Saturday, 19 October 2013 12:22

ኢትዮጵያ በዓለም ዋንጫ ዋዜማ ላይ!?

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(10 votes)

ኢትዮጵያና ናይጄርያ ወደ ዓለም ዋንጫ ጥሎ ለማለፍ የገቡት ትንቅንቅ ከወር በኋላ በመልስ ጨዋታ ይለይለታል። ዋልያዎቹ በናይጄርያዋ ከተማ ካላባር በሚገኘው ዩጄ ኡሱዋኔ ስታድዬም ህዳር ሰባት ለሚያደርጉት ፍልሚያ ዝግጅቱን ትናንት ጀምረዋል፡፡ በመልሱ ጨዋታ ናይጀሪያ ለ5ኛ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ለመብቃት ስታነጣጥር ኢትዮጵያ ምስራቅ አፍሪካን በመወከል የመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ማግኘቱን ታልማለች፡፡
ናይጄርያ በአዲስ አበባ በተደረገው የመጀመርያ ጨዋታ ኢትዮጵያን 2ለ1 ካሸነፈች በኋላ የማለፍ እድሏን እንዳመቻቸች ሲገለፅ፤ በሌላ በኩል በኳስ ቁጥጥር እና በጨዋታ ናይጄርያ ላይ ብልጫ ማሳየቱ የተነገረላት ኢትዮጵያ የማለፍ ተስፋዋን ከሜዳው ውጭ የምተወስንበት አጣብቂኝ ውስጥ ገብታለች። ናይጄርያ ኢትዮጵያን 2ለ1 ካደረገች በኋላ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ 27ኛ ግጥሚያዋን በማሸነፍ በአፍሪካ ደረጃ በብዙ ጨዋታዎች ያለመሸነፍ ክብረወሰን ሆኖላታል፡፡ ናይጄርያ በካላባር በምታደርገው ጨዋታ ተሸንፋ አለማወቋ በመልሱ ትንቅንቅ የኢትዮጵያን ፈተና ያከብደዋል፡፡ የእግር ኳስ ዘጋቢው ድረገፅ ጎል ዶት ኮም በመልሱ ጨዋታ ማን ያሸንፋል በሚል ጥያቄ አንባቢዎቹን አሳትፎ በሰራው የውጤት ትንበያ አሸናፊነቱ 76.2 በመቶ ለናይጄርያ 23.8 በመቶ ለኢትዮጵያ ግምት ተሰጥቷል፡፡ 3ለ0 ፤ 1ለ0 እና 3ለ1 ናይጄርያ እንደምታሸንፍ የጎል አንባቢዎች ተንብየዋል፡፡
አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በመልሱ ጨዋታ የማሸነፍ እድል መኖሩን ተናግረዋል፡፡ በመጀመርያው ጨዋታ እንዳሳየነው የኳስ ብልጫ ናይጄርያን በሜዳው ስንገጥም ከፍተኛ ትግል አድርገን 2-0 አልያም 2-1 ማሸነፍ እንችላለንም ብለዋል፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በቀሪው 1ወር በሚኖራቸው ዝግጅት የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያስፈልጋቸው ያስታወቁ ሲሆን ለቡድኑ የማለፍ እድል ቀላል ግምት መሰጠት እንደሌለበት በማሳሰብ ከትልቅ ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻው እንዲዘጋጅላቸው ሃሳባቸውን ገልፀዋል፡፡ አሰልጣኝ ስቴፈን ኬሺ በበኩሉ በተገኘው ድል የተሰማውን ደስታ በገለፀበት ወቅት ‹‹ያሸነፍነው እልህ አስጨራሽ ትግል በማድረግ ነው፡፡ በተለይ በጨዋታው ያደረግኳቸው ሁለት ቅያሪዎች ግጥሚያውን ወደራሳችን አጨዋወት በመቀየር ድላችንን ለማረጋገጥ ምክንያት ሆኖልናል፡፡›› በማለት ተናግሯል፡፡ ስቴፈን ኬሺ ለመልሱ ጨዋታ አዲስ እቅድ በመንደፍ እንሰራለን ብሎ በተናገረበት ወቅት ናይጄርያውያን ከኢትዮጵያን ድጋፍ አሰጣጥ ተምረው በካላባር በሚደረገው ጨዋታ ስታድዬሙን በነጭ እና አረንጓዴ ቀለሞች በማሸብረቅ እንዲደግፉ ጥሩ አቅርቧል፡፡
