Saturday, 26 October 2013 14:02

ተስፋዬ ገብረአብን ከሌላ ማዕዘን

Written by  ዮናስ ቢራብቱ
Rate this item
(3 votes)

             “የስደተኛው ማስታወሻ” የተባለውን የተስፋዬ ገ/አብ አዲስ መጽሃፍ “በብላሽ” ወስጄ አነበብኩት። መጽሃፉን በነጻ የበተነው እራሱ ነው ይላሉ። አንድ ሰው የለፋበትን ነገር በነጻ ሲሰጥ ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም። በተለይ ደግሞ እንዲህ አይነት አወዛጋቢ መጽሃፍ ሲሆን ይበልጥ ያስጠረጥራል። ከዚያም አልፎ አንዳንድ ሰዎች የሚሉትን ያጠናክራል። ተስፋዬ ደግሞ አሳታሚዎቹ “ጫልቱ እንደ ሄለን” ብዬ የጻፍኩትን ምዕራፍ አውጣ ስላሉኝ ነው ይላል።
ለማንኛውም ዛሬ ይህንን አወዛጋቢ መጽሃፍ ከሌላ ማእዘን ለመዳሰስ እሞክራለሁ። የተስፋዬን ስራዎች ከ-እስከ አንብቤአለሁ። ብዙ ቃለ መጠይቆቹን ሰምቼዋለሁ። በተደጋጋሚ ፓል ቶክ ላይ ሲያደንቁት፤ ሲያሞካሹት፤ ሲያፋጥጡት፤ ሲያበሻቅጡት እና ሲከሸክሹት አድምጫለሁ። የግል ድረ ገጹ ላይ የሚያትማቸውን ጽሁፎች ተሸቀዳድሜ አንብቤዋለሁ። በአላማው ሲጸና አይቻለሁ። ኮፍያ ሲቀያይር ታዝቤያለሁ። ሲገለባበጥ ተመልክቼዋለሁ። አሪፍ መልስ ሲሰጥ ሰምቻለሁ። ሲምታታበት አስተውያለሁ። ፈንጂ ሲረግጥ አይቻለሁ። እንደ ሀር ተለሳልሶ ሲያመልጥም ተገርሜያለሁ።
ስለዚህም የተስፋዬ ጉዳይ በጥንቃቄ መታየት እንዳለበት አምናለሁ።
ተስፋዬ “አሊጎሪካል” ጸሃፊ ነው። ማስተላለፍ የሚፈልገውን መልእክት በአሊጎሪ (ተምሳሌት) ይገልጻል። በዚህም የበአሉ ግርማ ተጽእኖ በደንብ ይታይበታል። በእርግጥ አሊጎሪ ጥሩ ዘይቤ ቢሆንም የተስፋዬ ግን ይበዛል። ሁሉን ነገር ተምሳሌት ማድረግ ያምረዋል። በእያንዳንዱ ትረካ ውስጥ ስለ መልእክቱ መጨነቁ ይታያል። ለመልእክቱ የበዛ ትኩረት በመስጠቱ የመጽሃፉን ርእስ የማይመጥን ትረካ አጭቆበታል። የስደትን ጉዳይ ችላ በማለት ብዙ ቅንጥብጣቢ አሊጎሪካል ታሪኮች አካቷል። ከአንዱ ወደ ሌላው የሚያደርገው ሽግግርም ድምዳሜውን (conclusion) ቀድሞ ይዞ የሚደግፍበት ታሪክ የሚፈልግ አስመስሎታል። ታሪኩ ከመልዕክቱ ጋር አልገጥም ሲለው ደግሞ “የደራሲነት ስልጣኔን ተጠቅሜ አስተካክዬዋለሁ” ይላል። ለማንኛውም ብዙ ርእሶችን ቢያነሳም ማስተላለፍ የሚፈልገው መልዕክት ግን ከአራት ወይም ከአምስት የሚበልጥ አይመስልም። ከዚህ ውስጥ የማንነቱ ጥያቄ ትልቁን ድርሻ ይይዛል።

