Print this page
Saturday, 19 October 2013 12:10

በላይአብ ሞተርስ ለሁሉም ሰው መኪና ለማዳረስ አቅዷል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(43 votes)

መኪና በዱቤ እየሸጠ ነው
መኪኖችን ወደ ውጭ ለመላክና አዳዲስ ሞዴሎች ለማቅረብ አቅዷል
የሚያሰራው ባለ 5 ኮከብ ሆቴል
ዘንድሮ ይመረቃል

ባለሀብቶቹ ሦስት ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ የትራንስፖርትና የኮንስትራክሽን ዘርፉን በተሽከርካሪ አቅርቦት በመደገፍ፣ በሀገሪቱ ልማት የበኩላቸውን ሚና መጫወት ስለፈለጉ፣ በ1996 ዓ.ም በአራት ሚሊዮን ብር በላይአብ ኢንተርፕራይዝ ኃ.የተ.የግ.ማ አቋቋሙ፡፡ የድርጅቱን አወቃቀር በማሻሻል በ100 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ወደ በላይአብ ሞተርስ ኃ.የተ.የግ.ማ አሳደጉት፡፡ በአሁኑ ወቅት የድርጅቱ ጠቅላላ ሀብት 230 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን በ10 ሠራተኞች ጀምሮ አሁን ከ200 በላይ ሠራተኞች እንዳሉት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ ግርማ ይናገራሉ፡፡
የድርጅቱ ዋነኛ ተግባር፣ የተለያዩ የመኪና አካላትን ከውጭ አገር በማምጣት የተለያየ መጠን ያላቸው መኪኖችን መገጣጠም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ፋዋ ቤላ ሴዳን (FAW Vela Seden) የተባለች የቤት አውቶሞቢል፣ የኒሳን ሞተር የተገጠመለት ባለ ሁለት ጋቢናና 3.2 ሲሲ የፈረስ ጉልበት ያለው ፒክ አፕና ኦቲንግ ስቴሽን ዋገን (ሁለቱም የመስክ መኪና) በመገጣጠም በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ እንደሚያቀርብ ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል። በተጨማሪም 16 ሜትር ኩብ የመጫን አቅም ያላቸው ፎቶን ሲኖ ትራክ ገልባጭና ከ15 እስከ 45 ኩንታል መሸከም የሚችሉ የጭነት ተሽከርካሪዎችን እያስመጣ እንደሚሸጥ ተናግረዋል፡፡ “የሥራ ዕድልና የቴክኖሎጂ ሽግግር በመፍጠር፣ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ በማዳን፣ ራዕዩን አሳክቷል” ይላሉ አቶ ፍቃዱ፡፡
በላይአብ ሞተርስ በአሁኑ ወቅት በአዳማ የመኪና መገጣጠሚያ፣ በአቃቂ ዋና መ/ቤትና ሾው ሩም አለው፡፡ በቃሊቲ ደግሞ ድርጅቱ ለሸጣቸውም ሆነ ከውጭ ለሚመጡ መኪኖች ሰርቪስና የጥገና አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የመለዋወጫ ችግርም እንደሌለ የክፍሉ ኃላፊ ይናገራሉ፡፡
ባለሀብቶቹ መኪና ለመገጣጠም እንደወሰኑ በቀጥታ ወደ ሥራ አልገቡም፡፡ ከአዲስ አበባና ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ የምህንድናስና ክፍል መምህራን ጋር በመመካከር መገጣጠም ያለባቸው የመኪና ዓይነቶችን መለየታቸውን የመገጣጠሚያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም ስነ ገልጿል፡፡ የመኪኖቹ ዓይነት ይመረጥ እንጂ ወዲያውኑ የሚያስፈልጉት ዕቃዎች መጥተው አልተገጣጠሙም፡፡ መጀመሪያ የተመረጡትን ዓይነት መኪኖች በማስመጣት ለአየር ንብረቱ፣ ለመልከዓምድሩ፣ … ተስማሚና ምቹ መሆናቸው ከታየ በኋላ ነው መገጣጠሙ የተጀመረው፡፡
