Saturday, 02 November 2013 11:28

“አባ ጅራፎ”

Written by  ኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(3 votes)

አባ ጅራፎ መነኩሴ ናቸው፤ ጅራፍና መስቀል ከእጃቸው ስለማይለይ “አባ ጅራፎ” የሚል ስም ወጥቶላቸዋል፡፡ በእርግጥ ስሙን ማን እንዳወጣላቸው አይታወቅም፤ “እርግጠኛ ስማቸውን አውቃለሁ” የሚል ምዕመንም የለም። በአጠቃላይ አባ ጅራፎ ትክክለኛ ስማቸውም አድራሻቸውም አይታወቅም፡፡ ብቻ ድንገት አንዱ ገዳም ወይም ደብር ይገኙና ይሰብካሉ፤ ምእመናኑን በጠበል ይጠምቃሉ፡፡
በእሳቸው እጅ ከሚጠመቁ በርካታ ምእመናን ውስጥ የማይለፈልፈው ጥቂቱ ብቻ ነው፤ ወይ “ዛር ውላጅ ነኝ” ይላል፤ አለዚያም የሆነ ስም ጠርቶ “ጋኔን” መሆኑን ይናዘዛል፤ በታማሚው ላይ ዳግም እንደማይደርስም በአርባ አራቱ ታቦት ይምል ይገዘታል፡፡ እንዲህ የሚያደርገው ታዲያ የአባ ጅራፎን ጅራፍ እየፈራ ነው፡፡ “አልናገርም” ያለ ተጠማቂ፣ ያ እንደወጨፎ ጥይት የሚጐነው ጅራፋቸው ይቆነዳዋል፡፡ ስለዚህ ሰይጣን ቢኖርበትም ባይኖርበትም፤ ዛር ውላጅ ቢያድርበትም ባያድርበትም ከአባ ጅራፎ ፊት ከጠበል መሃል ራቁቱን ቆሞ የማይለፈልፍ የለም። “ማነህ? ምንድነህ? የት አገኘኸው?” የማይቀሩ የአባ ጅራፎ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ተጠማቂውም የሚያውቀውን የዛር ወይም የሰይጣን ስም እየደረደረ፣ የወንዝ፣ የጫካ አይነት እየሰተረ “ከዚህ” ወይም “ከዚያ እንዲህ ሲያደርግ ያዝሁት” ማለት አለበት፡፡ አለዚያ የአባ ጅራፎ ጅራፍ እንደመብረቅ ድንገት ሊያስገመግም ይችላል፡፡
“ምስህ ምንድነው?” ሌላው የአባ ጅራፎ ጥያቄ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ የሚቀርበው ግን በተጠማቂው ላይ ያደረው መንፈስ ዛር፣ ወይም ሰይጣን መሆኑ ከታወቀ በኋላ ነው - የመሰነባበቻ ጥያቄ፡፡ ዛሩ ወይም ሰይጣኑ ምሱን ከተናገረ በኋላ ነው ሌላው የምእመኑ ጣጣ የሚቀጥለው፡፡ ተጠማቂው ምእመን ምስ ሲጠየቅ “አተላ፣ የዶሮ ኩስ፣ የአህያ ፋንድያ፣ አመድ” ሌላም” ሊል ይችላል፡፡ መከራው ግን የጠየቀው ምስ ሲቀርብለት ከመመገቡ ላይ ነው፡፡ አንዴ ለፍልፏልና ማንም አይለቀውም፡፡ ስለዚህ ወደደም ጠላ ፋንድያውን ወይም የዶሮውን ኩስ ወይም አመዱን፣ አተላውን መጋትና መገላገል አለበት፡፡
