Saturday, 19 October 2013 11:40

ለወጣቶች ስደት ተጠያቂዎቹ ወላጆች ናቸው!

Written by  ተስፋዬ ድረሴ
Rate this item
(1 Vote)

         ለበርካታ ወገኖቻችን ወደ አረብ አገሮች መሰደድ ዋናዎቹ ምክንያቶች ደላሎች አይደሉም። እውነቱ ይፈንዳ፤ የችግሩ ምንጮች ወላጆች ናቸው፡፡ ልጆቻቸው በጥሬ ፣በጥብስ፣በቅቅል መልክ ቢቀርቡላቸው እጃቸውን ታጥበው ለመብላት የማያቅማሙ “ሆዳም” ወላጆች! ይህ ሚስጥር ተፍረጥርጦ ካልወጣ በስተቀር ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች በስደት ማለቃቸው የሚቆም አይመስለኝም፡፡
ስሜቴን ወረቀት ላይ ለማስፈር ከአልጋዬ ላይ ከመነሳቴ በፊት ስደት ነክ ሰቆቃን አስመልክቶ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላይ ሲደረግ የሰማሁት አሳሳች ትንተና አሳዝኖኝ፣ ብርድልብሴን ተሸፋፍኜ ለመተኛት ሞክሬ ነበር፡፡ ግን እንዴት ብዬ! ውስጤ ተቃጠለ፣ተቀጣጠለ፡፡
ለምን ነደድክ? በሉኝ፡፡ ከዛሬ አራት አምስት አመት በፊት ጀምሮ የስደት ችግር የሚሳበበው፣የሚላከከው በደላሎች ላይ ነው፡፡ ደላሎች ግን (ህገወጦችን ነው ያልኩት) ቢበዛ የሌባ ተቀባይ እንጂ ዋናዎቹ ሌቦች አይደሉም፡፡ የጥቆማ ስህተት ያለበት የወንጀል ምርመራን ይመስላል አካሄዱ፡፡ ወላጆች ደላሎችን ያማርራሉ፤ የችግሩ ሰለባ የሆኑት ዜጎችም እንዲሁ። የማህበራዊ ጉዳይ ባለሙያዎች፣ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ መስሪያቤቶች፣የመንግስት ባለስልጣናት፣የኪነጥበብ ባለሙያዎች ወዘተ… ወላጆች ከዚህ አስከፊ ችግር በስተጀርባ ደፈጣ ይዘው መቀመጣቸውን አይደፍሩም፡፡ ይሄ እያሳዘነኝ መሰለኝ የምነደው፡፡
አንድ አስቀያሚ ታሪክ ልንገራችሁና የተነሳሁበትን ነጥብ ላብራራ፡፡ ቦታው እንትን ክልል፣እንትን ዞን፣እንትን ወረዳ፣እንትን ቀበሌ፣እንትን መንደር ነው፡፡ ማንም እራሱን ለመከላከል እንዳይሞክር ብዬ ነው ስም ሳልጠቅስ የማወራላችሁ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ከአንድ አመት በፊት ጎረቤታም ወላጆች የሚከፈለውን ገንዘብ ከፍለው ልጆቻቸውን ወደ አረብ አገር ይልካሉ፡፡ ልጆቻቸው