Print this page
Saturday, 26 October 2013 13:47

“መስዋዕትነት ‘በደብል ዲጂት’ ይቀነስ ቢሉ፣ ጦም እያደሩ መቆጠብ ትዝ አለኝ…

Written by  ብዕር ጂ.
Rate this item
(2 votes)

ዶ/ር ስንታየሁ፣ በነካ አፋቸው እንድንቆጥብ እንደነገሩን፣ “እንዳንሞሳስን” በመከሩን!
ባለፈው ሳምንት በዚሁ ጋዜጣ ላይ ከወጡ መጣጥፎች መካከል፣ በ”ነፃ አስተያየት” አምድና በ “ፖለቲካ በፈገግታ” አምድ የወጡ ሁለት ጽሑፎች በማዕከላዊ ጭብጣቸው ይመሳሰላሉ፤ እርግጥ ነው፣ በርዕዮተ ዓለም ምርጫቸውም አንድ ይመስላሉ። ሁለቱም፣ በመንግስት የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ አስተሳሰብና አተገባበር ምርጫ ሳቢያ፣ የዜጐች ኑሮ እየኮሰሰና ቅጥ ያጣ መስዋዕትነት እያስከፈለ እንደሆነ፣ አንደኛው ዝርዝር ማስረጃ አቅርቦ በማስማረር፣ አንደኛው በቀልድ አለዝቦ በማሸሞር ጭብጣቸውን አስረድተዋል፡፡

አንደኛው በንጽጽር ይሟገታል፤ ሌላኛው በፍጥርጥር ይሟገታል። የሁለቱም ጽሑፎች አገራዊ ንበት፣ ሌላ ሶስተኛ ጽሑፍ በመንግስት መጽሔት ላይ እንድማትር አንቅቶኛል፡፡ የዚህ ጽሑፍ የትኩረት አቅጣጫ ግን፣ የሁለቱን መጣጥፎች የርዕሰ ጉዳይ ምርጫ በስሱ አሳይቶ፣ ሦስተኛውን ጽሑፍ በመጠኑ አብዝቶ መጠየቅ ላይ ያተኩራል፡፡ ተተኳሪው ጽሑፍ፣ “በመንግስት የፋይናንስ ድርጅቶች ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ” ባሳተማት፣ “ዐውደ ፋይናንስ” (ቅጽ 1፣ ቁ.1፣ ሚያዚያ 2005 ዓ.ም) መጽሔት ውስጥ፣ ከዶ/ር ስንታየሁ ወ/ሚካኤል ጋር የተደረገው አጭር ቆይታ ነው፡፡ 

በነፃ አስተያየቱ አምድ፣ “ዜጐችን እያቀጨጨ የሚፈረጥም መንግስት…ብዙ አይራመድም፤ ስንት እድሜ ይኖረዋል?” በሚል ርዕስ በቀረበው መጣጥፍ፣ የንግድ ማኒስቴርን መረጃ ጠቅሶ፣ “የውጭ ንግድ ፈቀቅ አላለም፤ ባለበት ደንዝዞ ቆሟል” ይላል። በአይኤምኤፍ መረጃ ላይ ተመስርቶም፣ “የግል ኢንቨስትመንት ተዳክሟል፤ ድርሻው በግማሽ ቀንሷል” ብቻ ብሎ ለፍረጃ አልፈጠነም፤ ባይሆን፣ የአለም ባንክን ሪፖርትም መሠረት አድርጐ፣ “የአገሪቱ የባንክ ብድር፣ 90% ወደ መንግስት ይሄዳል” በማለት በማስረጃ ይሞግታል እንጂ!!
የፀሐፊው ስም ባልተገለፀበት በዚህ ሞጋች መጣጥፍ፣ “የመንግስት ፕሮጀክት ድርሻ እያበበ፣ የግል ኢንቨስትመንት ድርሻ እየተደፈጠጠና እየቀጨጨ የመጣው፣ በተለያዩ ምክንያቶች ቢሆንም፣ ትልቁና ዋናው ሰበብ ግን ከባንክ ብድር ጋር የተያያዘ ነው” በማለት፣ የባንኮች ብድር በየጊዜው ከግል የኢንቨስትመንት ተቋማት እየራቀ፣ ወደ መንግስት ተቋማትና ፕሮጀክቶች እየጐረፈ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

