Saturday, 19 October 2013 11:42

ለሰራተኞቹ መኖሪያ ቤት የሸለመው ጊፍት ሪል እስቴት

Written by  ማህሌት ፋሲል
Rate this item
(0 votes)

ጊፍት ሪል እስቴት፤ የዛሬ ሁለት ሳምንት በስራቸው የላቀ ስኬት ላስመዘገቡ ስምንት ሠራተኞቹ መኖሪያ ቤት ሸልሟል፡፡ የመኖሪያ ቤቶች ሽልማት ሲሰጥ የመጀመርያው እንደሆነ የተናገሩት የድርጅቱ ባለቤት አቶ ገብረኢየሱስ ኢጋታ፤ ከዚህ ቀደም በስራቸው ውጤት ላስመዘገቡ ሠራተኞቻቸው ነፃ የትምህርት ዕድል መስጠታቸውን ገልፀዋል፡፡
ጋዜጠኛ ማህሌት ፋሲል ስለ ድርጅቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴ፣ ስለመኖሪያ ቤት ሽልማቱና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ከጊፍት ሪል እስቴት ኩባንያ ባለቤት አቶ ገብረኢየሱስ ጋር አጭር ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡

ጊፍት ኩባንያ ስለተሰማራባቸው የስራ ዘርፎች ይንገሩኝ?