“የሚገጣጠሙት መኪኖች አካላት ከቻይና የመጡ ቢሆንም ከጃፓን ጋር በሚሠሩ ኩባንያዎች የሚመረቱ በመሆኑ ጥራታቸው አስተማማኝ ነው። ለምሳሌ የቤት መኪናዎች ዕቃ የሚመጣው ከቲያንጂን ቶዮታ ኩባንያ ሲሆን ፒክአፑን ደግሞ ከኒሳን ጆንጆ ኩባንያ ነው” በማለት አቶ ቢኒያም ስለ መኪናዎቹ ጥራት ገልጿል፡፡
አሁን ግን የመስክ ፒክአፖቹን እንደ ቀድሞው ለመሸጥ ቀላል አልሆነላቸውም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የመንግሥት የሆነው ድርጅት ተመሳሳይ የመስክ መኪና መገጣጠም በመጀመሩ ነው። በፊት የመንግሥት ድርጅቶች የመስክ መኪና ለመግዛት ጨረታ ሲያወጡ፣ እየተጫረቱ ይሸጡ ነበር፡፡ አሁን ግን መንግሥታዊ የሆነው የቢሾፍቱ ኦቶሞቲቭ ኢንተርፕራይዝ ፒክአፖቹን ስለሚሠራ፣ የመንግሥት ድርጅቶች የሚገዙት ከዚያ ነው፡፡ ይህም ገበያቸውን አቀዝቅዞታል፡፡
“የቤት ኦቶሞቢሎቹ ሽያጭ ግን ከጠበቅነው በላይ ነው፡፡ የግለሰቦች የመግዛት አቅም እየተሻሻለ በመሆኑና መኪኖቹ በአንድ ሊትር 18 ኪ.ሜ በመጓዛቸው በኅብረተሰቡ ዘንድ በጣም ተወደዋል። መንግሥት፣ ቤት ለሁሉም ሰው ለማዳረስ እንዳቀው ሁሉ፤ እኛ ደግሞ መኪና ለሁሉም ሰው ለማዳረስ የዱቤ ፕሮግራም አዘጋጅተን ብዙ ሰዎች ተጠቅመዋል፡፡ ሌሎችም በዕድሉ እንዲጠቀሙ በስፋት እየሠራን ነው” ብሏል አቶ ቢኒያም፡፡
የመኪና አካላት ብዙ ናቸው፡፡ ከውጭ አገር መጥተው እዚህ በትክክል መገጣጠማቸውን የሚጠራጠሩ ሰዎች አሉ፡፡ “በኮምፒዩተር በመታገዝ ከፍተኛ የጥራት ቁጥጥር ስለሚደረግ፣ በዚህ በኩል ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ አይግባችሁ፡፡ ለዚህ ደግሞ ከእኛ መኪና ገዝተው እየተጠቀሙ ያሉ ደንበኞቻችን እማኞች ናቸው” ይላሉ ሥራ አስኪያጁ በኩራት፡፡ ለመሆኑ እንዲህ እርግጠኛ ሆኖ ለመናገር ያበቃቸው ምን ይሆን?
“አንድ መኪና ምን ያህል ዕቃዎች እንዳሉት ይታወቃል፡፡ የታዘዙት ዕቃዎች ከአቅራቢው ድርጅት በትክክል መላካቸውን እናረጋግጣለን። በአንድ ጊዜ የሚመጣው የ36 መኪና ዕቃ ነው፡፡ ዕቃዎቹ ትክክለኛ መሆናቸውን፣ የዕቃዎቹን መጠን፣ ቁጥራቸውን፣ ለእያንዳንዱ መኪና ስንት ዕቃ እንደመጣ፣ በትክክል መግባታቸውን በኮምፒዩተር ተፈትሾ ይረጋገጣል፡፡ ከዚያ በኋላ፣ ዕቃዎቹ በሚገጠሙበት መስመር ተደርድረው ይቀመጣሉ። የዚያ መስመር ሠራተኛ ሥራ ከመጀመሩ በፊት፣ ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ ዕቃዎች መኖራቸውን አረጋግጦ ነው ሥራ የሚጀምረው፡፡ እዚህ ላይ ሁለት ዓይነት ቁጥጥር አለ፡፡ አንደኛው የመጣው ዕቃ ጥራት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ዕቃው በትክክል መገጠሙን ይቆጣጠራል፡፡