መጣጥፉ፣ በአንዳንድ የመንግስት ጽንፈኛ ካድሬዎች፣ “የኒዮ ሊበራሊስቶች የተሳሳተ አስተያየት፣ ወይም የልማታዊ መንግስት አቆርቋዦች ጭፍን ዕይታ” ተብሎ የመፈረጅ እድሉ የሚበዛ ይመስለኛል፡፡ በዚህ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ሂሣዊ ትንተና፣ “መንግስት ራሱን በራሱ ጠልፎ አልጣለም ትላላችሁ?” በማለት የኢህአዴግ ታህታዊ ሥሪትና ላዕላዊ ተክለ ሰውነት ሊሸከመው የማይችለውን ከባድ ጥያቄ ይሰነዝራል፡፡ የሚገርመው ግን፣ የኢህአዴግ ድንገተኛ ህፀጽ ላይ ተመሥርተው፣ አንዳንድ ጊዜ እነርሱም ወደ ሥልጣን ቢመጡ ሊያስወግዱት ቀርቶ ሊቀርፉት የማይቻላቸውን ሀገራዊ ችግሮች በማራገብ ላይ ሃይላቸውን የሚያባክኑት አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ እንደዚህ በመረጃ ላይ እየተደገፉ ሲሞግቱ አይታይም - ከአንድ የተቃዋሚ ድርጅት በቀር፡፡

ብዙዎቹ ብዙ ጊዜ፣ “ኢህአዴግ ሠፍሮ የሰጣቸውን አጀንዳ ነው የሚያራግቡት” የሚባሉትም፣ እንደዚህ መንግስት ሊደብቀው የማይችለውን ስህተቱን አንጥረው አውጥተው ስለማይሟገቱ ይመስለኛል፡፡
የ “ፖለቲካ በፈገግታ” አምድ ፀሐፊው አቶ ኤልያስ ያስነበቡን ሁለተኛው ተጠቃሽ መጣጥፍ፣ “ዲሞክራሲያችን በስንት ዲጂት እንዳደገ ይነገረን!” ይላል በርዕሡ፡፡ አምደኛው፣ “ለልማት የሚከፈለው መስዋዕትነት በ‘ደብል ዲጂት’ መቀነስ አለበት! ልማትና ትዕግስት ያላቸው ቁርኝት ዘንድሮ ገባኝ!” በማለት ያሸሞሩት፣ በምፀታዊ ገለፃ ፈገግታን ለማጫር ብቻ አልነበረም፤ ይልቁንም፣ የልማትንና በልማት ስም የሚደረግ መስዋዕትነትን በማነፃፀር፣ ሁለቱ ጉዳዮች በተቃርኖ ጽንፍ ላይ የሚቀመጡ፣ የአያዎ /Paradox/ አኗኗር ዘይቤያችን ወይም የአያዎ ፖለቲካችን ማናበቢያ ተምሣሌት መሆናቸውን ለመግለጽ እንጂ፡፡
መጣጥፉ፣ በምፀታዊና አሽሙራዊ አቀራረቡ፣ ፖለቲካዊ ምሬቶችን አለዝቦ የማህበራዊ ሂስ መልክ ቢያጐናጽፋቸውም፣ “የሰለጠኑ አገራት እኮ እንኳን ለልማት፣ ለጦርነት የሚከፈለውን መስዋዕትነት ለመቀነስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ሰው አልባ ተዋጊ ጀቶችን ለምን የፈጠሩ ይመስላችኋል?” የሚል የመረረ ጥያቄ ከማንሳት ያገደው የለም፤ በመቋጫ አረፍተ ነገሮቹ፣ “እኛም የልማት መስዋዕትነታችንን ‘ደብል ዲጂት’ መቀነስ አለብን!! (ሞትን እኮ!)” በማለት መንግስት በአሀዝ ላይ የተደገፈ የልማት ፕሮፖጋንዳ አብዝቶ ከሚለፍፍበት ማዕዘን በትይዩ፣ የዜጐችን “ልማታዊ መስዋዕትነት” በአሀዝ ተደግፎ እንዲገለፅለት ይጠይቃል፡፡ የዜጐችን መከራ አጉልቶ የማሣየቱ መራር እውነት የሚመነጨው ግን፣ የልማትን እና ለልማት ሢባል የሚደረግ መስዋዕትነትን፣ ያውም፣ በአህዛዊ ስሌት ተደግፎ እንዲገለጽ ከተፈለገበት፣ ምፀታዊ አቀራረቡ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እናም፣ የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ፣ “መስዋዕትነት በደብል ዲጂት ይቀነስ ቢሉ፣ ጦም እያደሩ መቆጠብ ትዝ አለኝ…” እስከ ማለት ደረሠ። አብዛኛው ዜጋ ከድህነት ወለል በታች በሆነ የቁልቁለት ኑሮ ውስጥ እንደሚዳክር እየታወቀ፣ “በአለፉት 37 ዓመታት አማካይ የቁጠባ መጠን ሲታይ 7 በመቶ አካባቢ ነው፡፡

