Print this page
Saturday, 26 October 2013 13:36

አቶ መላኩ ፈንታን ጨምሮ በሙስና የተከሰሱት ሃላፊዎች በሚሊዮን የሚቆጠር ሃብት አፍርተዋል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(11 votes)

በአቶ ገ/ዋህድ ቤት ሁለት ክላሽን ጨምሮ 10 የጦር መሣሪያዎች ተገኝተዋል
በሚሊዮን የሚቆጠር ግብር እስከዛሬ አልተሰበሰበም
ከአስር በላይ ተከሳሾች በቁጥጥር ሥር አልዋሉም

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ መላኩ ፋንታ እና ምክትላቸው አቶ ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስን ጨምሮ ሌሎች የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሃላፊዎች ከወርሃዊ ገቢያቸው በላይ በሚሊዮን የሚቆጠር ምንጩ ያልታወቀ ሃብትና ንብረት ማፍራታቸውን የፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ ባቀረበው ክስ አመለከተ፡፡
በቡድን እና በተናጥል የተለያዩ ክሶች የቀረቡባቸው አቶ መላኩ ፈንታ፤ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 164,228,68 ብር እንዲሁም በመኖሪያ ቤታቸው 12,271 ብር፣ በድምሩ 176,499.68 ብር በጥሬ ገንዘብ ይዘው እንደተገኙ ተገልጿል፡፡ አቶ መላኩ በተጨማሪም በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 9 ውስጥ 659 ኪ.ሜ ቦታ በ445,200 ብር መግዛታቸው፣ በቦታው ላይም 1,592,934.76 ብር በማውጣት ባለሁለት ፎቅ ግንባታ ማከናወናቸው እንዲሁም ለዚሁ ግንባታ ማስፈፀሚያ ከህብረት ባንክ ቦሌ መድሃኒዓለም ቅርንጫፍ 1,423,479.30 ብር መበደራቸው የተመለከተ ሲሆን በጠቅላላው ተከሳሹ በስልጣን ላይ በነበሩ ጊዜ ከወርሃዊ ገቢያቸው ጋር የማይመጣጠን 3,272,921.21 ንብረትና ገንዘብ አፍርተው በመገኘታቸው በፈፀሙት ምንጩ ያልታወቀ ሃብት ማፍራት የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
አቶ መላኩ አንዲት ባለትዳር የነበረችን ግለሰብ ስልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀም ከቀድሞ ባለቤቷ ጋር ያቋቋመችው ኩባንያ እንዲከፍል የተወሰነበትን ግብር እንዲቀነስላቸው በማድረግ በፈጠሩት የፍቅር ግንኙነት፤ የ3 ልጆች እናት የነበረችን ሴት በትዳሯ ላይ እያለች ከማማገጣቸውም ባሻገር ከቀድሞ ባለቤቷ ጋር እንድትፋታና እሣቸውን እንድታገባ አድርገዋል የሚል ክስም ቀርቦባቸዋል፡፡