ላይ ኢንቨስት አደረጉ፣ ወይም ደሞ ልጆቻቸውን ለባርነት አሳልፈው ሰጡ ብለን ለማሰብ እንችላለን፡፡ አንደኛዋ ልጅ ብዙ ሳትቆይ አትራፊ ሆነችና ለወላጆችዋ ጠቀም ያለ ገንዘብ ላከች፡፡ በዚያ ገንዘብ ወላጆቿ ቤታቸውን አሳመሩ፤ ጥሩ ጥሩ ለባበሱ፤ አልፈው ተርፈው ጠመንጃ ገዙ፣ ወደ አደባባይም ኮራ ብለው መውጣት ጀመሩ (እነዚህ ወላጆች ጥገኞች ! በልጅ ላብ ያለፈላቸው ሰነፎች! መሆናቸውን የሚያውቅ ያውቃል)፡፡ ጓደኛዋ ግን አክሳሪ ሆነች፤ ልጃቸው ምንም ገንዘብ ስላልላከችላቸው እፍረት (የበታችነት) የተሰማቸው ወላጆች (ወይ በልጅ መወዳደር!) “ምነው ልጄ ጨከንሽ? አዋረድሽን? አብራሽ የሄደችው እኩያሽ ወላጆችዋን ስታኮራ አንቺ ምን ሆነሽ ነው ድምጥሽን ያጠፋሽው?” ብለው መልዕክት ይልኩላታል (እስቲ አስቡት… ይሄ ነገር ፈጣጣነት ፣ይሉኝታ-ቢስነት አይደለም ትላላችሁ?) ልጃቸው በምላሹ የጠና ችግር ላይ መሆንዋን ትነግራቸዋለች፡፡ እየደረሰባት ያለውን የጥቃት አይነት ተንትናም ችግሯ በቀላሉ እንደማይፈታ ታረዳቸዋለች፡፡ “ሆዳምና” ይሉኝታ ቢስ ወላጆችዋ ግን የልጃቸውን ችግር ከምንም ሳይቆጥሩ “የፈለገው ችግር የኖረስ እንደሆን ከጓደኛሽ በምን ታንሺያለሽ”? ብለው ቁጣ አዘል መልዕክት ይልኩላታል፡፡ ያቺ መከረኛ ልጅ አሁንም መልስ መስጠት ነበረባት፡፡ “የምትሏት ልጅኮ ገንዘብ የምታገኘው ዝሙት አዳሪ ሆና ነው” በማለት ሳትወድ የግዷን የጓደኛዋን ሚስጥር ገልፃ ትነግራቸዋለች። ለልጃቸው ሳይሆን ለራሳቸው ክብርና ዝና ያሰፈሰፉት ወላጆች፤ “አንቺስ እንደሷ ሴት አይደለሽ? እሷ ያላት ነገር አንቺም አለሽ አይደለም እንዴ ታዲያ! ለምን እንደሷ አትሆኝም” ብለው ምላሽ ላኩላት፡፡ ይሄን ምን እንደምትሉት አላውቅም፡፡ እነዚህ ሰዎች ልጃቸው እጅና እግሯን ቆርጣ እየሸጠችም ቢሆን ገንዘብ ብትልክላቸው አይናቸውን በጨው አጥበው መቀበላቸው አይቀርም፡፡ ከዚያስ? ከዚያ ፀአዳ ነጠላና ጋቢ ለብሰው አደባባይ ይወጣሉ፡፡ ልጅት ሞተች ቢባልም አይከስሩም፤ ተቀምጠው (እድር ካላቸው) የእድር ብር ይበላሉ፡፡
