Saturday, 02 November 2013 11:06

“ጳጉሜ ስድስት” ስለየትኛው ዘመን መቁጠሪያ ነው የሚናገረው?

Written by  ሰሎሞን አበበ ቸኮል saache43@yahoo.com solomon.abebe.395@faceook.com
Rate this item
(5 votes)

ለምሑራኑ እና ለጸሐፊዎች በጭራሽ ሊገቡ ያልቻሉ የኢትዮጵያ ውርስና ቅርሶች አሉ ከተባለ የዘመን መቁጠሪያው አንዱ መሆን አለበት፡፡ በ1990ዎቹና ከ2000 ዓ.ም ወዲህ ብቻ አሥር የሚጠጉ ጽሑፎች በመጽሐፍና በድረ ገጽ ቀርበውበታል፡፡ ይህንኑ በቀጥታ የሚመለከቱ የምርምርና ጥናት ሥራዎች፣ ዓውደ ጥናቶችና ዓውደ ርዕይ ቀርበውበታል፡፡
የትኞቹም ግን ያላንዳች ጉድለት አያቀርቡትም። ምን ያህል በሚገባ እና በትክክል ገልፀውታል በማለት የሚሻለውን እንመርጥ ይሆናል እንጂ አንዳቸውም ያላንዳች እንከን ፈጽመውታል አንልም፡፡ (የዘመን መቁጠሪያው መምሕር የሆኑትን ያሬድ ፈንታ ያሳተሙትን አይመለከትም፡፡)
ብዙዎቹ እንደ ትልቅና ጠቃሚ ሥራ ከሚቆጥሩት የፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ መጽሐፍ ጀምሮ እስከ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ ጥናታዊ ወረቀት ድረስ ስለመቁጠሪያው ስያሜ፣ ማንነት፣ ስለዓይነቱ፣ ስለታሪኩ የሚገለፁትን ያለጥያቄ ምልክት አናልፋቸውም፡፡
ምናልባት ሻል አድርገው ያቀርቡታል በሚባሉትም አንዳንድ ችግሮች ይታዩባቸዋል:: ከቅርቦቹ የህሩይ ስሜን እና የአብርሃም ደሞዝን ሥራዎች አንዳንድ ነጥቦችን ሳንነቅስ አናነብም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን በሚያቀርባቸው የጥናትና ምርምር ሥራዎች ላይ ንፋስ የማያስገባ መሆኑ ይታወቃል። ይህን መቁጠሪያ በተመለከተው ዓውደ ርእይ ግን ፀሐያዊነቱን የሚነግር ገለጻ ነበር የቀረበው፡፡ የመቁጠሪያው ምንጭም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ መግለጹ ሐሳበ ዘመኑ ከልደት በፊት ቢሄድ እስከ ሙሴ ዘመን ድረስ ብቻ ማድረጉን ልብ አላለውም። “ሕገ ሊቃውንት፣ ሕገ ሐዋርያት፣ ሕገ ካህናት፣ ሕገ ነብያት፣ ሕገ አበው…”
እያሉ “ሕግ አዳም፣ ሕገ መላእክትና ሕገ አምላክ” ብለው የሚገልጹት በመጽሐፍ ቅዱስ ዕድሜ ብቻ ከመወሰናቸው ጋር ይጣላል፡፡ በሌላ በኩል “የራሷ መቁጠሪያ ያላት” እያሉ የጁልያን፣ የአሌግዛንድርያን የሚሉ በራሪ ጽሑፎችንና ፀሐፊዎችን እንዲሁም ጋዜጠኞችንም አይተናል፡፡
