Saturday, 02 November 2013 10:53

“ከበሮ የተደለቀውን ያህል ይጮሃል!”

Written by 
Rate this item
(11 votes)

አንድ አዋቂና አስተዋይ የተባ ለመምህር ተከታዮቹን ይዞ ረዥም መንገድ ይሄድ ነበር ይባላል፡፡ በመንገዳቸው ላይ አንዲት የታሠረች ጥቁር ላም ይመለከታል፡፡ ከዚያም ወደ ተከታዮቹ ዞሮ፤
“የዚችን ጥቁር ላም ወተት መጠጣት ውጉዝ ነው!” አለ፡፡
ተከታዮቹ በአንክሮ አዳመጡት፡፡ መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ ወደ አንድ መንደር ሲደርሱ፤ እኔ እዚህ አድሬ አረፍ ልበል፤ እናንተ ደግሞ ወደየመንደሮቻችሁ ተጠግታችሁ እደሩና ጠዋት ከዚሁ መንገድ እንቀጥላለን አላቸው”
ሁሉም ወደሚያድሩበት ሄዱ፡፡
በየደረሱበት ግን ለሰው ትምህርት ለመስጠት ሞከሩ፡-
“የጥቁር ላም ወተት ውጉዝ ነው እነዳትጠጡ” እያሉ አስተማሩ፡፡
ህዝቡም
“ይህንን ማን አለ?” ሲል ጠየቀ፡፡
“መምህራችን!” አሉት፡፡
ጥቁር ላም ያለው ሰው ሁሉ ከፊሉ አዘነ፡፡ ከፊሉ ግራ ተጋባ፡፡ ከፊሉ “መምህርን መጠየቅ አለብን፡፡ አንድ ደሀ ሰው ያለችው አንዲት ጥቁር ላም ብቻ ብትሆንስ? በምኑ ይኖራል?” ሲል አጉረመረመ፡፡
በነጋታው መምህሩ በመንደራቸው ሲያልፍ፣ “መምህር ሆይ የጥቁር ላም ወተት መጠጣት
ስለምን ተከለከለ፣ ስለምንስ ውጉዝ ነው አልክ?” ሲሉ ጠየቁት፡፡
መምህሩም፤
“ተከታዮቼ የጥቁር ላም ወተት መጠጣት የተወገዘ ነው” ብለዋችሁ ከሆነ ተሳስተዋል፡፡ እኔ ያልኩት ነገር የሚመለከተው፣ ትላንት መንገድ ላይ ያየናትን ጥቁር ላም ነው” አላቸው፡፡
ሰዎቹም “ያቺንስ ጥቁር ላም ምን የተለየ ነገር ብታይባት ነው? አሉና ደግመው ጠየቁት፡፡
“መልካም ጥያቄ ነው፡፡ ተከታዮቼም ይህን ጥያቄ ሊጠይቁኝ ይገባ ነበር፡፡ ያቺ ጥቁር ላም እበረት ውስጥ ታስራለች፡፡ ምንም ምግብ አይሰጥዋትም፡፡ ሆኖም ጠዋት ማታ ያልቧታል፡፡ ይሄ ተግባር ግፍ ነው፡፡ ወተቱም ከግፍ የተገኘ ወተት ይሆናል፡፡ ውጉዝ ነው ያልኩት ለዚህ ነው፡፡ የጥቁርዋ ላም ምሳሌነቱ በግፍ ለተገኘ ማናቸውም ገንዘብ ንብረትና ሀብት ሁሉ ነው!” ሲል አብራራላቸው፡፡
* * *
ነገርን በጅምላው መውሰድ ስህተት ላይ ይጥለናል፡፡ የዓለምን ተመራማሪዎች ሲያጣሉና ተከታዮችንም ሲያወዛግቡ የኖሩ አያሌ ጥያቄዎች ከትርጓሜ ስህተት የመጡ እንደሆኑ አንዘንጋ፡፡ በእኩይ መንገድ የተገኘ ማናቸውም ዓይነት ብልፅግና ያስጠይቃል ፡፡ ሊያስጠይቅ የሚችልን ማናቸውም ኢፍትሐዊ ነገር የፈፀመን አለቃም ሆነ ምንዝር፤ ባለሥልጣንም ሆነ ተከታይ ጉዳዩን አብራርቶ እንዲጠይቅ ማድረግ የተበዳይ መብት ነው፡፡ ላሚቱ ራሷም ተዟዙራ የምትበላው እንዳትፈልግ አስረን ስናበቃ ያልሰጠነውን ለመቀበል፣ ያልመገብነውን ለማለብ መፈለግ፣ የሚገኘውን