Print this page
Saturday, 02 November 2013 11:03

የገቢዎችና ጉምሩክ ተከሳሾች ቤተሰብ እንዳይጠይቀን ተደረግን አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

ማረሚያ ቤት የተከሳሾችን ህገመንግስታዊ መብት እንዲያከብር ታዘዘ
የከባድ ሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸውን በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት በመከታተል ላይ የሚገኙት የገቢዎችና ጉምሩክ ተከሳሾች፤ ማረሚያ ቤቱ ከትዳር አጋር እና ከልጆቻችን በስተቀር በወዳጅ ዘመድ እንዲሁም በሃይማኖት አባቶች እንዳንጐበኝ ተከልክለናል ሲሉ ያመለከቱ ሲሆን የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር በበኩሉ፤ ለደህንነታቸው ሲባል በሰጡን የጠያቂ ዝርዝር መሠረት እያስተናገድን ነው ብሏል፡፡
ተከሣሾቹ ባለፈው ማክሰኞ በራሳቸው እና በጠበቆቻቸው አማካኝነት ለፍ/ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ፤ የተወሰኑ የጠያቂ ቤተሰቦቻቸውን ዝርዝር እንዲያስመዘግቡ የተደረገ መሆኑን አመልክተው፣ በዝርዝሩ ውስጥ የተካተቱት ቤተሰቦቻቸውም ጭምር በአግባቡ እየተስተናገዱ አለመሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ስለ ጉዳዩ እንዲያስረዱ ችሎቱ እድል የሰጣቸው ተከሳሽ አቶ ማርክነህ አለማየሁ፤ ከወራት በፊት በቁጥጥር ስር ሲውሉ እና ምርመራ ሲደረግባቸው ቤተሰብ ጭምር እንዳይጠይቃቸው መደረጉን አስታውሰው፤ በወቅቱ ክልከላ የተደረገው ከምርመራ ስራ ጋር በተያያዘ እንደሆነ ግንዛቤ በመውሰድ አቤቱታ ከማቅረብ መቆጠባቸውን ተናግረዋል:: ምርመራው ከተጠናቀቀና ክስ ከተመሰረተብን በኋላም ክልከላው መቀጠሉ ግን አግባብ አይደለም ብለዋል:: በተለያዩ ወንጀሎች በተከሰሱትና በማረሚያ ቤቱ ሆነው ጉዳያቸውን በሚከታተሉት ላይ እንዲህ መሰሉ ገደብ አለመኖሩን ያመለከቱት አቶ ማርክነህ፤ በኛ ላይ ግን የጠያቂ ገደብ ተጥሎብናል ሲሉ አስረድተዋል::
የጠያቂ ቤተሰቦቻችሁን ውስን ስም ዝርዝር አስመዝግቡ በተባሉት መሰረት ማስመዝገባቸውን የሚገልጹት አቶ ማርክነህ፤ጠያቂ ቤተሰቦች በአግባቡ የማይስተናገዱ ከመሆኑም በላይ ስም ዝርዝራቸውን ያካተትናቸው የአንዳንዶቻችን ቤተሰቦች፣ በብዙ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ያለጠያቂ ቀርተናል ብለዋል:: ቀደም ሲል የማረሚያ ቤቱ ገደብ ጊዜያዊ ነው፤ ይስተካከላል ተብሎ እንደነበር በመጥቀስም እንደተባለው ለውጥ ባለመኖሩ፣ ፍ/ቤቱ በጉዳዩ ላይ ጠበቅ ያለ ትዕዛዝ ያስተላልፍልን ሲሉ አቶ ማርክነህ ጠይቀዋል::