አንዳንዱ ደግሞ በቅንነት፣ የጠቀምኩ መስሎት፣ ስለ ቀን መቁጠሪያው የተለየ ግንዛቤ የሚያስይዝ ጽሑፍ ያቀርባል፡፡ የዶክተር አበራ ሞላ የድረ ገጽ ጽሑፍ ከነዚህ መካከል ሊጠቀስ ይችላል፡፡ የዘመን መቁጠሪያውን የታሪክ ዘመን ያራቁት መስሏቸው ከጥንታዊው ግብጽ ጋር የሚመሳሰልበትን ለማሳየት ሞክረዋል፡፡አሁን ደግሞ (ይህን ለመጻፍ ምክንያት የሆነና) በጭራሽ ስለ ኢትዮጵያው ዘመን መቁጠሪያው ነው ለማለት የሚከብድ የምርምርና የጥናት ሥራ ቀርቧል፡፡ “ጳጉሜ ፮” የተባለ መጽሐፍ፡፡
መጽሐፉ፤ “የኢትዮጵያ ቀን መቁጠሪያ የማነው?” ይላል፡፡ ፋሲል ሰይፉ በተባሉ የኢኮኖሚክስ መምሕር የቀረበ ነው፡፡ መምሕሩ ስለቀን መቁጠሪያው ደገኛ ሐሳብን ይዘው ጥናትና ምርምር እንዳደረጉ አያጠያይቅም፡፡ ስለመጽሐፉ ይዘትም ሆነ አንዳንድ ዝርዝሮችን ማቅረብ ሳያስፈልግ፣ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ዘመን መቁጠሪያን፣ ከመቁጠሪያው (ክፍላተ ዘመን ወይም/እና አዕዋዳቱን ዕለት፣ ወርኅና አመት/ዓውደ ወርኅ እና ዓውደ አመትን) ሙሉ በሙሉ ፀሐያዊ እንደሆኑ አድርገው በመያዛቸው ብቻ በ፬ ክፍል/ምዕራፍ ከፍለው ምርምርና ጥናት በማድረግ ያቀረቡት በሙሉ ከንቱ ድካምን የደከሙበት ያህል ይሰማል፡፡ ይህም ሲገለጽ ኃዘንን ብቻ ሳይሆን ቁጭትንም ያመጣብን መሆኑን በማከል ይኾናል፡፡ “ያን ያህል በእጅጉ የለፉበትና አብዝተው የተጠበቡበት ምናለ ዘመን መቁጠሪያውን፣ በተለይም የአመት እና የወሩን አዕዋዳበት በሚገባ መጠን፣ ካልሆነም መሠረታዊ የሆኑትን በማወቅ፣ ያን ወደ መሰለው የምርምርና የጥናት ሥራ ባመሩ ኖሮ…የሚል ነው ቁጭቱ፡፡
በመምሕሩ ዘንድ የኢትዮጵያ ዘመን መቁጠሪያ በአጠቃላይ፣ በዕለታት የሚቆጠሩት አዕዋዳት፣ ዓውደ ወርህ እና ዓውደ አመቱ በተናጠል “ፀሐያዊ” እና “ፀሐያዊ” ብቻ ስለመሆን አለመሆናቸው በጭራሽ ብልጭ ያለ ነገር የለም፡፡ “አመት” እናም ወቅት የሚፈጠሩት ምድር በፀሐይ ዙሪያ በመዞሯ የተነሣ ነው፤ ዕለትም ምድር በራሷ ዛቢያ በመሾሯ የተነሣ ነው” የሚለውን “ሳይንሳዊ” አስተሳሰብ ማን ምን ብሎ ይጠይቃል? ያለቀለትና የታወቀ ጉዳይ ነው፤ ታዲያ የአንድን አመት ጊዜ ምድር በፀሐይቱ ዙሪያ ለመዞር የሚፈጅባት ጠቅላላ የጊዜ መጠን አድርጐ በመያዝ ምርምርና ጥናት ውስጥ አይገባም?...
