Saturday, 26 October 2013 13:20

“ኮብልስቶን ጠራቢዎች ከኔና ከናንተ የበለጠ ገቢ ያገኛሉ” የቢሮ ሃላፊ

Written by  መልካሙ ተክሌ
Rate this item
(5 votes)

ለከተማ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታ ድንጋይ (ኮብልስቶን) የሚጠርቡ ወጣቶች፣ “ከኔና ከናንተ የሚበልጥ ገቢ ያገኛሉ” ሲሉ በአዲስ አበባ የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ወርቁ ተናገሩ፡፡
የዘንድሮ እቅዳቸውን በሚመለከት አቶ ጥላሁን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ እያንዳንዱ ጠራቢ በቀን ሦስት መቶ እና አራት መቶ ብር እንደሚያገኝ ጠቅሰው፤ “ድንጋይን ዳቦ” የሚያደርግ ስራ ነው ብለዋል፡፡
በዲግሪ የተመረቁና የማስተርስ ዲግሪ ያላቸው ወጣቶች ድንጋይ እንዲጠርቡ ማድረግ፣ ለትምህርት የፈሰሰውን ገንዘብና ጊዜ በከንቱ እንዲባክን አያደርገውም? ተብለው የተጠየቁት አቶ ጥላሁን፤ ሥራ ማለት “White collar” እንደሚባለው ከረባት አስሮ ቢሮ ውስጥ መስራት ማለት እንዳልሆነ ገልፀዋል፡፡ “የ“White collar” አስተሳሰብ” ማስወገድና ሥራን ማክበር አለብን፤ ልማታዊነትን ለማስረጽ ማስትሬትም ሆነ ዶክትሬት ዲግሪ ይዞ በኮብልስቶን ስራ ላይ ቢሰማራ ችግር የለውም” ብለዋል - አቶ ጥላሁን፡፡ ሰዎች ወደ ኮብልስቶን እንዲገቡ ማስገደድ አይቻልም ያሉት አቶ ጥላሁን፤ የገቡ ሰዎች ግን ከፍተኛ የገንዘብ ምንጭ በመሆኑ ለመውጣት ይቸገራሉ ሲሉም አብራርተዋል፡፡ በኮብልስቶን ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች በአማካይ በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ሀብት አፍርተው ወደ ሌላ ሥራ መስክ እንደሚሰማሩ የተናገሩት አቶ ጥላሁን፤ በአዲስ አበባ 70ሺህ ሰዎች ኮብልስቶን በመጥረብና በማንጠፍ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ዘንድሮ 80ሺህ ሥራ ፈላጊዎችን በኮብልስቶን፣ በግንባታ፣ በአገልግሎት መስጫ እና በሌሎች ዘርፎች አሠልጥኖ ለማሠማራት መዝግበናል፤ ከነዚሁም አንድ ሺህ አምስት መቶ ያህሉ አካል ጉዳተኞች ናቸው ብለዋል - አቶ ጥላሁን፡፡
ቢሮው በዘንድሮው ዓመት 80ሺህ ሥራ ፈላጊዎች በኮብልስቶን፣ በግንባታ በአገልግሎት መስጫ እና ሌሎች ዘርፎች አሠልጥኖ ለማሠማራት የመዘገበ ሲሆን ከነዚሁ አንድ ሺህ አምስት መቶው አካል ጉዳተኞች ናቸው፡፡

Read 4096 times