Saturday, 02 November 2013 11:19

‘ቀይ ሽንኩርት…’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(7 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…መቼም የእኛ የብሶት ብዛት ቦታ ላይ እንደሚቆም የሚያውቀው አንድዬ ብቻ ነው። የምር…አንዳንዴ እኮ እንደው “ይቺ አገር የምር ባለቤት የላትም…” የምንለው ወደን አይደለም፡፡ አሁንም ብዙ ነገሮችን እያየን እንላለን… “ይቺ አገር ባለቤት የላትም እንዴ?” እንላለን፡፡
“እዚህ ቦታ የጎደለ ነገር አለ ይስከተካከል…” “እዛ ቦታ የተበላሸ ነገር አለና ይጠገን…” ምናምን ሲባል ለምን መደማመጥ እንዳቃተን አይገርማችሁም? ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…እኛ የሚሰማን አለ ብለን ስንናገር አቤቱታ የሚቀርብባቸው ባለስልጣኖች ወይም ሌሎች ግለሰቦች ፌስቡካቸውን ከፍተው (ቂ…ቂ…ቂ…) “ተወው እባክህ ካልደከመው ይለፍልፍ፣ ሀበሻ እንደሆነ ዘላላሙን እንዳለቃቀሰ ነው…” ምናምን የሚባባሉ ይመስለኛል፡፡
ለምሳሌ ስፖርት ላይ ‘ዋይኔ ሩኒ’ የሚባል ሰው እንደሌለና በዛ ስም እየጠራነው ያለው ተጫዋች ትክክለኛ ስሙ ‘ዌይን ሩኒ’ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይጠቀሳል፡፡ ተጥደን ከምንውልበት የዲ.ኤስ.ቲቪ የሱፐር ስፖርት ዘጋቢዎች በሏቸው፣ በሉት የጀዚራ ስፖርት ዘጋቢዎች በሏችው፣ በየጊዜው ማመሳከሪያነት የምንጠቀምባቸው ‘የህትመት ውጤቶች’ ዘጋቢዎች በሏቸው … አለ አይደል… ከእኛ በስተቀር እንዲህ ያለፍርድ ቤት ውሳኔ የተጫዋቹን ስም ለውጦ “ባርም አያርመኝ” የሚል ያለ አይመስለኝም፡፡ እናማ… እሺ ቀሸምንና ተሳሳትን እንበል…ማስተካካል ያቃተን ለምንድነው?
ስሙኝማ…እግረ መንገዴን በስፖርት ዘገባዎች በአተረጓጎም ስህተትም ይሁን በሚገባ ባለማየት ብዙ ስህተቶች ይሠራሉ፡፡ በኢንተርኔትና በ‘ዲሽ’ ዘመን ብዙ ታዛቢ እንዳለ ልብ ይባልማ! ሴትዮዋ ምን አለች አሉ…“አንድ ሰው አንዴ ካታለለኝ ማፈር ያለበት እሱ ነው፡፡ ሁለቴ ካታለለኝ ግን ማፈር ያለብኝ እኔ ነኝ፡፡” እናማ… ዘንድሮ በመረጃ ሰሞን ሁለቴ ተታለው ራሳቸው የሚያፍሩ ሰዎች ቁጥር እያነሰ መሆኑን ማወቀ አሪፍ ነው፡፡
ከተማዋ እየተገለባባጠች ነው፡፡ (“ፈርሳ እየተሠራች ያለች…” የሚለውን ሙሉ ለሙሉ ለመቀበል “ካልታዘልኩ አላምንም…” እንዳለችው ሙሽራ ጊዜ እየጠበቅን እንደሆነ ልብ ይባልልንማ!) ብዙ ቦታ እግረኞች እንደ ልብ መንቀሳቀስ አቅቷቸዋል፡፡ እናማ… ቀጠነችም፣ ጠበበችም መተላለፊያዎች ይሠሩልን እየተባለ ለምን “በእጄ!” ብሎ የሚያዳምጥ እንደጠፋ አይገርማችሁም! አሀ…‘በአፍሪካ መዲናዋ’ ገደሉን ስንወጣና ስንውርድ እኮ ልክ የናሽናል ጆግራፊን ዘጋቢ ፊልም የምንሠራ እያስመሰለብን ነው፡፡
ስሙኝማ…ከእኛው ከጋዜጠኞቹ ሳንወጣ…በኤፍ ኤሞች ላይ ከሚለቀቁ የውጪ ዘፈኖች መካካል ቅልጥ ያለ ‘ብልግና’ (ፖርኖ) ያለበት ብዙ ናችው፡፡ በየጊዜው “ይህንን ነገር ኧረ እባካችሁ…” ይባላል፡፡ ግን ምን መሰላችሁ…አሁንም የለየላቸው ‘የብልግና’ ግጥሞች (አዎ፣ ‘ብልግና’ የሚለው ቃል አሁንም ከመዝገበ ቃላታችን አልጠፋም፡፡) ያላቸው ዘፈኖች እየሰማን ነው፡፡ እና…በኢንተርኔት ዘመን ያልተለመዱ ቃላትን በቀላሉ ማወቅ በሚቻልበት ምነው የምንሰማ ጠፋን!