እርሳቸውም አስቀድሞ ዘመን መቁጠሪያው የጠራ ፀሐያዊ (Purely Solar) መቁጠሪያ በማድረግ የአመትንና የየወራቱንም ርዝማኔዎች በማጥናት ጠለቅ ያለ ምርመራን በማድረግ ደክመዋል፡፡ ስለሐሳበ ዘመኑ የተጻፉ አንዳንድ መጻሕፍትንም በመመልከት ዋቤዎች ቢያደርጓቸውም ድንገት በሐሳባቸው እንዲህ ያለ ጥያቄን ሊያመጡባቸው የሚችሉባቸውን ጥቆማዎች ያላገኙም ይመስላሉ። ሌላው ቀርቶ ከተመለካከቷቸውም ቢሆን (የፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ የኅሩይ ስሜን እና የአብርሃም ጤናው መጽሐፎች እንዲሁም የዶክተር አበራ ሞላን የድረገጽ ጽሑፍ) በሙሉ ቢመለከቷቸው ሳያሳውቋቸው እንደማይቀሩ የሚታሰቡባቸው አንዳንድ ሙያዊ ቃሎችን ከእንግሊዝኛው ራሳቸው እንደ አዲስ ሲተረጉሙና ሲጠቀሙ፣ ደሞም ያለውንና የሚታወቀውን የሐሳበ ዘመኑን ቃል ሌላ ውክልና ሰጥተው ስለሚገኙ ምናልባት እነዚህንም ቢሆን በደንብ አላዩአቸው ይሆን ያሰኛል፡፡
ለምሣሌ፣ “Equinox” የሚለውን በአማርኛ “እኩልታ”፣ “እኩሌ” ፤“Leap year” የሚለውን የ”እመርታ አመት” ሲሏቸው ይገኛሉ፡፡ “ኢኩዊናክስ” በሐሳብ ዘመኑ የማይታወቅ እና ፍቺም ያልተበጀለት አልነበረም፡፡ “ዕሪና፣ ዕሩይ” ተብሎ የሚታወቅ ነው።
“ሊፕ” ወይም “ሊፕ ይር” የሚባሉትም “ሠግር” እና “የሠግር አመት” ተብለው ይታወቃሉ። “ዘንድሮ ጳጉሜ ትሠግራለች” ሲሉም “አንድ ቀን ይጨመርባታል” ማለታቸው ነው፡፡ሌላ ውክልና ከሰጡዋቸው ቃሎች ደግሞ “ዓውደ ፀሐይ” የሚለውን እንጠቅሳለን፡፡ “የዓውደ ፀሐይ አመት” ሲሉ ይገኛሉ፡፡ “የፀሐይ ዓውደ አመት” ለማለት ይመስላል፡፡ “ዓውደ ፀሐይ” ግን በሐሳብ ዘመኑ ራሱን የቻለ አንድ ዓውድ ነው፤ የ28 ዓመት ርዝማኔ ያለው፤ በአመታት ከሚቆጠሩ 4 መሠረታውያን አዕዋዳት አንዱ ነው፡፡ ደግሞም የፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌን የተሳሳተ አገላለጽ ይዘው፤ “አመት በዕለታት ብቻ ሳይሆን በወራትም እንደሚለካ ማወቃችን” የሚለውን ተቀብለው ይጠቀሙበታል፡፡
የሐሳበ ዘመኑ ትምህርት ግን እንዲህ ይላል - “ሰባት አዕዋዳት አሉ፤ ከነዚህ ሦስቱ በዕለታት ይሰፈራሉ፣ ይቆጠራሉ፡፡ እነዚህም ዓውደ ዕለት፣ ዓውደ ወርሀና ዓውደ አመት፤ 4ቱ በአመት ይቆጠራሉ፤ እነዚህ ዓውደ አበቅቴ፣ ዓውደ ፀሐይ፣ ዓውደ ማህተም እና ዓውደ ቀመር” የዓውደ አመት አሐድም (Unit) ዕለት መሆኑን እናያለን፡፡ ሐሳበ ዘመኑ በአሐዶች እንኳ ልዩ ጥንቃቄ የሚያደርግ መሆኑን ጭምር እዚህ ላይ ጠቀስ አድርገን እንመለስ።
