Saturday, 02 November 2013 11:23

የፎርብስ የአመቱ ምርጥ የአለማችን ሃያላን

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(5 votes)

ከአፍሪካ የተገኘው አንድ ሃያል ብቻ ነው
ከ72 ሃያላን መካከል ሴቶች 9 ብቻ ናቸው
የቭላድሚር ፑቲን አንደኛ መባል አነጋጋሪ ሆኗል

ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት የራሱን መምረጫ መስፈርት ተጠቅሞ፣ ከአጠቃላዩ የአለም ህዝብ በመቶ ሚሊዮን አንድ ሃያል ስሌት የአለማችንን ሃያላን በየአመቱ መምረጥ የጀመረው እ.ኤ.አ በ2009 ነው፡፡
መጽሄቱ እየተገባደደ ባለው 2013 በተሰማሩበት የሙያ መስክ ተጽዕኖ መፍጠር ችለዋል ያላቸውን የአለማችን ሃያላን ግለሰቦች ዝርዝር ለአምስተኛ ጊዜ በዚህ ሳምንት ይፋ አድርጓል፡፡
‘ግለሰቦቹ በምን ያህል ሰው ላይ ሃይላቸውን ማሳረፍ ይችላሉ?’፣ ‘በስራቸው ምን ያህል ገንዘብ ይንቀሳቀሳል?’፣ ‘ከአንድ የሞያ መስክ በላይ ተጽዕኖ መፍጠር ይችላሉ?’ እንዲሁም ‘ተሰሚነታቸውንና ያላቸውን አቅም በመጠቀም አለምን ለመለወጥ ምን ያህል በንቃት ተንቀሳቅሰዋል?’ የሚሉት፣ የፎርብስ ሃያላንን መምረጫ መስፈርቶች ናቸው፡፡
እነዚህን መስፈርቶች በመጠቀም ነው፣ ፎርብስ 7.2 ቢሊዮን ከሚደርሰው የአለም ህዝብ፣ የአመቱ ሃያላን ያላቸውን 72 ግለሰቦች ዝርዝር ይፋ ያደረገው፡፡
በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የሩስያውን ፕሬዚዳንት ብላድሚር ፑቲንን ያካተተውና የአመቱ ሃያላን ፊታውራሪ በማድረግ ከፊት ያሰለፈው ይህ ዝርዝር፣ ባራክ ሁሴን ኦባማን በማስከተል የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ዋና ጸሃፊ ዢ ጂንፒንግን በሶስተኛነት አስቀምጧል፡፡
ፎርብስ በአገራቸው ፖለቲካ የነበራቸውን ስልጣን ለማጠናከርና በአለማቀፍ ደረጃ ያላቸውን ተደማጭነት ለማሳደግ የሚያደርጉትን ጥረትና ስኬት በማየት በቀዳሚነት አስቀምጫቸዋለሁ ያላቸው ብላድሚር ፑቲን፣ በብዙዎች ዘንድ ለዚህ ወግ አይመጥኑም የሚል ትችት ተሰንዝሮባቸዋል፡፡ የዘገባውን መውጣት ተከትሎ፣ ፑቲን የሃያላን ቁንጮ ተደርገው ከፊት መቀመጣቸው በተለያዩ የአለም መገናኛ ብዙሃንና በድረ-ገጽ አግባብ አለመሆኑ እየተዘገበና የመነጋገሪያ ርዕስ እየሆነ መጥቷል፡፡ ፎርብስንም ያሳማው ይዟል፡፡
ከ2010 በስተቀር ላለፉት አራት አመታት የፎርብስ ሃያላን ቁንጮ የነበሩት የአሜሪካው ፕሬዚደንት ባራክ ሁሴን ኦባማ፣ በሁለተኛው የስልጣን ዘመናቸው ጅማሬ አንዳንድ የሚያሳሙ ችግሮች ታይተውባቸዋል በሚል በዘንድሮው ዝርዝር አንድ ደረጃ ዝቅ ተደርገዋል፡፡
የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳስ ፍራንሲስ፣ የጀርመኗ መራሄ መንግስት አንጌላ መርኬል፣ ቢል ጌትስ፣ የአሜሪካ ፌደራል ሪዘርቭ ዋና ጸሃፊ ቤን ቤርናንኬ፣ የሳኡዲ አረቢያው ንጉስ አብዱላህ ቢን አብዱል አዚዝ አል ሳዑድ፣ የአውሮፓ ሴንትራል ባንክ ፕሬዚደንት ማሪዮ ድራጊ እና የዎልማርት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሚካኤል ዱክ ከ4ኛ እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡በፎርብስ የአመቱ ምርጥ የአለማችን ሃያላን ግለሰቦች ዝርዝር ውስጥ የአገር መሪዎች፣ የትርፋማ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚዎችና አስተዳዳሪዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች፣ በጎ አድራጊዎችና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ዳይሬክተሮች፣ ስራ ፈጣሪዎችና ቢሊየነሮች ተካተዋል፡፡