“አንደኛው ክፍል ገጣጥሞ ከጨረሰ በኋላ በትክክል መግጠሙን ፈትሾና አረጋግጦ ነው ለቀጣዩ ክፍል የሚያስተላልፈው፡፡ ሁለተኛው ክፍልም የመጣለትን ዝም ብሎ አይቀበልም፤ በቀደመው ክፍል መገጠም ያለባቸው ዕቃዎች መኖራቸውን አረጋግጦ ነው የሚረከበው፡፡ እሱም በተራው ለሦስተኛው ክፍል ሥራው በትክክል መጠናቀቁን ፈትሾና አረጋግጦ ያስተላልፋል፡፡ ሦስተኛውም በተራው ሁለቱ ክፍሎች እንዳደረጉት ፈትሾና አጣርቶ ለቀጣዩ ክፍል ያስተላልፋል፡፡ በዚህ ዓይነት የሚሠሩ ሦስት ስቴሽኖች አሉ፡፡ በእያንዳንዱ ስር ደግሞ ሦስት ሦስት ሳብ ስቴሽኖች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ክፍሎች በትክክል መግጠማቸውን አረጋግጠው ካሳለፉ በኋላ የጥራት ቁጥጥር (Quality control) ክፍሉ ፍተሻ ያደርጋል። ስለዚህም ምንም ዓይነት ዕቃ ሳይገጠም አያልፍም፡፡ መዘለል ብቻ ሳይሆን የአገጣጠም ስህተት እንኳ ቢኖር፣ በየክፍሉ እርምት ይደረግበታል፡፡ ስለዚህ ሦስት ጊዜ በክፍሉ፣ ከክፍሉ ሲወጣና በኳሊቲ ኮንትሮል ቁጥጥርና ፍተሻ ይደረጋል፡፡
“የዚህ ዓይነት እጅግ በርካታ (የቀለም፣ የመሪ፣ የፍሬን፣ …) ፍተሻና ቁጥጥር በየክፍሎቹና በኳሊቲ ኮንትሮል ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ፣ መሪው ወደቀኝ ወይም ወደግራ የሚጐትት ከሆነ፣የሚፈተሽበት መሳሪያ እጅግ ዘመናዊ በመሆኑ፣ ስህተት ካለ አያሳልፍም - ቀይ ያበራል፡፡ ስህተቱ ሲስተካከል አረንጓዴ አብርቶ ያሳልፋል፡፡ ይህን ሁሉ ፍተሻና ቁጥጥር ካለፈ በኋላ ወደመጨረሻ ፍተሻ (ሬን ቴስት) ይገባል፡፡ መስተዋቶች፣ በሮች፣ … በትክክል ካልተገጠሙ፣ ውሃና አቧራ ሊያስገቡ ይችላሉ። ስለዚህ፣ መኪናው ከስርም ሆነ ከላይ ኃይለኛ ግፊት ባለው ውሃ ውስጥ ይገባል፡፡ በዚህም ጊዜ ስህተት ከተገኘ እንደገና ወደ ኋላ ተመልሶ ስህተቱ ይታረማል። የመጨረሻ ምርመራ የሚሆነው መኪናውን በከፍተኛ ፍጥነት መሞከር ነው - ጭነት ጭኖና ሳይጭን፡፡ ለምሳሌ አምስት ሰዎች የምትጭነውን ትንሿን መኪና ብንወስድ፣ ሾፌሩ ብቻውን እየነዳ ሲሄድ ምንም ችግር ላይኖር ይችላል፡፡ ከዚያም አራት ሰዎች ጭኖ ይሄዳል። በዚህ ጊዜ የተለያዩ ድምፆች የሚያሰሙ ከሆነ፣ እንደገና ይስተካከላል፡፡ ስለዚህ፣ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻ ድረስ ድርድር የሌለው የኳሊቲ ኮንትሮል ፍተሻና ቁጥጥር ስለሚደረግ የመኪኖቻችን የጥራት ደረጃ ከፍተኛ ነው” በማለት አቶ ቢኒያም አስረድቷል፡፡
በመገጣጠሚያው ውስጥ በአመራር ደረጃ ያሉ ሠራተኞች በኦቶሞቲቭና በኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው፡፡ የተቀሩት ደግሞ ከቴክኒክና ሙያ የተመረቁ ናቸው፡፡ ድርጅቱ ትጉህ ሠራተኞችን ወደ ቻይና ልኮ ያሠለጥናል፤ ከቻይና ባለሙያዎችን አስመጥቶም የሥራ ላይ ሥልጠና ይሰጣል፤ ጥሩ የሥራ ውጤት ያላቸውን ሠራተኞች በኮሚቴ ታይቶ ትምህርታቸውን እንዲያሻሽሉ የገንዘብ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ በሌሎች መገጣጠሚያዎች የሠሩ ልምድ ያላቸው ሠራተኞችም አሉ፡፡
