Saturday, 26 October 2013 13:25

የህክምና ቡድኑ ለአራት ቀናት ነፃ የህክምና አገልግሎት ሰጠ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(5 votes)

ወደ ስምንት ሺህ የሚጠጋ ህዝብ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆኗል
ከተለያዩ የአለም አገራት የተውጣጡ 56 ዶክተሮችንና ነርሶችን ያካተተ የህክምና ቡድን፤ ለአራት ቀናት ነፃ የህክምና አገልግሎት ሰጠ፡፡ በአገልግሎቱ ወደ ስምንት ሺህ የሚጠጋ ህዝብ ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ 

የዘንባባ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር እንዲሁም የዓይን ህክምና ስፔሻሊስትና ጠቅላላ ሃኪም በሆኑት በዶክተር አግራው መሀመድ አስተባባሪነት ወደ አገራችን የመጡት የህክምና ቡድን አባላት የአይን፣ የጥርስ፣ የፅንስና ማህፀን፣ የቀዶ ጥገና ህክምና፣ የውስጥ ደዌ ምርመራና ህክምናዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ የፕሮግራሙ አስተባባሪ ዶክተር አግራው መሀመድ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ኒውዮርክ ከሚገኘው “ዶርካሶ ሜዲካል ሚሽን” ከተባለ የሚሽነሪ አገልግሎት ጋር በመነጋገር የህክምና ቡድኑ ወደ አገራችን መጥቶ ነፃ ህክምና እንዲሰጥ ያደረጉ ሲሆን የዘንባባ ሆስፒታል አስር ኢትዮጵያውያን ዶክተሮችም ከህክምና ቡድኑ ጋር ነፃ የህክምና አገልግሎቱን ሰጥተዋል፡፡ በሕክምና ቡድኑ የቀዶ ጥገና ህክምና የተሰጣቸው ህሙማን፤ በዘንባባ ሆስፒታል ውስጥ ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነና ህሙማኑ ለህክምናው ምንም አይነት ክፍያ እንደማይፈፅሙ ዶ/ር አግራው ገልፀዋል፡፡
የህክምና ቡድኑ አባላት ለአራት ቀናት በሰጡት ነፃ የህክምና አገልግሎት በርካታ ከባድ በሽታዎች፤ የጡት፣ የማህፀንና የውስጥ አካላት እባጮች መገኘታቸውንና ህክምና እንደተደረላቸው ተናግረዋል፡፡ ቡድኑ ለህብረተሰቡ በሰጠው ነፃ የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ በርካታ ህመምተኞች ከበሽታቸው ሲፈወሱ ማየታቸው የመንፈስ እርካታን እንደሰጣቸው የተናገሩት ዶ/ር አግራው፤ አገልግሎቱ ቀጣይነት እንዲኖረው የማድረግ ፍላጐት እንዳላቸውም ገልፀዋል፡፡ ነፃ የህክምና አገልግሎቱ መስቀል ፍላወር አካባቢ ከጥቅምት 11 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ቀን ነው የተሰጠው፡፡

Read 1795 times