Saturday, 02 November 2013 11:12

ንግስት ሳባ አረብ ሳትሆን ኢትዮጵያዊት ንግስት ናት!

Written by  በአንዱአለም ናስር andualemnassir@gmail.com
Rate this item
(36 votes)

በታላቁ መጽሃፍ “መጽሃፍ ቅዱስ” ላይ በመጽሃፈ ነገስት ቀዳማዊ ላይ በምዕራፍ 10 ከቁጥር 1 እስከ 13 ድረስ ንግስተ ሳባ ጠቢቡ ሰለሞንን ጎብኝታ ወደ ሃገሯ እንደተመለሰች ይናገራል፡፡ ዓረቦች ይህንን ታሪክ የግላቸው ለማድረግ መጠነ ሰፊ ጥረት አድርገዋል፤ ባይሳካላቸውም፡፡ ንግስተ ሳባ የራሳቸው ንግስት በመሆን ጠቢቡን ጎብኝታ ለመመለሷ እንደ ማስረጃ የሚያነሱት በዓረቦች ውስጥ የሳባ ዓረቦች የሚባሉ ነገዶች ነበሩና የነሱም መጠሪያ ይህችው ሳባ ናት በማለት ነው፤ የርሷም መነሻ ዓረብ ነው በማለት፡፡ “ንግስተ ሳባ የኛ የሃገራችን ንግስት ሆና ጠቢቡ ሰለሞንን ለማየት ወደ ኢየሩሳሌም ከኢትዮጵያ ሳይሆን ከሃገራችን ተነስታ ሄደች፡፡” የሚልም በመጽሃፋቸው “በቁርዓን ሲራ 27” ላይ ሰፍሯል፡፡ የኛ ኢትዮጵያኖች ደግሞ “አይደለም ተሳስታችኋል… ንግስተ ሳባ ኢትዮጵያዊት ነች እንጂ እናንተ እንደምትሉት ዓረብ አይደለችም፡፡” በማለት ቀደምት አባቶቻችን ሞግተዋል፡፡ እኔም ከዚህ በኋላ በየደረጃው ኢትዮጵያዊት መሆኗን የሚያስረዱ ምክንያቶችን እያነሳሁ አልፋለሁ፡፡
ከቀደምት አባቶቻችን ከወረስናቸው የታሪክ መጽሃፍት እንደምንረዳው@ ንግስተ ሳባ ኢትዮጵያዊት ንግስት ብሎም የቀዳማዊ ምኒልክ እናት መሆኗን አረጋግጠናል፤ በዘመኗ ከመንግስቷ ኃያልነት የተነሳ የግዛቷ ስፋት የዓረብ ሃገራትን ያካትት ነበር፡፡ በመሆኑም እርሷ ጠቢቡን ለመጎብኘት ግዛቷ በሆኑ የዓረብ ሃገራት በኩል ለንጉሱ የሚሆን እጅ መንሻና አምኃ በግመሎቿ አስጭና እንደሄደች የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ፡፡ እነርሱ እንደሚሉት ዓረብ ሳትሆን ኢትዮጵያዊት ንግስት ነች፡፡
በመጽሃፍ ቅዱስ የንግስተ ሳባ@ ንጉስ ሰለሞንን መጎብኘቷን ከመተረኩ በተጨማሪ በሌሎች ኢትዮጵያዊ መጽሃፍት ላይ ንግስተ ሳባ “ማክዳ” (በጊዜው የንግስት ሳባ መንግስት መቀመጫውን ያደረገባት የኢትዮጵያ ከተማ ነች) እየተባለች ተጽፋለች፡፡ በኢትዮጵያ ከሚገኙት ታላላቅ መጽሃፍት መካከል አንዱ “ክብረ ነገስት” ነው፡፡ በዚህ መጽሃፍ ላይ የኢትዮጵያ ንግስና በቀጥታ ከንጉስ ሰለሞንና ከንግስት ሳባ ልጅ በሆነው በቀዳማዊ ምኒልክ እንደወረደ እንዲህ ይተርካል “ከጌታ ልደት በኋላ በ325ዓም በኒቅያ ጉባዬ ለተሰበሰቡት ሮማዊው ፓትሪያርክ ዶሚስዩስ@ ከቅድስት ሶፍያን ቤተክርስቲያን ውስጥ ባለው መጽሃፍ ላይ “የኢትዮጵያ ንጉስ በቀጥታ (በብኩርና) መስመርና ተርታ ከሰለሞን ንጉስ ይወርዳል፤ የሮም ንጉስ ግን በታናሽነት መስመር ይወርዳል፡፡” የሚል አለ ይሄው መጽሃፍ ደግሞ የኢየሩሳሌንምን ግማሽና የዓለምን ደቡብ በሙሉ ለኢትዮጵያ ንጉስ’ የቀረውን የኢየሩሳሌምን ክፍልና የሰሜንን ክፍል ለሮም ንጉስ ይሰጣል ብሎ ለጉባዬው ነገራቸው፡፡” የሚል እናነባለን፡፡
