Saturday, 26 October 2013 13:30

ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ዛሬ ከስደት ይመለሳል

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(5 votes)

“ሞያው የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ለመክፈል ወስኜ ነው የምመጣው”
የአውራምባ ታይምስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ከሁለት አመታት የአሜሪካ የስደት ኑሮ በኋላ ጋዜጣውን እንደገና ለመጀመር ዛሬ ወደ አገሩ ይመለሳል፡፡
“ከሁለት አመታት በፊት ጋዜጣውን ዘግቼ ለመሰደድ የወሰንኩት በመንግስት መገናኛ ብዙሃን በተከፈተብኝ ዘመቻ ለደህንነቴ በመስጋት ነው” የሚለው ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ፤ “ከምታገልለት ህዝብና ከመረጃ ርቄ የጋዜጠኝነት ስራ መስራቴ ውጤታማ እንደማያደርገኝ ስለተገነዘብኩ ወደ አገር ቤት ለመመለስ ወስኛለሁ” ብሏል፡፡
ትላንት ወደ ኢትዮጵያ ለመብረር አውሮፕላን ከመግባቱ አንድ ሠዓት በፊት ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ በስልክ በሰጠው ቃለ ምልልስ፤ “በአሜሪካ ለተሰጠኝ የፖለቲካ ጥገኝነት አመሰግናለሁ፤ ነገር ግን ሞያው የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ለመጋፈጥ የፖለቲካ ጥገኝነት ፈቃድ አስረክቤ እየመጣሁ ነው›› ብሏል፡፡
ለመሰደድ መወሰኑ ስህተት እንደነበር ዳዊት ገልፆ፣ ምንም እንኳን ከፍተኛ ጫና ቢደርስብኝም ፈተናውን በአገር ውስጥ ሆኜ መጋፈጥና የሚጠይቀኝን ዋጋ መክፈል ይገባኝ ነበር ብሏል፡፡ በአሜሪካ ድረገጽ ከፍቼ መስራት ከጀመርኩ በኋላ በዚያው የሚገኙ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ከመንግስት ጋር ግንኙነት እንዳለኝ በማስመሰል ከፍተኛ የስም ማጥፋት ዘመቻ አድርገውብኛል የሚለው ዳዊት፣ ወደ አገር ቤት ለመመለስ የወሰንኩት ግን በዚህ ምክንያት አይደለም ብሏል፡፡
በጋዜጠኝነት ስራ ለመቀጠል ወደ አገር ቤት መመለስ፣ በአገሪቱ የፕሬስ ነፃነት ሁኔታ የተሻሻለ መሆኑን እንደማያሳይ የገለፀው ጋዜጠኛ ዳዊት፣ በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ለመስራት እችላለሁ ብሎ እንደሚያምን ተናግሯል፡፡
ዳዊት በ1997 ዓ.ም አገር አቀፍ ምርጫን ተከትሎ በተፈጠረው ቀውስ፣ ከቅንጅት አመራሮችና ከሲቪል ማህበራት መሪዎች ጋር ለ2ዓመት ገደማ ታስሮ መፈታቱ ይታወሳል፡፡

Read 5542 times