Saturday, 19 October 2013 12:43

“ቢዝነሱ”

Written by  በኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(17 votes)

ከምሽቱ አንድ ሰዓት በመሆኑ የአራት ኪሎ ጉራንጉሮች በደንበኞቻቸው መጨናነቅ ጀምረዋል። ሰካራሙ፣ ወፈፌው፣ ቅንዝራሙ፣ መንታፊው፣ ለፍላፊው፣ ሴተኛ አዳሪዋ፣ ወንድ አዳሪው፣ ሎተሪና ቆሎ አዙዋሪው…የአራት ኪሎ ጉራንጉሮች ቁዋሚ ደንበኞች ናቸው፡፡ መንገዱም፣ ቤቱም፣ ድንግዝግዝ ያለ ነው - በአራት ኪሎ ሸለቆዎች፡፡
በአራት ኪሎ ጉራንጉሮች ውስጥ ሀፍረት፣ ይሉኝታ፣ ባህል፣ እምነት…እምብዛም ቦታ ያላቸው አይመስሉም፡፡ ስርቆት፣ ዝሙት፣ ቅጥፈት፣ ውስልትና…የጉራንጉሮቹ መገለጫዎች ናቸው፡፡ አራት ኪሎ፤ ሞቃ፣ ግላ፣ ልትቀልጥ የምትደርሰው አመሻሽ ላይ በመሆኑ፤ ሲመሽ የነጋ፣ ሲነጋ ደሞ የመሸ ይመስላል፡፡ መንገዶችዋ የተጨናነቁ ናቸው፤ ኑሮ የተጨናነቀ ነው፡፡ ቤቶችዋ እጅግ የተጨናነቁ ከመሆናቸው የተነሳ፣ የሰው ሳይሆን የወፍ ጐጆ ይመስላሉ፡፡ የቤት ወጉ ሳይኖራቸው ቤት ተብለው ሰው ከሚኖርባቸው ውትፍትፍ ጐጆዎች አንድዋ የሃዳስ ገብሩ ክፍል ናት፡፡
የሃዳስ ክፍል፣ የተመረገችበት ጭቃ ወላልቆ በመውደቁ፤ በቡትቶ፣ በካርቶን እና በስሚዛ ቅጠል ተወታትፋ ላስተዋላት፣ ለሰው ሳይሆን፣ ለውሻ ማደሪያነት እንኩዋ፣ ብቃት የሌላት ትመስላለች፡፡ ክፍልዋ፣ ውስጥዋም እንደ ውጭዋ የተጐሳቆለ ነው።
ከአንድ የረጥባ አልጋና ከእንጨት ሳጥን በቀር ሌላ ንብረት አይታይም፡፡ ሳጥንዋ፣ የልብስ ማስቀመጫም ወንበርም ናት፡፡ ከሳጥኑ ጀርባ፣ በኮምፔልሳቶ የተጋረደች እጅግ ጠባብ ክፍል አለች - ጥቂት የሻይ ብርጭቆዎችና ባዶ የአረቄ ጠርሙሶች የሚቀመጡባት፡፡
ሀዳስ፤ እምብዛም ውብ፣ እምብዛም መጥፎ ያልሆነውን ጭንዋን በአግባቡ የሚያሳይ አጭር ጉርድ ቀሚስ ለብሳ፣ አምባሬጭቃዋን ተባብሳ፤ አንዴ ጐርደድ፣ እንደገና ቀጥ እያለች፣ እየተሽኮረመመች፣ እያሽኮረመመች፣ አላፊ አግዳሚውን ለመጥለፍ ያደረገችው ሙከራ አልሳካላት ስላለ፣ ደከማትና ወደ በርዋ ተመለሰች፡፡ “ምን አይነት ነጃሳ ቀን ነው? አስራ ሁለት ሰአት ሳይሞላ የወጣሁ እስከ አንድ ሰአት ድረስ እንዴት አንድ ሰካራም እንኩዋ አጣለሁ? ፎጋራ ቀን…” ባይሰማትም ምሽቱን ሰደበችው፡፡
በርዋን ተደግፋ ቆማ፣ የሰፈርዋን ሴቶች ስታይ፣ አንዳንዶች ከደንበኞቻቸው ጋር ቆመው “ዋጋ ጨምር፣ ቀንሽ” ይወጋወጋሉ፤ የቀናቸው፣ ይዘው ይገባሉ፡፡ ቀደም ብለው ያስገቡም፣ ቶሎ ብለው አስወጥተው፣ ሌላ ለመጥለፍ ይሽቀዳደማሉ፡፡