በተናጥልና ከሌሎች ጋር በጋራ ስልጣንን አላግባብ በመጠቀም ገልገል እንዲሁም የመንግስትን ስራ በማያመች አኳኋን መምራት የሚሉ ክሶች በስፋት የቀረበባቸው የቀድሞው ምክትል ዳይሬክተር አቶ ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ እና ባለቤታቸው ኮ/ል ሃይማኖት ተስፋዬ ላይ ነው፡፡ አቶ ገብረዋህድ በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከ1978 ዓ.ም ጀምሮ በቁጥጥር ስር እስከዋሉበት 2005 ዓ.ም ተቀጥረውና ተሾመው ሲሰሩ ከብር 247 እስከ ብር 5,719 ያልተጣራ ወርሃዊ ደመወዝ ይከፈላቸው የነበረ ሲሆን ባለቤታቸው ኮ/ል ሃይማኖት ደግሞ በአገር መከላከያ ሚኒስቴር ከ1989 እስከ 2000 ዓ.ም ተቀጥረው ሲሰሩ ከብር 790 እስከ ብር 2145 ያልተጣራ ወርሃዊ ደመወዝ ይከፈላቸው ነበረ፡፡ ሆኖም ተከሳሾቹ ያገኙት ከነበረው ደመወዝና ገቢ ጋር የማይመጣጠን ንብረትና ገንዘብ አፍርተው መገኘታቸው በክሱ ላይ ተመልክቷል፡፡
በአቃቤ ህግ የክስ ዝርዝር ላይ እንደተመለከተው፤ ባልና ሚስቱ በራሳቸው እንዲሁም በልጆቻቸው ስም በወጋገን፣ በእናት፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ በዳሽን እና በአንበሳ ባንኮች የተለያዩ ቅርንጫፎች ከብር 387 እስከ ብር 203,424 ብር ድረስ አስቀምጠዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ተከሳሾቹ ለጊዜው ግምታቸው ያልታወቀ አውቶቡስ እና የንግድ መኪና በንብረትነት አፍርተው የተገኙ ሲሆን በአንደኛው ልጃቸው ስምም የ10ሺህ ብር አክሲዮን መግዛታቸው ተገልጿል። በብርበራ ወቅትም በመኖሪያ ቤታቸው 200ሺህ ብር፣ 26,300 ዶላር (ግማሽ ሚሊዮን ብር ገደማ)፣ 19,435 ዩሮ (ግማሽ ሚሊዮን ብር ገደማ)፣ 560 ፓውንድ እና 210 የታይላንድ ገንዘብ የተገኘ ሲሆን መቀሌ ከተማ ከሚገኝ መኖሪያ ቤት በተጨማሪ ግምቱ ብር 596,868.24 የሆነ 500 ካ.ሜ ቦታ ይዘው ተገኝተዋል፡፡ በአጠቃላይ ግለሰቦቹ የኑሮ ደረጃቸው አሁን ባሉበትም ሆነ አስቀድሞ በነበሩበት የመንግስት ስራ ከሚያገኙት ገቢ ጋር የማይመጣጠን ብር 1,451,941 (አንድ ሚሊዮን አራት መቶ ሃምሣ አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ አርባ አንድ) እንዲሁም የተለያዩ የውጭ ሃገር ገንዘቦች ይዘው መገኘታቸው በክስ ማመልከቻው ተብራርቷል፡፡
በተናጥል በአቶ ገ/ዋህድ ላይ ብቻ በቀረበው 16ኛ ክስ ደግሞ የጦር መሣሪያ አያያዝና አጠቃቀም ደንብ ተከትለው ፍቃድ በማውጣት መሣሪያ መያዝ ሲገባቸው፣ በመኖሪያ ቤታቸው በተደረገ ብርበራ ሁለት ታጣፊ ክላሽ፣ አራት የተለያዩ የውግ ቁጥር ያላቸው ማካሮቭ ሽጉጦች፣ ሁለት የተለያዩ ቁጥር ያላቸው ኮልት ሽጉጦች እና አንድ ስታር ሽጉጥ በጠቅላላው አስር የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን ከተለያዩ ጥይቶች ጋር ይዘው በመገኘትም ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