1. የማንነት ጥያቄ
የሰው ማንነት የሚገነባው በትውልድ አካባቢው ባህል (ቋንቋ፣ አለባበስ፣ አመጋገብ፣ ሥነ ጥበብ…) ነው። ተስፋዬ በደም ኤርትራዊ ቢሆንም ያደገው ቢሾፍቱ ነው። ስለዚህ የተስፋዬ ማንነት የተገነባው በቢሾፍቱ ባህል ነው። ተስፋዬ ከኤርትራዊነት ይልቅ ኢትዮጵያዊነቱ ከፍተኛ ነው። እንደዛም ቢሆን ግን የተስፋዬ ማንነት እስከ ዛሬ ድረስ በጣም አወዛጋቢ ሆኖ ቀጥሏል። ኤርትራዊ ደም ስላለው ብቻ ብዙዎች አያምኑትም። “ኤርትራዊ ሆነህ ለምን ስለ ኢትዮጵያ ትጽፋለህ?” ተብሎ እስኪሰለቸው ተጠይቋል። በዚህ ምክንያት የማንነት ጥማት ያጋጠመው ይመስላል። አብዝቶ ስለ ቢሾፍቱ የሚጽፈው ከዚህ ጥማት የተነሳ መሆኑን መረዳት ይቻላል። ይህ የማንነት ጥማት በአብዛኛው ስደተኛ ዘንድ የሚያጋጥም ነው። የተስፋዬ ደግሞ የባሰ የሚሆነው ኢትዮጵያዊ ፓስፖርቱን በመነጠቁ ነው። በእርግጥ ፓስፖርቱን ቢያጣም ኢትዮጵያዊ ማንነቱን እንዳላጣ ለማሳመን የመጽሃፉን ሰባት ምዕራፎች ቢሾፍቷዊ አድርጎቸዋል።
ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ ኢትዮጵያ የነፈገችውን ማንነት ከኤርትራ ለማግኘት ይጣጣራል። “የወደዱትን ሲያጡ የጠሉትን ይቀላውጡ” መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ ተፈጥሯዊ ነው። ኢትዮጵያዊ አይደልህም ሲባል ኤርትራዊነቱን ማንቆለጳጰሱ አይገርምም። ለዚህም ይመስላል ኢትዮጵያን እና ኤርትራን በማወዳደር የተጠመደው። ውድድሩ ከታዕታይ ምስቅልቅል (inferiority complex) የመጣ ማካካሻ (coping mechanism) መሆኑ ነው። ይሄ ደግሞ በተስፋዬ ብቻ ሳይሆን በአብዛኛዎቹ ኤርትራዊያን ስደተኞች ዘንድ የተለመደ ሽምጠጣ ነው። ከዚህ ባሻገር ግን “የኤርትራ ሰላይ ነው” የተባለው ብዙም ውሃ አይቋጥርም። በእርግጥ የሚያውቀውን መረጃ ሁሉ ለወዲ አፎም እንዳስረከበ ግልጽ ነው። የወቅቱን መረጃ ግን ሊያገኝ አይችልም። ስለዚህ ሰላይ ነው ብዬ አላምንም።

