Saturday, 02 November 2013 10:57

የአገልግሎት አሰጣጥ የስነምግባር ጉድለቶች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

                  የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ ተደጋጋሚ የነዋሪዎች እሮሮዎችና አቤቱታዎች ሲስተጋቡ የቆዩ ሲሆን መንግስት የአገልግሎት አሰጣጡን ለማቀላጠፍ፣ የስነምግባር ጉድለቶችን ለማሻሻል የተለያዩ እርምጃዎች መውሰዱ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን አሁንም ችግሮቹ እንዳልተፈቱ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ባለፈው ሰሞን የማህበራዊ ጥናት መድረክ “የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ስነምግባርና ተጠያቂነት” በሚል ርዕስ በግዮን ሆቴል ዎርክሾፕ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዎርክሾፑ ላይም የቀድሞ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነርና አሁን በግል አማካሪነት የሚሰሩት አቶ አትክልት አሰፋ እና የቀድሞ ሲቪል ሰርቪስ ጀነራል ዳይሬክተርና አሁን በግል ስራ ላይ የተሰማሩት የህግ ባለሙያ አቶ መስፍን ታፈሰ እንዲሁም የማህበራዊ ጥናት መድረክ ስራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር፣ ዶክተር ምህረት አየነው የቀረበውን ፅሁፍ የሚተች ዳሰሳ አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያ አስራ አራት የመንግሥት አገልግሎት ማሻሻያ ፕሮግራም እንዳላትና ሁሉም ፕሮግራሞች አገር በቀል እንደሆኑ የገለፁት አቶ አትክልት አሰፋ፤ ዋናው ፕሮግራም የመንግስት አገልግሎት (ሲቪል ሰርቪስ) ማሻሻያ እንደሆነ አስረድተዋል። በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ ተቋማት መቋቋማቸውን፤ የተለያዩ የህግ ማእቀፎችም መዘጋጀታቸውን አቶ አትክልት ጠቁመዋል፡፡ ችግሮች ቢኖሩም ትልቅ ለውጥ መታየቱን የተናገሩት አቶ አትክልት፤ የሙስናውም ደረጃ በንፅፅር ሲታይ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች የሚስተዋሉ የስነምግባር ጉድለቶች እና ግድፈቶችን ዘርዝረዋል፡፡
በመጀመሪያ የተዳሰሰው የትምህርት ዘርፍ ሲሆን በፈተና እና በውጤት አሰጣጥ ላይ የሚፈፀሙ ማጭበርበሮች፣ ጉቦ መቀበል፣ የሀሰት ትራንስክሪፕትና ሰርተፊኬት መስጠት፣ የመምህራንን እድገት እና ዝውውር ከጥቅም ጋር ማያያዝ፣ ሴት ተማሪዎችን ለወሲብ ማስገደድና የመምህራን ለግል ስራ ቅድሚያ መስጠት እንዲሁም በስራ ገበታ ላይ አለመገኘት የሥነምግባር ጉድለቶች ተብለው ተጠቅሰዋል፡፡ በጤና ዘርፍ ደግሞ ለኤክስሬይ እና ለቀዶ ጥገና አገልግሎቶች ጉቦ መጠየቅ፣ የሆስፒታል አልጋ በጉቦ ወይም በዝምድና እንዲሰጥ ማድረግ፣ ለታካሚዎች ተገቢውን እንክብካቤ ያለማድረግ፣ የባለሙያ የብቃት ማነስ፣ የመድሀኒት እና የአምቡላንስ አቅርቦት ያለመኖር፣ አላስፈላጊ ምርመራዎችን በማዘዝ ታካሚዎችን ላላአስፈላጊ ወጪ መዳረግ፣ ታካሚዎችን ወደ ግል ፋርማሲ እና ክሊኒኮች መላክ፣ ተቆጣጣሪን በጉቦ መደለል እና የማጭበርበር ድርጊት መፈፀም፣ መገልገያ ቁሳቁሶችን መስረቅ እና ፈንድ ያለ አግባብ መጠቀም እንደ ጉድለት ቀርበዋል፡፡
