Saturday, 26 October 2013 14:09

የአትሌቶቹ ባለ 5 ኮከብ ሆቴልና ሪዞርት

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(7 votes)

በትውልድ ቀዬው ሆስፒታል ሊሠራ አቅዷል
ከቢዝነስ ጋር የተዋወቁት በአዳማ ከተማ ባሠሩት ባለ አራት ፎቅ ሕንፃ ነው፡፡ ከዚያም እግሩን ስላመመው አሜሪካ ሄዶ ቀዶ ሕክምና (ኦፕሬሽን) አደረገ፡፡ እግሩ በደንብ ድኖ ልምምድ ለመጀመርና ወደ ሩጫ ለመመለስ ረዥም ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ያንን ጊዜ በከንቱ ማባከን አልፈለገም፡፡ ከባለቤቱ ጋር ተመካከሩና ሁለቱም ያገኙትን ገንዘብ አንድ ላይ አድርገው ወደ ቢዝነስ ዓለም ገቡ - አትሌት ገዛኸኝ አበራና አትሌት እልፍነሽ ዓለሙ፡፡
አዲስ አበባ ውስጥ አሮጌ ቤቶች ገዝተው አፍርሰውና አሻሽለው በመሥራት መሸጥ ጀመሩ። ከዚያም አትሌቱ በሲድኒ ኦሎምፒክ በማራቶን አሸንፎ ሲመጣ፣ የደቡብ ክልል መንግሥት በሀዋሳ ከተማ 25ሺህ ካ.ሜ ቦታ ሸልሞት ነበር፡፡ በዚያ ስፍራ ገዛኸኝና እልፍነሽ ሆቴልና ሪዞርት ያካተተ ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ሠርተው የሙከራ አገልግሎት (Soft opening) ጀምሯል፡፡ በቢሾፍቱ (ደብረዘይት) ከተማም በቢሾፍቱ ሐይቅ ባለ 5 ኮከብ ሪዞርት ሠርተው በቀጣዩ ዓመት ይመረቃል፡፡ በአዲስ አበባም በተለያዩ ቦታዎች የእንግዳ ማረፊያ ሕንፃ እያስገነቡ ሲሆን፣ በጥቁር ውሃም ቦታ ተረክበው ምን መሥራት እንዳለባቸው እያሰቡ መሆኑን ተናግሯል፡፡
አትሌት ገዛኸኝ አበራ፤ ያኔ በአርሲ ክፍለ ሀገር አሁን በአርሲ ዞን ኢቴያ በተባለች የገጠር ከተማ በ1973 ዓ.ም ተወልዶ እዚያው አደገ፡፡ ትምህርቱን የተከታተለው ደግሞ በኢቴያና በሁሩታ ከተሞች ነው፡፡ አትሌቱ ገዛኸኝ ወደ ስፖርት የገባው በራዲዮ በሰማው ዜና ነው፡፡ አንድ ቀን ትንሿን ራዲዮ ክምር ስር አድርገው ከአባቱ ጋር እህል ሲወቁ፤ ራዲዮኗ “በፈረንሳይ በተደረገ የ21 ኪ.ሜ ውድድር እገሌ የተባለ አትሌት 1፡02 በመግባት ስላሸነፈ ተሸለመ” የሚል ዜና ሰማ፡፡ በዚያን ጊዜ እሱ፣ ከመንደሩ 21 ኪ.ሜ ርቃ በምትገኘው ኢቴያ ከተማ ነበር የሚማረው፡፡ ጣቷና ማታ የሚያደርገውን ጉዞ ሲያሰላ አትሌቱ ከተሸለመበት ርቀት በእጥፍ ይበልጣል፡፡ “እኔም አሸንፋለሁ” የሚል ስሜት ስለተፈጠረበት ለአባቱ ነገራቸው፡፡ ይኼ የሆነው በ1987 ዓ.ም ነበር፡፡
