Saturday, 26 October 2013 13:55

በአዳማ አባ ገዳ “የንጉሡ ነገር” ተስፋ የለውም!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

          የጥቅምትን የመጀመሪያ ቅዳሜና እሁድ ያሳለፈኩት በናዝሬት ማለትም በአዳማ ከተማ ነው። እኔና ስምንት ዘመዶቼ ወደ አዳማ ያመራነው በአንድ እህታችን የጋብቻ ሥነ ስርዓት ላይ ለመገኘት ነው፡፡ የናዝሬት ዘመዶቻችን አልጋ የተያዘልን መሆኑን አስቀድመው በስልክ ስለነገሩን፣ በቀጥታ ያመራነው አዳማ ጌጤ ሆቴል ጀርባ ገባ ብሎ ወደሚገኘው አባ ገዳ እንግዳ ማረፊያ ቤት ነበር፡፡ ናዝሬቶች፤ አልገዎቹ የተያዙት ለእኛ መሆኑን በመግለፅ፣ ከእንግዳ ማረፊያ ቤቱ ሠራተኞች ጋር አስተዋወቁንና፤ “እንደኛ ሆናችሁ አስተናግዱልን” በማለት አደራ ሰጥተው ወደ ፕሮግራማቸው ተመለሱ፡፡
የምሳ ሰዓት ደርሶ ወደ ሠርጉ ቦታ ከመሄዳችን በፊት አንድ ሰዓት ተኩል ያህል ጊዜ ስለነበረን በየክፍላችን ገብተን አረፍ አልን፡፡ በኋላም ከየክፍላችን ተጠራርተን ወደ ምሳ ግብዣው ስናመራ “ምን የጐደለ አለ?” የሚል ጥያቄ ላቀረቡልን የእንግዳ ማረፊያ ቤቱ ሠራተኞች፤ “ከውሃ በስተቀር ምንም” የሚል መልስ እንደሰጠናቸው አስታውሳለሁ፡፡
የእራት ፕሮግራም የተዘጋጀልን በዚሁ በአረፍንበት ቤት ስለነበር፣ ወደ ቦታው የተሰበሰብነው በጊዜ ነው፡፡ ሁለት ሰዓት ላይ ራት በልተን ለሙሽሪት የዳቦ ስም የማውጣት ስርዓት ቀጠለ፡፡ የሙሽራው እናትና ዘመዶቹ ይሆናል ያሉትን ስም ሲሰጡ፣ የሰጡበትን ምክንያት ሲያስረዱ፣ “የለም እኔ የተሻለ ስም አለኝ” ያለው ስም ሲያወጣ፣ የእሱም በተራው ተቀባይነት ሲያጣ ቆይቶ የሙሽራው እናት ያወጡት ስም በደምቡ መሠረት ፀድቆ ዳቦው ተቆረሰና ተመራረቅን፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን የእንግዳ ማረፊያው ቤት ሠራተኞች አብረውን ነበሩ፡፡ እንግዳም አስተናጋጅም ሆነው እያገለገሉ ቆይተዋል፡፡ ከምሽቱ አራት ሰዓት ግድም የናዝሬት ዘመዶቻችን ወደየቤታቸው ሲሄዱ እኛም ወደየመኝታ ክፍላችን ገባን፡፡ ከግማሽ ሰዓት በኋላ ያለሁበት ክፍል በር በኃይል ተደበደበ፡፡ በድንጋጤ በሩን ከፍቼ ወጣሁ።
“የአልጋ ሂሳብ አልተከፈለም” አለኝ፤ በር የደበደበው የአልጋ ክፍል ሠራተኛ፡፡
“እኛ አልጋ ተይዞላችኋል ተብለን ነው የመጣነው፡፡ ቀን ደግሞ አብረናችሁ ውለን አብረን አምሽተናል፤ ለምን አልጠየቃችሁንም?” አልኩ፤ እራሴን እየተቆጣጠርኩ፡፡ የአልጋ ክፍሉ ለጥያቄዬ መልስ ከመስጠት ይልቅ ገንዘቡን እንድከፍለው ብቻ መፈለጉን ከሁኔታው ተረዳሁ፡፡
“ነገ ጥዋት አልጋ የያዙልንን ሰዎች ጠይቀን፣ ካልከፈሏችሁ እንከፍላችኋለን” አልኩትና ወደ ክፍሌ ተመለስኩ፡፡