አቶ አትክልት፤ ፍርድ ቤቶች፣ አቃቤ ህጎችና ፖሊስ ዘንድ ይፈፀማሉ ያሏቸውን የስነምግባር ጉድለቶችም በዳሰሳቸው ዘርዝረዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል፡- ፍርድ ቤቶች እና አቃቤ ህጎች ውሳኔን ለማስቀረት ወይም ለመጀመር ጉቦ መጠየቅ ወይም መቀበል፣ የአቃቤ ህጎች ስልጣናቸውን በመጠቀም ክሶችን መግደል ወይም ነፍስ እንዲዘሩ ማድረግ፣ ክስን በአግባቡ ያለመያዝና በፍትህ አስተዳደሩ ላይ የሚታዩ መጓተቶች፣ የብቃት ማነስ እና ጉቦ በመቀበል ክስን ማቅለል… የሚሉት ይገኙባቸዋል። የፖሊሶችን የስነ ምግባር ጉድለቶች ሲጠቅሱም፤ እስረኞችን በአግባቡ ያለመያዝ፣ የትራፊክ ፖሊሶች ህገወጥ ሾፌሮችን በጉቦ ማሳለፍ እንዲሁም በፀጥታ ጥበቃ ላይ የተሰማሩ ፖሊሶች በጥፋት መጠየቅ ያለባቸውን በጥቅም በመደለል አለመጠየቅ፣ ማስረጃዎችን ለማድበስበስ ምስክሮችን እንዳይቀርቡ ማድረግ… የሚሉትን ዘርዝረዋል፡፡
በንግድና ኢንቨስትመንት ከሚስተዋሉ የስነምግባር ጉድለቶች ውስጥም ህገወጥ ፈቃድ መስጠት፤ በህገ ወጥ፣ ደረጃቸውን ባልጠበቁና ጥራታቸው በተጓደለ ምርቶች ላይ የሚደረግ ክትትልና ቁጥጥር የይስሙላ መሆን፣ የሸቀጦች እጥረት ላይ የሚደረግ ቁጥጥር ማነስ የተጋነነ የዋጋ ማሻቀብ እና የውድድር መንፈስን በሚቃረኑ እና ከእውነት በራቁ የሸቀጦች ማስታወቂያ ላይ የሚደረጉ ቁጥጥሮች ማነስ በጥናቱ ላይ ተጠቅሰዋል፡፡
ከመሬት ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ የስነምግባር ጉድለቶችን በተመለከተ ደግሞ በቤት ልማት ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶችን በቦታ አሰጣጥ ላይ በእኩል አይን አለማየት፣ የተጭበረበሩ የመሬት ባለቤትነት ሰርተፊኬትና ሰነድ አዘጋጅቶ መስጠት የሚሉት በዋናነት የስነምግባር ጉድለቶች ተብለው ተቀምጠዋል፡፡
የመንግስት ቤቶችን አስመልክቶም፤ ቤት ያለጨረታ ማከራየት፣ በኪራይ አሰባሰብ ላይ የብቃት ማነስና መዘግየት፣ በህገወጥ መንገድ ቤት በያዙና በተከራይ አከራይ ጉዳይ ላይ የክትትል ማነስ፣ ከህግና ደንብ ውጭ መስራት፣ በኪራይ ተመን ላይ ወጥ ያለመሆን እና የተቀናጀ የመረጃ ዘዴ ያለመኖር… የተጠቀሱ ሲሆን፤ በአገልግሎት ዘርፍም የእቃ ግዢና አቅርቦት ችግር፣ ተደጋጋሚ የመብራት እና የውሀ መጥፋት፣ የዘገየ የስልክ ጥገና እና ቀርፋፋ የኢንተርኔት አገልግሎት ጉድለት ተብለው ተዘርዝረዋል፡፡
የኮንስትራክሽን ዘርፉም ከስነምግባር ጉድለቶች አላመለጠም - በአቶ አትክልት ዳሰሳ መሰረት፡፡ ግንባታዎችን ማጓተት፣ ጥራቱን ያልጠበቀ ግንባታ መቀበል፣ የዋጋ መዛባት፣ በኮንትራክተሮች እና በሱፐርቫይዘሮች መካከል የሚደረግ መመሳጠር፣ ላልቀረቡ እቃዎች ክፍያ መፈፀም፣ ብክነት፣ ስርቆት እና አግባብ ባልሆነ መንገድ ተጫራቾችን መለየት የሚሉ ይገኙበታል፡፡
የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ላይ የሚታዩ የሥነምግባር ጉድለቶችን የዳሰሱት አቶ አትክልት፤ ህግን ባልተከተለ መንገድ ያለ እጣ ለነዋሪዎች ቤት መስጠት፣ ባልና ሚስትን የሁለት ቤቶች እድል ተጠቃሚ ማድረግ፣ የከተማዋ ነዋሪ ያልሆኑና ያልተመዘገቡ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ እና በርክክብ ላይ የሚታይ መዘግየትን ጠቅሰዋል፡፡ ለቀበሌ እና የወረዳ ተመራጮች
የሚሰጣቸው የቅድሚያ የቤት እድል፣ ብቃት የሌላቸውን ሰዎች ለስራ መመልመል፣ የነዋሪነት የቀበሌ መታወቂያና ሰርተፊኬት በጉቦ መስጠት፣ የገንዘብ ብክነት፣ በህገወጥ የቤቶች ግንባታ ላይ ወቅታዊ ቁጥጥር እና እርምጃ ያለመውሰድ እንዲሁም በስብሰባዎች መብዛት ሳቢያ የጊዜ አጠቃቀም ላይ የሚፈጠሩ ችግሮች ተዘርዝረዋል፡፡
ቀደም ሲል በብቃቱና በቅልጥፍናው የሚታወቀው ኢሚግሬሽን፤ በአሁኑ ወቅት ፓስፖርት ለመስጠት ረጅም ጊዜ እንደሚወስድበት የተጠቀሰ ሲሆን መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና በሲቪል ማህበራት ላይ ጠበቅ ያለ ቁጥጥር እንደማይደረግም አቶ አትክልት በጥናታቸው ገልፀዋል፡፡
በጥናቱ ላይ ትችት ያቀረቡት አቶ መስፍን በበኩላቸው፤ የስነምግባርና የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ዲዛይን ከጊዜ ጋር የመራመድ ሁኔታው ምን ይመስላል? ትግበራውስ ምን አይነት ቅደምተከተል የያዘ ነው? በማሻሻያ ፕሮግራሙ ላይ የሰው ሀይሉ ሚና ምን ይመስላል? ቢፒአር ምን ያህል ከፖለቲካ የፀዳ ነው? ውጤታማ ነው ሲባል ውጤቱ እንዴት ይለካል? የሚሉ ጥያቄ አዘል ትችቶችን ሰንዝረዋል፡፡
ዶክተር ምህረት ደግሞ ትኩረት ያደረጉት በጥናታዊ ፅሁፉ ጎልተው መውጣት አለባቸው ባሏቸው ነጥቦች ላይ ነው፡፡ በመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ስነምግባር እንዲሰፍንና ተጠያቂነት እንዲጎለብት በሙያው የዳበረ፣ ነፃና በችሎታው ብቻ የተመረጠ የመንግስት ሠራተኛ ወሳኝ ነው ብለዋል። “ሰራተኛው ከፓርቲ ወይም ከፖለቲካው ቁጥጥር ነፃ ሆኖ በሙያው የተካነና ለሀላፊነቱ ተጠያቂ ቢሆን አብይ መስፈርት ነው ብዬ አስባለሁ” ብለዋል፡፡ “የስነ ምግባር ወይም የአፈፃፀም ጉድለቱን በፓርቲ ጥላ ስር መደበቅ ያለበት አይመስለኝም፡፡ በሙያው ይፈረጃል፤ ይመለመላል፣ ያድጋል፣ ይደራጃል፡፡” ሲሉም አብራርተዋል፡፡
ነፃ የሆነና በሙያው የተካነ ጋዜጠኛና ሚዲያ መኖር ዋነኛ የፖሊሲ ጥያቄ እንደሆነም ዶ/ር ምህረት ተናግረዋል፡፡ ተንቀሳቅሶ ማንቀሳቀስ የሚችል ሲቪል ማህበረሰብ ያስፈልጋል፤ ይሄ ጎላ ብሎ መውጣት አለበት ያሉት ዶ/ሩ፤ ነፃና ጠንካራ የሙያ ማህበራት ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡ “ዎች ዶግ” ተቋማት ነፃ ሆነው በህግ መሰረት መጠናከር እንዳለባቸውም ገልፀዋል። “ማሻሻያው” ብዙ ነው፤ የአንዱ ጥቅምና ጉዳት ሳይታይ በላዩ ላይ መደረብ ጉዳት አለው” ብለዋል - ዶ/ር ምህረት ባቀረቡት ጥናት፡፡

Read 5776 times