ይህ በጠበሉ በኩል የሚስተዋለው ነው፡፡ በስብከት ረገድም “አባ ጅራፎ አሉ” ከተባለ እንኳን የሰበካው ነዋሪ፣ የጐረቤት አጥቢያ ደብር ነዋሪዎች በነቂስ ወጥተው እንዲያዳምጡ የተወሰነባቸው እስኪመስሉ ድረስ ልጅ አዋቂው፣ ህፃን ሽማግሌው ሳይቀሩ ዙሪያቸውን ይሰበሰቡና አፋቸውንም ጆሮአቸውንም ከፍተው ያዳምጧቸዋል፡፡
“እግዚኦ በይ! ወዮ በይ!” አባ ስብከታቸውን ሁልጊዜ በማስፈራራት ይጀምሩና በማሳቀቅ ይጨርሱታል፡፡
በረጅም ቁመናቸው ከቆዳ የተሰራ አጽፋቸውን (ካባ የሚመስል ቅርጽ ያለው) በላይ ደርበው፣ ከስር ያደፈ ቢጫ አንሶላ ለብሰው፣ እርስ በርሱ ተያይዞ የወለተ ፀጉር በሸፈነው አናታቸው ላይ ጭቅቂት የወረሰው ቆብ ደፍተው፣ ጅራፍና መስቀላቸውን አጣምረው ይዘው ሲታዩ በእርግጥም አባ ጅራፎ አንዳች የሚያስፈራ ነገር ተሸክመው የሚዞሩ ይመስላሉ፡፡
ጥር 18፤ ጐጃም ውስጥ አባዛዥ ጊዮርጊስ ክብረ በዓል ላይ…
“እግዚኦ በይ! ሁልሽም ንስሃ ግቢ! ከወደምስራቅ ክፉ ነፋስ ይነሳል፤ ነፋሱ የዋዛ አይደለም፤ ገለባ አንስቶ እንደሚጠፋ ወይም ደካማዋን ብናኝ እንደሚበትነው ቀላልና ተራ ነፋስ አይደለም፤ ሰማያትን ያናውጣል፤ ምድርን እንደቂጣ ይገለብጣል፤ ተራሮችን እንደ አክርማ ይሰነጥቃል፤ ወንዞችንና ሃይቆችን እንደ ቋንጣ ያደርቃል…” ስብከታቸውን ቀጥለዋል። ብዙው ምእመን ከንፈሩን እየመጠጠ ክፉ ነፋስ እንዳያገኘው በየሆዱ ፈጣሪውን ይለምናል፡፡
ከመሃል አንዱ ተጠራጣሪ “ውሃና ቋንጣን ምን አገኛቸው? ሌላ ምሳሌ አጥተው ነው?” ሲል አጠገቡ ለነበረ ጓደኛው ሹክ አለለት፡፡
“ዝም ብለህ አዳምጥ! እግዚሃር የገለጠላቸውን ነው፤ እሳቸው ምን ያርጉ” ጓደኛው መለሰለት፡፡
“ግን ለምንድን ነው ሁልጊዜ የሚያስፈራሩን?” ተጠራጣሪው መልሶ ጠየቀ፡፡
“የታያቸውን ነው አልሁህ’ኮ! እሳቸው እግዚሃር ሆነው የሚመጣውን መአት አይመልሱት…”
“መጣልሽ! ያው… የመከራው አውሎ ነፋስ እየገሰገሰ ነው፤ ወዮልሽ!…” አባ ጅራፎ የመከራ ምጽአት ስብከታቸውን ቀጠሉ፡፡
“…ጾም የገደፍህ ወዮልህ! ያመነዘርህ ወዮልህ! የዋሸህ፣ የቀጠፍህ ምላስህ ይቆረጣል! በሃሰት የመሰከርህ አንደበትህ ይዘጋል! ነፍስ ያጠፋህ…” አባ ጅራፎ ስብከታቸውን ድንገት አቋረጡና ዙሪያቸውን የከበበውን ህዝብ በስጋትና በፍርሃት ማስተዋል ጀመሩ፡፡ ሁልጊዜም ስለነፍስ ማጥፋት ወንጀል ክፉነት ሲሰብኩ ከምር ይሸበራሉ፡፡ ቢችሉ ቃሉን ባይናገሩት ይመርጣሉ፤ ግን ስብከት ሲጀምሩ የስብከታቸው መሰረቶች አሰርቱ ትእዛዛተ ኦሪትና ስድስቱ ቃላተ ወንጌል በመሆናቸው “አትግደል” የሚለውን ጥብቅ ትእዛዝ ማለፍ አይችሉም፡፡
