Saturday, 02 November 2013 11:14

የአዳማ ጉዞ ማስታወሻ!

Written by  ነቢይ መኰንን
Rate this item
(1 Vote)

የደብረ ብርሃን ጉዞዬ ማስታወሻ
ጉዞውን የጀመርነው የ60ዎቹ ወዳጅ ከሆነ ከላፍቶ ከሚመጣው የእየሩሣሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት አማካሪ፤ ጋር ነው፡፡ እኔን ከቄራ ይዘውኝ ወደ ሲ ኤም ሲ እናመራለን፡፡ ከዚያ የዱሮው የዕድገት በሕብረት ወዳጄን እናገኝና ከሱ ጋር ወደ ደብረብርሃን እንቀጥላለን፡፡ ደብረ ብርሃን ስንደርስ የዱሮ ት/ቤቴ፣ የናዝሬት አፃ ገላውዴዎስ፤ ዩኒት ሊደሬ (Unit Leader)ና የዛሬውን የእየሩሣሌም የህፃናትና ማ/ሰብ ልማት ድርጅት የደብረ ብርሃን ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አገኘን፡፡ ግጥምጥሞሹ ይገርማል፡፡ ለረዥም ጊዜ ስላለመተያየታችንና ስለኑሮ ውጣ-ውረድ ከተወያየን በኋላ ወደሥራችን አተኮርን፡፡
መሥሪያ ቤቱ እንዴት ሊቋቋም እንደቻለ እያስረዳኝ ነው ወደ ቀበሌዎቹ መንገድ የጀመርነው፡፡
“ጄክዶ” አለ፡፡ አቶ ዓለማየሁ፤ “ያኔ የነበረውን ችግር ለመቋቋም የተፈጠረ፣ ህፃናቱ ሲያድጉ ምን ይሁኑ በሚል ዓላማ ላይ የተመሠረተ የመጀመሪያ የእሳት አደጋ ሥራ የሠራ ድርጅት ነው!! ነብስ ማዳን!! ቀውሱ እንግዲህ ሲነግሩን በጣም ከፍተኛ ቀውስ ነበረ ነው እሚባለው፡፡ ሞቱ ከፍተኛ ነበር! መታረዙ… መራቆቱ… በሽታው… በየቀኑ ሞት ነበረ ነው እሚባለው፡፡ እዚህ ቦታ ላይ ወደ 500ሺ ሰው ሰፍሮ ነበረ አሉ (ላዕከ አምደሚካኤልን ታቀዋለህ እሱ የኢሠፓ አንደኛ ፀሐፊ ነበረ) ትልቅ ሚና ይጫወት የነበረው እሱ ነበረ… ጋሽ ሙሉጌታ ሀጐስንስ ታቃለህ፤ እሱ እዚህ ዋና ሃላፊ ነበረ፡፡ ሙሉጌታ ሀጐሥ የእኔ አስተማሪዬ ነው - ኤሌሜንታሪ፡፡ ህያው ዋጋ ነው።
አቅመ ደካማ የሆኑና እናት አባት የሌላቸው፤ ሲቀሩ፤ ማን እነዚህን ይታደግ ብለው ሲጠይቁ ጄክዶ ተወለደ፡፡ በጊዜ ሂደት 250 ልጆች ተወለዱ፡፡ ሲያሳድጉ ቆዩ፡፡ እዚሁ ግቢ ውስጥ መምህር ይቀጠርና ይማሩ የሚል ሃሳብ መጣ!”