ሌላው ምንጩ ያልታወቀ ሃብት አፍርቶ በመገኘት ክስ የቀረበባቸው በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና አቃቤ ህግ የሆኑት አቶ ማርክነህ አለማየሁ ናቸው፡፡ ተከሳሹ በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ግንቦት 2005 ተቀጥረው ሲሰሩ ከብር 2535 እስከ ብር 10234 ያልተጣራ ወርሃዊ ደመወዝ እየተከፈላቸው የነበረ ቢሆንም በባለቤታቸው ስም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጦር ሃይሎች ቅርንጫፍ ከ900ሺ ብር በላይ ማስቀመጣቸው እንዲሁም “ውጭ ሀገር የሚገኙ ጓደኞቼ የላኩልኝ ገንዘብ ነው፤ አንቺ ጋ ይቀመጥልኝ” በማለት ሃዋሣ በምትገኘው እህታቸው የባንክ ሂሳብ በድምሩ ብር 1,900.000 እንዲቀመጥ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም በእኚሁ እህታቸው ስም በሃዋሣ ከተማ 1,425,000 ብር የሚያወጣ መኖሪያ ቤት ማሠራታቸው ተመልክቷል፡፡ በተከሳሹ ቤት በተደረገ ብርበራም በኤግዚቢትነት ተመዝግቦ የሚገኝ 1, 388,899 ጥሬ ብር መገኘቱን የአቃቤ ህግ የክስ ዝርዝር ያስረዳል፡፡ በአጠቃላይ አቶ ማርክነህ፤ ከወርሃዊ ደሞዛቸው ጋር የማይመጣጠን በድምሩ ብር 6,551,532.62 አካብተው የተገኙ ሲሆን ይህን በሙስና የተገኘ ንብረትና ሃብት ምንጩን ለመደበቅ በቤተሰባቸው ስም እና በመሬት ውስጥ እንዲቀበር በማድረግ በፈፀሙት በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብና ንብረት ህጋዊ አስመስሎ የማቅረብ ሙስና ወንጀልም ተከሰዋል፡፡
አምስት ኩባንያዎችን ጨምሮ ሃያ አራት ግለሰቦች በተከሰሱበት ሶስተኛው የክስ መዝገብ የተካተቱት በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የጉምሩክ ስነስርዓት አፈፃፀም የስራ ሂደት መሪ የነበሩት አቶ አስመላሽ ወ/ማርያምም፤ በአጠቃላይ ከወርሃዊ ደሞዛቸው ጋር የሚይመጣጠን ግምቱ 4,459,179.5 የሆነ ከፍተኛ ንብረትና ገንዘብ በመያዝ የኑሮ ደረጃቸው የማይፈቅድላቸውን ሃብት አከማችተው መገኘታቸው ተመልክቷል፡፡ ተከሣሹ ከ1987 እስከ 2004 ዓ.ም በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ተቀጥረው ሲሰሩ በቆዩበት ወቅት ከብር 445 እስከ ብር 8,651 ወርሃዊ ደሞዝ ያገኙ የነበረ ሲሆን በመኖሪያ ቤታቸው በተደረገ ብርበራ ከተገኘው 1,947,676.10 ብር በተጨማሪ በተለያዩ ባንኮች እና አክሲዮኖች በስማቸው የተቀመጠ ብር 2,090,880.03 ተገኝቷል፡፡ በአቃቤ ህግ የክስ ዝርዝር ላይ እንደተመለከተው፤ ተከሳሹ በራሳቸው እና በባለቤታቸው ስም በድምሩ የ30ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸው እንዲሁም ምንም ገቢ በሌላቸው ባለቤታቸው ስም በአዲስ አበባ ልደታ ክ/ከተማ ወረዳ 24 ቀበሌ 02/03 ውስጥ የተሠራ ግምቱ 200,000 ብር የሆነ ባለሁለት መኝታ ክፍል ኮንዶሚኒየም ቤት እንደገዙ ተገልጿል፡፡ አቶ አስመላሽ ገቢ በሌላቸው ባለቤታቸው ስም የ5ሺህ ብር ቦንድ ከመግዛታቸውም ባሻገር በተለያዩ ባንኮች 185ሺ641.19 ብር ማስቀመጣቸው ተመልክቷል፡፡