ናይጄርያ ከኢትዮጵያ ጋር ከምታደርገው ጨዋታ በፊት ከዮርዳኖስ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ታደርጋለች፡፡ ከመልሱ ጨዋታ ሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ በለንደን ከተማ በሚገኘው የፉልሃም ክለብ ስታድዬም ክራቫን ኮቴጅ ከአራት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮኗ ጣሊያን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ እቅድ ይዛለች፡፡ ይህን የወዳጅነት ጨዋታ የናይጄርያ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ያዘጋጀው በዓለም ዋንጫ ከሚያደርገው ዝግጅት ጋር በተያያዘ 2013 ከመገባደዱ በፊት ከዓለም አስር ምርጥ ቡድኖች ከአንዱ ጋር ንስሮቹ መጫወት እንዳለባቸው አቅዶ ሲሰራ በመቆየቱ ነው፡፡
የጨዋታ ብልጫ፤ የዳኝነት በደልና መረብ ያልነኩት ኳሶች
በዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ከሳምንት በፊት በአዲስ አበባ ስታድዬም ኢትዮጵያ ከናይጄርያ የተገናኙበት የመጀመርያ ጨዋታ በአፍሪካ ዞን ከተደረጉ ሌሎች 4 ጨዋታዎች አነጋጋሪው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያው ግማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አስደናቂ አጨዋወት በማሳየት ናይጄርያን በከፍተኛ ደረጃ አጨናንቆ ነበር፡፡ ዋልያዎቹ በመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች ከሶስት በላይ ጎል የማግባት እንቅስቃሴዎች በናይጄርያ የግብ ክልል አድርገዋል በአጨራረስ ድክመት ከመረብ ለማዋሃድ አልሆነላቸውም፡፡ በ23ኛው ደቂቃ ላይ ሳላዲን ሰይድ ከመሃል የተሻገረለትን ኳስ የናይጄሪያ ተከላካዮችን አታልሎ በማለፍ ወደ ግብ መታ፡፡ ኳሷ የናይጄርያውን ግብ ጠባቂ ኢኒዬማ አምልጣ የግቡን መስመር ብታልፍም የናይጄሪያ ተከላካይ ከጐል ውስጥ አወጣት፡፡ በዚያች ቅፅበት ሳላዲን ሰይድ ደስታውን እየገለፀ ነበር፡፡ ካሜሮናውያኑ የመስመር እና የመሃል ዳኞች ግን ተነጋግረው ጎሏን ሳያፀድቋት ቀሩ።

ይህች የግብ አጋጣሚ መበላሸቷ የዋልያዎቹን በማጥቃት ላይ የተመሰረተ አጨዋወት እና በስታድዬም የነበረውን ደጋፊ ስሜት አዘበራረቀ፡፡ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተደረገው አስደንጋጭ ሙከራ በሳላዲን ሰይድ ነበር፡፡ በግራ መስመር ወደ ግብ የመታትን ኳስ ኢኒዬማ በአስደናቂ ብቃት አድኗታል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ዋልያዎቹ በማጥቃት ጨዋታቸው በናይጄሪያ ቡድን ላይ ተደጋጋሚ ጫናዎችን በመፍጠር ቀጠሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይም በ57ኛው ደቂቃ ላይ በሃይሉ አሰፋ በግራ መስመር ናይጄርያ ክልል ውስጥ ገብቶ ኳሷን ወደ ግብ ክልል አሻገራት። የናይጄሪያው ግብ ጠባቂ ቪንሰንት ኢኒዬማ ኳሷን ሲይዛት የግብ መስመሩን በሙሉ ሰውነቱ አልፎ ገብቶ ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ የመስመር ዳኛው ጎሏ እንደገባች በማሳወቃቸው ወዲያወኑ የመሃል ዳኛው ግቧን በማፅደቅ ኢትዮጵያ 1ለ0 መምራት ጀመረች፡፡ ጎሏ በስታድዬም የነበረውን ደጋፊ ከማነቃቃቷም በላይ በናይጄርያ ቡድን አቋም ላይ መሸበርን የፈጠረች ነበረች፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ማንም ባልጠበቀው ውሳኔያቸው አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የዋልያዎቹን አጨዋወት የሚያውክ የተጨዋች ቅያሪ አደረጉ። በመሃል ሜዳ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የቆየውን አዳነ ግርማን በአጥቂው ኡመድ ኡክሪ ቀየሩት፡፡