አንባቢያን ሆይ፤ አሁን እየተናደድኩ ነው። የምናደደውም ልጆቻቸውን “እየተመገቡ”፣ ልጆቻቸውን እየለበሱ፣ ልጆቻቸውን ቤት፣ ልጆቻቸውን ጠመንጃ አድርገው ለመኖር በሚፈልጉ ሰነፍ፣ጥገኛ እና ሆዳም ወላጆች ነው፡፡ ለክፋቱ ደግሞ ብዛታቸው በመቶዎች ሳይሆን በብዙ ሺህዎች የሚቆጠር ነው፡፡ እንደታዘብኩት ከተሰዳጆች ብዛት የተነሳ ከሽማግሌና አሮጊት ወይም ትናንሽ ህፃናት በስተቀር ከቁጥር የሚገቡ ወጣቶች የሌለባቸው ወይም አልፎ አልፎ ብቻ የሚታይባቸው ወረዳዎች (መንደሮች) እየተፈጠሩ ነው፡፡ እዚህ ላይ አስተውሉ፤ ወጣቶች ከሌሎች መንደሮች ይሞታሉ።
እስቲ አሁን ደግሞ ፊታችንን ወደ ስደት ሰለባዎቹ እናዙር፡፡ የስደት ሰቆቃ ሰለባ የሆኑ ህፃናትና ወጣቶች ለስደት ምን እንዳነሳሳቸው ሲጠየቁ፤ የአብዛኞቹ መልስ “ወላጆቼን ለመርዳት፣ቤተሰቤን ለመደገፍ” የሚል ነው፡፡ እነዚህ ዜጎች በአንደኛ ደረጃ የሚኖሩት ለራሳቸው ሳይሆን ለወላጆቻቸው ነው ማለት ነው፡፡ አያሳዝንም? ይህ የሚያሳየን የተሰዳጆቹ ወላጆች ራሳቸውን ያልቻሉ ደካሞችና ድሆች መሆናቸውን ነው፡፡
ለመሆኑ ወላጆቻቸው ለምን ድሆች ሆኑ? ለወላጆች ድህነት ወይም ለድህነታቸው መባባስ አንደኛው ምናልባትም ዋነኛው ምክንያት ከአቅማቸው በላይ (ብዙ) ልጆችን መውለዳቸው ነው፡፡ እዚህ ጋ የድህነትን አዙሪት ተመልከቱልኝማ። ድሃ ወላጆች ድሃ (በኑሮ የሚጎሳቆሉ) ልጆችን ይወልዳሉ፡፡ የወላጆቻቸውን ድህነት በቅርበት እያዩ የሚያድጉ ልጆች ለወላጆቻቸው ያዝናሉ፤የባለ እዳነት ስሜትም ይሰማቸዋል፡፡ እናም ገና ራሳቸውን ሳይችሉ ወላጆቻቸውን ከድህነት ለማውጣት ሲሉ ከትምህርት ገበታ ርቀው ጊዜያዊ የገንዘብ ምንጭ መፈለግ ይጀምራሉ፡፡ ልጆቹ ወላጆቻቸውን ለመርዳት በሚያደርጉት ሂደት ተመልሰው ድህነት ውስጥ ሊዘፈቁ ይችላሉ፡፡
አንዳንዴማ እንዲህም ሊሆን ይችላል፡፡ ልጆች በረሃ ለበረሀ እየተሰደዱ፣ በባርነት ውስጥ ሆነው ለወላጆቻቸው ገንዘብ ይልካሉ፡፡ የልጅ ስፖንሰር ያገኙት ወላጆች ተጣጥረው ከችግር ለመውጣት በመፍጨርጨር ፈንታ ተጨማሪ ልጆችን ይወልዳሉ፡፡ አለመማር በሚያመጣው የአስተሳሰብ ችግር የተነሳ፣ ሴት ሴቶቹን ገና በአስራ ሁለትና አስራ ሶስት አመት እድሜያቸው ከት/ቤት ጎትተው አውጥተው ይድሯቸዋል፡፡ ይህንን የሚያደርጉት ከልጆቹ ይልቅ ለራሳቸው እያሰቡ ነው፡፡ ትላልቅ ልጆች በኑሮ እሳት እየተቃጠሉ በሚልኩት ገንዘብ ከስር ከስር እየወለዱ ያሳድጋሉ፡፡ በዚህ መሃል ወላጆች ራሳቸውን ከሃላፊነት ገለል ያደርጋሉ፡፡ ጎበዝ ባህላችን መፈተሽ አለበት!