አቃቤ ህግ ካቀረባቸው የክስ አይነቶች ውስጥ “ጉቦ መቀበል” አንዱ ሲሆን በዚህም በሶስቱ የክስ መዝገቦች በሁለተኛነት የቀረቡት አቶ ገ/ዋህድ እና አቶ መርክነህ፤ ከአንድ ባለሃብት ከፍተኛ ጉቦ መቀበላቸው ተመልክቷል፡፡ ብስራት ኃ/የተ/የግ/ማህበር ያለቫት ደረሰኝ ግብይት ሲፈፅም ተደርሶበት ምርመራ ተጣርቶ ክስ ቀርቦበት ሳለ፣ ባለቤቱ በክርክር ላይ እያሉ አቶ ገ/ዋህድ ለኩባንያው ባለቤት አቶ ባህሩ አብርሃ በቀጥታ ስልክ በመደወል “አንተ ከማን ትበልጣለህ? ክስህን ወደ መደበኛ ፍ/ቤት አቅርበን ከፍተኛውን ቅጣት እንደምናስቀጣህ እወቅ” ብለው በማስፈራራት 250 ሺህ ብር ከተቀበሉ በኋላ፣ ባለሃብቱ አድርገውት የነበረውን ብራስሌት “የሱ አይነት ግዛልኝ” በማለት ግለሰቡ 30,000 ብር አውጥተው ብራስሌት እንዲገዙላቸው አድርገዋል፡፡ አቶ መርክነህም እንዲሁ 100ሺህ ብር ጉቦ ከተቀበሉ በኋላ፣ በባለሃብቱ ላይ የተመሰረተው ክስ ይግባኝ እንዳይጠየቅበት ማድረጋቸው ተመልክቷል፡፡
ጉቦ በመቀበል ከቀረቡ ክሶች መካከል በመዝገብ 3፣ በ26ኛ ክስነት በአቶ ገ/ዋህድ፣ በአቶ መርክነህ፣ ባልተያዘው የመስሪያ ቤቱ የግብር አወሣሠን ኦዲተር አቶ ዳንኤል ገ/ኪዳን እንዲሁም በአቃቤ ህግ አቶ አውግቸው ክብረት ላይ የቀረበው ይገኝበታል፡፡
ተከሣሾቹ ግብር ከፋይ የሆነውን ኦፊስ ቴክ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ባለቤት አቶ መሃመድ የሱፍን ድርጅቱ ኦዲት በሚደረግበት ወቅት በታክስ ማጭበርበር ወንጀል ከመከሠሡ በፊትና በኋላ በተለያየ ጊዜ በማግኘት ጉቦ እንደጠየቁ ተገልጿል፡፡ አቶ ዳንኤል በ2002 ዓ.ም ጥቅምት ወር ጀምሮ በተለያዩ ቀናት የግል ተበዳይን ተከታትሎ ካገኘው በኋላ “የላከኝ ገ/ዋህድ ነው፤ የደቡብ ፖሊስ ኮሚሽን አንተን እንድንቀጣህ ይፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ ሁለት ሚሊየን ብር አምጣ፤ ካልሆነ ግብርም ይጨመርብሃል፤ አንተም ትታሠራለህ” በማለት የግል ተበዳይን ጉቦ እንዲሠጠው በአካልና በስልክ የጠየቀ ሲሆን ተበዳይ ገንዘቡን ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ይቀራሉ፡፡ ባለሃብቱ ወደ ዱባይ በሄዱበት ወቅትም፣ ወደ ድርጅታቸው በመሄድ በአንድ ቀን ውስጥ ኦዲት አድርጐ አርባ ሁለት ሚሊዮን ብር ሂሣብ በማምጣት፣ በድርጅቱ ውስጥ በተለማማጅነት ትሠራ የነበረችን የመፈረም ስልጣን የሌላትን ግለሠብ አስፈራርቶ ማስፈረሙ ተመልክቷል፡፡ አቶ ገ/ዋህድ ደግሞ በ2003 ዓ.