Saturday, 19 October 2013 12:38

ሰው ነው የረቀቀ

Written by  ገብረክርስቶስ ደስታ
Rate this item
(6 votes)

ሰው ነው የረቀቀ
ከሜርኩሪ ቬነስ፤ ከጨረቃ ከማርስ
ከፕሉቶ ኔፕቱን፤ ኡራኑስ የላቀ
ከጁፒተር ሳተርን፤ ከጣይ የደመቀ
ባካባቢው ሁሉ እያሸበረቀ፤
ሰው አደገ አወቀ፤
መሬት እንቁላሉን ሰበረ መጠቀ፤
ሰው ዓለምን አየ
በጨለማው ቦታ ዶቃ አንፀባራቂ
ውብ ሰማያዊ ኩዋስ፤ ሮዝ አብረቅራቂ፡፡
በተጣራው አየር በነጣው ደመና
ባረንጉዋዴው ባህር ውሃ ተሸፍና፤
ውብ ሉል ኮከብ አለም፤ የጠፈር ላይ ጤዛ፤
የሰው ልጆች እናት፤ የሰው ልጆች ቤዛ፡፡

የማታ ጀምበር
ካንዱ ቤት ወዳንዱ በጣራው ተራምዳ፤
የጋራውን እናት እየነካች ሄዳ፤
እዩት ከስር ጥላው፤
የማይደርስበትን፤
እዩት ሰውን ጥላው፤
ሲለፋ ሲባክን፡፡

Read 3052 times