2. ኢትዮጵያ እና ኤርትራ
ተስፋዬ ኢትዮጵያንና ኤርትራን በብዙ ነገሮች ያወዳድራል። አንዳንዴ እንደ ህጻን ልጅ ብሽሽቅ ውስጥ ይገባል። ለምሳሌ ኤርትራ ከደርግ የተገነጠለችው በሻእቢያ የውጊያ ብቃት እንደሆነ በተደጋጋሚ ይገልጻል። ኢህአዴግ ባይኖር ሻዕቢያ ዘላለም መገንጠል አለመቻሉን ሽምጥጥ ያደርጋል። ይህንን ለማስረዳት በርካታ ታሪኮች ጽፎልናል።
- የጄኔራል ታሪኩ ዓይኔን ግድያ በስማ በለው መረጃ ላይ በመመስረት “ከሻዕቢያ ጋር እንደራደር በማለቱ” እንደሆነ ሊያሳምነን ይሞክራል።
- ውድድሩን በመቀጠልም “አጸደ አደዋ” የተባለች ታጋይ ታሪክ አንስቶ የህወሃት ሰራዊት የትም የወደቀ መሆኑን ለማሳየት ሲጠቀምባት፤ “ጥቁር ጽጌሬዳ” በሚለው ቀጣይ ምእራፍ ውስጥ ደግሞ የኤርትራዊቷን ወጣት ምቾች እና ውበት ያሳየናል።
- እናት አገር ኢትዮጵያን “በአባት አገር ኤርትራ” ተክቶ አንድ ምእራፍ ሰጥቶ ያሳየናል።
- ሁላችንም የምናውቀውን መለስ ዜናዊ ስል ኦሮማይ መጽሃፍ የሰጠውን “ትርጓሜ” በአንድ ምእራፍ
አድምቆ ተርኮታል።
- የንስር አሞራው ታሪክ እና የኦርዮሌዎቹ ታሪክ በማምጣት የኤርትራ ጦር የኢትዮጵያን ጦር እንድሚያሸንፍ ሊያሳምነን ይጥራል።
እነዚህ እና ሌሎች በርካታ ታሪኮች መተረክ የፈለገበት ምክኒያት ኢትዮጵያ የኤርትራን አይበገሬነት አምና መደራደር እንዳለባት ለማሳየት ይመስላል። ለነገሩ የሱማሊያዊው ስደተኛ ህጻን (ማሊክ) ታሪክም ተመሳሳይ ነው። ተስፋዬ ለማሊክ ኳስ ገዝቶለት እንዳታለለው ኢትዮጵያም ጥቂት ነገር በመስጠት የሱማሊያን ችግር መፍታት ትችላለች ይለናል። ሱማሊያ የሚለው ኦጋዴንን ይሁን ወይም ሞቃዲሾን አይገልጽም። የቀጠናው ችግር ግን ተስፋዬ እንደሚለው ቀላል አይደለም።

3. የጫልቱ ግርግር
ተስፋዬ እንደሚለው ከሆነ መጽሃፉ በነጻ የተበተነው በምእራፍ ሰባት ምክንያት ነው። በእውነቱ “ጫልቱ እንደ ሄለን” የሚለው ምእራፍ እንዴት አዋራ ሊያስነሳ እንደቻለ አልገባኝም። ሁላችንም ተመሳሳይ ታሪኮችን እናውቃለን። እንዲህ አይነት ታሪክ ተፈጽሞ አያውቅም የሚል ሰው ገጥሞኝ አያውቅም። ግን በደፈናው ለምን ጻፈ የሚል ተቃውሞ በብዛት አንብቤያለሁ። የጫልቱ ታሪክ መታተሙ በሁለት ምክንያት ትክክል ነው ብዬ አምናለሁ። የመጀመሪያው ሃሳብ በነጻነት እንዲገለጽ ስለምፈልግ። ሁለተኛው ችግሮችን በማለባበስ ትክክለኛ መፍትሄ ይመጣል ብዬ ስለማላምን ነው።
በእርግጥ የጫልቱ አይነት ችግር በዚህ ዘመን እጅግ ቀንሷል። ታዲያ ተስፋዬ ለምን ከዚህ ሁሉ አመት በኋላ ሊጽፈው ፈለገ? ታሪኩ ከስደተኛነቱ ጋር የሚያይዘው ምንም ጉዳይ የለም። ይህንን ታሪክ በመጽሃፉ ውስጥ እንዲካተት የፈለገበት ትልቅ ምክንያት እንዳለው አስባለሁ። ከነዚህም አንደኛው ተስፋዬ እራሱን እንደ ኦሮሞ ስለሚቆጥር፣ የኦሮሞን ችግር ማስተጋባት እንዳለበት በማመኑ ሊሆን ይችላል። ከዚህ በፊት ለሰራው ስራ በውጪ የሚኖሩ የኦሮሞ መብት ታጋዮች “ኦቦ” የሚል ማእረግ እንደሰጡት ነግሮናል። በተጨማሪም ከተስፋዬ አጻጻፍ ተነስተን ጫልቱን በገሃዱ አለም ብንፈልጋት የምናገኛት ይመስለኛል። የጫልቱን ታሪክ ተስፋዬ በደራሲ ብእሩ እንደለወጠው ጽፎዋል። ይህም ማለት ጫልቱ በዚህ ዘመን ያለ ሰውን ታሪክ እንድትወክል ተፈልጓል ማለት ነው። ከዚህ በመነሳትም የጫልቱ ሚደቅሳ ታሪክ፤ የብርቱካን ሚደቅሳ ታሪክ እንደሆነ መገመት ይቻላል። ምክንያቱም ብርቱካን ኦሮሞ መሪ ሆና የአማራ ማንነት እንደሸፈናት ጽፎ አንብቤያለሁ። መቼም ተስፍሽ “Conspiracy theory” በጣም ይወዳል። የ”ሰው ለሰው” ድራማ መሪ ተዋናይ የሆነው አስናቀ፤ መለስን የሚወክል ነው ሲል ከርሞ ነበር። ወዲያው ግን የአስናቀ ሚስት አዜብን አትመስልም በማለት ነገሩን አፍርሶታል።