ም መጨረሻ ላይ እኚኑ የግል ተበዳይ “ግብር ዜሮ እንዲሆንልህና ክሡም እንዲቋረጥልህ ሁለት ሚሊዮን ብር ዱባይ በሚገኝ ሠው አማካኝነት አስገባ” ይሉታል፡፡ ይህንን ጉዳይ ለማጣራት የግል ተበዳይ ወደ አቶ ገ/ዋህድ ቢሮ ይሄዳሉ፡፡ ወደ ቢሮ እንዲዘልቁ ከፈቀዱላቸው በኋላ “አንተ አመፀኛ፤ ይህን የከተማ ጮሌነት ከአንተ በላይ አውቀዋለሁ፤ ኦሎምፒያ አካባቢ ከቀጠሩህ ሠዎች ጋር ጨርስ” በማለት የግል ተበዳይን በማስፈራራት፤ በቀጥታ ገንዘቡን እንዲከፍሉ ጠይቀዋል ይላል-የክስ ማመልከቻው፡፡ አቶ ማርክነህ እና አቶ አውግቸው ደግሞ የግል ተበዳይ ላይ ቀርቦ በሂደት ላይ እያለ፣ ቀጠሮ ለማራዘምና ለተከሣሹ ጊዜ ለመስጠት በሚል ጉቦ እንዲሠጣቸው በመደራደር ሁለት ቶሺባ ላፕቶፖች፣ ሁለት ሲዲኤምኤ እና 20ሺህ ብር ተቀብለው ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው ተመልክቷል፡፡
በሶስት የተለያዩ መዝገቦች በቀዳሚነት ክስ የተመሠረተባቸው የገቢዎችና ጉምሩክ ዋና ዳይሬክተርና ምክትላቸው፣ ከሌሎች በመዝገቦቹ ከተካተቱ ባለ ድርሻ አካላት ጋር በጣምራ እና በተናጥል የመንግስትን ስራ በማያመች አኳኋን መምራት የሚል ክስም በስፋት ቀርቦባቸዋል፡፡
ተከሣሾቹ በተለይ ከተለያዩ ታክስና ግብር ከፋዮች ጋር በመደራደር፣ ህገ ወጥ የቴክኒክ ኮሚቴ አቋቁመው፣ ህገወጥ ድርጊትን ማስፈፀም የሚያስችል መመሪያ በ2004 ዓ.ም ያወጡ ሲሆን ይህንኑ መመሪያ መሠረት በማድረግ፣ ሐዋስ አግሮ ቢዝነስ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ለመንግስት ገቢ እንዲያደርግ ይጠበቅበት የነበረ ብር 22,379,145.28 በህገ ወጥ አሠራር መጠኑ ዝቅ እንዲል ከማስደረጋቸውም ባሻገር፣ ገንዘቡ እስከዛሬ እንዳይሠበሠብ አድርገዋል ተብሏል፡፡ በተመሣሣይ በሶስቱ መዝገቦች ሁለተኛ ተከሣሽ የሆኑት አቶ ገ/ዋህድ፤ ከሼባ ስቲል ሚልስ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ላይ ይፈለግ የነበረ 104,487,978.40 ብር፣ ከኤጂኤች ኃ/የተ/የግ/ማህበር ላይ ይፈለግ የነበረ 6,809,763.42፣ ከሱሁራ 571 ኃ/የተ/የግ/ማህበር ይፈለግ የነበረ 91,747,355.68 ብር በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን እንዳይሠበሠብ አድርገዋል ይላል ክሱ፡፡ በተጨማሪም አቶ ገ/ዋህድ ከሌሎች ጋር በጣምራ በቀረበባቸው ክስም ከ7 የተለያዩ የንግድ ድርጅቶችና ኩባንያዎች ይፈለግ የነበረ በሚሊዮን የሚቆጠር ገቢ የመንግስት ስራን በማያመች አኳኋን በመምራት እስካሁን እንዳይሠበሠብ ማድረጋቸው ተመልክቷል፡፡ ሌሎች የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተለያዩ ሃላፊዎችም በተመሣሣይ መልኩ ግብርና ታክስ ከድርጅትና ኩባንያ ባለቤቶች ጋር በመመሣጠር እንዳይሠበሠብ ያደረጉ ሲሆን መንግስት ሊያገኘው የሚገባ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አሣጥተዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