ታሪኩ ዱሮ፤ እንዲህ ነው፡፡ አሁን ቢሮው ያለበት ግቢ ውስጥ ግማሽ ሚሊዮን ህዝብ አርፎ ነበረ - ለመጠለያ፡፡ ከዛ ውስጥ በተወሰነ እርሾ ተጀመረ - ህፃናትን መርዳት፡፡ ማን ይታደጋቸው ሲባል ነው ጆክዶ (የእየሩሳሌም የህፃናትና ማ/ሰብ ልማት ድርጅት) የተወለደው፡፡ ያን ጊዜ ስሙ ጂሲኤች) ጂሩሳሌም ቺልድረንስ ሆም ነው የመጀመሪያው፡፡ እየሩሳሌም የህፃናት ማሳደጊያ፡፡ የደብረብርሃን የህፃናት ማሳደጊያ፣ የባህር ዳር፣ ያዲሳባ፣ የመንደፈራ ማሳደጊያ ነው በየቦታው ስሙ፡፡ የመጀመሪያው አዲስ ዓለም ነው፡፡ ቀጥሎ ደብረ ብርሃን ነው፡፡ ቀጥሎ ባህር ዳር፡፡ ከዛ መንደፈራ ነው፡፡ በዩኒፊኬሽኑ (መልሶ መቀላቀሉ) ብዙ ልጆች በሪኢንቴግሬሽኑም እንደዚሁ ብዙ ልጆች ነው ከቤተሰብ የተዋሃዱት፡፡ የልጆቹ ቁጥር እያነሰ ሄደ በግቢው ውስጥ ያሉት፡፡ ሲጀመር፤ ውስጥ የነበሩትና ቀጥሎ ደግሞ ከትግራይ፣ ከወሎ፣ ከጐጃም ወዘተ የመጡት ቁጥር ሰፊ ነው፡፡
በብዛት ከትግራይ የመጡ ናቸው፡፡ ሁለተኛው ወሎ ነው። ከዛ ሰሜን ምሥራቅ ሸዋ አለ፡፡ ጐጃም (በቁጥር ትንሽ)፣ ጅማም (በቁጥር ትንሽ)፡፡
አሁን ቀበሌ 02 ውስጥ ነን (ብሎ መኪናውን አዞረው። “መንግሥት ተቀበሉ ሲለን እምቢ ስንል ቆየንና ተቀበልን፡፡ በኋላ self assessment (ራስን መፈተሽ) ተጀመረ፡፡ በህፃናት ማሳደጊያ ማሳደግ፤ ምንድን ነው ችግሩ? የሚለውን እናይ ነበረ - እኔም ደርሼአለሁ፡፡ ልጆቹ ህብረተሰቡን ይሸሻሉ፡፡ ከውጪ እንኳን ጓደኛ አይዙም፡፡ እዛው ነው በቃ የራሳቸው ደሴት የሚመሠረተው ውጪ አይቀላቀሉም፡፡ ት/ቤትም እንደዚሁ ነበሩ፡፡ በትምህርት ግን በጣም የሚገርሙህ ናቸው፡፡ ለምን? ግማሽ ቀን ነበር የሚማሩት፡፡ ቲቶሪያል አለ፡፡ ግማሹን መምህራን ተቀጥረው ያስተምሯቸዋል፡፡ በቃ መማር ነው ሥራቸው፡፡ ሙሉ ቀን ትምህርት ናቸው፡፡ “የኢየሩሳሌም ልጆች ተማሪዎች” ምርጥ ውጤት ያላቸው ናቸው፤ ነው ሚባሉት፡፡ Reunified አንሆንም ነበረ አቋማቸው ግን! አይፈለግማ!
ቅዳሜ ቅዳሜ ገበያውን እንዲያዩ ማድረግ፣ አትክልት እንዲሸጡ (ገንዘብ ምንዛሪውን እንዲያውቁ) ብዙ እንጥር ነበር። በማ/ሰባዊ ግንኙነት አንፃር ከእናቱ፣ ካክስቱ ጋር የሚኖር ልጅ ይለያል፡፡ እራሱን ትዳብሰዋለች - ፍቅር አለ፡፡ የእኛ አርቲፊሻል ነው፡፡ እዛ ሰብዓዊ ትኩሳት ነው ስለሆነም እንቀላቅላችሁ ስንል የነበረው ግርግር ሌላ ነው፡፡ ከዛ ዞሮ ዞሮ ተቀላቀሉ፡፡ ከመንግሥት ጋር በመሆን በየገበያው ሁሉም የሥራ ባልደረቦች ተረባርበን ሠራን፡፡ ከዛ የራሳችንን ግምገማ ማካሄድ ጀመርን፡፡ ቀድሞም ጥናቱ ነበረን፡፡