እዚያው በመንደሩ ሮጥ ሮጥ በማለት ልምምድ ካደረገ በኋላ፣ አሰላ ከተማ ሄዶ በ12 ኪ.ሜ አገር አቋራጭ (ክሮስ ካንትሪ) ተወዳድሮ አሸነፈ። እዚያው በአሰላ ስታዲየም በ5 ሺህና በ10ሺህ ሜትሮች ተወዳድሮ አሸነፈ፡፡ ይኼኔ በፈረንሳይ በተደረገው የዓለም ዋንጫ ውድድር በ21 ኪ.ሜ ኢትዮጵያን እንዲወክል ተመረጠ፡፡ በዚያ ውድድር ግን አልቀናውም፣ 16ኛ ነበር የወጣው፡፡
ከፈረንሳይ ሲመለስ አዲስ አበባ መኖር ስለጀመረ፣ በሙገር ስፖርት ክለብ ታቀፈ፡፡ በዚያን ጊዜ 17 ዓመቱ ነበር፡፡ በሙገር ስፖርት ክለብ ሲለማመድና ሲወዳደር ቆይቶ፣ በ1993 ዓ.ም በሲድኒ በተዘጋጀው ኦሎምፒክ በማራቶን ተወዳድሮ ሲያሸንፍ 22 ዓመቱ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ የኦሎምፒኩ አዘጋጆች “በ22 ዓመቱ ማራቶን ያሸነፈ የመጀመሪያው ወጣት” በማለት አሞካሽተውታል፡፡
አትሌቱ አሁን 34 ዓመቱ ሲሆን ከባለቤቱ ከአትሌት እልፍነሽ ዓለሙ ሁለት ልጆች አፍርቷል፡፡ በአምላክና ያኔት ገዛኸኝ ይባላሉ፡፡ አትሌት እልፍነሽ ሁለተኛ ልጃቸውን ከ6 ወር በፊት ነው የወለደችው።
የቢዝነስ ሰው ጊዜ የለውም፡፡ ገዛኸኝ ሀዋሳ፣ ቢሾፍቱና አዲስ አበባ፣ … ብዙ ሥራዎች ስላሉት እየተዘዋወረ ያሠራል፣ ይከታተላል፡፡ ስለዚህ ሥራ ይበዛበታል-ቢዚ ነው ማለት ነው፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት ለሥራ ሀዋሳ ሄጄ ነበር፡፡ እዚህ ከደረስኩ ለምን ሆቴሉን አላይም ብዬ ወደ ሆቴሉ ሄድኩ። አጋጣሚ ሆኖ አትሌት ገዛኸኝ ሀዋሳ ነበር፡፡ ሥራ አስኪያጁ ደውሎ ከ“አዲስ አድማስ” የመጣ ጋዜጠኛ እንደሚፈልገው ነገረው፡፡ እሱም፣ ከከተማ ውጭ መሆኑን ጠቅሶ “በ20 ደቂቃ ውስጥ ስለምደርስ ይጠብቀኝ” የሚል መልዕክት አስተላለፈ፡፡ እኔም እሱ እስኪደርስ ድረስ ግቢውንና ክፍሎቹን እየተዘዋወርኩ ስጐበኝ ቆየሁ፡፡
ሥራው አልቆ አገልግሎት የጀመረው የሀዋሳው ባለ 5 ኮከብ ሆቴልና ሪዞርት ስለሆነ እሱን ላስቃኛችሁ። ሆቴሉ የተሠራው ከሀዋሳ ከተማ ዳር ነው፡፡ ከሀዋሳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ፊት ለፊት፣ ወደ ይርጋዓለም፣ ዲላ፣ ሞያሌ፣ … ከተሞች በሚወስደው አውራ ጎዳና ቀኝ ጠርዝ ነው፡፡ ወደ ሆቴሉ ሲታጠፉ የባለቤቶቹ ስም የተጻፈበት እብነበረድ አለ፡፡ ከዚያ ጥቂት ሜትሮች እንደተራመዱ፣ የሆቴሉን ትልቅ ባለ ቅስት መግቢያ ያገኛሉ፡፡ በሩ ሰፊ በመሆኑ፣ ወደ ሆቴሉ የሚገቡና የሚወጡ መኪኖች መተላለፊያቸው የተለያየ ነው፡፡