ብዙ ወላጆች እንደ ወላጅ ከሚጠበቅባቸው ሃላፊነቶች ውስጥ ሩቡን እንኳን ሳያሟሉ ነው “እናት” እና “አባት” ተብለው የሚጠሩት። ልጅን በቂና የተመጣጠነ ምግብ ሳያበሉ፣ በቂ የጨዋታና የመዝናኛ እንዲሁም የዕረፍት እድል ሳይሰጡ፣ ንፅህናና ጤና ሳይጠብቁ፣ የትምህርት መሳሪያ አሟልተው ሳያስተምሩ እንዲሁ በጭፍን ወልደው፣ በጭፍን ነው የሚያሳድጉት፡፡ (የማሳደግ ከተባለ) ሰዎች ለመውለድ ከመወሰናቸው በፊት ያለባቸውን ሃላፊነት ልክ የሚያሳይ ዝርዝር የሚፈርሙ ቢሆን ኖሮ እንዴት ጥሩ ነበር፡፡
በዓለም ላይ እንደ ኢትዮጵያ ህፃናትና ወጣቶች አድገው ሳይጨርሱ ወላጆቻቸውን ለመጦር የሚተጉ (የሚያልሙ) ዜጎች መኖራቸውን እጠራጠራለሁ፡፡ ከፍ ብለው ወደ ስደት ከሚያቀኑት ሌላ በመኖሪያ አካባቢያቸው ጎዳና ላይ ሰርተው ወላጆቻቸውን ለመደገፍ የሚተጉ ብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያን ህፃናት አሉ፡፡ ወላጆቻቸውም ቢሆኑ እነዚህን ልጆች ለመሸጥ፣ ለማከራየት (በቤት ሰራተኝነት በሞግዚትነት፣ በገበሬነት፣ ወዘተ ከማሰማራት) ወደ ኋላ አይሉም፡፡
በርካታ ወላጆች የልጃቸውን ህይወት አስይዘው (መድበው ልበል በቁማርተኞች ቋንቋ) ቁማር ይጫወታሉ፡፡ አንድ ቁማርተኛ ቁማር የሚጫወተው ትርፍ ለማግኘት (ለመብላት) ቢሆንም ሊከስር (ሊበላ) እንደሚችልም ያውቃል፡፡ ቁማርተኛ ወላጆችም ልጆቻቸውን (አስይዘው/መድበው ሲቆምሩ) ወይም ወደ አረብ አገር ሲልኩ ልጆቻቸው ሊሞቱ እንደሚችሉ ያውቃሉ፡፡ ሆኖም የሚጠፋው የነሱ ሳይሆን የምስኪን ልጆቻቸው ህይወት መሆኑን ስለሚያውቁ “ልጄ ይሞትብኛል” ብለው ከመስጋት ይልቅ ልጄ በረሃውን አቋርጦ፣ከውሃ ጥም፣ ከጊንጥ ወዘተ ተርፎ ገንዘብ ይልክልኛል ብለው ያስባሉ። ቁማርተኛ ለምሳሌ ካርታ ተጫዋች የአሁኑን ባሸንፍ (ብዘጋ)፣ ከዚያ ደግሞ የሚቀጥሉትን ሁለት ጨዋታዎችም በተከታታይ ባሸንፍ ብሬን ላስመልስ እችላለሁ ወይም ብዙ ብር ልበላ እችላለሁ ብሎ ተስፋ እያደረገ እንደሚጫወተው ሁሉ፣ ጨካኝ ወላጆችም ልጆቻቸው ቁጥር ስፍር በሌለው አደጋ ውስጥ አልፈው የገንዘብ ምንጭእንዲሆኑላቸው ተስፋ ያደርጋሉ (ይቆምራሉ)፡፡
በነገራችን ላይ ሴት ልጆቻቸውን በህፃንነታቸው የሚድሩ ወላጆችም ያው ቁማርተኞች ናቸው፡፡ ሴት ልጅን ያለ እድሜዋ መዳር ያለውን ጣጣ በከፊል ያውቁታል፡፡ ለምሳሌ ለፊስቱላ፣ ለማህፀን ካንሰር፣ ለኤችአይቪ ኤድስ ወዘተ መጋለጥ አለ፤ በምጥ መሞትም አለ፡፡ ራስ ወዳድ ወላጆች ግን የሚያስቡት የራሳቸውን ጥቅም ብቻ በመሆኑ “በልጅ አመካኝቶ ይበላል አንጉቶ” እንዲሉ ከወግና ባህል ጀርባ ተደብቀው ለልጆቻቸው ያሰቡ በመምሰል ነው ልጆቻቸውን የሚድሩት፡፡