መገጣጠሚያው፣ ግንባታውና የማሽን ተከላው ተጠናቆ ሥራ የጀመረው በመስከረም 2003 ዓ.ም ነው፡፡ በመገጣጠሚያው ውስጥ ብቻ የሚሠሩ 65 ሠራተኞች ሲኖሩ፣ የሕክምናና የትራንስፖርት አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ ያኔ ካፒታሉ 60 ሚሊዮን ብር እንደነበር አቶ ቢኒያም ገልጿል፡፡
የከባድ መኪና መገጣጠሚያ መስመር የተጠናቀቀ ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶች ግን መገጣጠም አልጀመረም፡፡ ምን ዓይነት ተሽከርካሪ እንገጣጥም? ስንት ሰው የመጫን አቅም ያለው (28 ሰው፣ 48 ሰው፣ 65 ሰው፣ …) አውቶቡስ እንሥራ በማለት እያጠኑ ነው፡፡
ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ፍቃዱም ሆኑ አቶ ቢኒያም፣ ጉምሩክ የሚያስከፍላቸው ቀረጥ ከፍተኛ በመሆኑ የሚያበረታታ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ አቶ ቢኒያም የቀረጥ ማበረታቻው አነስተኛ ነው ይላል። “ማንኛውም መኪና አስመጪ ከሚከፍለው ያላነሰ ነው የምንጠየቀው፡፡ እኛ እዚህ ለዜጐች የሥራ ዕድል ፈጥረን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር አምጥተን፣ እሴት ጨምረን መሸጣችን፣ ምንም አልታሰበም፡፡ መርካቶ ሱቅ ተከራይቶ መኪና እያመጣ ከሚሸጠው እኩል ነው የምንቀረጠው፡፡ ይህ አሠራር ተወዳዳሪ ሆኖ መቀጠል ስለማያስችለን የቀረጥ አስተያየት እንዲደረግልን ጥያቄ አቅርበን እየተጠባበቅን ነው” ብሏል፡፡
በጉምሩክ አካባቢ እስካሁን ምንም ችግር አልገጠመንም ነበር ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ በቅርቡ በወጡ አዋጆች ላይ የአተረጓጐምና የአፈጻጸም (ደብል ታክሴሽን) ችግር መኖሩን ገልፀዋል፡፡
“ይኼ አሠራር ችግር አለው ብለን አመልክተናል፤ በጐ ምላሽም እንደምናገኝ እንጠብቃለን፡፡ ነገር ግን አሠራሩ አይሻሻልም፤ ይኸው ነው ከተባለ፣ መኪና አገር ውስጥ ከመገጣጠም ይልቅ ከውጭ አምጥቶ የሚከፈለው ታክስ ይመረጣል፡፡ ደብል ታክሴሽን የሚፀና ከሆነ፣ በፊት የሚከፈለውን እጥፍ ያደርገዋል፡፡ ይህ ደግሞ ኢንዱስትሪውንም ይገድላል” ብለዋል፡፡ ሌላው አቶ ፍቃዱ ያነሱት ችግር፣ ከፋይናንስ ተቋማት በሚፈለገው መጠን የገንዘብ ብድር ከማግኘት ነው፡፡
በላይአብ ሞተርስ፣ በቀን 18 መኪና የመገጣጠም አቅም አለው፡፡ አሁን ግን በሙሉ አቅሙ ማምረት ደረጃ አልደረሰም፡፡ የመስክ ፒክአፑን ለመገጣጠም 2፡30፣ የቤት መኪናዋን ለመገጣጠም ደግሞ 2፡00 ይወስድበታል፡፡ መኪኖቹን የሚገጣጥሙት መጋዘን ባለ ዕቃ ስለሆነ ብዙ ጊዜ ሽያጩ እጅ በእጅ ነው። ገዢው ክፍያውን ሲፈጽም ወዲያውኑ መኪናውን ይረከባል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሽያጭ በርክቶ ከመጋዘን ዕቃ ሲያልቅና የታዘዘው እስኪመጣ ድረስ ብቻ ቀጠሮ እንደሚሰጡና ቅድምያ ክፍያ እንደማይጠይቁ አቶ ቢኒያም ተናግሯል፡፡
“ብዙ ጊዜ ገንዘብ ተቀብለን ቀጠሮ አንሰጥም። በዚህም ደንበኞች ይመርጡናል፡፡ ሌላው ጥሩ ነገር ደግሞ 6ሺህ የቀለም ዓይነት መያዛችን ነው፡፡ ሰዎች የተለያየ የቀለም ምርጫ ስላላቸው፣ መኪናው ቀለም ከመቀባቱ በፊት፣ ደንበኞች የፈለጉትን የቀለም ዓይነት እንዲመርጡ ዕድል እንሰጣቸዋለን። ድርጅቱ ከሚቀባቸው አምስት ቀለሞች ውጭ ደንበኛው የመረጠውን፣ ለመቀባት የአንድ ሳምንት ቀጠሮ እንሰጣለን፡፡ ይህም ተመራጭ አድርጐናል” በማለት አብራርቷል፡፡
