Saturday, 26 October 2013 13:57

ጉደኛዋ የኒው ኦርሊንስ ከተማ!

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(2 votes)

     “ያኔ በኒው ኦርሊንስ ነገሮች አስቸጋሪ ነበሩ፤ እንኳንስ ለትምህርታችን ሊከፈልልን ይቅርና በልተን ካደርንም ዕድለኞች ነን፡፡ በህይወት መኖር እንቀጥል ዘንድ የሙዚቃ ፍቅር በደማችን ውስጥ ሊኖረን የግድ ነበር”
(ሉዊስ አርምስትሮንግ፤ የትራምፔት ተጫዋች)
አገሬ ምድር ላይ እያለሁ አገሬ የናፈቀኝ መሰለኝ፡፡ የማውቀው ሰው አጣሁ እንጂ፣ አገር ምድሩን ጠንቅቄ አውቀዋለሁ፡፡ ህንፃዎቹ፣ ሙዚቃ ቤቶቹ፣ መንገዱ ወዘተ… አዲስ አልሆኑብኝም፡፡ ሠራተኛ ሰፈር፣ እሪ በከንቱ፣ ውቤ በረሃ፣ ዶሮ ማነቂያ፤ ገብረትንሳይ ኬክ ቤት፣ መሃሙድ ሙዚቃ ቤት፣ ሲኒማ አምፒርና ሀገር ፍቅር ቲያትር፣ ገበጣ መጫወቻ የሚመሳስሉ አስፋልቶች፣ ጣልያን የሰራቸው ጥንታዊ ፎቆች፣ ጣራቸው የዛገ አሮጌ ቤቶች … ቁጭ ፒያሳን - የሸገሯን። በአሜሪካ ኒው ኦርሊንስ ከተማ፣ በሉዚያና መንገድ እየተዘዋወራችሁ ዙሪያ ገባውን ስትቃኙ “ፒያሣ ነው እንዴ ያለሁት?” ብላችሁ መደናገራችሁ አይቀርም፡፡

በአሜሪካ ቆይታዬ እንደዚህች ከተማ ማንም ያደነጋገረኝ የለም፡፡ በነገራችሁ ላይ ኒው ኦርሊንስ የተቆረቆረችው በ17ኛው ክፍለ ዘመን ሉዚያና በተባለ ፈረንሳዊ የጦር አበጋዝ ነው፡፡
ከፒያሣ (ከራስ መኮንን ድልድይ እስከ ሲኒማ አምፒር) ያለው መንገድ በቸርችል ጎዳና፣ በቦሌ፣ በካዛንቺስ፣ በሜክሲኮ፣ በአራት ኪሎ፣ በጦር ሃይሎች፣ በመገናኛ፣ በጨርቆስ፣ በቺችንያ… በአዲስ አበባ ባሉ ሰፈሮች በሙሉ ሲዘረጋ፤ በደቡብ ምስራቅ ሉዚያና የምትገኘውን ኒው ኦርሊንስ ከተማ ይፈጥራሉ። ከተማዋ የአውሮፓውያን የስነህንፃ ጠበብቶች የእጅ ስራ ውጤት በመሆንዋ የተነሳ ‹‹በአሜሪካ የምትገኝ የአውሮፓ ከተማ›› እያሉ ይጠሯታል፡፡ ኒው ኦርሊንስ በዕድሜ ጠገብነቷም ሆነ በጥንታዊ ቤቶች ባለታሪክነቷ የሚወዳደሯት ሌሎች የአሜሪካ ከተሞች የሉም፡፡ ጥንታዊ ቤቶቿ እንደታሪክ መዘክር ስለሚቆጠሩ፣ ያለፈቃድ ማደስም ሆነ ንክች ማድረግ አይሞከርም፡፡
እቺ ጥንታዊና ታሪካዊት ከተማ እ.ኤ.አ በ2005 ዓ.ም በሃሪኬን ካትሪና ክፉኛ ተመትታ እንዳልነበረች መሆኗን ነዋሪዎቿ ይናገራሉ፡፡ በአሜሪካ ታሪክ እጅግ አደገኛ የተባለው አውሎነፋስ ያናወጣት ኦርሊንስ፤ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባታል፡፡ በአደጋው 1ሺ 700 ገደማ ሰዎች ሲሞቱ፣125 ቢ.ዶላር የሚገመት ንብረትም ወድሞባታል፡፡