“ልጆቼ፤ አትግደሉ!” አሉ፤ ሲቃ ቢጤ እየተናነቃቸው፡፡
“አትግደሉ” ድምጻቸው ድክም አለ፡፡
“የሚወዱት የቅርብ ዘመድ በሰው ተገድሎባቸዋል ማለት ነው?” አለ ተጠራጣሪው ሰውዬ ያን ጊዜ ብቻ እያዘነላቸው፡፡
“እሳቸው የሚጠልዩት ለዓለም ነው፤ ምን ዘመድ ይኖራቸዋል” ጓደኛው በሀዘን መለሰለት፡፡
“እሱማ እውነትህን ነው፤ መቸም ሰው ተሰው እንጂ ተሌላ አይፈጠርም ብዬ ነው”
“ቢሆንም ማቄን ጨርቄን ሳይል የመነነ መነኩሴ፤ ለዓለሙ ህዝብ እንጂ ለራሱና
ቤተሰቦቹ አይጨነቅም”
አባ ጅራፎ ስብከታቸውን ቀጠሉ፤ ህዝቡም ያለመታከት እያዳመጣቸው ነው፡፡ አብዛኛው ህዝብ የሚመለከታቸው “ይመጣል” ካሉት የመከራ ወጀቦ እንዲታደጉት በእግዚአብሔር የተላኩ መሲህ አድርጐ ነው፡፡
ዕለቱ ሰማዕቱ ጥር 18 በመሆኑ የሰባር አጽሙን ክብረ በዓል ለመታደምና ከጻድቁ ረድኤት በረከት ለመካፈል የተሰበሰበው ህዝብ የትየለሌ ነው፡፡ መደበኞቹ ሰባክያነ ወንጌልም ሆኑ ተጋባዥ ሰባክያን አውደ ምሕረት ላይ ቆመው ከሚያስተምሩት ይልቅ አባ ጅራፎን ለማዳመጥ ዙሪያቸውን የተሰበሰበው ህዝብ በእጅጉ ይበዛል - የሚታመነው የበቁ፣ የነቁ፣ ምእመናንን ከዲያብሎስ መንጋጋ፣ ከድንገተኛ የመቅሰፍት አደጋ ሊጠብቁ የተላኩ ቅዱስ ተደርገው ነዋ!
“ወዮልህ!”…” አባ ጅራፎ ስብከታቸውን እንደቀጠሉ ናቸው፡፡ የቆሙበት ቦታ ጉብታ ስለሆነ ለሁሉም በደንብ ይታያሉ፡፡
“ዘንዶው ይመጣል፤ ሰውን ብቻ አይደለም ዕጸዋትን አዕባንን እንደ ቅቤ ይውጣል፡፡ በዚያ ጊዜ ሰው ሆኖ ያልተፈጠረ ምንኛ የተባረከ ነው!”
“ድንጋዩንም እንጨቱንም ዘንዶው የሚውጠው ከሆነ ሰው ሆኖ አለመፈጠር ምን ጥቅም አለው?” ተጠራጣሪው ሰውዬ ጓደኛውን ጠየቀው፡፡
“ዝም በል እባክህ ልስማበት! የዘመኑን ክፋት፣ የሃጢአታችንን ብዛት በምሳሌ እየነገሩን እኮ ነው” ጓደኛው መለሰ፡፡
“ዘጠኝ ሞት መጣ ቢለው አንዱን ግባ በለው” አለ አሉ የአገሬ ሟች፤ አንድ ጊዜ አውሎ ነፋስ፤ አንድ ጊዜ ዘንዶ፤ ሞት ካልቀረ ምን ያስጨንቀኛል?”
“ንስሐ ግቡ ብለዋል’ኮ፤ ንስሐ ከገባን ቢያንስ ሞታችን የክፉ ሞት፣ የስቃይ ሞት አይሆንም” ጓደኛው በለሆሳስ መለሰ፡፡
“ፍካሬ ኢየሱስ እንዲህ ይላል፤ የመጨረሻው ቀን ሲመጣ ህዝብ በህዝብ ላይ፣ ንጉሥ በንጉሥ ላይ ይነሳል” ተጠራጣሪው ሰውዬ ሳቁ መጣ፡፡ “ምን ንጉሥ አለና በሌላ ንጉሥ ላይ ይነሳል? ሸህ ጅብሪል” የሚባሉ ወሎዬ ያሉትን አያውቁም ማለት ነው?”