ግቢው በጣም ሰፊ ሲሆን፣ አረንጓዴ ሳር፣ በየስፍራው የተተከሉ በርከት ያሉ ዛፎችና አበቦች ሲያዩ ሆቴል ሳይሆን ዘመናዊ መናፈሻ ውስጥ የገቡ ይመስልዎታል፡፡ መግቢያውን እንዳለፉ በስተግራ፣ ግራውንድ ቴኒስ መጫወቻ፣ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ እንግዳ መቀበያውን፣ አዳራሽ እንዲሁም ትንሽ ራቅ ብሎ ባርና ሬስቶራንቱን ያገኛሉ፡፡ ከዚያ ፊት ለፊት ራቅ ብሎ የመዋኛ ገንዳው ይታያል፡፡
እስካሁን ክፍሎቹን አላየሁም፡፡ በባርና ሬስቶራንቱ ጐን፣ ሰፊ ስፍራ አለ፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የተሠራው የአስተዳደርና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ሕንፃ ነው። መኝታ ክፍሎቹን የሚያገኙት ከዚያ ሕንፃ ጀርባና ጐን ነው፡፡ ሕንፃዎቹ ሁሉ የጐጆ ቤት ቅርፅ አላቸው። በመጀመሪያው ምዕራፍ የተሠሩት 32ቱ ክፍሎች ፎቅ የላቸውም፡፡ በሁለተኛው ምዕራፍ የሚሠሩት 75 ክፍሎች ፎቅ ሲኖራቸው፣ ግንባታቸው ተጀምሮ መሠረቱ መውጣቱን ባለሀብቱ ተናግሯል፡፡
ገዛኸኝ፣ በሀዋሳ ከተማ የተሠራው ሆቴልና ሪዞርት፣ ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ሊኖረው የሚገባውን ፋሲሊቲ አሟልቶ በኢትዮጵያ የተሠራ የመጀመሪያው ሆቴል እንደሆነ ይናገራል፡፡ ክፍሎቹ በአራት ደረጃ የተከፈሉ ሲሆን ባለ አንድ፣ ባለ ሁለት አልጋ፣ ትዊንና ልዩ የቤተሰብ መቆያ ኤግስኩቲቭ ቪላ (ባንጋሎ) ናቸው፡፡ ቪላው ራሱን የቻለ የታጠረ ግቢ ሲኖረው፣ የደህንነት ጥበቃውም ልዩ ነው፡፡ ምግብ ማዘጋጃ ኪችን መመገቢያ ጠረጴዛ፣ የወላጆችና የልጆች መኝታ ክፍል፣ እሳት ማንደጃ፣ ግቢው ውስጥ ደግሞ መኪና ማቆሚያ፣ ካምፋየር ማዘጋጃ ስፍራ፣ የጓሮ ፍራፍሬ፣ ማንጐ፣ ፓፓያ፣ አቡካዶ፣ … አለው፡፡ እዚያ ያረፉ እንግዶች ፍሬዎቹን ቀጥፈው መብላትና መጭመቅ እንደሚችሉ ገዛኸኝ ገልጿል። ኪችኑ፣ በተሟላ ምግብ ማዘጋጃ ዕቃዎች የተሟላ ነው፡፡
የልጆች ክፍል፤ ሁለት አልጋ፣ ቁም ሳጥን፣ መታጠቢያ ገንዳ፣ መፀዳጃ፣ ሆቴል ቲቪ፣ … አለው። የወላጆች ክፍል ደግሞ ማስተር ቤድ፣ መታጠቢያ ገንዳና ጃኩዚ፣ ሆቴል ቲቪ፣ ስልክ፣ መፀዳጃ፣ ቁምሳጥን፣ የመልበሻ ጠረጴዛ፣ … ይዟል፡፡ ሳሎኑ፤ ቲቪ፣ ጠረጴዛና ወንበር፣ ፍሪጅ፣ ስልክ፣ የምግብ ጠረጴዛ፣ … በአጠቃላይ አንድ ዘመናዊ ቪላ ሊኖሩት የሚገባውን ነገሮች አሟልቶ ይዟል፡፡ ክፍያው ታዲያ የተጋነነ አይደለም፡፡ አሁን ያለው ሆቴሉ በይፋ ተመርቆ እስኪከፈት ድረስ ጊዜያዊ ዋጋ ቢሆንም፣ በሥራ (በአዘቦት) ቀናት 79 ዶላር ወይም 1,469 ብር፣ ቅዳሜና እሁድ 99 ዶላር ወይም 1,841 ብር ነው፡፡