ይህ በአስረጅነት ያቀረብነው መጽሃፍ እንደሚለው’ንጉስ ሰለሞንን ለመጎብኘት የሄደችው ኢትዮጵያዊቷ ንግስት ማክዳ ናት፡፡ የሳባ ነጋዴዎች በባህር እስከ ህንድ፣ በየብስም እስከ ሴኤን (አስዋን የግብጹ) ድረስ እየሄዱ ትልቅ ንግድ ይነግዱ ነበር፡፡ ከነዚህ ነጋዴዎች አንዱ “ታምሪን” የተባለው ነጋዴ ስለ ንጉስ ሰለሞን እጅግ በጣም የሚያስገርም ነገር ነገራት፤ ይህን በሰማች ጊዜ ንጉስ ሰለሞንን ሄዳ ለመጎብኘት ተመኝታ ለንጉስ የሚገባ እጅ መንሻና አምኃ የሚሆን በብዙ ግመል አስጭና ኢየሩሳሌም ሄደች፡፡ ንጉሱን ካየች በኋላ ወደ አገሯ ተመለሰች፡፡ ዳሩ ግን አገርዋ ሳትገባ “በላ-ዘዲዛርያ” አጠገብ አንድ ልጅ ወለደች፡፡ ልጁም “በይነ ለሐኪም” (የሳባ ልጅ በክብረ ነገስት ላይ “በን ለሐኪም” ብሎ ይጠራዋል፡፡ በን ለሐኪምን በይብራይስጡ “በን ሀሐካም”፣ ዓረቦቹ “ኢብን ኤል ሐኪም” የተባለው ፍቺው “የጠቢብ ልጅ” የሚል ነው፡፡ በግዕዙ “መኑ ይልህቅ” በመጨረሻም “ምኒልክ” ብሎ ይፈታዋል።) በይነ ለሐኪም 22 ዓመት ሲሞላው የንጉሱን ጥበብ ለንግስቲቱ ከነገራት ነጋዴ ታምሪን ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፡፡ የሄደበትም ምክንያት ንጉስ ሰለሞን ለኢትዮጵያ ንጉስነት እንዲቀባውና ሃገሪቱንም ከአረመኔነት (ከአረማዊነት) ለማውጣት በማሰብ ነበር፤ አካሄዱም ከንግስት ሳባ የተላከ መልዕክተኛ ሆኖ ነበር፡፡ ንጉስ ሰለሞን ግን የመልኩን መምሰልና ለንግስቲቱ ማስታወሻ ብሎ የሰጣትን ቀለበት በማየት ልጁ እንደሆነ ካረጋገጠ በኋላ’ “ሮብዓም” የተባለው ልጁ ገና የስድስት ዓመት ልጅ ስለነበረ’በን ለሐኪምን በእስራኤል መንግስት ላይ ወራሹ እንዲሆን ፈልጎ ነበር፤ በን ለሐኪም ግን ፈቃደኛ አልነበረም፡፡
የበን ለሐኪምን ፈቃደኛ አለመሆን የተቀበለው ንጉስ ሰለሞን ‘ልጁን ከሸዋ ደቡብ እስከ ህንድ ምስራቅ ድረስ በተዘረጋው ምድር ላይ የኢትዮጵያ ንጉስ አድርጎ በጊዜው በነበረው ካህን “ሳዶቅ” አስቀባው፡፡ ንጉሱም በኢየሩሳሌም የሚሰሩትን ታላላቅ ስራዎች በኢትዮጵያ ከበን ለሐኪም ጋር እንዲፈጽሙ በማሰብ’ ከእስራኤል ትልልቅ ሰዎች የተወለዱትን ጨምሮ ላከው፤ እነሱም ከኢየሩሳሌም ሲነሱ ጽላተ ሙሴን ከቤተ መቅደስ አውጥተው ወሰዷት፡፡ ታቦተ ጽዮን መወሰዷን የሰማው ንጉስ ሰለሞን@ልጁ በን ለሐኪምን ተከታትሎ ሊመልሳት ፈልጎ በጣም በመራራቃቸው የተነሳ ሊደርስባቸው ባለመቻሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ፡፡ በን ለሐኪምና ተከታዮቹ በሰላም ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ገቡ፡፡ ወደ ግዛታቸው ከገቡም በኋላ በአዜብ፣ በዋቂሮና በሜዛስ አልፈው ከከተማቸው ደብረ ማክዳ ደረሱ፡፡ ጽላተ ኪዳኗንም ከተራራ አናት ላይ አኖሯት፡፡ በይነ ለሃኪምም የመንግስቱን ስልጣን ከንግስት እናቱ ሳባ ተረከበ፡፡ ሌዋውያንና ሌሎቹ ከኢየሩሳሌም የመጡት ነገዶች ሁሉ በመንግስቱ ግዛት ላይ ሃይማኖትንና የብሉይ ሥርዓትን (የእስራኤል ትዕዛዛት) አቆሙ፡፡ መንግስቱም በሃይልና በብስለት የተጠናከረ ሆነ፡፡
