Saturday, 19 October 2013 11:46

የ“ጋ” እና የ“ጋር” ልዩነት!

Written by  ተስፋዬ ድረሴ
Rate this item
(2 votes)

   “ጋ” ቦታን፣ አካባቢን፣ መድረሻን (አቅጣጫን)እና አድራሻን አመልካች ቃል ነው፡፡ “እዚህ ጋ…” ማለት እዚህ ቦታ ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው “ሰዓቴ የወደቀው እዚህ ጋ ነው” ካለ “እዚህ የምታዩት ቦታ፤ መሬት ወይም የሆነ ቁሳቁስ ላይ ነው” ማለቱ ነው። ጋዜጠኞች “እዚህ ጋ አንድ ጉዳይ እናንሳ” ሲሉ አሁን እያነበብን ወይም እየተናገርን የደረስንበት “ቦታ” (ቆም ብለን) ማለታቸው ነው፡፡ “አደባባዩ ጋ…” እንገናኝ ያለን ሰው የምንገናኝበትን አካባቢ ወይም ቦታ እየጠቆመን ነው፡፡ “ወንድሜ ጋ መሄዴ ነው” ያለችን ሴት የምትጓዝበትን አቅጣጫ ወይም መድረሻዋን እየነገረችን ነው፡፡ እስከ አስር ሰዓት ድረስ “ወንድሜ ጋ እቆያለሁ” ካለችን እስከዚያን ሰዓት ድረስ መገኛ አድራሻዬ እዚያው ወንድሜ ዘንድ (ጋ) ነው ማለቷ ይሆናል፡፡ ወንድሟን ልታገኘው ወይም ላታገኘው ትችላለች፡፡
“ጋር” አብሮ መሆንን፣ አብሮ መገኘትን የሚገልጽ ቃል ነው፡፡ “ጋር” ብቻውን አይቆምም፤ “ከ”ን አስቀድሞ “ከ…ጋር” ሲሆን ነው ትክክል የሚሆነው፡፡ “ጋር” ቦታን፣ አካባቢን፣ አቅጣጫን፣ መድረሻን እና አድራሻን አያመለክትም፡፡
“እዚህ ጋር አንድ ነጥብ እናንሳ…” ያለ ጋዜጠኛ የሰራው ዓረፍተ ነገር ብላሽ ነው፡፡ ትርጉምም አይሰጥም፡፡ ጋዜጠኛው “አሁን የደረስንበት ቦታ ላይ ሆነን” ለማለት ፈልጐ ከሆነ መጠቀም ያለበት “ጋ”ን እንጂ “ጋር”ን አይደለም፡፡ ሃሳቡ ተያያዥነት ያለውን ወይም አብሮ የሚሄድን ሌላ ጉዳይ ማንሳት ከሆነ ደሞ መጠቀም ያለበት “ጋር”ን ነው ለዚያውም “ከዚህ…ጋር”ን፡፡
“ጋ” እና “ጋር”ን ማምታታት ጉልህ የትርጉም ስህተት ያመጣል፡፡ አንድ እናት ለልጃቸው ስልክ ደውለው “የት ነሽ?” ሲሏት “ወንድሜ ጋ ነኝ” ብላ ብትመለስ “አሁን የምገኘው የወንድሜ ቤት ውስጥ ነው፣” አሊያም “ያረፍኩት ወንድሜ ዘንድ ነው” ማለቷ ነው፡፡ በአጭሩ “ወንድሜ ጋ” ብላ ከመለሰችም “ወደ ወንድሜ ዘንድ በመሄድ ላይ ነኝ” ማለቷ ሊሆን ይችላል፡፡ “ከወንድሜ ጋር ነኝ” ካለች ግን እናቷን በምታነጋግርበት ወቅት ወንድሟ ከአጠገቧ አለ ማለት ነው፡፡
ብዙ ወጣት የሬዲዮ ጋዜጠኞች በ”ጋ” እና “ጋር” መካከል የትርጉም ልዩነት መኖሩን የሚያውቁ አይመስለኝም፡፡ እንደ መሰላቸው ነው የሚጠቀሙባቸው፡፡ “…አርቲስት እገሌ ጋር በተደጋጋሚ ስልክ ደውለን አልተሳካልንም” ሲሉ ሰምተን ሊሆን ይችላል፡፡ ለማለት ያሰቡት “አርቲስት እገሌ ጋ” ነው እንጂ “አርቲስት እገሌ ጋር ” አይደለም፡፡ አርቲስት እገሌ ጋር ሆነን ደወልን ማለት ከአርቲስቱ ጋር አብረን ሆነን ደወልን ማለት ነው እንጂ ወደ አርቲስቱ ደወልን ማለት አይደለምና፡፡
በሁለቱ ቃላት ዙሪያ ያለው መደበላለቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደመጣ ታዝቤያለሁ። የሬዲዮ ጋዜጠኞች ቀደም ሲል እንዳልኩት በተለይም ወጣቶቹ ጋ ችግር አለ፡፡ ጋዜጠኞቹ በዚህ ጉዳይ ላይ ከኤዲተሮቻቸው ጋር መነጋገር ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ኤዲተሮቻቸውም ቢሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጐች ጋ የሚደርሱ ዓረፍተ ነገሮች ሲበላሹ ዝም ባይሉ ጥሩ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዤ ላንሳና በቅርቡ የታተመ አንድ የግጥም መጽሐፍ ላይ ገጣሚው የአንደኛውን ስንኝ መጨረሻ ቃል በስህተት “ጋር” አድርጐ አንብቤያለሁ፡፡ ለማለት የፈለገው “ጋ” ወይም ዘንድ ነበር፡፡ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ በመስክ ስራ ላይ ከኔ ጋር እየሰራ የሚገኝ አንድ ወጣት የሁለቱን ፊደሎች ጉዳይ ለአዲስ አድማስ አንባቢዎች ላቀርብ ነው ስለው ለምን እኔን ምሳሌ አታደርገኝም? ይሄውኮ ልዩነታቸው ሳይገባኝ አንድ ሳምንት አለፈኝ” አለኝ፡፡
ለጨዋታ ያህል ይህንን ያህል ካልኩ ይበቃል። ከየወዳጆቻችሁ ጋር ተነጋገሩበት፡፡ እኔም ስጽፍ ተሳስቼ ከሆነ ስህተቴ የቱ ጋ እንደሆነ ጠቁሙኝ። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ ጋር ያደረገችው የእግር ኳስ ጨዋታ እንዴት ነበር? አስደሳች ነበር አይደል፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ጋ ችግር ያለ አልመሰለኝም፡፡ አንዳንድ ተጫዋቾች ጋ ግን አለ፡፡ ብልጠት ይጐድላቸዋል፡፡ ያንን ፈጣን ቅብብላቸውን ተጠቅመው የባላጋራ ቡድን የፍፁም ቅጣት ክልል ጋ መጠጋትና መውደቅ ሲገባቸው…በደህና ሰንብቱ!

Read 2165 times