በተመልሶ ከቤተሰብ መዋሃድ የልጆቹ ቁጥር እያነሰ እያነሰ ሲሄድ ኮሙኒቲ ውስጥ ገባን፡፡ በመጀመሪያ የገባነው ቀበሌ ዘጠኝ ነው፡፡ ቀጥሎ ቀበሌ 4 ቀጥሎ ወደ 5 ቀበሌዎች ገባን፡፡ እንግዲህ እንሠራ የነበረው ሥራ መጀመሪያ ሁለት ሥራ ነው፡፡ የሠራነው 1ኛ/ ዕውቀቱ ስለነበረን፣ እኛ ቀደም ቀደም አልንና ፕሮጄክት እየሰራን ጀመርን (ቀበሌ 9 ላይ) ማደራጀት ጀመርን፡፡ ጥናታችን ታሪካዊ ነው፡፡
ስንጀምር ከዞን ጀምረን እስከ ወረዳ የሚመለከታቸውን የትምህርት፣ የጤናም፣ የግብርናም፣ የከተማ ትምህርትም ብቻ ሁለት ሁለቱን እያጣመድን አመጣን፡፡ ያ ዘዴ እንዴት እንደጠቀመን ግን ልነግርህ አልችልም፡፡ ራሳቸው ፋሲሊቴተር ሆነው ቁጭ አሉልህ፡፡ እናቶችን ለብቻ፡፡ ወጣቶችን ለብቻ፡፡ አረጋውያንን ለብቻ፡፡ እነሱ አመቻች ሆኑልን፡፡ ወደዛው ፕሮጄክት አደረጉልን ማለት ነው፤ ባለቤት ሆኑልን ማለት ነው፡፡ ታሪካዊ እምልህ ለዚህ ነው፡፡”
“ለምን ከ09 ጀመራችሁ?” አልኩት፡፡
09 ካምፕ ነው፡፡ ስትገባ የመጀመሪያው - ጠባሴ፡፡ አባት የለም (አብዛኛውን አባት የለም family headed ይሆን የነበረው በእናቶች ነው) አባት ወይ ሰሜን ጦርነት ሄዷል፤ ወይ ሞቷል፣ አንዳንዱም ምንም አይታወቅም፡፡ የወታደር ባህሪ ነው ያለው። ከመንግሥት ጋራ በጋራ አጥንተን፣ እያንዳንዱን ቀበሌ ተንትነን አውቀን፣ የመጨረሻው ደሀ አዚህ መሆኑን አየን። በትክክል ከዛ ጀመርን፡፡ የትምክህት ኮሚቴ፤ የጤና ኮሚቴ፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናት ኮሚቴ፣ አቋቋምን፡፡ ቀስ በቀስ ወደ ማህበረሰብ ይዞታ አሸጋገርን! ኮሚቴዎችን አንድ ላይ አደረግንና የመጀመያውን ማኅበራችንን ያቋቋምነው ቀበሌ 9 ነው፡፡ ይሄንን ልምድ ወደ ሌሎቹ ቀበሌዎች ወሰድን፡፡ አብዛኛዎቹ ከኛ ጋር የሚሠሩት ማህበራት ራሳቸውን ችለዋል፡፡ ቀበሌ 9 የነበረው ዛሬ በሁለት ተከፈለ 09/07፡፡
አሁን የምታየው እንግዲህ አንድ ራሱን ችሎ የቆመ (graduate ያደረገ) ማህበር ነው፡፡ እያንዳንዱ ቀበሌ ላይ የምታየውን አሁን መንግሥት “የልማት በጐ አድራጐት” ብሎታል፡ ምዝገባው (Registration) ላይ አታግሎናል፡፡
ጐጃም ውስጥ የልምድ ልውውጥ ፕርግራም ወሰድን፡፡ እዚያ ሄደው አይተው ሲመጡ፤ በዕውነት ትልቅ ለውጥ ነው ያየነው፡፡ አገዘን፡፡ ሌላጋ አዩት፡፡ የተቀደሙና የቀሩ መሆኑን አዩት፡፡ ለውጥ መጣ!! ከዛ አዲስ ነገሮችን አመጣን - የዕድሮችን ህብረት ማቋቋም ጀመርን፡፡ አንዳንዱ ቀበሌ ላይ የዕድሮች ህብረት አለ Self Help Group፣ Cluster Level Association፣ Federation እና Confederation፡፡”