ይሄ አደጋ ቀደም ሲል በከፍተኛነቱ ሪከርዱን ይዞ ከነበረውና ፍሎሪዳን ከመታው ሃሪኬን አንድሪው በአምስት እጅ ይልቃል ተብሏል፡፡ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የከተማዋ ክፍል በጐርፍ ተጥለቅልቆ የነበረ ሲሆን ከአደጋው በኋላም አገር አማን ሲሆን “በውሃ ላይ የቆመች ከተማ”፣ “የካትሪና ትራፊ” እና የመሳሰሉ ቅጽል ስሞች ወጥቶላታል፡፡ ሚሲሲፒ ወንዝን ከጐንዋ፣ ፓሲፊክ ውቂያኖስን እና የሜክሲካን ባህረ ሰላጤን ከግርጌዋ የተንተራሰችው ኦርሊንስ፤ በጥንት ጊዜ የባህር ላይ ዘራፊዎች “ዱር አገሬ” ብለው በመሸሸግ “አሸሼ ገዳሜ” የሚሉባት ከተማ እንደነበረች ይነገራል፡፡
የኒው ኦርሊንስ ሌላ መታወቂያ የጃዝ ሙዚቃ ነው፡፡ “የጃዝ ከተማ” ይሏታል፡፡ ከተማዋ አያሌ የጃዝ ሙዚቃ ቀማሪዎችን ፈጥራለች፡፡ ከ40 በላይ ታሪካዊ ሙዚየሞችን ይዛለች፡፡ የሆሊዉድ የፊልም መንደር ዋና መስሪያ ቤት በኒው ኦርሊንስ ነው። እ.ኤ.አ በ2012 መጨረሻና በ2013 ዓ.ም ከተሰሩ አስራ ሁለት ፊልሞች መካከል አስር ያህሉ በዚህች ከተማ ውስጥ የተቀረፁና በከተማዋ ላይ ያነጣጠሩ እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ለአብነት ያህል ኦፕራ ዊንፍሬይ፤ የተወነችበት “ዘ ባትለርስ” ፊልም ይጠቀሳል፡፡ ኒው ኦርሊንስ የፀሐፊዎች፣ ሙዚቀኞች፣ ሰዓሊዎችና የፊልም ተዋናዮች መናኸሪያ ናት፡፡ የኢትዮ- ጃዝ አባት በመባል የሚታወቀው አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ፤ በየዓመቱ በከተማዋ በሚካሄደው የጃዝ ፌስቲቫል ላይ እንደሚገኝ ኢትዮጵያውያን ወዳጆቼ አጫውተውኛል፡፡

