Saturday, 19 October 2013 12:05

ህፃናትን በተቅማጥ ከመሞት የሚታደግ አዲስ ምርት ገበያ ላይ ዋለ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(2 votes)

ህፃናት በተቅማጥ በሽታ ሲጠቁ በአፋጣኝ የሰውነታቸውን ፈሳሽ በመተካት ከሞት የሚታደጋቸውና አቅማቸው እንዲመለስ የሚያደርገው የኦ.አር.ኤስ እና ዚንክ ውህድ የሆነ “ለምለም ፕላስ” የተሰኘ አዲስ ምርት ገበያ ላይ ዋለ፡፡
በዲኬቲ ኢትዮጵያ ተዘጋጅቶ ለገበያ የቀረበው አዲስ ምርት፤ ህፃናት በተቅማጥ በሽታ በሚጠቁበት ጊዜ ከሰውነታቸው የሚወጣውን ፈሳሽ ከመተካትና አቅማቸውን ከመመለስ ባሻገር በተከታዮቹ ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ በተቅማጥ በሽታ የመያዝ ዕድላቸውን የሚያስወግድና የሚከላከል መሆኑ ተጠቁሟል። ከዚህ በተጨማሪም ውህዱ ህፃናቱ በተቅማጥ በሽታ ቶሎ ቶሎ እንዳይያዙ የሚያደርግ አቅም እንደሚገነባላቸውም ተገልጿል፡፡
ምርቱ የተዘጋጀው ዲኬቲ ኢትዮጵያ በማይክሮ ኒውትሬት ኢንሺየቲቭ በኩል በአለማቀፍ የካናዳ መንግስት የልማት ትብብር በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ሲሆን በአገር ውስጥ እየተመረተ አገልግሎት ላይ እንደሚውልም ተገልጿል፡፡ ስርጭቱ የሚከናወነው በዲኬቲ ኢትዮጵያ ሲሆን በመንግስትና የግል ተቋማትና የመድሃኒት መሸጫ መደብሮች ውስጥ በማከፋፈል ለህብረተሰቡ እንዲዳረስ እንደሚደረግ ከትላንት በስቲያ በሂልተን ሆቴል በተካሄደ የምርት ማስተዋወቂያ ስነስርዓት ላይ ተገልጿል፡፡

Read 2417 times