በ1940ዎቹ በኣባ ፓስፓራኒ (በጊዜው የአስመራ ኮምቦኒ ኮሌጅ ዳይረክተር ነበሩ) “የኢትዮጵያ ታሪክ” በሚል መጽሃፍ ላይ የመንግስቱን ሃያልነት ሲናገሩ “በን ለሐኪም መንግስቱን ካደላደለ ከጥቂት ወሮች በኋላ ዘመቻ አደረገ፡፡ ሰፈሩንም “ከማየ አበው፣ የአባቶች ውሃ” (በዓባይ ዙሪያ ላይ ያለ ቦታ እንደሆነ ይገመታል) ላይ አደረገ፡፡ ከዚያ የዞውንና የሃዲያን መሬት ያዘ፤ ከዚያ ቀጥሎ ኖባንና ሶባን ወግቶ እስከ ግብጽ ወሰን ድረስ ዘመተ፡፡ የግብጽና የምድያም ነገስታት በጣም ፈርተው ሰላማዊነታቸውን የሚያስታውቅ መተያያ ላኩለት፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ሃገሩ ተመልሶ ከከተማው ገብቶ እንደገና ወደ ህንድ ቢዘምት ንጉሱ እጅ መንሻ አቅርቦለታል፡፡” በማለት የቀዳማዊ ንጉስ ምኒልክ መንግስት ምን ያህል ኃያል እንደነበረ ገልጸዋል፡፡
የንግስተ ሳባ ጠቢቡ ሰለሞንን መጎብኘት እጥፍ ድርብ የሆኑ አላማዎችን ያካተተ ነበር፤ ንግስተ ሳባ የሄደችበት ዓላማ በራሱ እርሷ የኢትዮጵያ ንግስት እንደነበረች ያመለክታል፡፡ አንድ ሁለቱን እንመልከት:-
የመጀመሪያው ዓላማ ተብሎ የሚወሰደው በእንቆቅልህና በምሳሌ የሰለሞንን ጥበብ ለመርመርና ለመፈተን መጓዟ ነው፤ ንጉሱ ጥበብ አዋቂ በመሆኑ መደነቋም የግብጽና የባቢሎን ነገስታት አስቸጋሪ ጥያቄዎችን (እንቆቅልሾችን) ምሳሌ እየቀረቡ ከሊቃውንት ጋር መነጋገር መውደዳቸውን በታሪክ እናገኛለን፤ ኢትዮጵያም የዚህ አካል ነበረች፡፡
ሌላኛው የንግስተ ሳባ ዓላማ በእርሷና በሰለሞን መንግስት መካከል የንግድ ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ መፈለጓ ነበር፡፡ እርሷ በሃገሯ የሞላውን ሽቱ፣ ወርቅ፣ ዝባድና የተከበሩ ድንጋዮችን (የነዚህ ማዕድናት መገኛ ኢትዮጵያ መሆኗን ልብ ይሏል) በመላክ በሃገሯ የማይገኙትን የንግድ እቃዎች መውሰድ በመፈለጓ ነው፡፡
ለዚህ ጽሁፍ የመጨረሻ የማደርገውና በርግጥ ንግስት ሳባ ኢትዮጵያዊ መሆኗን ማስረዳት የሚችለው የንጉስ ሰለሞንና የንግስት ሳባ የንግስና ዘመናቸው አንድ መሆኑ ነው፡፡ በክብረ ነገስት ላይ እንደሚገኘው ታሪክ@ ንጉስ ሰለሞን ከጌታችን ከእየሱስ ክርስቶስ ልደት በፊት በ1972 እስከ 1932 ዓዓ ድረስ በኢየሩሳሌም ላይ ልክ ለ አርባ ዓመታት መንገሱን ይነግረናል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ንግስተ ሳባ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የነገስታትን ተርታና ትውልድ ያየን እንደሆነ’ ሳባ ከጌታችን ከእየሱስ ክርስቶስ ልደት በፊት ከ1982 እስከ 1957 ዓዓ ድረስ በኢትዮጵያ ላይ ለሃያ አምስት ዓመታት እንደነገሰች የሚያመለክት የታሪክ ጽሁፍ እናገኛለን፡፡ በመሆኑም ጠቢቡ ንጉስ ሰለሞንና ኢትዮጵያዊቷ ንግስት ሳባ የነገሱባቸውን አዝማናት ያየን እንደሆነ ያለ ጥርጥር ይህች ንግስት ኢትዮጵያዊት ነች ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ ነገስታት ታሪክ ላይ የሚገኘው ቀዳማዊ ምኒልክም የስሙ ትርጓሜ “የጠቢብ ልጅ” ተብሏልና ይህም ጠቢብ ታላቁ የኢየሩሳሌም ንጉስ ጠቢብ ሰለሞን ነው፡፡

Read 25405 times