ባርበን ጐዳና
ባርበን ስትሪት (ጐዳና) ገብቶ ያልጠጣ፤ በማዲግራስ ያልተወዛወዘ፣ በዞሎ ዳንስ ያልተውረገረገ፣ በጃዝ ሙዚቃ ያልተመሰጠ፣ መጠጥ በእጁ ይዞ በዚህች ጐዳና ላይ ያልተንጐራደደ፣ ኦርሊንስን አውቃታለሁ ሊል አይችልም ይላሉ፤ ከተማዋን አብጠርጥረው የሚያውቁ ኢትዮጵያውያን፡፡ ከሠኞ እስከ ሰኞ ባርበን ጐዳና በላይቭ ሙዚቃ እየነጐነች ጠብቶ ይነጋል፡፡ ጐዳናው የመጠጥ ቤትና የሬስቶራንት ችግር የለበትም፤ በሽበሽ ነው፡፡ በአንድ ረድፍ ብቻ ከ40 በላይ መሸታ ቤቶች ተደርድረዋል፡፡ በሙዚቃ የሞቁና የደመቁ፡፡ ከትናንሽ ካፌዎች እስከ ስመጥር ሬስቶራንቶች ድረስ በዓይነት በዓይነት መመገብያ ማግኘት አይቸግርም።
ዓመታዊ ክብረ በዓሎችን የሚከበሩበት ዝነኛ ጐዳና ነው- ባርበን፡፡ ዓመታዊ የጃዝ ፌስቲቫል፣ ዓመታዊ የጥቁሮች በዓል፣ ዓመታዊ የተመሳሳይ ፆታዎች ክብረበዓልና ሌሎችም በድምቀት ይከበርበታል፡፡ ባርበን ቱሪስቶች ከሚርመሰመሱባቸው የከተማዋ ክፍሎች ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ጐዳናው ሌላ የሚታወቅበት መለያም አለው፡፡ ለዓይን በሚዘገንን ቆሻሻና አፍንጫ በሚሰነፍጥ ክፉ ጠረኑ ይታወቃል፡፡ ይሄ የቱሪስት ጐዳና፤ የእኛን አገር አትክልት ተራ አስታውሶኛል - የፒያሳውን፡፡
የባርበን ጐዳና እንኳንስ ክብረበዓል ሲኖር በአዘቦቱም ቀን በቆሻሻና በትርኪምርኪ ከአፍ እስከገደፉ የሞላ ነው፡፡ የሲጋራ ወረቀቶች፣ ሶፍት፣ የፈረሶች ሽንት፣ የመጠጥ ፕላስቲኮች ወዘተ … ጐዳናውን በክለውታል፡፡ ዓይን ከሚቆረቁረው ጭስና አፍንጫ ከሚሰረስረው ጠረን በተጨማሪ የሰው ግፊያው የመርካቶን ገበያ ያስንቃል፡፡ በነገራችሁ ላይ የኒው ኦርሊንስ ፖሊሶች የፀጥታ ጥበቃቸውን የሚያከናውኑት በእግራቸው ወይም በቢኤምደብሊው ሞተራቸው ላይ ተፈናጠው አይደለም፡፡ ቢኤምደብሊው የሚያስከነዱ ሰንጋ ፈረሶች እየጋለቡ ነው፡፡
እነዚህ ፈረሶች ሽንታቸውን እንደ ዥረት የሚለቁት በአውራ ጐዳናው ላይ ነው፡፡ እንደ ፖሊስ ውሾች የሰለጠኑ አይደሉም፡፡ የእነሱ ሽንትና ሌላ ሌላውም ሲቀያየጥ የሚፈጥረውን “ኮክቴል ጠረን” ልትገምቱት ትችላላችሁ፡፡ የጐዳናው ጠረን ከመቅጽበት ጉንፋን የሚያሲዝና አላሳልፍ የሚል ቢሆንም ቱሪስቶች አካባቢውን ሲጠየፉት ወይም አፍንጫቸውን ሲይዙ እንኳን አይታዩም፡፡ በከተማዋ የሚኖር አንድ ኢትዮጵያዊ የታክሲ ሾፌር እንደነገረኝ፤ ቱሪስቶቹ ጠረኑ የተስማማቸው ነው የሚመስሉት፡፡ በጎዳናው ዘና ብለው ሲዘዋወሩ እንጂ ሲማረሩ ሰማሁ የሚል የለም፡፡ “ጠረኑ ሱስ ሳይሆንባቸው አይቀርም” ብሎኛል-የታክሲ ሾፌሩ።
ኒው ኦርሊንስ የጃዝ ሙዚቃ ከተማ ናት ብያችሁ የለ! ታዲያ ሙዚቃው ሁሉ ላይቭ (ህያው) ነው እንጂ ዲጄ የሚባል “ጨዋታ” የለም፡፡ የሙዚቃ ጠበብቶች የማንን ጎፈሬ ሲያበጥሩ?! ሙዚቃ በዲጄ ማጫወት በከተማዋ እንደ ነውር (taboo) የሚታይ ነው- ጥበብን እንደማርከስ ይቆጠራል። ሙዚቃው ሌት ተቀን ሲቀወጥ፣ የድምፁ ነገር እንዴት ይሆናል፤ ማንስ ማንን ያዳምጣል? ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ ሁሉም እንዳሻው የሚለቀው ይመስላል እንጂ፤ የሚፈቀደው የድምፅ መጠን ይታወቃል፡፡ የተፈቀደውን ልክ ካለፉ ቅጣት ይከተላል፡፡ እንደኛ አገር በምንግዴ እስከ ጣራ ድረስ መልቀቅ ህገ ወጥነት ብቻ ሳይሆን ነውርም ነው፡፡ ከስንዴ መሃል እንክርዳድ አይጠፋምና ህግ ወጦች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ለእነሱ ግን ተቆጣጣሪዎች አሉላቸው፡፡ በየአካባቢው እየተዘዋወሩ የድምፅ መጠን በመለካት ህግና ስርዓት የሚያስከብሩ፡፡ ያለዚያማ የጩኸት ጎዳና ይሆን ነበር፡፡
ባርበን ጎዳና ለዓለማውያን ብቻ ሳይሆን ለመንፈሳውያንም ክፍት ነው፡፡ የሁለቱም ጐራ ተዋንያኖች ተቻችለው ዓላማቸውን ያራምዳሉ። ‹‹መንግስተ ሰማያ ደርሳለችና ንስሃ ግቡ!›› የሚል ማሳሰቢያ የሚለፍፍ ሃይማኖተኛ እንዲሁም የመፅሃፍ ቅዱስ ጥቅሶችን እንደመፈክር ይዞ በመሃል ጐዳና የሚንጎማለል ሰባኪ ማየት እንግዳ ነገር አይደለም - በነፃነት ጎዳናዋ ባርበን ስትሪት!
በተለይ ለአበሻ ‹‹አበስ ገበርኩ!›› የሚያሰኙ ትዕይንቶች ጐዳናዋን አያጧትም፡፡ ምን ጠፍቶ በባርበን ጎዳና!! በየመጠጥና ጃዝ ቤቱ በር ላይ የሚያማምሩ እንስቶች ተደርድረው ቆመዋል - እንደ ኤግዚቢሽን፡፡ ቆነጃጅቱ ለዓመል ያህል የጡታቸውን ጫፍ ከመሸፈንና ደልደል ያለ መቀመጫቸውን እንዲሁም ሃፍረተ ስጋቸውን በመናኛ ፒኪኒ ከመሰወራቸው በቀር፤ እርቃናቸውን ናቸው ቢባሉ ይሻላል፡፡ መለሎ ቁመናና ሰፊ ደረት ያለው ወንድ ደግሞ በፓንት ብቻ ቆሞ፣ 5 ዶላር ለሚከፍሉ ሴቶች ብልቱን አውጥቶ ያስጐበኛል፡፡ አብረውት ፎቶ የሚነሱም አሉ። የባሰባቸው ደግሞ እንዲያስነካቸው እየጠየቁ የፍላጎታቸውን ያደርጋሉ፡፡ ሌላው ቢቀር ምናለ ጓንት እንኳን ቢኖር?!

