Saturday, 26 October 2013 13:10

“በቋንቋችን እንማር” በሚል ጥያቄ 38 ት/ቤቶች ተዘጉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

“በቁጫ ከ34 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ተስተጓጉለዋል”

በጋሞ ጎፋ ዞን ቁጫ ወረዳ “በአፍ መፍቻ ቋንቋችን በቁጫቶ መማር እንፈልጋለን” በሚል በተነሳ ቅሬታ፣ በወረዳው ከሚገኙ 56 ት/ቤቶች 38ቱ መዘጋታቸውንና ወደ 34 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች ከትምህርት መስተጓጎላቸውን ምንጮች ተናገሩ፡፡
እድሜያቸው ከ18 አመት በታች የሆኑ 40 ተማሪዎች ለአንድ ሳምንት ታስረው መፈታታቸውንም ምንጮች ጨምረው ገልፀዋል፡፡
“የቁጫ ማህበረሰብ ተማሪዎች የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ቁጫቶ ሆኖ ሳለ በጋማቶ ቋንቋ እንዲማሩ መደረጉ አግባብ አይደለም” ያሉት የአካባቢው ነዋሪ ይህን ጥያቄ ያነሱ ተማሪዎች ታስረው መፈታታቸውን በፖሊስ ከቤታቸው እየተወሰዱ እንዲማሩ መደረጋቸውንና አሁንም ከ20 በላይ የተማሪ ቤተሰቦች መታሰራቸውን ገልፀዋል፡፡
ቀደም ሲል “የቁጫ ማህበረሰብ እውቅና ይሰጠው” በሚል በተደጋጋሚ ጥያቄ ማንሳታቸውን ያስታወሱት ምንጮቹ፤ የአሁኑም የቋንቋ ጥያቄ ጥያቄ ጋር የተያያዘ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ከጋሞ ጎፋ ዞን ከአርባ ምንጭ ከተማ ልዩ ሀይል ተሰማርቶ ተማሪዎቹን እያስገደደ ት/ቤት ያስገባ ነበር ያሉት ምንጮቹ፤ በአሁኑ ሰዓት ልዩ ሀይሉ ወጥቶ የሰላም በር ከተማ ፖሊስ፣ በተማሪዎቹ ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን የተማሪ ወላጆች ተናግረዋል፡፡ የወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ደማ ሻራን በተደጋጋሚ ስልክ ደውለን ስልካቸው ዝግ በመሆኑ ምላሽ ሳናገኝ ቀርተናል፡፡ የወረዳው ፖሊስም ሆነ የአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ ስልኮች ባለመነሳታቸው ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት አልቻልንም፡፡

Read 1012 times