ሌሎች፣ እንዲህ አይነት እድል ሲገጥማቸው፣ እስዋ ለምን እንደሚጠምባት እያሰላሰለች፣ በጉዋደኞችዋ እየቀናች ሳለ፣ ጐረቤትዋን ሲያነጋግር የነበረ አንድ ጐረምሳ በአጠገብዋ ሲያልፍ አየት አረጋት፤ ጠቀሰችው፡፡ ዋጋ ጠየቃት፤ ነገረችው። ተስማሙ፡፡ ተከትሎዋት ገባ፡፡ ሞከረ፣ ግን፣ ሰውነቱን የሆነ ነገር ቀፈፈው፡፡
“ታረጋለህ አርግ፤ አለዚያ ውረድልኝ ሰውዬ” ሀዳስ ድንገት አንባረቀችበት፡፡
“ቆይ በእናትሽ? ስሜቴን አትዝጊው…” ኤፍሬም በማባበል ስሜት ጠየቃት፡፡
“ስሜት? እንዲህ አርጐም ስሜት የለ…” የሽሙጥ ሳቅ ሳቀችበት፡፡
“እንዴት ስሜት የለኝም!”
“ስሜት ታለህ ታዲያ ምን ያልፈሰፍስሃል?” በንቀት አየችው፡፡
“ማን ነው ልፍስፍስ?”
“እኔ ልበልህ ወንድም? ለጭቅጭቅ ጊዜ የለኝም፤ ከቻልህ አርግ፤ ካልሆነልህ ደሞ ውረድ” መረር አለችበት፡፡
“በእናትሽ አባብይው?”
“እ…? አባብይው? ማሙሽዬ አይዞህ … ባባ ኬክ ይዞልህ ይመጣል ልበለው?”
ምስኪንዋ ጐጆ እስከምትሰነጠቅ ሳቀችበት፡፡
“በእናትሽ? ትንሽ ሞክሪ?” ድጋሚ ተማፀናት፡፡
“ውረድ ልፍስፍስ…”
“ለምን ነው የምወርድ?”
“እና አዝየህ ላድር ነው? በቢዝነስ ቀልድ የለም፤ ይገባሀል?”
“ቢዝነስ? የቱ ነው ደሞ ያንች ቢዝነስ?”
“ሚስትህ መሰልሁህ? እየሰራሁ ያለሁትኮ ቢዝነስ ነው”
“ኧ…ሽርሙጥና በበረሃ ስሙ ሲጠራ ነው ቢዝነስ ማለት?” ኤፍሬም የፌዝ ሳቅ ሳቀባት፡፡
“በበረሃም ጥራው በደጋ ስሙ፣ ለኔ ቢዝነሴ ነው። ልቀቀኝ” ቀኝ እግርዋን ከራቁት ገላው ላይ አነሳች፡፡
“አንቺ እንቢ ካልሽ፣ ጉዋደኛሽን አላጣት፤ ምን ቸገረኝ፡፡ ብሬን መልሽልኝ”
“የምን ብር?” ተኮሳተረችበት፡፡
“የሰጠሁሽን አምስት ብሬን ነዋ”
“ኧረ ባክህ? እስካሁን ስታለፋኝ የቆየህ ያባትህ ቅሬላ መሰልሁህ” ኤፍሬም ተኝቶበት የነበረውን ግራ እግርዋን ለማስለቀቅ ታገለችው፡፡ ማንም እየመጣ ሲጨፍርባት የተሰላቸችው የረጥባ አልጋም አብራት ተነጫነጨች፡፡ “ልቀቀኝ ብዬሃለሁ ሰውዬ! ሁዋላ ትዋረዳለህ”
“ምን አባትሽ ልትሆኝ? ጥንብ ሸርሙጣ…” ኤፍሬም መልሶ ደፈቃት፡፡
“ሽርሙጥናዬን ፈልገህማ ነው የመጣኸው፤ ስብሰባ የተጠራህ መሰለህ? ባለጌ ልፍስፍስ! ወንድ ሆኜ ያንተን ድርሻ ላረግልህ ትፈልጋለህ? ሙትቻ! ወንድ ከሆንህ ያውልህ አርግ?” በጣትዋ ወደ ጭኖችዋ መሀል ጠቆመችው፡፡
ኤፍሬም የበታችነትና የመጠቃት ስሜት መላ አካላቱን ሲወርረው ተሰማው፡፡ እናም፣ ድንገት በጥፊ አጮላት፡፡ ሃዳስ፣ እየጮኸች እንደድመት ትቡዋጭረው ጀመር፡፡ እንደምንም ገፍትሮ ወደ አልጋዋ ጫፍ ጣላትና በችኮላ፣ ሱሪውን ከጣለበት ሳጥን ላይ ቢፈልገው አጣው፡፡
“ሱሪዬን የት አባትሽ ነው የደበቅሽው?”