በነገራችን ላይ የልጅ ጉልበት ላይ ጥገኛ መሆን፣በልጅ የመደገፍ አባዜ በብዙ ወላጆች ላይ ይታያል፡፡ ልጆችን መላክ፣ ማዘዝ፣ ስርዓትና ስራ ለማስተማር የሚረዳ መሆኑ ባይካድም ወላጆች የምንፈፅመው ግን ከዚያ አልፎ “የጉልበት ብዝበዛ” በሚያሰኝ ደረጃ ነው፡፡ እስቲ እንትን አምጣልኝ፣እንትን አቀብለኝ፣እንትን እጠብልኝ…ማለቂያ የሌለው ትእዛዝ! ለምን? ይህ በጥሩ ባህል ወይም ልማድነት “ተመዝግቦ” የምናገኘው ኢትዮጵያዊ የወላጅና ልጅ ግንኙነት (መስተጋብር) ሲመቸው ወደ ከፋ ብዝበዛ ማምራቱ ይስተዋል ካልኩ ይበቃል፡፡
ያዝረከረኩትን ሰብሰብ ላድርግ፡፡ ልጆቻቸውን ለስደትና ለመዘዙ የሚያጋልጡት ራስ ወዳድ ወላጆች ናቸው፡፡ ደላሎች በሚፈፅሙት የህግ ጥሰት ይጠየቁ። ወላጆችም ልጆቻቸው ላይ የሚያደርሱትን ጫና እንዲቀንሱ፣ከልጆቻቸው ትከሻ ላይ እንዲወርዱ ይመከሩ፣ ይወቀሱ፡፡ ወላጆች በልጆቻቸው ገንዘብ እርስ በርስ መፎካከራቸውን ያቁሙ፤ ይፈሩ። በልጅ ገንዘብ የከበሩ፤በልጅ የድጎማ ገንዘብ ያለፈላቸው ወላጆች፤ በሰፈርተኛው መሞገሳቸው ይቁም፡፡ ወላጆች ህፃናት ልጆቻቸው አረብ አገር እንዳይሄዱባቸው ሰልፍ ይውጡ፣ ይፈራረሙ፡፡ በዚህ አስተሳሰብ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ካልተፈጠረ ልጆች “ወላጆቻቸውን” ለመርዳት ሲሉ ከዚህም የከፋ ችግር ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡
ጥሩ ወላጆች ያደረጉትን ነገር ልንገራችሁና ፅሁፌን ልቋጭ፡፡ እናትና አባት እዚሁ አገራችን ውስጥ ልጃቸውን በተገቢው መንገድ አሳድገውና አስተምረው ለጥሩ ደረጃ ያደርሳሉ፡፡ ልጃቸውም ጥሩ ትምህርት የቀመሰች ነበረችና ውጪ አገር ስራ አግኝታ መኖር ትጀምራለች፡፡ ከዚያም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ልጅ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለእናትና አባቷ የኑሮ መደጎሚያ ገንዘብ ትልክላቸው ጀመር። ወራት አለፉ፣ አመታትም ተከተሉ፡፡ ልጂት በሆነ ጊዜ ወላጆችዋን ለማየት ወደ አዲስ አበባ መጣች፡፡ እናትና አባቷ እጅግ አስደናቂ ነገር አድርገው ቆዩዋት። ድል ያለ ድግስ እንዳይመስላችሁ፡፡ ልጃቸው በላከችላቸው ብር ጥሩ ቤት ገዝተውላት ኖሮ እንዲህ አሏት፡፡ “ይህ ያንቺ ቤት ነው፤ የገዛንልሽም በብርሽ ነው፡፡ እኛ ያለን የጡረታ ገንዘብ ይበቃናል፡፡ ውጪ አገር መኖርና መስራት በበቃሽ ጊዜ ትኖሪበታለሽ ብለን ነው የገዛንልሽ” ልጅት ወላጆቿ ማስተማርና ከፍ ያለ ደረጃ እንድትደርስ ማድረጋቸው አንሶ ለቀጣይ ዘመንዋ የሚበጃትን ስጦታ ስላበረከቱላት የደስታ እንባ አንፎለፎች፡፡ አቅፋ ሳመቻቸው፡፡ ተሳሳቁ፡፡ እንዲህም አለ ለማለት ያህል ነው፡፡

Read 1990 times