በዘንድሮው የፎርብስ ዝርዝር ውስጥ የሮማውን ጳጳስ ፍራንሲስ፣ የሳምሰንግ ስራአስኪያጁን ሊ ኩንሂ፣ የኒዮርክ ታይምስ ዋና አዘጋጁን ጂል አብራምሰንና የቮልስ ዋገን ግሩፕ ሊቀመንበሩን ማርቲን ዊንተርኮርንን ጨምሮ 13 አዳዲስ ሃያላን በአዲስ ገቢነት ተካተዋል፡፡
በሃያላኑ ሰልፍ ውስጥ የሴቶች ድርሻና ደረጃ ከአመት አመት እያደገ እንደመጣ የሚያመለክተው የፎርብስ ዝርዝር፣ ከአለም ህዝብ ቁጥር ግማሽ ያህል ከሆኑት ሴቶች መካከል ተመርጠው በዘንድሮው የሃያላን ሰልፍ ውስጥ የገቡት 9 መሆናቸውንና የሃያላኑን 12 በመቶ ድርሻ መያዛቸውን ያሳያል፡፡
ከእነዚህ የዘንድሮ ሃያላን ሴቶች መካከል የጀርመኗ መራሄ መንግስት አንጌላ መርኬል(5ኛ)፣ የህንድ ብሄራዊ ኮንግረስ ፕሬዚደንት ሶኒያ ጋንዲ(21ኛ) እና የአይ ኤም ኤፍ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክርስቲን ላጋርዲ(35ኛ) ይጠቀሳሉ፡፡
ፎርብስ በዘንድሮው የሃያላን ዝርዝር ውስጥ 26 የአለማችን ታዋቂ ቢሊየነሮችን ቢያካትትም፣ ለአብዛኞቹ ባለጸጎች የሃያልነት ክብር ያጎናጸፈው ያካበቱትን ሃብት ብቻ ሳይሆን በበጎ ምግባር ስራ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን ገልጧል፡፡
ያካበቱትንም የመጸወቱትንም በመገምገም ሃያል ብሎ ከመረጣቸው ቢሊየነሮች መካከል፣ ዋረን ቡፌት(13ኛ)፣ ሚካኤል ብሉምበርግ(29ኛ)፣ ሊ ካሺንግ(30ኛ) እና ሞማመድ ኢብራሂም(71ኛ) የሚጠቀሱ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አራቱ ቻይናውያን፣ አራቱ ደግሞ ህንዳውያን ናቸው፡፡
በዝርዝሩ ውስጥ የተካተቱት ቢሊየነሮች የሃብት መጠን አጠቃላይ ድምር፣ ከ564 ቢሊየን ዶላር በላይ መሆኑንና ይህም ከስዊድን ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት እንደሚበልጥ፣ የአለም ባንክን መረጃ በመጥቀስ ፎርብስ ዘግቧል፡፡
መጽሄቱ በስራ ፈጠራ መስክ ተጠቃሽ ስራ ሰርተዋል ብሎ በዝርዝሩ ውስጥ ካካተታቸው 12 ግለሰቦች መካከል፣ የጎግል መስራቾች ላሪ ፔጅና ሰርጂ ብሪን(17ኛ)፣ የስፔስ ኤክስፕሎሬሽን ቴክኖሎጂስ ኮርፖሬሽን መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ኤለን ሙስክ እና ከዘንድሮ ሃያላን በእድሜ ለጋ ተብሎ የተጠቀሰው የፌስቡክ መስራቹ ማርክ ዙከርበርግ(24ኛ) ይጠቀሳሉ። አብዛኞቹን ሃያላን ከሰሜን አሜሪካ፣ እስያና አውሮፓ አገራት የመረጠው ፎርብስ ወደ አፍሪካ ፊቱን ሲያዞር ከአንድ ሃያል በቀር አልታየውም፡፡
“አገሬን በወጉ እየመራሁ ነው፣ ህዝቤን የዲሞክራሲ ተጠቃሚ እያደረግሁ ነው፣ ስልጣኔን በአግባቡ እየተጠቀምኩ ነው” እያሉ ምለው ከሚገዘቱ ሃምሳ ምናምን የአፍሪካ መሪዎች መካከል፣ አንዳቸውም የፎርብስን ሚዛን አልደፉም፡፡
“ስራ ፈጣሪ ዜጎችን አፍርተናል” ብለው ከሚመጻደቁ የአፍሪካ አገራት ዜጎች መካከል፣ ለስም እንኳን የፎርብስን ቀልብ የገዛና የሃያልነትን ክብር ሊጎናጸፍ የታደለ ስራ ፈጣሪ አልተገኘም፡፡ ‘በጎ ስራ ሰርተናል’ ብለው በአደባባይ ድምጻቸውን ጎላ አድርገው ከሚያሰሙ ህልቆ መሳፍርት የአፍሪካ መንግስትታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ዳይሬክተሮች፣ ፎርቢስ ለአንዳቸውም ጆሮ አልሰጠም፡፡ አንዳቸውንም አልመረጠም፡፡
‘ሃያላን ልጆች እንዳትወልድ የተረገመች አህጉር’ ተብላ ከመታማት ያዳናት የአፍሪካ ብቸኛ የቁርጥ ቀን ልጅ፣ እንደምንም በፎርብስ አይን ውስጥ የገባው ‘አንድ ለአህጉሩ’ ዳንጎቴ ነው - የዳንጎቴ ግሩፕ ኩባንያ መስራች ናይጀሪያዊው ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ(64ኛ)።

Read 5016 times