4. የታሪክ እና የሃይማኖት ክለሳ
ተስፋዬ በአዲሱ ማስታወሻው አይነኬ አርዕስቶችን አንስቷል። ማንሳት ብቻ ሳይሆን ዘርጥጧቸዋል። ታሪክ እና ሃይማኖትን በተመለከተ ጥልቅ ጥናት ቢያስፈልግም ተስፋዬ ግን በድፍረት ብቻ ተጋፍጦታል። ይህ ትክክል አይመስለኝም።
የአቡነ ተክልዬን ገድል መሰረት የሌለው ነው ለማለት ሞክሯል። በዛም ሳይገደብ የፕሮቴስታንትን “ጌታ ተናገረኝ” የሚሉት ከህሊናቸው ጋር እያወሩ ነው ብሏል። በእርግጥ “የፍቅር በለጠ” ታሪክ በጣም አስቂኝ ነው። የፍቅር እየሱስ “ስለ ቁሳቁሶች ዋጋ ለመንገር የሚሯሯጥ የንግድ ወኪል” ይመስላል ብሏታል። እውነትም እንዲህ አይነት አማኞች ያሉ ይመስለኛል።
በተጨማሪም እኛ ኢትዮጵያዊያን ስለ አካል ጉዳተኞች ያለንን አመለካከት በሚገባ ተችቶበታል። “የጨለለቃ ዝይ” እና “ደስተኛ ዝይ” በሚለው ጽሁፉ ውስጥ ይህንን በደንብ ማየት ይቻላል።
ተስፋዬ ታሪክን ከአፈ-ታሪክ እያደበላለቀ ሊጋግረው ሞክሯል። እነዚህን ርዕሶች መፈተሹ ባልከፋ ነበር። ሆኖም ግን በጥልቅ ጥናት ላይ ተደግፎ እና ማስረጃውን አደራጅቶ ቢሆን ምንኛ ጥሩ በሆነ ነበር።
እነዚህ ሁሉ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች እንደ ችግር ተይዘው የበለጠ ጥናት ሊደረግባቸው እንደሚገባ የተስፋዬ መጽሃፍ ጥሩ ማመላከቻ ነው።
መጀመሪያ ባሳተመው “የጋዜጠኛው ማስታወሻ” መጽሃፉ ላይ ላይ የነቆረውን የኢትዮ-ሚድያ ባለቤት አብርሃ በላይን ለመካስ እዚህ ግባ የማይባል የራያ ላይ ገጠመኝ በአንድ ምእራፍ አትሟል። እጅ መንሻ ካልሆነ ጥቅም የለውም። ከዚህም ሌላ በመጀመሪያ መጽሃፉ “ሙት” ብሎ ስላላገጠባቸው፤ ሁለተኛ መጽሃፉን በኢንተርኔት በተኑብኝ ካላቸው የኢህአፓ አባላት ጋር እሰጥ አገባው ቀጥሏል። በዚህ መጽሃፉ ውስጥ ኢህአፓን “ኢሃባ” በሚባል ውሻ መስሎ አቅርቦታል። “ኢሃባ” መልኩ የማይለይ የሰፈር ውስጥ ልክስክስ ውሻ ነው ይላል።
በእርግጥም ተስፋዬ በዚህ መጽሃፉ “ፈንጂ” ረግጧል። ይህ ጉዞው የት እንደሚያደርስው ወደፊት የምናየው ይሆናል።

 

Read 3900 times