የክፍሎቹን ብዛት ያየን እንደሆነ 5 ትዊንስ፣ 15 ሲንግል፣ 10 ደብልና 2 ቪላ ናቸው፡፡ ሲንግሉ፣ ቀዝቃዛ ሻወር አለው፡፡ ደብሉ ጃኩዚ፣ ትዊኑ በረንዳ ላይ ዐረቢያን መጅሊስ አላቸው፡፡ ቲቪ፣ ስልክ፣ ሚኒባር፣ ካዝና፣ በሆቴሉ ስም የተሠሩ የተለያየ መጠን ያላቸው ፎጣዎች፣ ሳሙና፣ የፀጉር ሻምፑ፣ ሎሽን፣ የጥርስ ብሩሽና ሳሙና፣ ፀጉር ማድረቂያ፣ መፀዳጃ ቤት፣ ቁም ሳጥን፣ ወንበርና ጠረጴዛ፣ ሶፋ፣ … በሁሉም ደረጃ ባሉ ክፍሎች የሚገኙ ናቸው፡፡
አልጋ የያዙ እንግዶች በተጓዳኝ የሚያገኟቸው ጥቅሞችም አሉ፡፡ ጂም የፀጉርና የጥፍር ውበት (ስፓ)፣ ስቲምና ሳውና ባዝ፣ ዋና፣ ከረንቦላ፣ ግራውንድ ቴኒስና ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቁርስ፣ .. ለሁሉም በነፃ ይሰጣል፡፡
ሆቴሉ የተሠራው ከውጭ በመጡ ዕቃዎች ሳይሆን ግቢው ውስጥ ባሉ ወርክሾፖች በተመረቱ ዕቃዎች ነው፡፡ “የራሳችን የእንጨት፣ የብረታ ብረት፣ የኮንስትራክሽን፣ ወርክሾፖች አሉን፡፡ የሚያማምሩ ዲዛይን ያላቸው ሞልዶች ከውጭ አስመጥተን ግቢ ውስጥ ያነጠፍናቸውና ለጣራ ክዳን የተጠቀምንባቸው ታይልሶች እዚሁ የተመረቱ ናቸው፡፡ እነዚህን የኮንስትራክሽን ዕቃዎች እዚህ ማምረታችን፣ የዋጋና የጥራት ልዩነት አለው፡፡ አንድ ብሎኬት ስታመርት፣ አሸዋውን፣ ሲሚንቶውን … በምትፈልገው የጥራት ደረጃ ቀላቅለህ ትሠራለህ፡፡ ከውጭ አገር ለምሳሌ ከቻይና ስታስመጣ፣ የጥራት ደረጃውን ሳታውቅና ሳታይ ትቀበላለህ፡፡ ለሆቴላችን ክፍሎች የገጠምናቸውን መስኮትና መዝጊያ ስታይ እዚህ አገር እንደዚህ ይሠራል ወይ? ብለህ በጣም ትገረማለህ። ጥራታቸው ከውጭ ከሚመጡት ስለሚበልጥ እዚህ ግቢ ተመረቱ ብሎ ማመን ያስቸግራል፡፡ እነዚህን ነገሮች ለሆቴላችን ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊት፣ ለአገራችንም ገበያ ቢቀርብ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ” በማለት በወርክሾፑ ስለሚመረቱት ቁሶች ጠቃሚነት ገልጿል፡፡
መዋኛው ትልቅ እንደሆነ አትሌት ገዛኸኝ ይናገራል። የራሱ ጃኩዚ ሲኖረው፣ 26 ሜትር ቁመትና ከ20.55 እስከ 85 ሜ. ጥልቀት አለው፡፡ “የሕፃናት መዋኛው ጥልቀት 90 ሳ.ሜ ስለሆነ ማንኛውም ሕፃን እንደ ልቡ መጫወት ይችላል” ትላለች፤ የገንዳው ሕይወት አድን ሠራተኛ፡፡ በማከልም፣ “ውሃው ያለውን ኬሚካል በፒኤች ለክተን፣ ክሎሪን ወይም አሲድ እንደጐደለው አውቀን የጐደለውን እንጨምርበታለን። ኬሚካል ስንጨምርበት ከስር ዝቃጭ ይፈጥራል፡፡ በዚህ ጊዜ ቆሻሻውን በቫክዩም ስበን በማስወጣት እናፀዳለን” ብላለች፡፡