ተጨማሪ ጐል ዋልያዎቹ እንዲያገቡ ከመፈለግ አንፃር ነበረ፡፡ ይህ የተጨዋች ለውጥ በብሄራዊ ቡድኑ አጨዋወት ላይ የፈጠረው ተፅእኖ ቀላል አልነበረም፡፡ ከአዳነ መውጣት በኋላ አሰልጣኝ ስቴፈን ኬሺ የመሃል ሜዳውን ለመቆጣጠር ሁለት ተጫዋቾች በአስር ደቂቃዎች ልዩነት ቀይሮ አስገባ፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይም በ67ኛው ደቂቃ ላይ ኢማኑዌል ኤሚኒኬ ከመሀል ጀምር ኳስ በመግፋት ከፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውጪ ወደግብ አክርሮ መታ፡፡ ድንገተኛዋን ኳስ ያልጠበቀው ጀማል ጣሰው ሊያድናት የቻለውን ያህል ቢወረወርም ናይጄሪያውያን አቻ ያደረገች ጎል ሆነች፡፡ ጨዋታው 1 እኩል በሆነ አቻ ውጤት ቀጠለ፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት በአዳነ ቅያሪ የሳሳውን አማካይ መስመር ለማስተካከል በሚመስል ውሳኔ ሽመልስ በቀለን በማስወጣት አዲስ ህንፃ እንዲቀየር አደረጉ፡፡ ይሁንና ይህ ቅያሬ ናይጄርያውያን ጨዋታውን አሸንፎ ለመውጣት የጀመሩትን የተጠናከረ እንቅስቃሴ የመገደብ አቅም አልነበረውም፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ኢማኑዌል ኢሚኒኬ ተከላካዩን አይናለም ሃይሉን በማለፍ ወደ ፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ገባ፡፡ አይናለም ያመለጠው ኢሚኒኬን ማልያ ጎትቶ በማስቀረቱ ዳኛው የፍጹም ቅጣት ምት ለናይጄሪያ ሰጡ፡፡ ወዲያውኑ ኢማኑዌል ኢሚኒኬ ለራሱና ለቡድኑ ሁለተኛውን ጐል በቀላሉ ለማስቆጠር ችሏል።
ከኢትዮጵያና ናይጄሪያ ጨዋታ ማግስት በተለያዩ የመገናኛ ብዙሐናት የዋልያዎቹ አጨዋወት ቢደነቅም በግብ ክልል ወሳኝ የጐል አጋጣሚዎችን በመፍጠር ቡድኑ የተዳከመ መሆኑ ለሽንፈት ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ዋልያዎቹ ማራኪ የኳስ ቅብብልና ቁጥጥር በማሳየት የአፍሪካ ሻምፒዮን የሆኑትን ንስሮቹን ማስጨነቃቸው እና ከተለያዩ የአውሮፓ ክለቦች ምርጥ ተጫዋቾች የተሰባሰቡበትን የናይጄርያቡድን በመግጠም ልዩ ብቃት ማሳየታቸው ስፖርት አፍቃሪ የገጠመውን ሽንፈት በፀጋ እንዲቀበል ያስቻለ ነበር፡፡ የሱፕር ስፖርት ዘጋቢ ስለጨዋታው ባሰፈረው ትንተና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአጨዋወታቸው በኳስ ቁጥጥር ተሽለው ቢታዩም ለጎል የሚበቁ የመጨረሻ ኳሶችን በማቀበል ውጤታማ እንዳልነበሩና ይህን ውጤት አልባ እና ተረከዝ የበዛበት የኳስ ቅብብል ለሰርከስ ካልሆነ ውጤት ለሚያስፈልገው ወሳኝ ግጥሚያ ማድረጋቸውን አሰልጣኙ ማረም ነበረባቸው ብሏል፡፡ በአዲስ አበባው ጨዋታ ኢትዮጵያውያን ደጋፊዎች ቡድናቸው በሜዳው ሁለት ለአንድ መመራት ጀምሮ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ 23 ደቂቃዎች እየቀሩ ሊያበረታታ ከሚችል ድጋፍ መቆጠባቸው እንዳሳፈረው በትንተናው የገለፀው ዘጋቢው በስታድዬሙ ከ35ሺ የዋልያዎቹ ደጋፊዎች ይልቅ በመቶዎች የሚቆጠሩት ናይጄርያውያን ጩሀት ጎልቶ መሰማቱን እንደታዘበ አብራርቷል፡፡