ሮያል ስትሪት
ይሄ ጐዳና እጅግ ፀጥታ ያረበበበት ነው፡፡ “የጥበብ ጐዳና” እያሉ ይጠሩታል፡፡ ዝነኛ የዓለም ሰዓሊያን ተጠራርተው የመጡ በሚመስሉበት ሮያል ስትሪት፤ ሰዓሊያን ተደፍተው ከቀለም ጋር ይጫወታሉ፡፡ በሮያል ጐዳና የስዕል ስራዎች ከ20ሺ ዶላር ጀምሮ ይቸበቸባሉ፡፡ የስዕል ጋለሪዎች በሽበሽ ናቸው፡፡ ጊታር የሚጫወቱ ነጮች በየቦታው ተቀምጠዋል፡፡
ቱሪስቶችና ሙዚቃ አድናቂዎች ኪሳቸውና ቦርሳቸው ውስጥ ዘው እያሉ እጃቸው ያወጣውን ጣል እያደረጉላቸው ያልፋሉ፡፡ እንደኛ አገር የአዝማሪ ሽልማት መሆኑ ነው፡፡ እንዲህ ስላችሁ ግን ሙዚቀኞቹ ምንም የማያውቁ ምስኪኖች እንዳይመስሏችሁ፡፡ የሙዚቃ ሊቆች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ወዳጆቼ እንደነገሩኝ፤ አብዛኞቹ የበርክሌ ዩኒቨርስቲ ምሩቃን ናቸው፡፡ በሮያል ስትሪት ሙዚቃ የሚጫወቱት የጥበብ ፍቅራቸውን ለመወጣት ነው፡፡ ከጥበብ በረከት ለመቋደስ!
የሰዎችን እጣ ፈንታ የምትተነብይ አንዲት ሴትም በዚሁ ጐዳና ላይ በስራ ተጠምዳ ስትባትል ታዝቤአለሁ፡፡ ጥንቆላ በሮያል ጐዳና ወደጥበብ ደረጃ ሳያድግ የቀረ አይመስለኝም፡፡ ሳይንስ ነው የሚሉም እንዳሉ ሰምቻለሁ፡፡ ሳይንስነቱ እንኳን አልተዋጠልኝም፡፡

