Saturday, 26 October 2013 13:28

ሃዋሳ ዩኒቨርስቲ በ“ኢትዮ ምህዳር” ላይ የ300ሺ ብር ክስ አቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

ዩኒቨርሲቲው ቀደም ሲል “አዲስ አድማስ”ን መክሰሱ ይታወቃል
የ“ሪፖርተር” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅም ታስሮ ወደ ሃዋሳ ተወስዶ ነበር

 “ኢትዮ ምህዳር” ጋዜጣ “የሃዋሳ ዩኒቨርስቲ የማኔጅመንት አባል በሙስና እጅ ከፍንጅ ተያዘ” በሚል ርዕስ ካወጣው ዜና ጋር በተያያዘ ስሜ ጠፍቷል በማለት 300ሺ ብር ካሳ እንዲከፈለው ዩኒቨርስቲው ክስ ያቀረበ ሲሆን፣ ፍ/ቤት ብይን ለመስጠት ለሚቀጥለው ረቡዕ ቀጠሮ ሰጠ፡፡ 

የጋዜጣው አሳታሚ፣ ዋና አዘጋጅ እና ስራ አስኪያጅ እያንዳንዳቸው 100ሺ ብር ካሳ ሊከፍሉኝ ይገባል በማለት ዩኒቨርስቲው ክስ ያቀረበው፣ በሃዋሳ ለሚገኘው የሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ሲሆን ተከሳሾቹ ሰኞ እለት የመቃወሚያ መልስ አቅርበዋል፡፡ በእለቱ ያስከስሳል ወይስ አያስከስስም የሚል ብይን እንዲሰጥላቸው ተከሳሾቹ ቢጠይቁም፣ ዩኒቨርስቲው “የመልስ መልስ ለመስጠት ጊዜ ይሰጠኝ” በማለቱ ለሚቀጥለው ረቡዕ ተቀጥሯል፡፡
“ኢትዮ ምህዳር” ጋዜጣ በፊት ለፊት ገፁ ላይ “የሃዋሣ ዩኒቨርስቲ የማናጅመንት አባል በሙስና እጅ ከፍንጅ ተያዙ” የሚል ዜና ያወጣው ሰኔ 19 ቀን 2005 ዓ.ም ሲሆን፣ የዩኒቨርስቲው የፍትሐ ብሄር ክስ በካሳ ጥያቄ ላይ ያተኮረ ሆኗል። ዜናው ታትሞ በተሰራጨበት ወቅት ዩኒቨርስቲው በደብዳቤው ምላሽ ሰጥቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ዩኒቨርስቲው ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በላከው ደብዳቤ፣ የሙስና ወንጀል መፈፀሙን እንዳልካደ የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ አስታወሰው፤ “በሙስና የተያዘው ግለሰብ የማናጅመንት አባል ሳይሆን የቡድን መሪ ስለሆነ ማረሚያ እንድታወጡ” የሚል ደብዳቤ ነው የደረሰን ብሏል፡፡

ይህንንም ማረሚያ በጋዜጣችን አስተናግደናል ብሏል - ዋና አዘጋጁ፡፡
ቀደም ሲል ዩኒቨርስቲው በ “አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ላይ የወንጀል ክስ እንዲመሰረት ለፖሊስ አቤቱታ አቅርቦ እንደነበርና እንዳልተሳካለት የሚታወቅ ሲሆን፤ የፍትሐ ብሄር ክስ በመመስረት የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ሃዋሳ ሄደው እንዲከራከሩ መደረጋቸው ይታወሳል፡፡
የዩኒቨርስቲው ክስ በሃዋሳ ፍ/ቤት ውድቅ እንዲሆን ከተደረገ በኋላም እስከ ጠቅላይ ፍ/ቤት ድረስ ይግባኝ በመጠየቅ ተከራክሮ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡
የ“ሪፖርተር” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅም እንዲሁ ከሁለት ሳምንት በፊት ታስሮ ወደ ሃዋሳ ከተወሰደ በኋላ፣ ስትፈለግ ትመጣለህ ተብሎ መለቀቁ ይታወሳል፡፡

Read 2921 times