እንግዲህ ዓውደ ዓመት የሚባለው ሙሉ በሙሉ ፀሐያዊ እንደሆነ “ዓመት ማለት ምድር በፀሐይ ዙሪያ ለመዞር የሚፈጅባት 365 ከ1/4 ዕለት መሆኑ ይታወቃል” በማለት (ገጽ 4) መነሻቸው ላይ በገለጹት ዘግተውታል፡፡
የኢትዮጵያ ዘመን መቁጠሪያ ዓመት የተባለውን አንድ ዓውድ እንዲህ በተፈጥሮአዊ ዓውድ ርዝማኔ የሚፈታ ስለመሆኑ ቅንጣት ባለመጠራጠር ወይም ይህን ባይፈታም ከዚህ ውጭ የሚሆን ዓመት የለም በማለት ይሆናል፡፡ ይኼ ይቆየንና ለመሆኑ አንድ አመት 365 ¼ኛ ቀን የተባለውስ በየትኛው የፀሐይ አመት ነው? ምድር ለመዞር ይህን ያህል ቀን የሚፈጅባት ከፀሐይ አመቶች በአንደኛው ብቻ እንደሆነ፤ የፀሐይ አመቶችም ቢያንስ ሦስት ዓይነት እንደሆኑ ለምን አልተመለከቷቸውም?
በዘመን መቁጠሪያዎች ዘንድ (ፀሐያዊ በሚባሉት) የተያዙት የፀሐይ አመቶች እንኳ ሁለት ዓይነቶች ናቸው፡፡ ሐሩራዊ የፀሐይ አመት (Tropical Solar year) እና ፈለካዊ የፀሐይ አመት (Sideral Solar year) ይባላሉ፡፡ ዛሬ ላይ ሳይንስ እነዚህን ሁለቱንም ምድር በፀሐይ ዙሪያ ለመዞር የሚፈጅባትን ትክክለኛ ጊዜ እንዳልያዙ በመጠቆም፣ ሌላ ሦስተኛ የፀሐይ አመት አስተዋውቋል “አኖማሊስቲክ ሶላር ይር” የተባለ፡፡
በእርሳቸው 365 ከ1/4ኛ የተባለው የሐሩራዊው ፀሐይ አመትን ርዝማኔ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህን የያዙት ቀን መቁጠሪያዎች ደግሞ እነ ግሪጐሪያንና ጁሊያን የመሳሰሉት ናቸው፡፡
ሰዎች ይህ ሐሩራዊ የተባለውን የፀሐይ አመት፣ እያደር ጊዜውን እየዛባው መሄዱን ዓውቀው የተሻለ ፀሐያዊ አመትን የሚይዘበትን ፈልገው፣ ከሺ አመት በፊት “ፈለካዊ” ያልነውን “ሳይድራል ሶላር” አመትን በመያዝ ያንን አርመውት ይገኛሉ፡፡ ፐርሺያዎች ከስንትና ስንት አመት በፊት የተውትን፣ ዛሬ እነ ኢራን የያዙት (ጃለሊ) ፣ አፍጋኒስታንና አንዳንድ የሂንዱ ውላጅ ካላንዴሮች ሁሉ የጣሉትን ሐሩራዊ አመት በመያዝ ነው እንግዲህ “ሳይንሳዊ” ምርምር ውስጥ የገቡት፡፡ “እንዲያው በነገራችን ላይ” ለማለት እንጂ የኢትዮጵያ ሐሳበ ዘመንስ እንዲህ ያለ በተፈጥሮ እንቅስቃሴ ላይ ይህን ያህል የወደቀ ሐሳበዘመንም አይደለም፡፡ እንዲህ ያለ የዘመን ፍቺም የለውም፡፡