(ስሙኝማ…እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ… የሆኑ ወጣት እንትናዬዎች ደረት ላይ ‘የፈረንጅ አፍ’ ጽሁፍ የተጻፈባቸው ‘ቲ—ሸርቶች’ ለብሰዋል፡፡ እናላችሁ… የጽሁፉ ትርጉም በጣም፣ እጅግ በጣም የሚዘገንን ነው፡፡ እንትናዬዎቹ እንደማያውቁት እርግጠኛ ነኝ፡፡ ቢያውቁ ኖሮ እንዴት ሊሳቀቁ እንደሚችሉ ይታየኛል፡፡ አሀ…ጽሁፉ ገና ለገና ብሎው (Blow) የሚለው ቃል ስላለበት ከፊኛ ጋር ብቻ የተያያዘ ነው ማለት አይደለማ!
ስሙኝማ…የዘንድሮ የሙዚቃ ‘ክሊፕ’ መቼስ እንደምታዩት ነው፡፡ መኮረጅ ምን ያህል እንደለመደብን ያሳያል፡፡ ‘ኦርጂናል’ የምትሉት ‘ክሊፕ’ በጣም አናሳ ነው፡፡ እናላችሁ…ቅልጥ ያለ የትከሻ እንቅጥቅጥ ባህላዊ ዘፈን ‘ክሊፕ’ ላይ…አለ አይደል…ከዓለም ሽክርክሪት አሥር እጥፍ በሆነ ፍጥነት ‘ነገርዬውን’ ማሽከርከርን “ኧረ እባካችሁ!” ሲባል ምነዋ ሰሚ ጠፋ!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይሄ አዲስ የትራፊክ መብራት እኮ ምን ያህል “ሁሉም ነገር ለእኔ ብቻ…” ባዮች እንደሆንን የሚያሳይ ነው፡፡ መብራቱ ‘ቁም’ ከማለቱ፣ ‘እለፍ’ ከማለቱ ቀደም ሲል ያለችው የማስጠንቀቂያ ብልጭ፣ ድርግም ‘ለመንቀሳቀስ ተዘጋጅ’ ማለት ይመስለኛል፡፡ ግንላችሁ…በዚች ሦስትና አራት ሰከንድ መቆም ያለበትም፣ ለመንቀሳቀስ መዘጋጀት ያለበትም ፈጥኖ ለማለፍ እየተሽቀዳደመ…አለ አይደል… “ዘመናዊነታችን የሪሀናን ዘፈን ከመስማት ሳያልፍ “ሌላኛው ሚሌኒየም ሊመጣ ነው!” ያሰኛል፡፡
አንዳንድ ‘ቦሶቻችን’ ይኸው እስከ አሁን ድረስ ልክ ልካችንን እየነገሩን ነው፡፡ ልትሰሙት ይገባል የሚሉትን ፈቀድንም አልፈቀድንም መንገራቸው አይቀርም፡፡ ግን ቢያንስ፣ ቢያንስ ቃላቶቹን ለምን አይመርጡም፡፡ እዚሀ አገር ሰዉ ወንበር ሲሰጠው አብሮ የማስፈራራት ‘ግሪን ካርድ’ ይሰጠዋል እንዴ! አንዳንዴ ሳስበው…ድሮ ‘ስዩመ እግዚአብሔር’ ይሉ የነበሩት ንጉሣውያን ናቸው፡፡ ዘንድሮ ከኮሚቴ ሰብሳቢ ጀምሮ ያለው ሁሉ ‘ስዩመ እግዚአብሔር’ ነኝ ያዐ ነው የሚመስለው፡፡ እናማ…“ቦታው ላይ የተቀመጣችሁት ልታስተዳድሩን እንጂ እንደፈለጋችሁ ከፍ ዝቅ የምታደርጉን የግል ንብረቶቻቸሁ አይደለንም” ስንል ምነው የሚሰማን ጠፋ፡፡
(ስሙኝማ…እዚህ አገር እንደፈለጋቸው የስሙኒ ኳስ ሲያደርጉን የሚቆዩ ሰዎች ሁሉ በአንድ ወይም በሆነ ምክንያት የሆነ ፌርማታ ላይ “አታስፈልግም” ተብለው ሲጣሉ ለመብታችን ሲከራከሩልን እንደከረሙ ሲያስመስሉ ልክ ግን…አለ አይደል… “እዚህ አገር ክፉ መሆን ብቻ ነው የሚያተርፈው?” ያሰኛል፡፡ ዘንድሮ ነው የምር ጅቦች በማያውቋቸው ሀገራት “ቁርበት አንጥፉልን…” እያሉ ያሉት፡፡)