እንግዲህ ይሄን ይሄን ስናወራ ቀበሌው ጋ ደረስን፡፡ ጋሽ ዓለማየሁ ከአመራሮቹ ጋር አስተዋውቆኝ ሄደ፡፡ እኔ ከማህበሩ ፀሐፊ ከወይዘሪት ኤልሳቤጥ በርሃኑ ጋር ውይይት ቀጠልኩ፡፡
“ቀድሞ ጄክዶ እዚህ ቀበሌ 08 ውስጥ ልማታዊ ሥራዎችን ይሠራ ነበር፡፡ እኔ በጐ ፈቃደኛ ሆኜ ሰርቻለሁ - ሲመሰረት ጀምሮ አለሁኝ፡፡
ይህ ማህበር 96/97 ዓ.ም ከተቋቋመ በኋላ ይሄንን ማህበር የነሱ ሥራ ቀጣይነትና ዘላቂነት እንዲኖረው ለማድረግ፣ ማ/ሰቡ ንዑሳን ኮሚቴዎችን በማሰባሰብና በማደራጀት እንዲቋቋም ተደረገ፡፡ በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉ የማ/ሰብ ክፍሎች ናቸው:: ሲመለመሉ በዕድሮች ነው፡፡ በንዑሳን እድሮች በየቀጠናው ኮሚቴዎች አሉ፡፡ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያለ ብለን የመጣውን ሰው እንመዘግባለን፡፡ የዕድሮች አመራሮች፣ የቀጠና ንዑሳን ኮሚቴዎች፣ የቀበሌ አመራሮች ባሉበት ቁጭ ብለን እናያለን::
አሁን ግን ቀበሌ ላይ ጥምረትና እንክብካቤ ተቋቁሟል። በዛ መሰረት፤ ችግርተኞች ዞረን አይተን ድጋፍ ይገባቸዋል የምንለውን እናረጋግጣለን:: ወደ ድጋፉ እንገባለን:: 5 ፕሮግራሞች አሉን:- 1ኛ/ ህፃናት ላይ 2ኛ/ ትምህርት ማጠናከሪያ ላይ 3ኛ/ግብርና ላይ 4ኛ/ ጤና ላይና 5ኛ/ ኑሮ ማሻሻያ ላይ፡፡
ማህብረሰቡ /ዝቅተኛ ሁኔታ ላይ ያለው/ ተጠቃሚ እንዲሆን ነው የምንሠራው:: ማህበሩ የሚመራው በቮለንቲር ኮሚቴዎች ነው:: ነፃ አገልግሎት ማለት ነው፡፡ ቢያንስ እኔና እሱ/ ታምራት /እዚህ እምታዩት ሱቅ - የተወሰነ የኪስ ገንዘብ ለጠባቂ ለሻጭ(ማረጋጊያ ሱቅ) እና ለኛ የኪስ ገንዘብ እየተሰጠን ነው እምንሠራው:: ሰባት አባላት ያሉት ንዑስ ኮሚቴ ኦዲትና ቁጥጥር አማካሪ ቦርድ አለን:: ማህበሩ ሲቋቋም ከማህበረሰቡ የተውጣጣ ከሚቴ ነው በበላይነት የሚመራው፡፡
“ገቢያችሁ ምንድን ነው?” አልኳቸው፡፡ ገንዘብ ያዡ አቶ ግርማ መለሱልኝ፡- የእህል መጋዘን አለን፡፡ አንድ ባጃጅ አለችን - በተገኘው ገንዘብ የተገኘች፡፡ ዕድሜ ለጄክዶ (የእየሩሣሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ድርጅት) የተገኙ የወተት ላሞች አሉ። ጽ/ቤት፤ በፊት እየተከራየን ነበር - ከቦታ ቦታ እየሄድን ነበር የምንሠራው፡፡ አሁን ግን ደፈር አልን፡፡ ቦታውን ገዝተን የማኅበሩን ቢሮ እዚህ አደረግን፡፡ ድጋፍ አድራጊዎቹ ፌዝ-አውት አድርገዋል:: እኛ ግን ራሳችንን ችለናል::
የጄክዶን አስተዋጽኦ ስትል ኤልሳቤጥ ፍጽም ፈገግታ አላት፡፡ ታምሩ ኪዳኔ የተባለው የበጐ አድራጐት ሥራ ባልደረባዋ ተቀበላት -
