረገችው 2.7 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ በ20ኛው ዓለም ዋንጫ የብራዚል ወጪ ደግሞ እስከ 14 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል እየተባለ ነው። በ2018 እኤአ ራሽያ 21ኛውን የዓለም ዋንጫ ለማዘጋጀት እስከ 50 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ማድረግ ሲጠበቅባት በ2022 ኤአ ደግሞ ኳታር ለ22ኛው የዓለም ዋንጫ መስተንግዶ ወጭዋ እስከ 200 ቢሊዮን ይደርሳል፡፡
በ20ኛው ዓለም ዋንጫ ብራዚል ላይ የምንጊዜም ምርጥ እግር ኳስ እንደሚታይ የተገመተው ያለምክንያት አይደለም። በ20ኛው የዓለም ዋንጫ በፊፋ ለሽልማት ከቀረበው ዝርዝር የሚገኘውን ገንዘብ ማስላት ነው፡፡ በመጀመርያ ከ32 አገራት አንዱ በመሆን ብቻ 1 ሚሊዮን ዶላር ይገኛል፡፡ በሌሎች የውድድሩ ምዕራፎች ያለው የሽልማት ድርሻ አከፋፈልም ይታወቃል፡፡ በምድብ ማጣርያው 32 ብሄራዊ ቡድኖች እያንዳንዳቸው ሶስት ጨዋታዎች ካደረጉ በኋላ 8 ሚሊዮን ዶላር ነው የሚከፈላቸው፤ ለጥሎ ማለፍ የደረሱት 16 ብሄራዊ ቡድኖች 9 ሚሊዮን ዶላር፤ ሩብ ፍፃሜ የገቡት 8 ብሄራዊ ቡድኖች 14 ሚሊዮን ዶላር፤ ለ4ኛ ደረጃ 18 ሚሊዮን ዶላር ፤ ለ3ኛ ደረጃ 20 ሚሊዮን ዶላር፤ ለሁለተኛ 24 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ለሻምፒዮን 30 ሚሊዮን ዶላር ይታሰባል። በ20ኛው ዓለም ዋንጫ የዓለም ምርጥ ተጨዋቾች በብቃታቸውጫፍ መሳተፋቸውም እያጓጓ ነው፡፡ ሊዩኔል ሜሲ በ27 ዓመቱ፣ ዋይኔ ሩኒይ በ28 ዓመቱ፣ ሜሱት ኦዚል በ25 ዓመቱ እንዲሁም ኔይማር በ22 ዓመቱ ለየብሄራዊ ቡድኖቻቸው መጫወታቸው የውድድሩን ምርጥ ሁኔታ የሚያመላክት ነው፡፡ ዓለም ዋንጫው በኢንተርኔት የማህበረሰብ ድረገፆች ቲውተር፣ ፌስቡክና ሌሎችም ተስተካካይ አይኖረውም ተብሏል፡፡ አምና ከተካሄደው የለንደኑ 30ኛው ኦሎምፒያድ በኋላ በስፖርቱ ታሪክ አዳዲስ ከብረወሰኖች እንደሚኖሩትም የተገመተበት ነው። ተሳታፊዎቹ 32 ብሄራዊ ቡድኖች የምድብ ጨዋታዎችን በተለያዩ 6 የብራዚል ከተሞች በሚገኙ 6 ስታዲዬሞች በመዟዟር ማድረጋቸው ሌላው ልዩ ገጽታ ነው፡፡ ደጋፊዎች ብሔራዊ ቡድናቸው በምድብ የምድባቸውን ጨዋታዎች ለሌሎች በብራዚል ከተሞች እስከ 2000 ኪ.ሜ እንደሚጓዙ ተገልጿል፡፡ የውድድሩ አዘጋጅ ብራዚል ከ180 ሚሊዮን በላይ የህዝብ ብዛት ስላላት የ20ኛው ዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች በተመልካች መድመቃቸውም ተጠብቋል፡፡ በየስታድዬሞቹ በአማካይ ከ50ሺ በላይ ተመልካች መኖሩ እየተተነበየ ነው፡፡ የ20ኛው ዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች በ12 ከተሞች በሚገኙ የብራዚል 12 ትልልቅ ስታድዬሞች ለመመልከት ከመላው ዓለም እስከ 5 ሚሊዮን ትኬት ግዢ መጠየቀቁ ክበረወሰን ነው፡፡ የትኬት ዋጋውም ለምድብ ጨዋታዎች ከ90-175 ፓውንድ፤ ለጥሎማለፍ ከ110 -220 ፓውንድ፣ ለሩብ ፍፃሜ ከ165-330 ፓውንድ፣ ለግማሽ ፍጻሜ ከ275-660 ፓውንድ እንዲሁም ለዋንጫ ጨዋታ ከ440 እስከ 990 ፓውንድ ነው፡፡

Read 5376 times