እንደዚሁም ይህን አሀዝ ከአፍሪካና ከሌላው የዓለም ክፍል ጋር ስናወዳድረው ከአማካይ በታች ሆኖ እናገኘዋለን” የሚል ግርድፍ መረጃ ሢቀርብ ማየት ስሜት ውስጥ የሚከት ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም፣ የዜጐችን የገቢ መጠንና የመንግሥትን ሥራ የመፍጠር አቅም ያልነካና ያልገለፀ በመሆኑ፣ በግልባጩ “ዜጐች ጦማችሁን እያደራችሁ፣ ያላችሁን ጥሪት በእኔ ቋት ውስጥ አስገቡና እኔ ለፈለግሁት ተግባር ላውለው” የሚል የፈርጣማ ጡንቸኛ መንግስት መገለጫ ይመስላልና፡፡
ቀደም ሲል በተጠቀሰው መጽሔት፣ “የእንግዳችን ዐምድ” ላይ የመጀመሪያው እንግዳ ሆነው የቀረቡት፣ የመንግስት የፋይናንስ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የተከበሩ ዶ/ር ስንታየሁ ወ/ሚካኤል ናቸው፡፡ ዶክተሩ የመንግሥታቸውን አቋም በሚያስረግጠው መግለጫቸው፣ “በቅርብ ጊዜ ታሪካችን፣ ከድህነት ባሻገር የከፋ ችግር የዲሞክራሲና መልካም አስተዳደር ዕጦት እንደነበረ … ይህን ድህነትና ያልተመጣጠነ የሀብትና የገቢ ክፍፍል ከሥር መሠረቱ በመናድ በምትኩ በየጊዜው ዕድገት እየተመዘገበና ይህ ዕድገት ደግሞ ተመጣጣኝና ዜጐች በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሥርዓት ለመፍጠር … የልማት እንቅስቃሴውን በታሰበበት ለማስኬድ ትክክለኛ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል” ይላሉ፡፡
በዋና ዳይሬክተሩ ንግግር ውስጥ “ትክክለኛ አቅጣጫ” የሚለውን ልኬት ጠቋሚ፣ ሚዛን ሠፋሪ ገለፃ ሣንረሣ፣ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ 4 ዋነኛ ግቦች መብራራታቸውን ልብ ይሏል፡፡ “የአገራችን የኢኮኖሚ እድገት በከፍተኛው የእድገት አማራጭ (Scenario) 14.9 በመቶ ዕድገት ላይ “መድረስ እና “የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ” መፍጠር የሚሉት ሁለቱ ዋነኛ ግቦችን ለማሣካት ቁልፍ ጉዳይ፣ ቀጣይነት ያለው የቁጠባ ሥርዓት ሢዘረጋ እንደሆነ ዳይሬክተሩ በአፅንኦት ያስረዳሉ፡፡
