Saturday, 26 October 2013 13:12

በሣኡዲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስጋት ላይ ነን አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

የመኖሪያ ፍቃድ ሳያገኙ በሳውዲ አረቢያ በጥገኝነት ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን የሃገሪቱ መንግስት በሰጣቸው የ5 ወራት የምህረት ጊዜ ህጋዊ ለመሆን የሚያስችላቸውን የዜግነት ማረጋገጫና ፓስፖርትን ጨምሮ ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በሃገሪቱ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሊፈፀምላቸው ባለመቻሉና የጊዜ ገደቡም በመጠናቀቁ ከሀገሪቱ ሊባረሩ እንደሚችሉ ምንጮች ገለፁ፡፡
የሳውዲ መንግስት ህገወጥ ስደተኞችን አስመልክቶ ያወጣውን መስፈርት ለሚያሟሉ ስደተኞች የመኖሪያ ፈቃድ ለመስጠት ያስቀመጠው የተራዘመ የምህረት አዋጅ ጥቅምት 24 ቀን 2006 የሚጠናቀቅ ሲሆን ለጊዜው ቁጥራቸው በውል ያልተገለፀ በርካታ ኢትዮጵያውያን የህጋዊ ዜግነት ማረጋገጫና ፓስፖርት ለመስጠት የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለመተባበሩ በጭንቀት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ፓስፖርት እንዲሰጣቸው ኢትዮጵያዊ ለመሆናቸው ማረጋገጫ እንዲያቀርቡ በጂዳ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በጠየቀው መሠረት ማረጋገጫውን ቢያቀርቡም “ፓስፖርት ሃገር ቤት ተሠርቶ እስኪመጣ ጠብቁ” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው የሚገልፁት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ በተጓተተው የኤምባሲው አሠራር ምክንያት በሃገሪቱ የመኖር ህልውናችን አደጋ ላይ ወድቋል ብለዋል፡፡ የሃገሪቱ መንግስት ቀደም ሲል ያወጣውን አዋጅ ሽሮ የ5 ወራት የምህረት ጊዜ መስጠቱ የሚመሰገን ነው ያሉት ኢትዮጵያውያኑ፤ የሌሎች ሀገራት ዜጐች የተሰጣቸው ተመሳሳይ እድል እንዳይበላሽባቸው ኤምባሲዎቻቸው ባደረጉላቸው ትብብር የሚፈለገውን የመኖሪያ ፍቃድ ማውጣት እንደቻሉ ገልፀዋል፡፡
ኤምባሲው ለስራው መጓተት “በቂ የሰው ሃይል የለኝም” የሚል ምክንያት ማቅረቡን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ “በሃቀኝነት ለዜጐቹ የሚያስብ ኤምባሲ ቢሆን ኖሮ ከሃገር ቤትም ቢሆን የሰው ሃይል በመጨመር እድላችን እንዳይበላሽ መጣር ይችል ነበር ብለዋል፡፡
የተራዘመው የጊዜ ገደብ እየተገባደደ ባለበት ወቅትም የሃገሪቱ መንግስት መስፈርቱን አሟልተው ህጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ያልተቀበሉትንም ሆነ ያስጠጓቸውን እንደሚቀጣ እያስጠነቀቀ መሆኑን የዜና ምንጮች ገልፀዋል፡፡
በጂዳ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አንድ ዲፕሎማት ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው ሲመልሱ፤ የፓስፖርት ጉዳይ ከደህንነት ጋር የሚያያዝ እና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው መሆኑን አመልክተው፤ ዜጐች ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ እስካቀረቡ ድረስ ፓስፖርት የማያገኙበት ምክንያት እንደሌለ መግለፃቸው ተመልክቷል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ አዲስ አድማስ በስልክ ያነጋገራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሣደር ዲና ሙፍቲ፤ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተውን በሣውዲ የኢትዮጵያ ኤምባሲን ማነጋገር የተሻለ እንደነበር አመልክተው “የኤምባሲው ዋነኛ ተልእኮ ዜጐችን ማገልገል ነው፣ ስለዚህ ለዜጐች ጥቅም ምንጊዜም መቆምና መስራት አለበት” ብለዋል፡፡ አክለውም እንዲህ ያለ ቅሬታ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማመልከት ይችላሉ ብለዋል፡፡

 

Read 1245 times