“እበት ብላ! ጅል የወንድ አልጫ! ደሞ አንተ ምን ሱሪ አለህ?”
ኤፍሬም እንደ ገና በጥፊ ሲያልሳት፣ አራት ኪሎን በጩኸት አደበላለቀችው፡፡ ወዲያው፣ የሃዳስ ክፍል ወደ ሲኦልነት የተቀየረች መሰለች፡፡ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ፣ ምክንያቱን ያወቁትም ያላወቁትም፤ ብቻ የወሬ ሱስ ያለባቸው የአራት ኪሎ ሴትኛ አዳሪዎች፣ ጩኸቱንም ግርግሩንም እያባባሱት መጡ፡፡
ከአካባቢው የማይጠፉት የፖሊስ አባላት ግን፣ “የተለመደ የቁራ ጩኸት ነው” በማለት ነገሩን ችላ ብለውት ነበር፡፡ ሆኖም፣ ሃዳስ ቤት ሰው መገደሉን የስሚ ስሚ ሲሰሙ፣ በቸልታቸው ተፀፀቱና አካባቢውን በፍጥነት ተቆጣጠሩት፡፡
ፖሊሶች፣ ጩዋሂዋንም፣ አጩዋጩዋሂውንም እየገፈተሩ ከሃዳስ በር ሲደርሱ፣ ኤፍሬም ከወገቡ በታች እንደተራቆተ፣ እንጨት ሳጥኑ ላይ በአፍጢሙ ተደፍቶ፣ ደም እንደጐርፍ ሲወርደው አዩ፡፡
ሁለት የፖሊስ አባላት የኤፍሬምን አስከሬን በአንቡላንስ ይዘው፣ ወደ ምኒልክ ሆስፒታል ሲከንፉ፣ ሌሎች ግን፣ ወንጀለኛውን ለመያዝ፣ አራት ኪሎን ያተራምሱዋት ጀመር፡፡ ብዙም ሳይቆዩ፣ በርካታ ተጠርጣሪዎችን በመያዝ ወደ ጣቢያቸው ተመለሱና፣ የተለመደውን ምርመራ ቀጠሉ፡፡ ብዙዎችን የያዙዋቸው ቀድሞውንም ለማስረጃ ያህል ስለነበር፣ እንደነገሩ እየጠያየቁ፣ ወደ መቆያ ክፍል ላኩዋቸው፡፡ “ገዳዩ እሱ ነው” ተብለው በጥቆማ ከያዙት ዋናው ተጠርጣሪ ላይ ግን፣ ምርመራቸውን ጠበቅ አደረጉ፡፡
“ስም?” መርማሪ ፖሊሱ ጠየቀ፡፡
“የሰፈር ስሜን ነው ወይስ ዋናውን?”
“መ..ጀመሪያ የሰፈሩን ንገረኝ”
“ብዙ ነው”
“ለምሳሌ?”