የድሆች ሰፈር (“ዘጠነኛው ዓለም”)
በከተማዋ ካስገረሙኝ ስፍራዎች መካከል የድህነት ወለል ወይም “ዘጠነኛው ዓለም” ተብሎ የሚታወቀው የጥቁሮች ሰፈር ነው፡፡ ወደዚህ ሰፈር ለመዝለቅ እንኳን እንግዳ ነዋሪዎቹም አይደፍሩም ተብያለሁ፡፡ አብዛኞቹ ባለታክሲዎች ዳጐስ ያለ ክፍያ ቢከፈላቸውም እሺ አይሉም፡፡ ብዙ ሰዎች ገብተው ቀልጠዋል ይባላል፡፡ በማን እንደተተኮሰ ባልታወቀ ጥይት ክልውት ያሉ መኖራቸውን ሰምቻለሁ፡፡ “ፖሊስ እንኳን ወደ አካባቢው ዝር አይልም” አለኝ፤ የታክሲ ሾፌሩ ጓደኛዬ፡፡ ይሄኔ የበለጠ ፈራሁኝ፡፡ ግን ደግሞ “ዘጠነኛው ዓለም” ምን እንደሚመስል ለማየት ክፉኛ ጓጉቼ ነበር፡፡
የታክሲ ሾፌር ወዳጄን እንደምንም አግባባሁት። እግዜር ይስጠው! ነፍሱን ሸጦ በታክሲው ወደ “ዘጠነኛው ዓለም” ይዞኝ ሄደ፡፡ ሰፈሩ ጭር ያለ ነው፤ የተወረረ ከተማ ይመስላል፡፡ አብዛኞቹ ቤቶች አሮጌና ጉስቁልቁል ያሉ ናቸው፡፡ እላያቸው ላይ ሳር የበቀለባቸው ሁሉ አሉ፡፡ ሰፈሩ የምርም ድሆች የከተሙበት ነው፡፡ ያጡ የነጡ ጥቁሮች የሚኖሩበት። ይባስ ብሎ እ.ኤ.አ በ2005 ዓ.ም ከተማዋ በሄሪከን ካትሪና ስትመታ ክፉኛ ከተጐዱ አካባቢዎች አንዱ ነበር፡፡ እኒህ ጥቁሮች የሚኖሩት ከአሜሪካ መንግስት የሚያገኟትን የ180 ዶላር ወርሃዊ ድጐማ ብቻ እየጠበቁ እንደሆነ ወዳጄ አውግቶኛል፡፡ በሰፈሩ ውስጥ ለአራት ደቂቃ ያህል እየነዳን ከተመለከትን በኋላ ለመቀጠል አቅማማን።
ድንገት ወደ ጐን ዘመም ብሎ መስኮቱና በሩ ከተወለጋገደ ደሳሳ ቤት ታዛ ላይ ቁጭ ካለች ሴት ጋር ተፋጠጥን፡፡ ሴትየዋ በአራት ትናንሽ ጥቋቁር ህፃናት ተከባለች፡፡ ልጆቿ ሳይሆኑ አይቀሩም ብለን ገምተናል፡፡ ህፃናቱ ሲላፉና ሲሰዳደቡ ነበር፡፡
“ትሰሚያቸዋለሽ…በዚህ ዕድሜያቸው ብልግና እኮ ነው የሚሰዳደቡት” አለኝ - የታክሲዋን መዘውር የጨበጠው ጓደኛዬ፡፡ ከዚህ በላይ በአካባቢው ለመቆየት አልቻልንም፡፡ እንዳመጣጣችን ተመልሰን ወጣን - ከጐስቆላዋ የጥቁሮች ሰፈር፡፡ ይሄን ይሄን አሳይታኛለች ጉደኛዋ የኒው ኦርሊንስ ከተማ!

Read 4199 times