Print this page
Saturday, 26 October 2013 13:38

ቤቱን በእሳት ለኩሶ “እንዴት ያለ ብሩህ ቀን እንደሆነ ተመልከቱ” ይላል

Written by 
Rate this item
(7 votes)

አንድ እሥር ቤት ውስጥ የሆነውን ነገር ቆይተው ሲያስቡት ተረት እንጂ በዕውነት በታሪክ የተከሰተ አይመስልም፡፡
የእሥር ቤቱ ክፍል አራት በአራት ነው ፡፡ ከሃምሣ እስከ ስልሣ የሚሆኑ እሥረኞች ታጭቀውበታል፡፡ የሚተኙት እንደጨፈቃ ተጨፍቀው ነው፡፡ ጠዋት ሲነጋ ቀኑን ለመግፋት ዳማ፣ ዶሚኖ፣ ቼዝ እና እዚያው በተሠራ ወረቀት ካርታ ይጫወታሉ፡፡
የእሥረኛው ዓይነት እንደየጉዳዩ የተለያየ ነው፡፡ በፖለቲካ የታሠረ አለ፡፡ በኢኮኖሚ (ገንዘብ ነክ) ጉዳይ የሚመጣ አለ - ደረቅ ወንጀል ይሉታል፡፡ በእግሩ ድንበር አልፎ ለመሄድ ሲሞክር ተይዞ የሚታሠር አለ “እግር እላፊ” ይሉታል በእሥረኞቹ አጠራር፡፡ የዘማች ሚስት በማማገጥ የሚታሠር አለ “ጭን እላፊ” ይሉታል፡፡ በስርቆሽ የሚታሠር አለ “እጅ - እላፊ” ይሉታል፡፡ በዘለፋ፣ መንግሥት (መሪ) በመሰደብ የሚታሠር አለ - “አፍ -እላፊ” ይሉታል፡፡
እሥር ቤቱ ክፍል አሁን ዳማ የማጫወቱት ሁለት ሰዎች፤ አዕምሮአቸውን ነካ የሚያደርጋቸው ናቸው፡፡ በአፍ - እላፊ ነው የታሠሩት፡፡ ዳማ እየተጫወቱ ይወያያሉ፡፡
“ይሄ መንግሥት ዕብድ ማሠሩ አይገርምህም?” ይላል አንደኛው፡፡
“አሣሪው ይሁን ታሣሪው ዕብዱ? ገና አልለየምኮ” ይላል ሁለተኛው፡፡
“እኔ መንግሥት ይመስለኛል ዕብድ”
“እኔ ግን እኛ ዕብድነታችንን ቢያዘልቅልን ከመንግሥት እንሻላለን እላለሁ”
“ይልቅ ዳማችንን እንጫወት፡፡ ለሁላችንም የሚሻለን፤ ህዝብ ቢያብድ ነበር”
“ለምን?”
“አለዛ ድንዝዝ ፍዝዝ ብሎ ይቀራላ!”
“በል እሺ ዳማችንን እንጫወት?”
ዳማቸውን መጫወታቸውን ይቀጥላሉ፡፡
አንደኛው የሌላኛውን ንጉሥ፤ በወታደርም፣ በንጉሥም የሚበላት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡
ሁለተኛው - “በንጉሥ ትገደዳለህ፡፡ ንጉሤን በንጉሥ ነው እንጂ በወታደር አትበላኝም” ይላል፡፡
አንደኛው - “በየትኛውም ብበላህ ጨዋታው ያልቃል፡፡ በፈለኩት እበላለሁ”
ሁለተኛው - “በጭራሽ! በንጉሥ ትገደዳለህ”
አንደኛው - “እኔ እምልህ፤ አንዴ ሞት ከተፈረደብህ በቺቺ ግደሉኝ በክላሽ ግደሉኝ እያልክ ምን ያጨቃጭቅሃል?” አለው፡፡
* * *
በትንሹም በትልቁም ነገር ከማበድ ይሰውረን፡፡ የመሞቻ መሣሪያ ከማማረጥ ያድነን፡፡ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ እንከኖቻችን ጥቅል ውጤት ማስጨነቁና ማሳሰቡ የሀገርና የህዝብ ስሜት ላለው ሁሉ አይቀሬ ነው፡፡ በተለይም ዱሮ የእጅ - እላፊ ይባል የነበረው የምዝበራና አገርን የማራቆት ተግባር፣ (ዛሬ ሙስና የተባለውን)፤ “ባንዱ ያለማ ባንዱ ያደለማ” ሆኗል፡፡ አገር ትልቅ ለውጥ ላይ ናት፤ ከፍተኛ የትራንስፎርሜሽን ሂደት