“የድርጅቱ ባለቤት ሳታስከፍሉ እንዳታሳድሩ ብሎናል” አለኝ፤ ሠራተኛው፡፡ እኔም ከመነታረክ ብዬ የራሴን ከፍዬ ወደ ክፍሌ ገባሁ፡፡
ከእኔ በኋላ የተቀሰቀሱት በየተራ እየተነሱ ከአልጋ ክፍል ሠራተኛው ጋር ክርክር ገጠሙ። እኔም ተመልሼ ከእነሱ ጋር ተቀላቀልኩ፡፡ እኔ በትዕግስት ያለፍኩት የበር ድብደባ ከሁላችንም መጨረሻ ለተቀሰቀሰው አሊ፣ በጣም የሚያበሳጭ ጉዳይ ሆነ፡፡
“ለምን በስርዓት አታንኳኩም? የእናንተን ብር ይዞ የሚጠፋ አለ?” አለ አሊ፤ በጣም እንደተቆጣ።
“ሳትከፍል ለማደር ነው የፈለግኸው” አለ ድንገት የደረሰው የአባ ገዳ የእንግዳ ማረፊያ ባለቤት፡፡
“ማን በነፃ አሳድሩኝ አላችሁ” አሁንም ይበልጥ እየተቆጣ አሊ ተናገረ፡፡ “አሁን መነጋገር አይኖርብንም፤ የሁሉንም እኔ ልከፍልህ እችላለሁ። አንተ ደረሰኝ ብቻ ስጠኝ፡፡ ነገ ከነሱ ጋር እንነጋገራለን” የአሊ መፍትሄ ነበር፡፡
ባለቤቱ ደረሰኝ በመጠየቁ የተደሰተ አይመስልም፡፡ እያጉረመረመ ሄደ፡፡ ወዲያው ግን ተመለሰ - የአባ ገዳ ማረፍያ ባለቤት፡፡ እናም በቁጣ ድምፀት “እንዲያውም አንተ አልቃኢዳ ልትሆን ትችላለህ! እዚህ ቤት አታድርም” ሲል አሊ ላይ አምባረቀበት፡፡
ሁላችንም መብረቅ የወደቀብን ያህል ነው የደነገጥነው፡፡ መጀመርያ ላይ ለምን እንዲህ እንዳለውም አልገባኝም ነበር፡፡ ድንጋጤዬ ሲቀንስልኝ ግን በስሙ የተነሳ እንደሆነ ገባኝ። በጣምም አዘንኩ፡፡ እንዲህ አይነቱ ፍረጃ በስንቶች ላይ እንደተፈፀመ፣ ወደፊትም ሊፈፀም እንደሚችል ሳስበው በጣም ከበደኝ፡፡ ቀጥሎ ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት አስቸጋሪ አልነበረም፡፡ አሊን እየገፋሁ ወስጄ መኝታ ክፍሉ ውስጥ አስገብቼው ተመለስኩ፡፡
ጭቅጭቁን ለማብረድ ከመካከላችን አንዱ የአልጋውን ሂሳብ ከፈለ፡፡ የድርጅቱ ባለቤት ግን አሁንም በማን አለብኝነት መናገሩን ቀጥሏል፡፡
በሆቴል ቤቶች አካባቢ “ደንበኛ ንጉሥ ነው” ተዘውትሮ የሚነገር አባባል አለ፡፡
እኛን ግን እንኳን እንደ ንጉስ እንደ ሰው የሚቆጥረንም አላገኘንም፡፡
ባለቤቱ ገንዘቡን ተቀብሎ ሲወጣ የአልጋ ክፍል ሠራተኛውን ጠርቶ “ነገ አንድም ሰው ሳይቀር እንድታስወጣ፡፡ ማንም መቀጠል አይችልም!” በማለት ትእዛዝ ሰጠ፡፡ እኛም በነጋታው ለሁለት ቀን የተያዘልንን ክፍል ለቀን ወጣን፡፡
ማንም ሰው በሃይማኖቱ፣ በፖለቲካ አስተሳሰቡ ወዘተ መገለል ሊደርስበት እንደማይገባ በሕግ ተደንግጓል፡፡ እንዲህ አይነት በደል የደረሰበት ሰው መብቱን እንዴት ነው የሚያስከብረው?
ለአፍ ያህል “ደንበኛ ንጉሥ ነው” እያሉ ማጭበርበር ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ንጉሡ ተገቢውን መስተንግዶና አገልግሎት ማግኘት አለበት፡፡ በአባ ገዳ የእንግዳ ማረፊያ ግን “የንጉሡ ነገር” ተስፋ ያለው አይመስልም፡፡ ያሳዝናል፡፡

Read 1764 times