የናይጄርያ የስፖርት ሚኒስትር ንስሮቹ የሚገባቸውን ድል እንዳስመዘገቡ የተናገሩት እንደአፍሪካ ሻምፒዮን ተጫውተው የመጀመርያውን ምእራፍ እንደዘጉ በማስገንዘብ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ለአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ተገኝተው የነበሩት ፕሬዝዳንት ጉድላክ ጆናታን ቡድናቸውን ከጨዋታ በፊት በመጎብኘት ማበረታቻ ማድረጋቸውንም አመስግነዋል። በናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ የነበሩት ፋቲ አማዎ ንስሮቹ ለመልሱ ጨዋታ እንዳይዘናጉ አስጠንቅቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን ያልተጠበቀ ድል የማስመዝገብ አቅም እንደሚኖራቸው በማሳሰብም ለዓለም ዋንጫ የመድረስ እድላችው ገና 75 በመቶ የተረጋገጠ በመሆኑ ለሚቀረው የ90 ደቂቃ ጨዋታ አቻ ለመውጣት ወይም ለማሸነፍ ታስቦ መሰራት አለበት የሚል ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ ሌላው የቀድሞ የናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ኦገስቲን ኢግዌቨን እንደተናገረው ደግሞ ናይጄርያውያን የአዲስ አበባውን ጨዋታ ድል ሊያደርጉ የቻሉት ባላቸው ልምድ ከኢትዮጵያ የተሻሉ ሆነው በመገኘታቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያውያኑ በኳስ ቁጥጥር የላቁ እንደነበሩ የመሰከረው ኢግዌቨን በመልሱ ጨዋታ ንስሮቹ ሃላፊነታቸውን አሳክተው መጨረሳቸውን እጠብቃለሁ ብሏል፡፡
ከዋልያዎቹ አስደናቂ አጨዋወት ባሻገር በከፍተኛ ደረጃ ያነጋገረው በካሜሮናዊው ዳኛ የተሻረው የሳላሃዲን ሰኢድ ግብ ነበር፡፡ በጨዋታው ማግስት ይህ ጎል ፀድቋል ተብሎ ግራ መጋባት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ሰኞ አመሻሹ ላይ ኢትዮጵያ አቻ ሆናለች በሚል የተናፈሰው መረጃ ሃሰት ነበር። መስመሩን እንዳለፈች በብዙ ዘገባዎች የተወራላት ጎል ትክክለኛ ብትሆን እንኳን ጎሏን ያላፀደቀው ዳኛው መቀጣቱ እንጂ ጎሉ የሚፀድቅበት ሁኔታ አልነበረም ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ይህን በተመለከተ የክስ ማመልከቻውን ለአለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ አቅርቦም ነበር። ፈፋ ለፌደሬሽኑ በላከው ምላሽ በመተዳደሪያ ህጉ አንቀፅ በመጥቀስ ክሱን ተቀባይነት እንደሌለው አሳውቋል፡፡ ቪንሰንት ኢኒዬማ ለኢትዮጵያ የተመዘገበችው የመጀመርያ ጐል ብዙዎች እንደሚያስቡት የግብ መስመሩን አላለፈችም ብሎ በልበሙሉነት የተናገረው በጨዋታው ማግስት ነው። “እንደ እኔ አቋም ግብ አልነበረችም፡፡ ለምን እንደተሰጠ አላውቅም፡፡ ኳሷን የያዝኳት መስመሩን አልፋ አይደለም። የመስመር ዳኛው እንዴት ጐሉን እንዳፀደቀ መረዳት አልቻልኩም” ሲልም አስተያየት ሰጥቷል፡፡ ኢትዮጵያ ተሽሮበታል ስለተባለችው መረብ ያልነካች ኳስ አስተያየቱን ሊሰጥ ደግሞ “በእኔ እይታ ጐል አልገባችም፡፡ በተለያየ አንግል