የኢኮኖሚ እድገት (ያውም 14.9 በመቶ) ለማስመዝገብ ከሚያስፈልጉ ነገሮች አንዱ ኢንቨስትመንት መሆኑ ተገልጿል፡፡ “ኢንቨስትመንት ደግሞ የሚመጣው ቀጣይነት ያለው ቁጠባ ሲኖር ነው” ይላሉ፡፡ አስከትለውም፣ ሦስቱ የመንግስት ባንኮች ቁጠባን እንዴት እንደሚያሣልጡ ሢያብራሩ፣ የኢንቨስትመንቱን ጉዳይ በዝርዝር አላስተነተኑም፡፡ ይህ የሚያመለክተው ደግሞ፣ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚና ኢንቨስትመንት ካልተሥፋፋ፣ ዜጐች ተቀጣሪና አምራች የሚሆኑበት ተጠያቂዊ ሥርዓት ለመፍጠር እንደሚከብድ ግምት ውስጥ አለመግባቱን ነው፡፡
በሌላ በኩል ዳይሬክተሩ “ትክክለኛ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል” ሲሉ፣ የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚና ኢንቨስትመንት ከማበረታታት ይልቅ፣ የመንግሥትን ጡንቻ የሚያፈረጥም፣ አካሄድን ማሞገሳቸው ነው፤ የተሻለ የሥራ ፈጠራና ምርታማነት ማሣደግን ያላጤነ “ጦም እየታደረም ቢሆን ቁጠባ እንዲደረግ” ማለታቸውም ይመስላል፡፡ ለዚህ ደግሞ፣ “በዚህ የለውጥ እንቅስቃሴ ሊደረጉ ከሚገባቸው ነገሮች ውስጥ ቁጠባን ማሰባሰብና ለተገቢው ቦታ ማዋል … ሶስቱም ባንኮቻችን ይህንን እንደ ዋነኛ ተልዕኮ የሚረዱበትና የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ ላይ ነው ያለነው” የሚለውን መግለጫ ብቻ ማስተንተን ሊበቃ ይችላል፡፡
እዚህ ላይ ዳይሬክተሩ እንዳሉት፣ የቁጠባ ባህል መፍጠር የቆጠቡትንም ለተገቢው ቦታ ማዋል ተመራጭ መንገድ ነው፡፡ ጉዳዩ ግን፣ እንደሚባለው፣ “በትክክለኛ አቅጣጫ” ተግባራዊ እየሆነ ነው ወይ? ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው ምላሽ ፈታኝ መሆኑ ነው፡፡
ዶ/ር ስንታየሁ፣ “ቸር ተመኝ፤ ቸር እንድታገኝ” የሚለውን ሀገራዊ ብሂል ሠንቀው፣ በጐ አሣቢ ወይም “ባለ ራዕይ” ሊያሥብላቸው የሚችሉ፣ ግን መሠረት የሌላቸው የሚመስሉ ሀሣቦችን አንስተዋል፡፡ ለምሣሌ፡- “በወጣትነት ዘመናችን በአብዛኛው ከ18-25 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ለወደፊት የሚያስፈልገንን ቤት፣ መኪና፣ የልጆች ት/ቤት ወጪና ሌሎች ወጪዎች በተለይ የመንግስት ሠራተኛው በአንድ ጊዜ ሊያገኝ አይችልም፡፡ በመሆኑም ለእነዚህ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከወዲሁ በማስቀመጥ ለሚፈለገው ዓላማ ማድረግ ይቻላል” ይላሉ፡፡
