Saturday, 02 November 2013 11:22

በ28ቱ የሽብር ተከሣሾች ላይ ምስክሮች እየተሰሙ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

“ሀረስቱል ሽባበል ሙጃህዲን ፊ ቢላደል ሂጅራተይታን” በሚል ስያሜ ተደራጅተው ከአልቃኢዳ አልሸባብ ጋር የቀጥታ ግንኙነት በመመስረ፣ በኢትዮጵያ የተለያዩ የሽብር መዋቅሮችን በመፍጠር ህገመንግስታዊ ስርአቱን ለማፍረስ ተንቀሳቅሰዋል በሚል በተከሰሱት 28 ግለሰቦች ላይ ምስክሮች እየተሰሙ ነው፡፡
ከጥቅምት 19 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ ለ10 ተከታታይ የስራ ቀናት ከ40 በላይ የሚሆኑ ምስክሮች በልደታ ከፍተኛ ፍ/ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ይሰማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በመጀመሪያዎቹ ቀናት ተከሣሾች በተጠርጣሪነት ሲያዙ የአይን እማኝ የነበሩ የአቃቤ ህግ ምስክሮች የተሰሙ ሲሆን ቀሪ ምስክሮችም መሰማታቸው ይቀጥላል፡፡
በእነ አማን አሠፋ መዝገብ ስር የተካተቱት 28 ተከሳሾች፤ የአልቃኢዳ አልሸባብ የሽብር ህዋስ ነው በተባለው ስብስብ ውስጥ በተለያዩ ሃላፊነቶችና አባልነት የተሳተፉ መሆናቸው በአቃቤ ህግ የክስ ዝርዝር ተመልክቷል፡፡
በሁሉም ተከሳሾች ላይ የቀረበው ጥቅል ክስ እንደሚያስረዳው፤ ግለሰቦቹ የወንጀሉ ዋና ተሳታፊና ፈፃሚ በመሆን ህገመንግስታዊ ስርአቱን በማፍረስ በሼሪያ ህግ የሚተዳደር እስላማዊ መንግስት መመስረት የሚል አላማ በመስቀመጥ፣ ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ ከአልቃኢዳ አልሸባብ የሽብር ተልዕኮ በመቀበል፣ ለዚሁ በመደራጀት፣ ድጋፍ በማሰባሰብ፣ አባላትን በመመልመል፣ በማደራጀትና ተከታታይ የጦር መሣሪያ አጠቃቀምና አጠቃላይ የሽብር ስልጠና በመውሰድ ሲሳተፉ ቆይተው፤ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሶማሊያ በመሄድ ወታደራዊ ስልጠና ለመውሰድ ሲንቀሳቀሱ ቆይተው፤ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሀገር ቤት በመመለስ፣ አባላትን በማደራጀትና በመመልመል መቆየታቸውን ያስረዳል፡፡
በተከሳሾቹ ላይ ከቀረቡት ምስክሮች በተጨማሪ የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎች እና በኤግዚቢት የተያዙ ማስረጃዎች ተጠቅሶባቸዋል፡፡
ቀደም ሲል በእነዚህ ተከሣሾች ዙሪያ በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት “ጅሃዳዊ ሃረካት” የሚል ዶክመንተሪ ፊልም መተላለፉ ይታወሳል፡፡

Read 1761 times