ድርጅቱ፤ ከቀረጥ ነፃ መኪና እንዲያስገቡ ለተፈቀደላቸው ድርጅቶችም አገልግሎት ይሰጣል። “እኛ የመኪና አካላትን የምናስገባው ቀረጥ ከፍለን ነው፡፡ ከቀረጥ ነፃ ፈቃድ ያላቸው ድርጅቶች፣ የመኪኖቹ አካላት አገር ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ማዘዝ አለባቸው፡፡ እኛም ፈቃዱን አሳይተን ‘እነዚህን መኪኖች የምናስገባው ከቀረጥ ነፃ ነው’ ብለን ቀረጡን ማስቀረት እንችላለን” ብሏል አቶ ቢኒያም፡፡
ከበላይአብ ሞተርስ በፊት መኪና መገጣጠምና ሪልእስቴት የጀመሩ ድርጅቶች የገቡትን ቃል ሳያከብሩ ከአገር በመውጣታቸው መኪና ለመግዛትና ቤት ለማሠራት ገንዘብ የከፈሉ ሰዎች ችግር ውስጥ ወድቀዋል፡፡ በዚህ ድርጅት አስቀድሞ ገንዘብ መክፈል ባይኖርም፣ አንዳንድ ሰዎች “መኪና ገዝቻቸው ካገር ቢጠፉ መለዋወጫ አላገኝም” የሚል ስጋት ሊያድርበት ይችላል፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ችግር ምን ምላሽ ይኖራቸው ይሆን?
“የመለዋወጫ ችግር እንዳለ ጥናት አድርገን ስለነበር፣ መኪኖችን ከመገጣጠማችን በፊት የተለያዩ የመኪና አካላትና መለዋወጫቸውን አንድ ላይ ስላዘዝን ከእኛ መኪና የገዙ ደንበኞች አንዳችም ችግር አልገጠማቸውም፡፡ ለምንሸጣቸው መኪኖች የሁለት ዓመት ወይም የ40 ሺህ ኪ.ሜ ዋስትና እንሰጣለን፡፡ ኅብረተሰቡ በዚህ ዘርፍ በተፈጠረው ችግር የተነሳ፣ በተለያዩ ጊዜያት ስጋታቸውን ሲገልጹ ሰምተናል፡፡ ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ድርጅት ያለው አቅም ምንድነው ብሎ መገምገም ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ኢንቨስትመንት ሌላ ምን አለው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም አንድ ኢንቨስትመንት ብቻ ከሆነ ዘግቶ ሊሄድ ይችላልና ነው፡፡
“በላይአብ ሞተርስ ከእርሻ እስከ ማኒፋክቸሪንግና ሆቴል ኢንዱስትሪ የተሠማራ ድርጅት ነው፡፡ በላይአብ አንድ ነገር ሠርቶ አላቆመም፤ በማስፋፋት ላይ ነው ያለው፡፡ ከዚህ ፋብሪካ ጐን በ50ሺህ ካሜ ቦታ ላይ ትልቅ የኬብል ማኑፋክቸሪንግ እየሰራ ነው፡፡ ቦሌ አካባቢ ባለ 5 ኮከብ ሆቴል እየተገነባ ሲሆን በዚህ ዓመት ይመረቃል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ ፓዌ ላይ የእርሻ ልማት፣ በአዳማ ደግሞ የዶሮ እርባታ አለው፡፡ ኒኮን የተባለ የኮንስትራክሽን ድርጅትም ከፍተናል፡፡ ሌሎች ሊሠሩ የታቀዱና በጥናት ላይ የሚገኙም ፕሮጀክቶችም አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ የበላይአብን አቅምና ለአገር ልማት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ያሳያሉ፡፡ መኪኖቻችንን ለሰው በዱቤ ስንሰጥ የእኛ ገንዘብ ሰው ጋ አለ እንጂ እኛ ጋ የሰው ገንዘብ የለብንም፡፡ ገንዘባችንን በትነን የት ነው የምንሄደው? ስለዚህ በላይአብ እምነት የሚጥሉበት እንጂ አገር ጥሎ በመጥፋት የሚጠረጠር ድርጅት አይደለም” በማለት አቶ ቢኒያም ድርጅቱ ያለበትን ደረጃ አብራርቷል፡፡