አሁን ታዲያ፣ “ይኼ ማብራሪያ እንኳን ከኢትዮጵያ ጋር፣ ከአሜሪካ ጋርስ አብሮ ይሄዳል?” ብለን ብንጠይቅ ይፈረድብናል? ለመሆኑ ከ18-25 ዓመት ባለው የእድሜ ክልል ያለ የመንግስት ሠራተኛ ቀርቶ፣ በ40ዎቹ መጨረሻ እድሜ ላይ የሚገመቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከደመወዛቸው ቆጥበው፣ እንኳን ቤትና መኪና መግዛት ቀርቶ ልጆቻቸውን ከፍለው ማስተማር ይችላሉ!? (ማለቴ፣ አሁን ተጨምሮላቸው ካልሆነ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር “ለህዳሴው ግድብም፣ ለድርጅትም…” ተቆራርጦባቸው ከእጃቸው የሚገባው፣ ከ4ሺ 5መቶ ብዙም እንደማይበልጥ ወይዘሮ አዜብ የነገሩንን አስታውሼ ነው - ምን ላድርግ?)
በነገራችን ላይ፣ የሀገራችን ማዕከላዊ ስታስቲክሥ ኤጀንሲ በ2005 ዓ.ም ባወጣው መረጃ መሠረት፣ ከ15-29 ዓመት እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ወጣቶች በሀገሪቱ ውስጥ ከተንሠራፋው ሥራ አጥነት የ23.3% ድርሻ አላቸው፡፡ ወይም ከሀገሪቱ ሥራ አጦች መካከል ሩብ ያህሉ፣ ከ15-29 ዓመት ያሉ ወጣቶች ናቸው ማለት ነው፡፡ የእርሻው መሬት ተበጣጥሶ በተራቆተበት፣ ሥራ ፈጣሪ የኢንቨስትመንት አማራጮች በመንግስት ፈርጣማ ጉልበት ሣቢያ እየተቀዛቀዘ ባሉበት በአሁኑ ጊዜ የወር ደመወዝተኛ፣ በተለይ የመንግሥት ተቀጣሪዎች ከየት አምጥተው እንደሚቆጥቡም አልተገለፀም፡፡ የዋጋ ግሽበቱ ጥሬ ገንዘብ በባንክ ከማስቀመጥ፣ እንደ ወርቅ ባሉ ቁሦች ቀይሮ ሥለማስቀመጡ አማራጭ ጠቃሚነትና ጐጂነት አልተወሣም፡፡
የክቡር ዳይሬክተር መግለጫ፣ የቁጠባን ባህል አስፈላጊነት ለማስረዳት በተጨባጭ ማስረጃዎች ላይ ለመቆም ድፍረት ያነሰው ይመስላል፡፡ “ጦም እያደሩና እየተበደሩ” መቆጠብ ግድ የሚል ያህል በተሠበከበት በዚህ ንግግር፣ ዜጐች “ልማታዊ መስዋዕትነት” ከፍለው የቆጠቡት ገንዘብ “በተገቢው ቦታ ይውላል” ተባለ እንጂ እንዴት እየዋለ እንደነበረ ጥቂት አመላካች ማስረጃ ማቅረብ አልተቻለም፡፡ በዜጐች ላይ የመንግሥት ጡንቻ እንደሚፈረጥም እኛ ጠረጠርን እንጂ፣ የዶክተሩ ማብራሪያ ሰሞኑን በሙስና ክስ የተመሰረተባቸውን አይነት ትናንሽ የቡድን መንግሥታትን ረጅም እጆች ሊጠቁም አልቻለም፡፡
እናም ዶ/ር ስንታየሁ፣ ምን አለ ዛሬ እንኳን እንድንቆጥብ እንደነገሩን፣ “እንዳንሞሳስን” በመከሩን! “ሙስና እንዳንሠራ” የሚለውን፣ “እንዳንሞሳስን” እንዲል የኢትዮጵያዊያን ቋንቋ በአማርኛ፡፡

Read 2501 times