“አሞራው፣ እ…ገንድስ፣ ቆሪጥ፣ አጅሬው፣ እ…ሌላም ይሉኛል፡፡ ግን ይኸ ሁሉ ለአንተ ምን ያረግልሃል?” ተጠርጣሪው መርማሪውን ጠየቀው፡፡
“ሌላ ማን ይሉሃል?” መርማሪው ያልሰማ መስሎ ጠየቀው፡፡ “አፍን”
“ሌላስ?”
“በቃ ይኸው ነው”
“ይሄን ሁሉ ስም ያወጣልህ ማነው?”
“ግማሹን ጉዋደኞቼ፣ሌላውን ደግሞ የሰፈር ሰው”
“ለምን ነው እንዲህ አይነት ስም ያወጡልህ?”
“በአንዳንድ ድርጊቴ…”
“ለምሳሌ?”
“አሞራው ያሉኝ ሞባይል ስለምሰራ ነው”
“መስራት ማለት?”
“ያው አንዳንድ ሰዎች ተዝናንተው በሞባይል ሲያወሩ ፣ነጥቄያቸው ስለምሮጥ እ…‹አፍን› ያሉኝ ደሞ፣ ሀርድ የምታበዛ ሴት ስታጋጥመኝ በግድዋ ስለማወጣት ነው፡፡ ብቻ፣ሰው ማካበድ ስለሚወድ፣ የሆነ ስራ ስሰራ፣ የሆነ ስም ያወጣልኛል” የተጠርጣሪው መዝናናት መርማሪውን አስገርሞታል፡፡
“እሺ ዋናው ስምህስ?”
“ወርቁ በላቸው”
“ያያት ስም?”
“የእናቴን ነው የአባቴን?”
“የአባትህ አባት..?”
“ገመቹ”
“እድሜ?”
“እድሜዬ?”
“አዎ እድሜህ ስንት ነው?”
“ሀያ አምስት ቢሞላኝ ነው”
“የትምህርት ደረጃህ?”
“አንድ ጊዜ ካራቴ ተምሬያለሁ”
“ማን ነው ያስተማረህ? የት ነው የተማርኸው?”
“ያስተማረኝ ‹ዘንጥል› የሚባል ጉዋደኛዬ ነው። የተማርሁት እንጦጦ ጫካ ውስጥ” የመርማሪው ጆሮዎች ይበልጥ ተቀሰሩ፡፡
“ዘንጥል ማነው? አሁንስ የት ነው ያለው?”
“ትላንት ደየመ፡፡ እንዴት ያለ ጎበዝ ልጅ ነበር መሰለህ!”
“በምን ምክንያት ሞተ?” መርማሪው እንደ ዋዘ ጠየቀው፡፡
“አንድ ከእሱ የባሰ ጉልቤ በስኪኒ ወጋና ገደለው። እኔ እንኩዋ ከእሱ ጋር መሳፈጥህን ተው ብየው ነበር”
“እሺ ስራ?”
“ምን አይነት ስራ?”
“ስራህ ምንድነው? ነው የምልህ!” መርማሪው በተሰላቸ አንደበት ጠየቀው፡፡
“የተገኘውን ነው የምሰራ”
“ለምሳሌ?”
“በቃ፣ ቋጠሮም ተገኘ ሌላ የጉልበት ስራ እሰራለሁ”
“የጉልበት ስራ ስትል?”
“ያው እ…ሞባይል፣ቦርሳ፣እ..አንዳንዴ ሀንግ…” አንገቱን በግዴለሽነት ሰበቀ፡፡
“ሞባይል፣ቦርሳ ትነጥቃለህ፡፡ ‹ሀንግ አረጋለሁ› ስትል ምን ማለትህ ነው?”
“ይህ ጠፍቶህ ነው? ያው ፍሉስ አለው ብዬ የገመትሁትን ሰው አፍኜ እዳብሰዋለሁ”
“እዳብሰዋለሁ?” መርማሪው ትኩር ብዬ እያየ ጠየቀው፡፡
“አዎ፣ ኪሱን እፈትሻለሁ”
“አልሰጥም ብሎ ቢታገልህስ?”
“ዋጋውን ያገኛላ”
“ማለት?”
“ኪል አረገዋለሁዋ”
“ጥሩ፣የቅድሙን ሰውዬ ታውቀዋለህ?”