“በዝቅተኛ ዋጋ ለህብረተሰቡ እህል ያቀርባል:: ገበያውን የሚያረጋጋና ህብረተሰቡን ተደራሽ ነው:: ላሞቹ አንድ አመት ግድም ነው ከመጡ:: ይታለቡና ወተት ለሚሰበስቡ ድርጅቶች ይሰጣል:: ባንክ ገቢ ይደረጋል፡፡ የራሳቸው አካውንት አላቸው። ከዛ ለቀለባቸው ይወጣል፡፡ ተዘዋዋሪ ፈንድ ይደረጋል” አለ::
ኤልሣ ቀጠለች “ወተቱ ላካባቢው አገልግሎት ይሰጣል፤ ተረፈ ምርት ነው፡፡
አካባቢው አረቄ አውጪ ስለሆነ ኩበት የመግዛት ዕድል ያገኛል
ቫይረሱ በደማቸው ላለ ህፃናት የትኩስ ወተት ድጋፍ እናደርጋለን
ከቀለብ በተረፈው ንፅህና አልባሳት፣ የጫማ፣ የትምህርት መሳሪያ፤ ድጋፍ እናደርጋለን
ሁለት ሥራ አጥ ወጣት ተንከባካቢና አላቢ በመሆን የሥራ ዕድል አግኝተዋል”፡፡ በረት ጠራጊ + ወተት አመላላሽ + ጥበቃ ሠራተኞችም አሉ::
ዕድሜ ለእየሩሳሌም የህፃናትና የህብረሰብ ልማት ድርጅት!” አለች፡፡
“ወደ ፊትስ ለዘለቄታችሁ ምን አደረጋችሁ?” አልኳት፡፡
“ወደፊት እዛው አካባቢ ላይ ሻይ ቤት ነገር ከፍተን ወተቱን ለነጋዴ ከመስጠት እርጎም፣ አይብም፣ አጓትም እንሸጣለን፡፡ ገቢ ማስገኛ ነው፡፡ ነገ ይገባል ብለን የምናስበው የዳቦ ማሽን ከበጐ አድራጊ አግኝተናል:: ዳቦና ወተት በቅናሽ! ማህበረሰቡ ይጠቀማል፡፡ በተጨማሪ በጉባዔው በዓመት ሁለት ጊዜ ስብሰባ አለን፡፡ ወጣቱንም፣ ሴቱንም፣ ጎልማሳውንም የሚወክለውን እናገኘዋለን:: የሃይማኖት አባቶችንም እናወያያለን፡፡”
“ቀበሌውም አብሮን አለ” አሉ አቶ ግርማ:: አመኔታው ላይ መጀመሪያ ብዥታ ነበር:: ለ3ዓመት ተመርጠን ነው - ሁለተኛ ዙር ላይ ነው ያለነው፡፡ መጀመሪያ ህብረተሰቡ አልገባውም ነበር፡፡ “ከኔ እሚበልጡ ታዋቂ ተደማጭነት ያላቸው አሉ… ለምዝበራ ማይጋለጡ መሆናቸውን ጠንቅቆ ያውቃል:: ሂሳብ አያያዛችን አይጠረጠርም- ዘመናዊ ነው፡፡ ቦርዶች አሉን - መጥተው ይገመግሙታል::
ወደፊት ውጤታማ እንሆናለን! ቮለንተሩ አይደክምም በውጤቱ ደስተኛ ነው! ጥቅምም ባይኖረው በህብረተሰቡ ጥቅም ስለምንረካ ጉልበታችንን መስዋዕት እናደርጋለን:: ከሌላ ቀበሌዎች ጋራ የልምድ ልውውጥ እናደርጋለን:: ጄክዶ ፕሮጄክቱን ጨርሶ ቢወጣ እንዴት ዘላቂ እንደምንሆን ስላሰለጠነን እናውቅበታለን፡፡
ህብረተሰቡ የራሱን ፈጠራ ይሰራል:: ራሱ መንቀሳቀስ ሲችል እንጂ በእርዳታ የትም አይደረስም! ገቢውን ማምጣት፣ ማመረትና ራሱን መቻል አለበት”::
ልበ - ሙሉነታቸው በጣም ደስ አለኝ፡፡
ከሰዓት በኋላ የከተማ ግብርናን መሠረት አድርጐ ወደተመሠረተው የቀበሌ ማህበራት ስብሰባ ልሄድ ተሰናብቻቸው ከጋሼ ዓለማየሁ ጋር ወደምሣዬ ተጓዝኩ፡፡
(ጉዞዬ ይቀጥላል)

Read 2576 times