“ዘመን ማለት በጊዜ ውስጥ ያለ የተወሰነ ጊዜ ነው፣ ብሎ በማስተማር የሚነሳ ብቸኛው ቀሪ የዘመን መቁጠሪያ ነው፡፡ ይህም ማለት ዓመት ዓውደዓመት፣ ወር (ዓውደ ወርኅ) ቢባል ዕለት በልቁ፣ በኩለንታው፣ በመላው ጊዜ ውስጥ ያሉ የጊዜ ወሰኖች እንጂ፤ “ዓመት ማለት መሬት በፀሐይ ዙሪያ (ተቃራኒውንም ቢሆን)፣ ዕለት በራሷ ዛቢያ እያለ አጉል መጠበብ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ እንዲያውም አንጻራዊ ጊዜን/ዘመንን የያዘ፣ እንደነ አልበርት እና ስቴፈን ሆውኪንግ ያሉ የሳይንስ ጭንቅሎዎች በ20ኛው መቶ ክ/ዘመን ከልደት ወዲህ ሊደርሱበት የቻሉትን የጊዜ/ዘመን ፍቺ ከጥንት ጀምሮ ይዞ፣ ተግባራዊ ጥቅም ላይ በሚያውልበት አያያዝ አውርዶ ሲጠቀምበት የኖረ የዘመንና የዓለም ሐሳብ ነው፡፡
ወደ አዕዋዳቱ ስንገባም የኢትዮጵያ ዘመን መቁጠሪያ በዓለም ላይ ካሉት ከአርባ በላይ የሆኑ መጠቀሚያና ሌሎችን ካሌንደሮች (አዳዲስ እየተሰሩ፣ ይህ ይሻለናል እያሉ በየድረገጹ የሚወተውቱትን) ሁሉ በዓይነት ለመክፈል የሚጠቀሙባቸውን ፀሐያዊ፣ ጨረቃዊ፣ ጨረቃ ፀሐያዊ፣ ፀሐይ - ጨረቃዊ እና ጨረቃ ኮከባዊ፣ ወዘተ እያሉ ለመክፈል በሚሞክሩባቸው እንኳ አንድ መግቢያ ቤትን ሊያገኙለት የሚከብድ የቀን መቁጠሪያ ነው፡፡
አንድ ዓውድ እንዴት ሆኖ ነው የፀሐይ፣ የጨረቃ፣ የሚባለው?
ይህን መመለስ ስንችል፣ የኢትዮጵያውስ ብለን በመጠየቅ የዘመን መቁጠሪያው የየትኛው ሰማያዊ ብርሃን እንደሆነ ልናውቅ እንችላለን፡፡ ይህንን ለመበየን ሦስቱን ዋና ዋና ዘመኖች ወይም አዕዋዳት መመልከት ይበቃል፡፡ እነዚህም አመት (ዓውደ አመት)፣ ወርኅ (ዓውደ ወርኅ) እና ዕለት (ዓውደ ዕለት) ናቸው፡፡
የነዚህንም ርዝማኔ በምን ምልክት ምን ያህል እንደሚያደርገው፣ እያንዳንዱም ዓውድ በአደ ቁጥር በየትኛው ምልክትነት እንደሚቆጠር ወይም እንደሚለይ (በስም እየጠራም ቢኾን) መመልከት ይጠይቃል፡፡
በዚኹ መሠረት የኢትዮጵያ ዘመን መቁጠሪያ የፀሐይን፣ የጨረቃንና የከዋክብትን ምልክትነት የሚጠቀም ብቸኛው የምድሪቱ ዘመን መቁጠሪያ እንደኾነ ማግኘት ይቻላል፡፡ እነዚህንም በምን ያህል መጠን ነው የሚጠቀመው የሚለው ደግሞ ሌላው የኢትዮጵያው የዘመን መቁጠሪያ አጠቃቀም የሚያስነሳው ጥያቄ ይሆናል፡፡
