Saturday, 02 November 2013 11:10

“የቱሪስት ያለህ” የምትለው ሰሜን ሸዋ

Written by  መልካሙ ተክሌ
Rate this item
(3 votes)

አድዋ ላይ ከወደቁት ጀግኖች ኢትዮጵያውያን አንዱ የሆኑት ፊታውራሪ ገበየሁ፤ “ጠላትን ስሸሽ ከሞትኩኝ አስከሬኔን እዚያው ቅበሩ፤ ጠላትን ፊት ለፊት ተጋፍጬ ከሞትኩ ግን አስከሬኔን በሀገሬ ይቅበሩልኝ” ሲሉ አፄ ምኒልክን ቃል አስገብተዋቸው ነበር፡፡ የአድዋ ጦርነት ተጀመረ፡፡ ባልቻም እያዋጉ ጠላት ያለበት ድረስ በድፍረት ዘለቁ፡፡ ጠላት አናታቸውን በጥይት ሲነድል የፊት ጥርሳቸው ረግፎ በክብር ለአገራቸው ነፃነት ወደቁ፡፡ በሕይወት እያሉ-
“የአድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው
ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው” የተባለላቸው ገበየሁ፤ አድዋ ሥላሴ ተቀብረው ከቆዩ በኋላ አፅማቸው ወደ አምባላጌ ጊዮርጊስ ተወሰደ፡፡ በቃል ኪዳናቸው መሠረት ከሰባት ዓመት በኋላም አጽሙ በአገራቸው በአንጎለላ ኪዳነምሕረት አረፈ፡፡ አሁን የፊታውራሪ ገበየሁ አጽም፤ አቶ አብርሃም ደምሴ በተባሉ ግለሰብ በመስታወት ውስጥ እንዲቀመጥ ቢደረግም ጉስቁልቁል ብሎ ይታያል፡፡
ከቤተክርስትያኑ በአጭር ርቀት ደግሞ በባቄላና ስንዴ ማሳ መሃል፣ የአያትየው ሳሕለ ሥላሴ ቤተመንግስት ፍራሽ ይታያል፡፡ የፍራሹ ምድር ቤት ግን አሁንም አለ፤ ቢጎሳቆልም፡፡ አጠገቡ የብዙዎችን ቀልብ የሳበውና ሳሕለሥላሴ ጠጅ እያጠጡ አሳደጉት የተባለ መንታ የሾላ ዛፍም አለ። በአንጎለላ ኪዳነምሕረት ቤተክርስትያን ውስጥ ጥንታዊ የቤተክርስትያን መገልገያ ቁሳቁስ፣ የተለያዩ የድሮ አልባሳት፣ የብራና መጻሕፍትና የምኒልክ ዳግማዊ የወርቅ ዘውድ ተቀምጠዋል፡፡ በቦታው የምኒልክ ሐውልት ቆሞ ጤና ጣቢያ ቢቋቋምበትም ጃንሆይ ምኒልክ ተወለዱባት የተባለችው ቤት፣አሁን ሣር የበቀለባት የድንጋይ ቁልል ሆናለች፡፡ ቦታው የቤተመዘክር (ሙዚየም) ያለህ የሚል ይመስላል፡፡
ቅርሳቅርሶች በግለሰቦች ቤትና በቤተክርስትያኒቱ ዕቃ ቤት ውስጥ የሚገኙ ሲሆን የቅርስ ምዝገባ አልተካሄደባቸውም፡፡ ለምን ቅርሶቹ እንዳልተመዘገቡ የተጠየቁ አንድ የአካባቢው ቤተክርስትያን አስጎብኚ “ከተመዘገበ ይጠፋብናል” ብለዋል፡፡ ትኩረታችን እኒህ ስለሆኑ ነው እንጂ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ሸዋ ዞን፣ በእያንዳንዱ ኪሎ ሜትር በርካታ ቅርሶች አሉ፡፡ ባሉበት መጠበቅ አሊያም በቤተመዘክር መቀመጥ ይገባቸዋል፡፡ በየቤተክርስትያኑ እና በየግለሰቡ ቤት መቀመጣቸው በቀላሉ ለብልሽትና ለመጥፋት ይዳርጋቸዋል፡፡
በመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ፣ታዋቂ የሙስሊም ሥልጣኔ መገለጫ የሆነውና በሱልጣን ይተዳደር የነበረው ይፋት የሚገኘውም በዚሁ ዞን ሲሆን ታሪካዊ መስጊዶች የጠባቂ ያለህ እያሉ ነው። ጥበቃና እንክብካቤ ሲኖር እኮ ነው ጐብኒዎችን መማረክ የሚቻለው፡፡