አቶ መስፍን ብዙነህ፣ የድህረ ሽያጭ ጥገና አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ቃሊቲ በሚገኘው የተንጣለለ የድርጅቱ ዎርክሾፕ በዋነኛነት የሚሰጠው አገልግሎት ድርጅቱ ለሸጣቸው ተሽከርካሪዎች ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ ድርጅቱ ለመጣ ማንኛውም ተሽከርካሪ የጥገናና የሰርቪስ አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡
የመለዋወጫ ግብይት፣ የመጫንና የማውረድ አገልግሎት እንደሚሰጡም አቶ መስፍን ገልፀዋል። ከሚገጣጥሟቸው መኪኖች በተጨማሪ፣ ፉቶን ዳምትራክ፣ ፉቶን ፒክአፕ በብቸኝነት የሚያስመጣው በላይአብ ነው፡፡ ሲኖ ዳም ትራክም፣ ያስመጣሉ፡፡ ከከባድ መሳሪያ ደግሞ ሎደርና ግሬደር በኮንቴይነር አስመጥተው በወርክሾፑ ይገጣጥማሉ፣ የሰርቪስና የጥገና አገልግሎት እንደሚሠጡም ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
የበላይአብ የወደፊት ዕቅድ የሚገጣጥማቸውን መኪኖች ለምሥራቅ አፍሪካ ገበያ በማቅረብ ለአገሩ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ነው፡፡ “ይህን ለማድረግ ኅብረተሰቡና ደንበኞቻችን በሚገባ ሊያውቁን ይገባል፡፡ በአንድ ወይም በጥቂት ድርጅቶች የተፈጠረ ጥፋት፣ በሁሉም ድርጅቶች ይፈጠራል ብሎ ማሰብ አይገባም፡፡ ሌላው ደግሞ ሰዎች አመለካከታቸውን መለወጥ አለባቸው፡፡
“የሚያወዳድሩትን ነገር ወይም ድርጅት በትክክለኛ መመዘኛ ማወዳደር አለባቸው፡፡ አንድም ኪ.ሜ ያልተነዳ፣ ጌጁ (ኪ.ሜ ቆጣሪው) ዜሮ ላይ ያለ አዲስ መኪናና ከ25 ዓመት በፊት ተመርቶ በየበረሃው ጨው የበላውን መኪና ከመግዛት በፊት ቆም ብሎ በማሰብ እውነታውን መረዳት ያስፈልጋል። እውነቱን ሳይለዩ በአሉባልታ መመራት በጣም መጥፎ ባህርይ ነው፡፡
ነገሮችን የማጥላላት ባህርይ ያለው ሰው “መጥፎ ነው” ያለውን ከመቀበል፣ የእኛን መኪኖች የገዙ ሰዎችን በማነጋገር ስለመኪኖቹ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ይበጃል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ገበያው ሁሉ በአሉባልታ የተሞላ ይሆናል፡፡ ችግሮች እንኳ ቢኖሩ ከአገር አኳያ ማየትና ችግሩን በመነጋገር መፍታት ነው የሚሻለው። ድርጅቱ ዛሬ ባያተርፍ ለመጪው ትውልድ መነሻ ትተን ነው የምናልፈው፡፡ ከዚህ አንፃር ነው መታየት ያለበት” በማለት የመገጣጠሚያው ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም መልዕክት አስተላልፏል፡፡
የበላይአብ ሞተርስ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ ግርማ ደግሞ በቀጣዩ ዓመት የሥራ አድማሳቸውን በማስፋት የሚገጣጥሟቸውን ተሽከርካሪዎች ወደጐረቤት አገሮች ለመላክ፣ በሀገር ውስጥም፣ አካባቢን የማይበክሉ አዳዲስ ሞዴል ተሽከርካሪዎችን ለማቅረብ ማቀዳቸውን ገልፀዋል፡፡

Read 19166 times