ከላይ “ምልክት” እያልን ስንጠራ በከንቱ እንደ ፖለቲከኛ ቃል አፍ ላይ በወደቀው ቃል ለመሙላት ስንል አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ዘመን መቁጠሪያ፤ ምድር ከፀሐይ ወይም “ፀሐይ ከምድር” ጋር በሚያደርጉት ተፈጥሮአዊ ቅንየት ጊዜው ይፈጠራል የሚል ቢኾን ኖሮ የተቀሩትን መቁጠሪያዎች ባለቤቶች የሚያዩትን መከራ እና “የተሻለ” እየተባለ ዐሥሩን መቁጠሪያ ማሰብና መምጣት ጣጣ ውስጥ ባስገባ ነበረ፡፡
ምድር ፀሐይን ለመዞር የሚፈጅባት ጊዜ ሳይንስ በተጠበበ፣ ቴክኖሎጂ በተራቀቀ ቁጥር የተሻለ ልኬት ተደረገ እየተባለ የየዘመኑን፣ የዓውደ ዘመኑን እንደ ዓውደዓመት ያለውን ርዝማኔ ለማስተካከል የመቁጠሪያ ለውጥ ያውም ተጠናቅቀው ላይጠናቀቁት እያወጁ የነበረውን፣ በተለይ ያለፈውን የዘመን ቁጥር እስከማጣት ድረስ የተደረሰበትን መደነጋገርና መሳሳት በፈፀመ ነበር፡፡ ጁሊያን 365.25 ቀን አድርጐታል ተብሎ በግሪጐሪያን 365.2324 ተተካ፡፡
በዚሁ ርዝማኔ ዓውደ አመት ተላክቶ በዖደ ቁጥር ይቆጠር ሲባል፣ ወደኋላ ሄደው ሲቆጥሩ በ10 ቀን ልዩነት የተለያዩ የሼክስፒር እና የሰርቫንቴስ ሞት ዕለት በአንድ ቀን የዋሉ ኾነው ተቆጠሩ፤ (ዛሬ ዩኔስኮ “የመጻሕፍት ቀን” ብሎ የሚጠራው ቀን እነዚህ ሁለት የአውሮፓ ደራሲያን የሞቱበት ቀን ኾኖ በመገኘቱ የተወሰነው ነበር፡፡ ኹለቱ ቀን በአንድ ቀን አልነበሩም የሞቱት::
የእንግሊዙ ልዑል በሕፃንነቱ ዘውድ የተጻፈለት ቀን መቼ እንደሆነ በተሻሻለው መቁጠሪያ ሲቆጥሩት፣ ጭራሽ በእናቱ ማኅፀን ውስጥ ገብተው በልዩ ሥነሥርዓት ዘውድ እንደጻፉለት ተደርጐ የሚታሰብበት ቀን ላይ ዐረፈ፡፡
ያለፈውን በማሳየት ብቻ አይደለም ይህ ዓይነቱ አያያዝ የማያመጣው፣ አሁንም በአንድ ወቅት በተያዘ መረጃ የዓመቱ ርዝመት ይህን ያህል የተባለው ተይዞ በዚያ መሠረት ለመቁጠር ሲቀጥሉ ከአመታት በኋላ ክረምት ይገባል የተባለበት በልግ የሚሆንበት፣ በልግ ነው ሲባል በጋ ሆኖ የሚገኝበት ሆኖ ቁጭ እያለ መከራ ውስጥ መግባት፣ እንደገና ሌላ መለኪያ መቁጠሪያ መፈለግ፡፡
ጳጉሜ 6 “የቀን መቁጠሪያው የማነው?” የሚል ጥያቄንም እንደ ርዕስ ተጠቅሟል፡፡ የኛም ጥያቄ ነው፡፡ያን ያህል የተለፋበት የቀን መቁጠሪያ የማነው? የኢትዮጵያውያንን ቀን መቁጠሪያ እንደማይመለከት በግልጽና በቀጥታ ስንናገር ግን በሀዘን ብቻ ሳይሆን በቁጭትም ጭምር ነው፡፡ ግን ግን ለምንድነው ይሄ ቀን መቁጠሪያ እንዲህ በምሑራኑ ሳይቀር በሚገባ ላይታወቅ የቻለው? ስለርሱ ከተጻፉት ውስጥ አንዳችም ስህተት የሌላቸው ስንቶቹ ይሆኑ?

Read 2044 times