“ምን አሉ?”
“ግባ በቀላጤ፣ ውጣ በቀላጤ፤
ከተፈሪ ወዲያ አይባልም አጤ ”ተፈሪ ማለት አፄ ኃይለሥላሴ ናቸው”
“ገጣሚው ሸህ ናቸው አይደል?”
“አዎ”
“ታዲያ አባ ጅራፎኮ መናኝ መነኩሴ ናቸው፤ አንተ ከምትላቸው ሸህ እሳቸው አይበልጡም?”
“ሁሉም በየቤቱ ትልቅ ነው፤ እግዜር አመለከተኝ ነው የሚል” ጓደኛሞቹ በሸክሹክታ ማውራታቸውን ሲያዳምጥ የነበረ ሶስተኛ ሰው ዝም እንዲሉ ገሰፃቸው።
“አባት በልጁ፤ ልጅ በአባቱ ላይ ይነሳል፤ ሁሉም ቤቱን ይገነባል፤ ግን አይኖርበትም፡፡ በየመንደሩ ሹመት ይበዛል፣ ግን መደማመጥ የለም” አባ ጅራፎ ስብከታቸውን ገፉበት፡፡
“በየመንደሩ ሹመት ይበዛል” ያሉትኮ ቀበሌን ነው፤ እውነታቸውንኮ ነው፡፡
ቀበሌ ማንን ያዳምጣል? የቀበሌን ስልጣንስ ማን ከቁብ ይቆጥረዋል?” የተጠራጣሪው ጓደኛ በመገረም አስተያየቱን ለገሰ፡፡
“በያገሩ የምድር መናወጽ ይሆናል፤ ራብ ቸነፈር ይበዛል፤ አስረሽ ምቺው የየሰው የዕለት ተዕለት ተግባር ይሆናል፤ በዚህም እግዚአብሔር ፊቱን ከህዝቡ ያዞራል…” አባ ስብከታቸውን ቀጥለው ሳለ፣ ድንገት የተሰማ ከፍተኛ ጩኸት አቋረጣቸው፡፡
“ራሱ ነው! ይህን መልቲ ያዙልኝ! ጐበዝ በጻድቁ ይዣችኋለሁ፤ እንዳትለቁት!” ከህዝቡ መሃል እንደ እብድ የሚጮኸው ሰውዬ ፊት ለፊቱ ያገኘውን ሁሉ እየገፈተረ ወደ አባ ጅራፎ መገስገሱን ቀጠለ፡፡
“እብድ ነው! ያዙት!” የብዙ ሰው ድምጽ ደጋግሞ አስተጋባ፡፡ ሰውየው ግን ሊቆም አልቻለም፡፡
“ይህን ነፍሰ ጉዳይ ያዙልኝ! መነኩሴ አይደለም ሲያታልል ነው፡፡ የዛሬ አስራ አምስት ዓመት ታላቅ ወንድሜን ገድሎ ሲታደን የኖረ ወንጀለኛ ነው ያዙልኝ!” አይኑን አፍጥጦ ወደ አባ ጅራፎ ገሰገሰ፡፡ ንግግሩን የሚያዳምጠው ሁሉ “በእርግጥም እብድ ነው” ብሎ አሰበ፡፡
አንዳንዶች ብቻ አባ ጅራፎንም የሰውየውን ንግግርም እኩል ጠረጠሩ፡፡
“አንት ጭራቅ አገኘሁህ! ወንድሜን እንደበላኸው አልቀረህም” ብሎ ዱላውን መዝዞ ወደ አባ ጅራፎ ሲጠጋ፣ መስቀላቸውን ወደ ኪሳቸው አስገቡ፤ በዚያው ቅጽበት በአጽፋቸው ውስጥ ደብቀውት የነበረውን ፍሻሌ ሽጉጥ አወጡና የሰውየውን ግንባር እንደ አክርማ ለሁለት ሰነጠቁት፡፡

Read 4029 times