የሚቀርፁ ካሜራዎች የተለያዩ ምስሎችን ሊያመለክቱ ይችላሉ፡፡ የግብ መስመር ቴክኖሎጂ አስፈላጊነት እዚህ ላይ ነው፡፡›› ብሎ ተናግሯል፡፡ ሌላው የውዝግብ አጀንዳ ደግሞ የናይጄሪያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኢትዮጵያ ደጋፊዎች ድንጋይ ውርወራ ጉዳት እንደደረሰ በመግለፅ ፊፋ እርምጃ እንዲወስድ መክሰሱ ነው፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ለዚሁ ክስ እስከትናንት በስቲያ ምላሽ አልሰጠም፡፡
ለ20ኛው የዓለም ዋንጫ 18 ደርሰዋል፤ 14 ይቀራሉ፡፡
ባለፈው ሰሞን በ20ኛው የዓለም ዋንጫ አፍሪካን በመወከል የሚሳተፉ 5 ቡድኖች ለመለየት በተደረጉት የጥሎ ማለፍ የመጀመርያ ዙር ጨዋታዎች በኋላ አልጀሪያ፣ ካሜሮን፣ አይቬሪኮስት፣ ናይጄሪያና ጋና በመልስ ጨዋታቸው ወደ ዓለም ዋንጫ የሚያልፉበትን የተሻለ ዕድል ይዘዋል፡፡ ከዓለም ዋንጫው የጥሎ ማለፍ ትንቅንቆች ኢትዮጵያ በሜዳዋ ናይጀሪያ አስተናግዳ 2ለ1 ከተሸነፈችበት ጨዋታ ባሻገር፣ አይቬሪኮስት ሴኔጋልን 3ለ1፤ ቡርኪናፋሶ አልጀሪያን 3ለ2 እንዲሁም ጋና ግብጽን 6ለ1 በሆነ ውጤት በየሜዳቸው አሸንፈዋል፡፡ ቱኒዚያ ደግሞ በሜዳዋ ካሜሮንን አስተናግዳ ያለምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ከወር በኋላ በሚደረጉት የመልስ ጨዋታዎች ከ4 ዓመት በፊት ደቡብ አፍሪካ ባስተናገደችው 19ኛው ዓለም ዋንጫ አፍሪካን የወከሉት ቡድኖች በብራዚሉ 20ኛው ዓለም ዋንጫ ላይ ውክልናቸውን እንደሚደግሙ ግምት አሳድሯል፡፡

እነሱም አልጀሪያ፣ ካሜሮን፣ አይቬሪኮስት፣ ናይጄሪያና ጋና ናቸው። ከአፍሪካ ባሻገር ባለፈው ሳምንት በመላው ዓለም ከተካሄዱ ሌሎች የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ውድድሮች በኋላ ለ20ኛው የዓለም ዋንጫ ያለፉት ብሔራዊ ቡድኖች ብዛት 18 ደርሷል፡፡ ከ1 ወር በኋላ በቀሩት የ14 ብሔራዊ ቡድን ኮታዎች ተሳትፏቸውን የሚያረጋግጡ ብሄራዊ ቡድኖች ተለይተው ይታወቃሉ፡፡ ከአውሮፓ ዞን ያለፉት 9 አገራት ሆላንድ፣ ጣልያን፣ ቤልጅየም፣ ጀርመን፣ ስዊዘርላንድ፣ ስፔን፣ እንግሊዝ፣ ሩስያ እና ቦስኒያ ሄርዞጐቪና ናቸው፡፡ ለአውሮፓ በሚቀሩት የአራት ቡድኖች ኮታዎች ፖርቱጋል፣ ክሮሽያ፣ ዩክሬን፣ ግሪክ፣ ፈረንሳይ፣ ስዊድን፣ ሮማንያ እና አይስላንድ በጥሎ ማለፍ የመጨረሻ ትንቅንቅ የሚደረግላቸውን የጨዋታ ድልድል በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ ከኤሽያ ዞን ለዓለም ዋንጫው ማለፋቸውን ያረጋገጡት አራት አገራት ጃፓን፣ አውስትራሊያ፣ ኢራንና ደቡብ ኮርያ ናቸው፡፡ በሚቀረው የአንድ ብሔራዊ ቡድን ኮታ ከኤሽያ ዞን የምትወከለው ዮርዳኖስ እና የደቡብ አሜሪካ ተወካይ የሆነችው ኡራጋይ በጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ይገናኛሉ፡፡ ከደቡብ አሜሪካ ዞን አዘጋጇን ብራዚል ጨምሮ አርጀንቲና ፣ ኮሎምቢያ ቺሊና ኢኳዶር ማለፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ከሰሜንና መካከለኛው አሜሪካ ዞን አሜሪካ፣ ኮስታሪካና ሆንዱራስ ማለፋቸውን ሲያረጋግጡ በቀረው የአንድ ብሔራዊ ቡድን ኮታ ከዚሁ ዞን የምትወከለው ሜክሲኮና ከኦሽንያ የምትወከለው ኒውዝላንድ በጥሎ ማለፍ ይተናነቁበታል፡፡

Read 5802 times