በተመሳሳይ የኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለቤት የሆኑት የአቶ ከተማ ከበደ ጠበቃ ባቀረቡት አቤቱታ፤ በህጉ መሰረት አንድ ታሳሪ የሃይማኖት አባትን ጨምሮ በቤተሰቦቹና በወዳጅ ዘመዶቹ ያለገደብ የመጎብኘት መብት እንዳለው አመልክተው፣ ጥየቃ በሰዎች መልካም ፍቃደኝነት ላይ ተመስርቶ የሚከናወን እንጂ እገሌ ሊጠይቀኝ ይችላል ተብሎ የሚታሰብ አይደለም፤ ስለዚህ እነ እገሌ ናቸው የሚጠይቁኝ ተብሎ ስም ዝርዝራቸው ሊሰጥ አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል:: ደንበኛቸው የደህንንት ስጋት አለብኝ አለማለታቸውንም ጠበቃው አክለው ለችሎቱ አስረድተዋል::
ከተከሳሾቹ ጠበቆች ለቀረበው አቤቱታ ምላሽ ለመስጠት ፍ/ቤት የቀረቡት የማረሚያ ቤት አስተዳደር ሃላፊ፤ ውስን ቤተሰቦች ብቻ እንዲጠይቁዋቸው የተደረገው ታራሚዎቹ እራሳቸው ደህንነታችን መጠበቅ አለበት በማለታቸው ነው ብለዋል:: ማረሚያ ቤቱ የታራሚዎችን ደህንነት መጠበቅ አለበት ያሉት ሃላፊው፤ ለዚህም ሲባል የጠያቂዎች ስም ዝርዝር አሰራርን መተግበር እንዳስፈለገ አስረድተዋል:: በጥየቃ ሥርዓቱ ላይ የሚፈጠሩ ቅሬታዎችን ለመፍታትም በየ15 ቀኑ ከጠያቂ ቤተሰቦች ጋር ውይይት እንደሚደረግ ጨምረው ገልጸዋል::
ችሎቱ በእለቱ በዋናነት አቶ መላኩ ፈንታ እና አቶ ገ/ዋህድ ወ/ጊዮርጊስ አንደኛና ሁለተኛ ተከሳሽ ሆነው የቀረቡባቸው ሶስት መዝገቦች ጉዳይ ተመልክቶ የተለያዩ ትዕዛዞችን አስተላልፏል::
ቀደም ሲል በዋለው ችሎት፤ አቃቤ ህግ የማስረጃ ዝርዝር ሰነዶችን ለተከሳሾች እንዲያቀርብ እንዲሁም በመዝገቦቹ በተከሳሽነት ተጠቅሰው ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ግለሰቦች እንዲቀርቡ መታዘዙ ይታወሳል:: በዚህ መሰረት አቃቤ ህግ ሰነዶቹን አያይዞ ያቀረበ ሲሆን በሰነዶቹ ላይ ከአንዳንድ ጠበቆች ቅሬታ ቀርቧል:: ሰነዶቹ የተሟሉ አይደሉም ከሚለው ቅሬታ ባሻገር፣ ማስረጃዎቹ በደፈናው ተጠቃልለው የቀረቡ ናቸው፣ ለተከሳሹ ይህ ነው የተገኘብህ ማስረጃ ተብሎ የቀረበ ባለመኖሩም፣ ለመከራከር አመቺ አይደለም ብለዋል - ጠበቆቹ:: በጉዳዩ ላይ ፍ/ቤቱ በሰጠው ብይን፣ ችሎቱ አሁን ባለበት ደረጃ የማስረጃውን ዝርዝር ጉዳይ የማየት ስልጣን እንደሌለው ገልጿል::
ኮሚሽኑ በታዘዘው መሰረት፤ በሁለተኛው መዝገብ ስር ተከሳሽ ከሆኑት ግለሰቦች መካከል ፍርድ ቤት እስከቀረቡበት እለት በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የዋና ዳይሬክተሩ አማካሪ አቶ አመሃ አባይ፣ በባለስልጣኑ የሃገር ውስጥ ታክስ ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ታፈሰ፣ በባለስልጣኑ የዋና ዳይሬክተሩ ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ ነብዩ ሳሙኤል፣ በባለስልጣኑ የህግ ማስከበር የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሙሉጌታ ባልቻ፣ በባለስልጣኑ የአዳማ ቅርንጫፍ የገቢ ሂሣቦች ቡድን አስተባባሪ ወ/ሮ ሃይማኖት አለሙ እንዲሁም በግል ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ተስፋዬ ቤተ እና መተዳደሪያ ስራ እንደሌላቸው ያመለከቱት አቶ ደሜ አበራ በፍርድ ቤት መጥሪያ አቅርቧል:: በእለቱ ለቀረቡት ተከሳሾች በዚሁ መዝገብ የተከሰሱት ባለስልጣናት ባቋቋሙት ህገወጥ ኮሚቴ ውስጥ አባል በመሆን ከተለያዩ ኩባንያዎች ይፈለግ የነበረ ግብርና ታክስ በተገቢው መልኩ እንዳይሰበሰብ በማድረግ፤ የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን መምራት የሙስና ወንጀል መከሰሳቸው ተመልክቷል::
በእለቱ ተከሳሾቹ ክሳቸውን ካደመጡ በኋላ ስለ ጠበቃ እና የዋስትና ጉዳይ ለጽ/ቤቱ ያመለከቱ ሲሆን አብዛኞቹ መከሰሳቸውን በሚዲያ ሰምተው በገዛ ፍቃዳቸው ወደ ኮሚሽኑ በመሄድ ስለጉዳዩ መጠየቃቸውን እንዲሁም ፍ/ቤት እስከቀረቡበት ሰአት ድረስ በገቢዎችና ጉምሩክ መስሪያ ቤት በስራ ገበታቸው ላይ መሆናቸውን ገልጸው፣ ከዚህ አንፃር እምነት ተጥሎባቸው በዋስ ይለቀቁ ዘንድ ፍ/ቤቱን ጠይቀዋል::
አቃቤ ህግ በበኩሉ፤ ሁሉም ተከሳሾች የተጠቀሰባቸው አንቀጽ ከ10 አመት በላይ የሚያስቀጣ በመሆኑ የዋስትና መብት ጥያቄውን እንደሚቃወም አመልክቷል:: ፍ/ቤቱም በዚህ መዝገብ በሰጠው ትዕዛዝ፤ የተከሳሾችን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ አዝዟል:: ከተከሳሾቹ መካከል አቶ ግርማ ታፈሰ፤ ወደ ፍ/ቤት ሲመጡ የመንግስት መኪና ይዘው መምጣታቸውን በማመልከት፣ መኪናውን ለማስረከብ እንዲፈቀድላቸው የጠየቁ ሲሆን ፍ/ቤቱም ጉዳዩን የልደታ ፖሊስ ከተከሳሹ ጋር በመነጋገር እንዲያስፈጽም አሳስቧል:: በሌላ በኩል በእለቱ በ5ኛው መዝገብ ተከሰው በፍ/ቤት መጥሪያ የቀረቡትና ክሳቸው የተነበበላቸው አቶ አውግቸው ክብረት፣ የዋስ መብታቸው ተከብሮላቸው በ15 ሺህ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ተደርጓል:: ረቡዕ ቀጥሎ በዋለው ችሎት፣ የቀሪ 3 መዝገቦች ማለትም ሶስት ሰዎች የተካተተበት በእነ ጌታሁን ቱጂ፣ አምስት ሰዎች የተከሰሱበት በእነ ዳዊት ኢትዮጵያ መዝገብ እንዲሁም በተናጥል ክስ የቀረበባቸውን የባለሃብቱ አቶ ምህረተአብ አብርሃ ጉዳይ ተመልክቷል::