ላይ ነን እየተባለ፤ በጐን የዝርፊያ የኮንትሮባንድ እና “በአንድ ጀንበር ፎቅ ሠርቼ ልደር” ዓይነት ዘመናዊ ምዝበራ ይታያል፡፡ “በአንዴ ዘጋ/ዘጋች” ዛሬ የተለመደ ቋንቋ ነው፡፡ እንደነናይጄሪያና እንደነናይሮቢ (“ናይሮበሪ” እንደተባለው) ዐይን - ያወጣ የቀን ተቀን ዘረፋ የሚመጣው ከላይ እስከታች እየተወሳሰበ ያለው ሙስና ፍፁም ወደፈጠጠ ደረጃ ሲደርስ ነው፡፡ “ልጄን የእንቁላሉ ዕለት ቆንጥጬው ቢሆን በሬ ሲሰርቅ አይያዝም ነበር” አለች እንደሚባለው ነው፡፡
አንድም ሙስናው በየአቅጣጫው መሆኑ፤ አንድም ደግሞ ቢሮክራሲያዊ መጠቅለያ መኖሩ እጅግ ውስብስብ ያደርገዋል፡፡ (ዱሮ “ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ይውደም” የሚል መፈክር ነበር፤ ነብሱን ይማረው!) በዚህ ላይ የግለሰቦች አሻጥር ሲጨመርበት፣ ከቁጥጥር ውጪ ወደሆነ ደረጃ ይሸጋገራል፡፡ የመሬት አሰቃቂ አወሳሰድ፣ ከፍተኛ የኮሚሽንና የድለላ ሥራ፣ አደገኛ ወገናዊ አሠራር…በአስደንጋጭ የድህነት መቀመቅ ውስጥ ለገባች አገር ከምትሸከመው በላይ ትከሻ አጉብጥ ሸክም ይሆንባታል፡፡ የባሰ ዘግናኝ የሚሆነው ደግሞ ከዕለት ወደ ዕለት በምዝበራ ምክንያት መታሰር ራሱ እየተለመደና ቀላል እየመሰለ መምጣቱ ነው፡፡ “እገሌ ታሠረኮ” ሲባል፤
“ተወው በልቷል - የሚበቃውን ቀለብ አከማችቷል”
ማለት እንደሰላምታ የሚነገር መሆኑ አሳዛኝ ነው፡፡
ዱሮ “በሥራው አጋጣሚ በእጁ የገባውን የመንግሥት ገንዘብ ለግል ጥቅሙ በማዋሉ” የሚለው ሐረግ ነበር ሬዲዮንና ቴሌቪዥን ያጣበበው፡፡ ዛሬ ዳር እስከዳር በየሰው አፍ የሚወራ ነገር ሆኗል፡፡ ዝርፊያው ዓይነት በዓይነት ሆኗል፡፡ ተወርቶም በቀላሉ ይረሳል፡፡ በተለይ ለህብረተሰብ ቀጥተኛ መጥፊያ የሚሆኑ እንደመድሃኒት ያሉ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ባመቸው መንገድ ሁሉ ተበርዘው ከተባዙ፣ ምን ያህል አሰቃቂ የሆነ ዕልቂት እንደሚያስከትሉ መገመት አያዳግትም፡፡ የሚያስገኙት ገንዘብ የትየለሌ፣ የሚፈጁት ህዝብ የትየለሌ!!
ማናቸውንም የጥፋት ድርጊት የሚፈጽሙ ወገኖች ለሀገር እንደቆሙ፤ የህዝብ ልጆች እንደሆኑ አድርገው መጮሃቸውና ሀቀኛ መምሰላቸው፤ ሌላው እንዳይናገር በር ይዘጋል፡፡ They shout at most against the vices they themselves are guilty of እንደሚሉት ነው ፈረንጆቹ - ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮህ እንደማለት ነው፡፡ ጩኸቱ በቅጡ ለገባው አገር - ወዳድ ሰው ግን፤ “ቤቱን አቃጥሎ እንዴት ብሩህ ቀን እንደሆነ ተመልከቱ” አለ እንደተባለው ነው፡፡ ልዩነቱ ያኛው ለግሉ እየተጠቀመ፤ ይሄኛው የገዛ ንብረቱን ጭምር እያወደመ የሚጃጃል መሆኑ ነው፡፡ ሁለቱንም መዋጋት ተገቢ ነው!

Read 4299 times
Administrator

Latest from Administrator