“የቱን?”
“ሀዳስ ቤት ወድቆ የተገኘውን”
ከዛሬ በፊት አላውቀውም”
“ታዲያ ለምን መታኸው?”
“ሲመታት እያየሁ ዝም ልበል?”
“እንዴት?”
“እንዴትማ..ሲቅለበለብ መጥቶ፣ለሾርት አምስት ብር ከፈላት”
“እሺ..?” ፖሊስ እያንዳንድዋን ቃል በጥንቃቄ መመዝገብ ጀመረ፡፡
“ከዚያ፣ አልጋ ላይ ወጣና ቢለው፣ ቢለው አልቆምለት አለ፡፡ በዚህ የተነሳ፣ ብሬን መልሽልኝ አልመልስም፣ ከሀዳስ ጋር ጭቅጭቅ ጀመረና እንደማትመልስለት ሲያውቅ ይደበድባት ጀመር፡፡ በዚህ የተነሳ ያው…በቃ በቦክስ ስሰጠው ሳጥኑ ላይ ወደቀ”
“ሲመታት እንዴት አየህ?”
“እዚያው ነበርሁዋ”
“የት?”
“ከምስጢር ክፍልዋ”
“ከማን?”
“ከሀዳስ ነዋ”
“ምን ልትሰራ?”
“ቢዝነስ ነዋ”
“ምን አይነት ቢዝነስ?”
“ያው እሱ ችክ አገኘሁ ብሎ ሲያፎደፍድ፣እኔ ኪሱን እፈትሻለሁ”
“ብዙ ጊዜ እንዲህ ታረጋለህ?”
“አዎ በቸሰትሁ ጊዜ ሁሉ እሰራለሁ”
“ለመሆኑ ሀዳስ ምንህ ናት?”
“ሚስቴ”
“ሚስቴ?” መርማሪ ፖሊስ ተገረመ፡፡
“አዎ ሚስቴ፡፡ ምነው?”
“አንተ አልጋ ላይ ፣ሚስትህ ከሌላ ወንድ ጋር ስትተኛ ትንሽ አትናደድም?”
“ምን ሀርድ አለው? ነካው እንጂ፣እንዳለ ይዞብኝ አይሄድ፡፡ ወዲያውስ፣ቢዝነስ እኮ ነው”
“ቢዝነስ?”
“አዎና ቢዝነስ”
“እንዲህ የምታደርጉት ተስማምታችሁ ነው? ወይስ እያስገደድሀት?”
“ለምን አስገድዳታለሁ? ለቢዝነስ አይደል እንዴ ካገርዋ የመጣችው?”
“የፈፀምኩት ድርጊት ትክክል ነው ብለህ ታስባለህ?”
“ቢዝነስ ስትሰራ’ኮ፣ ያው መሳሳትህ አይቀርም”
“እና? ተሳስቻለሁ ነው?”
“ባልሳሳትም ያው መትቸዋለሁ፡፡ ፊልም አታይም እንዴ? ለቢዝነስ ሲባል ስንት ወንጀል ነው የሚሰራ?”
“እና ፊልም ላይ ያየኸውን ለመድገም ስትል፣ የምስጢር ቦታ አዘጋጅተህ ሚስትህን ከሌላ ወንድ ጋር እንድትማግጥ ታረጋለህ፡፡ በአጋጣሚውም ዘረፋ ታካሂዳለህ?”
“ዘረፋ አይደለም፤ ቢዝነስ ነው፡፡ ቆይ እስኪ? አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ፤ ሚስት አለህ የለህም?”
“አለችኝ”
“ጥሩ፣ ስራስ አላት?”
“የላትም” ፖሊሱ መጨረሻውን ለመስማት ጓጓ።
“በጣም ጥሩ፣ ስራ ከሌላት መቼም ዝም ብለህ ስትቀልባት አትኖርም፡፡ ቀን ቀን ቢዝነስ ስትሰራ ብትውልኮ ማታ የአንተው ናት፡፡ እ….”
“በቃ…!”መርማሪው ድንገት አንባረቀበትና ወደ ማረሚያ ቤት ላከው፡፡

 

Read 9301 times