ወተት የግፍ ንብረት እንደሚያደርገው ማስተዋል ዋና ጉዳይ ነው፡፡ የበታቾቻችን፣ ተከታዮቻችን፣ ካድሬዎቻችን በየደረጃው ለመርሆች፣ ለመመሪያዎችና ለራዕዮች የሚሰጡት ትርጓሜ የተሳሳተ ከሆነ፤ የሚሳሳተው ብሎም የሚጎዳው፣ አገር ሙሉ ሰው ነው፡፡ ስህተቱ እጅግ የከፋ የሚሆነው ደግሞ የሚሰጠውን መግለጫ ህዝብ አብራሩልኝ ሲል “እኔ ያልኩህን ብቻ ተቀበል” የምንል ከሆነ ነው፡፡ አንድም ያለዕውቀት አንድም በዕብሪት፣ ይህን ግትርነት ካሳየን አስከፊ ጥፋት ከመሆን አይዘልም፡፡ የመንግሥት ሠራተኛም ቢሆን የህዝብ አገልጋል እንጂ ገዢ ነኝ የሚል አስተሳሰብ ካለም አደገኛ ነው! አገርና ህዝብን መበደል ነው፡፡ ዋና ዋና መርሆቻችንና የፖለቲካ አቋሞቻችንን ከመመርመርና ቆም ብለን ከማየት ይልቅ በደመ-ነብስ መከተልና እንደቦይ ውሃ አብሮ መፍሰስ ከዚያም ይልቅ የበለጠ መጮህ፤ ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡
አሌክሳንደር ፓፕ የተባለው ገጣሚ “በጭፍኑ መስማማት መዋሸት ነው” ይለናል /To blindly comply, is to lie/፡፡
በሀገራችን ተጠይቀው ያልተመለሱ፤ ተመልሰው ያላጠገቡ፤ ከናካቴው ያልተጠየቁ ወይም ለመጠየቅ የሚፈሩ፤ በርካታ የፖለቲካም፣ የኢኮኖሚም፣ የማህበራዊም፣ የባህልም ጥያቄዎች በልማድ ታጅለው ብዙ ጊዜ አልፏቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ፤ ብንጠይቅ ማን ይመልስልናል በሚል ሰበብ፣ እንደተዳፈኑ የሚቀሩ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ብንጠይቅ እንጠየቃለን በሚል ፍርሃት የሚዳፈኑ ናቸው፡፡ ጥቂቶቹ መጠየቅ እንዳለባቸው ሳናውቅ እንደቀለጡ የሚቀሩ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ በምን ያገባኛልና በምን-ግዴ፣ ቸልታ የተሸፋፈኑ ናቸው፡፡ ዞሮ ዞሮ ሁሉም ጉዳት ሲያደርሱብን ማየታችን አልቀረም፡፡ በተናጠል የምናብጠለጥላቸውና የምንሸሙርባቸው፤ እንዲሁም በንቀት የምናንጓጥጥባቸው ግን፤ ሲደርሱብን እሪ የምንልባቸው፤ በርካታ የዕለት-ጉርስ የዓመት-ልብስ ተኮር አንገብጋቢ ጥያቄዎች እንደ ዐባይ ከዓመት ዓመት ይፈስሳሉ፡፡
“ከበሮ የተደለቀውን ያህል ይጮሃል” የሚለው ተረት፤ የመቺውን እንጂ የተመቺውን ድምፅ የማያስተጋባበት ሁኔታ ውስጥ ከሆነ ያለነው፣ የትርጓሜ ስህተት አለ ማለት ነው፡፡ ያ ደግሞ የጥቁሯን ላም ያህል አሳሳቢ ችግር ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የበደሉንን ይቅር ማለት ብቻ ሳይሆን መጠየቅም መልካም ሥነ-ምግባር ነው! የከበሮ መቺውንም፣ የተመቺውን ከበሮም፣ ነገር ለማወቅ የጠያቂነት ባህል እናዳብር!!

Read 3844 times