ዘንድሮ እንደሁ መተማመን አገር ትቶ ተሰዷል። እናማ ምስጢር ምንቋጠር የሚችሉ ሰዎች ኢነዴነጀርድ ስፒሺየስ እየሆኑ ነው፡፡ ብዙዎቻችን የሰማሁትን መቼ ባወራሁት ብለን የምንቁነጠነጥ ሆነናል፡፡ የኃይማኖት አባቶች፣ የማህበረሰብ ጠበብት…ስለመተማመን ሁሌም እያወሩ ነው — ሰሚ ጆሮ ጠፋ እንጂ፡፡
እናላችሁ…ድሮ የአርበኞችን ምስጠር እየሰለሉ ለጣሊያን ሹክ የሚሉ ‘እንቁላል ሻጮች’ ነበሩ አሉ። በዚህ ዘመንም…አለ አይደል… ‘አርአያነታቸውን’ የተረከብን ቁጥራችን የበዛ ይመስላል፡፡ “ስማ…እባክህ ከባለቤቴ ጋር ችግር ገጥሞናል…” ብለን የምናዋየው ሁነኛ ወዳጅ ያጣንበት ዘመን መድረሳችን የምርም የሚያሳዝን ነው፡፡ ምነዋ ምክር አልሰማ አልን!
እንግዲህ ነገሬን ከከንፈሬ አልለቅም
የሰው ዶሮ አለና ከአፍ፣ ከአፍ የሚለቅም
የምትለዋ ነገር ለዘንድሮ ‘በልክ’ የተሠራች ትመስላለች፡፡
ስሙኝማ… አሁን፣ አሁን ከተማ ውስጥ የአሥራ ሁለትና የአሥራ ሦስት ዓመት ህጻናት በጠራራ ጸሀይ ሰክረው ሲንገዳገዱ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ልክ በቲቪ የማይተላለፍ የህጻናት ጣጤዎች ‘ሪያሊቲ ሾው’ ሊመስል ምንም አይቀረው፡፡ የመጠጥ ማስታወቂያዎች ሁሉ ‘ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች የተከለከለ’ የሚል ነገር አላቸው፡፡ ማለትም የመጠጥ ነጋዴዎች “እባካችሁ ለህጻናትና ታዳጊዎች አልኮል አትሽጡ…” እየተባለ ነው፡፡ እናማ… ምነው ሰሚ ጠፋ! ምነው ነገረ ሥራችን ሁሉ “እኔ ከሞትኩ…” አይነት ሆነ! አይደለም ስለሚጠጡ ህጻናት ማሰብ፣ መጠጥን በተመለከተ አዋቂዎችም የሚመከሩበት ዘመን ነበር፡፡
በመጠጥ ደስታ ይገኛል ብላችሁ
መጠን አትለፉ ትቃጠላላችሁ
ተብሏል፡፡ ይህንን ስንኝ የጻፉ ሰዎች የዘንድሮ ነገረ ሥራችንን ቢያዩ ምን ይሉ ይሆን! ስንቱ ያለ የሌለውን በመጠጥ እያሟጠጠ አይደል!
እኔ የምለው…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የወጪን ነገር በተመለከተ ይቺን ስሙኝማ፡፡ ሰውየው ወጪ…ወጪ…ወጪ… ብቻ ሲሆንበት ምን አለ መሰላችሁ…“የእኔ የገንዘብ ቦርሳ እንደ ቀይ ሽንኩርት ነው፣ በከፈተኩት ቁጥር ያስለቅሰኛል፡፡”
እናማ…የሚነገር በዝቶ የሚሰማ ሲጠፋ ነገሩ ሁሉ ‘ቀይ ሽንኩርት’ እየሆነብን ነው፡፡
(‘የሚያስለቅስ የገንዘብ ቦርሳ’ን በተመለከተ…አለ አይደል… እስቲ ለቦርሳ የሚበቃ ፈረንካ ይኑረንና እናየዋለን፡፡”)
ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

Read 4479 times