በፍ/ቤቱ ትዕዛዝ መሰረት፣ በባለስልጣኑ የታክስና ኦዲት የሥራ ሂደት አስተባባሪ የነበሩት አቶ ቶሌራ ዳንጌ በቀረበላቸው ጥሪ ተገኝተው የቀረበባቸው ክስ በንባብ ተሰምቷል:: ተከሳሹ የቀረበባቸው ክስ በመዝገቡ 1ኛ ተጠሪ ከሆኑት ከአቶ ጌታሁን ቱጂ ጋር በመሆን አቶ አደም ሃሰን ሳዲቅ የተባለ አስመጪ ከሰኔ 2002 እስከ ሚያዚያ 2003ዓ.ም ድረስ 1780 ካርቶን የቲማቲም ስልስና 2180 ካርቶን ብስኩት ከቀረጥና ከታክስ ነፃ እንዲያስገባ በማድረግ፣ መንግስትን ከ423 ሺህ ብር በላይ አሳጥተዋል የሚል ነው::
በእነ ዳዊት ኢትዮጵያ መዝገብ ደግሞ በተመሳሳይ በዕለቱ ፍ/ቤት የቀረቡት አቶ ዘሱ ወ/ጊዮርጊስ የላጋር ጉምሩክ ኦፕሬሽን ክፍል ሃላፊ እና አቶ ኢዮብ ጌታቸው በባለስልጣኑ የላጋር ጉምሩከ የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ዋና ሃላፊ፣ በመዝገቡ ከተከሰሱ ሌሎች ተከሳሾች ጋር በመሆን አዳሽ አብድራህማን የተባለች አስመጪ ያስመጣችው አልባሳት በፍተሻ ከተያዘ በኋላ ተወርሶ ለመንግስት ገቢ መደረግ ሲገባው፣ ህጋዊ ነው በማለት አሳልፈዋል፣ በዚህም በመንግስት ጥቅም ላይ ጉዳት አድርሰዋል የሚል ነው::
ተከሳሾቹ በእለቱ የተለያዩ ምክንያቶችን አቅርበው የዋስትና መብታቸው እንዲከበር የጠየቁ ቢሆንም የተከሰሱበት አንቀጽ ከ10 አመት በላይ ሊያስቀጣቸው ስለሚችል በፍ/ቤቱ ውድቅ ተደርጎባቸው፣ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ታዟል:: በ3ኛ መዝገብ ከኩባንያቸው ምፋም ትሬዲንግ ጋር በጋራና በተናጥል ክስ የቀረበባቸው አቶ ምህረተአብ አብርሃ፣ ቀረጥ ባለመክፈል መንግስትን ከ3.5 ሚሊዮን ብር በላይ አሳጥተዋል የሚል ክስ የቀረበባቸው ሲሆን ክሱ የፀረ ሙስና ሳይሆን የጉምሩክና ገቢዎች ቢሆንም የኮሚሽኑ አቃቤ ህግ ውክልና ተሰጥቶት ነው ክሱን ያቀረብነው ብሏል:: በዚህ መዝገብ ላይ ብይን ለመስጠትም ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ለጥቅምት 28 ቀጥሯል::
ፍ/ቤቱ ማክሰኞ እለት በተመለከታቸው አንደኛ፣ ሁለተኛ እና ሶስተኛ መዝገቦች ላይ የተለያዩ ትዕዛዞችን ያስተላለፈ ሲሆን ክስ ተመስርቶባቸው ያልቀረቡ ተከሳሾች በቀጣይ ቀጠሮ አፈላልጎ እንዲያቀርብ፣የተከሳሾች ህገመንግስታዊ መብት በተሟላ መልኩ እንዲከበር፣ማረሚያ ቤትም ይህን በተሟላ መልኩ እንዲያከብር እንዲሁም በመዝገብ ቁጥር 141354 ባስተላለፈው ትእዛዝ መተማመኛ ፈርመው ያልቀረቡ ታስረው እንዲቀርቡ፣ መጥሪያ ያልደረሳቸው ደርሷቸው እንዲቀርቡ፣ ጠበቃ ያላቀረቡ ከጠበቆቻቸው ጋር እንዲቀርቡ፣ በተመሳሳይ በመዝገብ ቁጥር ር141352 ያልቀረቡ ተከሳሾች በቀጣይ ቀጠሮ እንዲቀርቡ በማለት ሂደቱ የሚታይበትን አግባብ ለመወሰን ሶስቱንም መዝገቦች ለጥቅምት 25 ቀን 2006ዓ.ም ቀጥሯል::
በሌላ በኩል የእነ አቶ ጌታሁን ቱጂን መዝገብ ለጥቅምት 28 እንዲሁም የእነ ዳዊት ኢትዮጵያን መዝገብ ለህዳር 3 ቀጥሯል::

Read 2584 times