ዞኑ ከ “ሐገሬ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን” ጋር በመተባበር፣በአካባቢው ያሉ ታሪካዊ መስሕቦችንና ሰው ሰራሽ ቅርሶችን የሚያስተዋውቅ “የሰሜን ሸዋ ዞን የቱሪዝም ማውጫ” ያሳተመው ጎብኚዎችን ለመሳብ አስቦ ነው፡፡ በዞኑ የሚገኝ እያንዳንዱ ወረዳ ያለውን መስሕብ በማውጫው ላይ የማስተዋወቅ እድል ተሰጥቶታል፡፡ ባለፈው ቅዳሜ የቱሪዝም ማውጫው የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሙሉጌታ ሰኢድ በተገኙበት ሲመረቅ፤ ትኩረቱ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ላይ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ ችግሩ ግን የቱሪዝም ማውጫው የታተመው በአማርኛ ብቻ ነው፡፡ ማውጫው በባለቀም ፎቶግራፎች ደምቆ ደረጃውን በጠበቀ ወረቀት ቢታተምም አንዳንዶቹ ፎቶግራፎች መግለጫ (Caption) የላቸውም፡፡ በማውጫው ውስጥ ከተጠቀሱ በርካታ መስሕቦች መካከል በአራተኛው ክፍለ ዘመን የተሠራው ኦፍና አማኑኤል ቤተክርስቲያን፣ አስከሬን የማይበሰብስበት የመልከጼዴቅ ገዳም፣ የለበቃ ኢየሱስ ፍልውሃ፣ የኢትዮጵያ አርበኞች ማሕበር የተመሠረተባት ግራር፣ በነቢዩ መሐመድ ጊዜ እንደተገነባ የሚነገርለት ሸዋ ሮቢት አካባቢ የሚገኘው የጐዜ መስጊድ፣ “የወፍ ዋሻ” የተፈጥሮ ደን፣ የሣህለሥላሴ ቤተመንግስት ፍርስራሽ፣ “ስድስት” መስጊድ፣ አሸም አገር መስጊድ፣ መገዘዝ ተራራ፣ ሊቅ ማረፊያ፣ አንኮበር ቤተመንግስት፣ ልበሊት ኢየሱስ ገዳም፣ የልቼ ከተማ ፍርስራሽ፣ የደብረሲና ዋሻ እና ከፍልፍል አለት የተሰራው ደብረ ከርቤ ዳግማዊት ጐልጐታ ገዳም ይገኙበታል፡፡
ለአዲስ አበባ ቅርብ የሆነው ሰሜን ሸዋ፤ በርካታ መስህቦች ቢኖሩትም ከቱሪዝም እምብዛም አልተጠቀመም፡፡ በተለይ ደግሞ ከውጭ አገር ቱሪስቶች፡፡ “ቱሪዝምን ለነጮች ብቻ ካደረግን ዶላር ናፋቂ ሆነን መቅረታችን ነው” የሚለው ባላገሩ አስጐብኚ ድርጅት፤ በሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ላይ በማተኮር እንደሚሰራ በቱሪዝም ማውጫ ምረቃው ላይ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ተናግረዋል፡፡
የዳግማዊ ምኒልክ፣ የአቡነ ተክለሃይማኖት፣ እግዚአብሔርን እና ሰይጣንን ለማስታረቅ የሞከረችው ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ፣ የአማርኛ ፊደል ገበታ በስፋት በማሰራጨት የሚታወቁት ተስፋ ገብረሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋ እና የሌሎችም ታዋቂ ኢትዮጵያውያን የትውልድ ስፍራ የሆነችው ሰሜን ሸዋ፤ በርካታ መስሕቦች ይኑሯት እንጂ በቂ በጀት እና በቱሪዝም መስክ የሰለጠነ በቂ ባለሙያ የላትም፡፡ በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ጥናት መሠረት፤ ከሁለት ሚሊዬን በላይ ሕዝብ ያላት ሰሜን ሸዋ፤ በቱሪዝም ከፍተኛ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ሦስት ባለሙያዎች ብቻ ናቸው ያሏት፡፡
ሰሜን ሸዋ ቱሪስቶችን ለመሳብ የምትሻ ከሆነ ቤተመዘክሮች መሥራትና ቅርስ መሰብሰብ፣ ስርቆሽና ዘረፋን መከላከል፣ በባለሙያ መደርጀት፣ ሆቴሎችና መንገዶችን ማሟላት እንዲሁም በቂ መረጃ መስጠት እንደሚጠበቅባት በቱሪዝም ማውጫው ምርቃት ላይ የተገኙ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡

Read 5156 times