ውሃውን እያጣራ የሚመልስ (ሰርኩሌት የሚያደርግ) መሳሪያ ያለው ሲሆን እንግዶች ዋና ሲደክማቸው ወደ ዳር ተጠግተው፣ ውሃው ውስጥ ባለ መቀመጫ ላይ አረፍ በማለት የተለያዩ ለስላሳ መጠጦችና ፋስት ፉድ የሚስተናገዱበት ስዊሚንግ ባር አለ፡፡
ገዛኸኝ፣ ለሆቴሉ ግንባታ እስካሁን 200 ሚሊዮን ብር መውጣቱንና ማስፋፊያው ሲጠናቀቅ ካፒታሉ በእጥፍ እንዲጨመረ ጠቅሶ ለ120 ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልጿል፡፡ “ከመንግሥት ዋነኛ እቅዶች አንዱ የሥራ አጡን ቁጥር መቀነስ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ማስፋፊያው ሲጠናቀቅ፣ ከ250 እስከ 300 ለሚደርሱ በክልሉ ያሉ ዜጐች የሥራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል፡፡ እኔም ትንሽም ቢሆንም በመንግሥት ዕቅድ ተሳትፌ የበኩሌን ድርሻ በማበርከቴ ደስተኛ ነኝ” ብሏል፡፡
አትሌቱ በማኅበራዊ ተሳትፎም አይታማም፡፡ በግል ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ፣ ከመንግሥት ጋር በመሆን፣ በተወለደበት አከባቢ ጥሩ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ይናገራል፡፡ “የአካባቢው ሕዝብ በአሁኑ ወቅት ምንድነው የሚያስፈልገው? ት/ቤት፣ ሆስፒታል፣ ውሃ፣ … በማለት ባደረኩት ጥናት፣ የሕዝቡን ፍላጐት (ፊድ ባክ) አግኝቻለሁ፡፡ በተወለድኩበት አካባቢ ሆስፒታል የለም፡፡ ሕዝቡ፤ ከኢተያና ከሁሩታ አካባቢ አሰላና አዳማ እየሄድ ነው የሚታከመው፡፡ አካባቢው ሰፊና ሕዝቡም ብዙ ነው። በዚያ አካባቢ ሆስፒታል ለመሥራት አቅጃለሁ፡፡ አሜሪካ፣ ፊንላንድና ጀርመን እግሬን ኦፕሬሽን ካደረጉ ሐኪሞችና ሰዎች ጋር መሳሪያዎችን በዕርዳታም ሆነ በሌላ መንገድ ለማስገባት ተነጋግሬ ጥሩ ምላሽ አግኝቻለሁ፡፡ ስለዚህ፣ ሕዝቡ በአነስተኛ ክፍያ ሊጠቀምበት የሚችል ሆስፒታል ለመገንባት እያሰብኩ ነው፡፡ በቅርቡም መሬት እረከባለሁ የሚል ሐሳብ አለኝ” ብሏል፡፡
በሐሳብ ደረጃ ይሁን እንጂ በተወለደበት አካባቢ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ያሰባቸው መስኮች እንዳሉ ገልጿል፡፡

Read 5972 times