በ3ኛው የክስ መዝገብ ከባለቤቶቻቸውና ስራ አስኪያጆቻቸው ጋር በመመሣጠር ኬኬ ኃ/የተ/የግ/ማህበር፣ ጂ ኤች ሲሜክስ (ኢንተርኮንቲኔንታል) ኃ/የተ/የግ/ማህበር፣ ነፃ ኃ/የተ/የግ/ማህበር፣ ጌታስ ኃ/የተ/የግ/ማህበር እና ኮሜት ኃ/የተ/የግ/ማህበር በሚሊዮን የሚቆጠር ታክስና ግብር ባለመክፈል እንዲሁም በማጭበርበር ወንጀል ክስ የቀረበባቸው ሲሆን ስራ አስኪያጆቻቸውም ከየኩባንያዎቹ መንግስት የሚፈልገውን ገንዘብ ተከታትለው ባለመክፈል የጣምራ ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
በሌላ በኩል ፍርድ ቤቱ ባለፈው ረቡዕ በዋለው ችሎት፣ በቀሪዎቹ 3 መዝገቦች የተከሠሡ አስራ ሶስት ግለሠቦችን ክስ በንባብ አሠምቷል፡፡ መዝገቦቹ በእነ ጌታሁን ቱጂ ሶስት ግለሠቦች፣ በእነ ዳዊት ኢትዮጵያ አምስት ግለሠቦች እንዲሁም በእነ ብርሃነ አርአያ አምስት ግለሠቦች ሲሆኑ በሁሉም ላይ ስልጣንን ያለ አግባብ የመጠቀም ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
ተከሣሾቹ ስልጣናቸውን ተጠቅመው ከባለ ድርጅቶቹ ጋር በጥቅም በመተሣሠር ከንግድ ድርጅቶች እና ኩባንያዎች ይጠበቅ የነበረው የግብር መጠን እንዲቀነስና የንግድ ድርጅት ባለቤቶች በግብር ጉዳይ እንዳይከሠሡ በማድረጋቸው እንዲሁም ከኮንትሮባንድ ህገወጥ ንግድ ጋር በተያያዘ የጥቅም ተካፋይ ሆነው መገኘታቸውን የአቃቤ ህግ የክስ ዝርዝር አስረድቷል፡፡
አቃቤ ህግ በ6 መዝገቦች አደራጅቶ የመሠረታቸው ክሶች በአጠቃላይ 138 ሲሆኑ አቶ መላኩ ፈንታ እና አቶ ገ/ዋህድ ወ/ጊዮርጊስ እያንዳንዳቸው በሶስት መዝገብ አንደኛ እና ሁለተኛ ተጠሪ በመሆን በርካታ ክስ በተናጥልና ከሌሎች ጋር በቡድን ቀርቦባቸዋል፡፡
በመዝገቦቹ ከተካተቱ ከ40 በላይ ተከሣሾች መካከል የጌታስ ሃላፊነቱ የተወሠነ የግል ማህበር ባለቤትን አቶ ጌቱ ገለቴ ጨምሮ ከ10 በላይ ተከሣሾች በቁጥጥር ስር ባለመዋላቸው በሌሉበት ጉዳያቸው ታይቷል፡፡
ለሶስት ተከታታይ ቀናት ስድስቱን መዝገቦች በንባብ ያሠማው ችሎቱ፤ የተከሣሽ ጠበቆች ከክሡ ጋር አብሮ ማስረጃዎች ተያይዘው አልቀረቡልንም በማለታቸው፣ ችሎቱ በቀጣይ ቀጠሮዎች አቃቤ ህግ ህጉ በሚያዘው መሠረት ማስረጃዎችን አያይዞ ለጠበቆችና ተከሣሾች እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሠጥቷል፡፡ በተጨማሪም ያልተያዙ ተከሣሾች በህግ ተይዘው እንዲቀርቡ ፍ/ቤቱ አዝዟል፡፡ ቀጣይ ሂደቶችን ለመመልከትም ሁሉንም መዝገቦች ለጥቅምት 19 እና 20, 2006 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡

Read 7552 times