ድርጅታችን በአሁኑ ሰአት በአራት የተለያዩ የሥራ ዘርፎች ውስጥ ነው የሚሰራው፡፡ በትሬዲንግ፣ በኢንዱስትሪ፣ በኮንስትራክሽንና በሪል እስቴት ስራዎች ላይ ተሰማርቷል፡፡ ጊፍት ትሬዲንግ ከተቋቋመ ሀያ ሁለት አመቱ ነው፡፡ የድርጅቶቹ እናት ኩባንያ ነው፡፡ በቅርቡ ለህንፃዎች ግብዓት የሚሆኑ እቃዎች ማምረቻ ፋብሪካ ከፍተን ሥራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ነን፡፡ እስካሁን 1500 ለሚሆኑ ሰራተኞች የስራ ዕድል ፈጥረናል፡፡ ፋብሪካው ስራ ሲጀምር ደግሞ ቁጥራቸው ይጨምራል፡፡
ጊፍት ሪል እስቴት በቅርቡ ለሰራተኞቹ መኖሪያ ቤቶችን ሸልሟል፡፡ እስቲ ስለሽልማቱና አሸላለሙ ይንገሩን….
አንድ ድርጅት ስራውን ለማከናወን ካፒታልና የሰው ሀይል ያስፈልገዋል፡፡ በስራው ስኬታማ ሊሆን የሚችለው ሰራተኞች ተበረታተውና ጠንክረው ሲሰሩ ብቻ ነው፡፡ በድርጅታችን ውስጥ ለሶስትና አራት አመት የሰሩ ስምንት ጠንካራ ሰራተኞችን በስራ ብቃታቸው አወዳድረን ነው ቤት የሸለምናቸው፡፡ የቤት ሽልማቱ ወደፊትም ቀጣይነት አለው፡፡ በየአመቱ በስራቸው የላቀ ስኬት ላስመዘገቡ ሠራተኞች የመኖርያ ቤት ሽልማቱ ይሰጣል፡፡
ሽልማቱ የተሰጠው ለሪል እስቴቱ ሰራተኞች ብቻ ነው ወይስ በእህት ኩባንያ ውስጥ ለሚሰሩትም ነው?
አብዛኛዎቹ ተሸላሚዎች የሪል እስቴቱ ሰራተኞች ናቸው፡፡ በእህት ኩባንያ ያሉ ጥቂት ሰራተኞችም ተሰጥቷቸዋል፡፡ ወደፊት ግን ከአራቱም ድርጅቶች አወዳድረን ነው የምንሸልመው፡፡
ድርጅቱ ከዚህ በፊት ለሰራተኞች የቤት ሽልማት ሰጥቶ ያውቃል? ሰራተኞቹ የተሸለሙት መኖሪያ ቤት ምን ዓይነት ነው?
አፓርትመንት ነው፡፡ ከዚህ በፊት የቤት ሽልማት ሰጥተን አናውቅም፡፡ ነገር ግን በስራቸው የተለየ ብቃት ላሳዩ በርካታ ሰራተኞች የትምህርት እድል ሰጥተናል፡፡ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ አስተምረናል፡፡ አሁንም እያስተማርናቸው ያሉ ሰራተኞችም አሉ፡፡ የትምህርቱን ሙሉ ወጪ የሚሸፍነው ድርጅቱ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት አራት ሰራተኞችን በማስተርስ ድግሪ እያስተማርን ሲሆን ለአንድ ተማሪ ሁለት መቶ ሺህ ብር ገደማ ነው የምንከፍለው፡፡ የሚማሩትም ውጪ አገር ነው። አንድ ሰራተኛ ሲማር ራሱን ብቻ አይደለም የሚጠቅመው፡፡ ድርጅቱንም ይጠቅማል፡፡
የቤት ሽልማት የሰጣችሁት በየትኛው የስራ ዘርፍ ላሉ ሰራተኞች ነው?
ሽልማቱን የሰጠነው በኢንጂነሪንግና በማኔጅመንት ውስጥ ላሉ ሰራተኞች ነው፡፡ ለኢንጂነሮች ከሶስት አመት በላይ በድርጅታችን ተግተው ለሰሩ፣ በማኔጅመንት ደግሞ ከአራት አመት በላይ ላገለገሉ ታታሪና ትጉህ ሰራተኞች አወዳድረን ነው የሸለምነው፡፡
የቤቶቹ ዋጋ ምን ያህል ነው?
ለሰራተኞች የሰጠነው በሶስት ደረጃ ነው፡፡ ባለ ሶስት መኝታ ክፍል በአንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሺህ ብር፣ ባለ ሁለት መኝታ ቤቱ ዘጠኝ መቶ ሀያ ዘጠኝ ሺህ ብር፣ ባለ አንድ መኝታ ቤት ስድስት መቶ አስር ሺህ ብር ነው የሚያወጡት፡፡
ለደንበኞች በቅርቡ የምታስረክቧቸው ቤቶች ይኖራሉ?
በህዳር ወር በሳይት አንድና ሁለት ላይ የሚገኙ ከሀምሳ በላይ ቤቶችን ለማስረከብ ዝግጅት ጨርሰናል፡፡ ቪላና ታውን ሀውስ የሚባሉ ቤቶች ናቸው፡፡ መጋቢት ላይም እንዲሁ የአፓርትመንት ቤቶች የማስረከብ እቅድ አለን፡፡
በክልሎችስ መኖሪያ ቤቶች ትገነባላችሁ?
እስካሁን አልጀመርንም፤ ምክንያቱም የያዝነውን ስራ ማጠናቀቅ አለብን፡፡ ሪል እስቴት ጥንቃቄ ይፈልጋል፤ በእቅዳችን ውስጥ ግን ተይዟል፡፡ በክልሎችም የመስራት ሃሳብ አለን፡፡ ይሄ የማይቀር ነው፡፡
አንዳንድ የሪል እስቴት ኩባንያዎች ለደንበኞች የገቡትን ቃል ባለመፈፀማቸው የተፈጠረው ጥርጣሬ ስራችሁ ላይ ተፅዕኖ አልፈጠረም? እንዲህ ያሉ ችግሮች የሚከሰቱት በምን ምክንያት ነው?
እስካሁን ምንም ችግር አልፈጠረም፤ ምክንያቱም ቤቶቹን ቶሎ ሰርተን እናስረክባለን። የችግሮቹ መንስኤ እንደሚመስለኝ ሁለት ናቸው። ውስጣዊ ችግርና ውጫዊ ችግር የምንለው ነው። በደንብ ሳይቀናጁ ስራ ይጀምሩና አይሳካም ሁለተኛው ደግሞ የብዙ ሪል እስቴት ችግር የሆነው ውጫዊ ችግር ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ የመጀመሪያው የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ናቸው፡፡ ሲሚንቶ፣ ብረት፣ የመሳሰሉት እጥረትና ጥራት እንዲሁም ዋጋ ሲሆን ሌላው ችግር የሰለጠነው የሰው ሀይል አንድ ቦታ ተቀጥሮ አለመስራት ነው፡፡ በአንድ ቦታ ረግተው አይቆዩም።
ስራ ከጀመራችሁ አንስቶ ስንት ቤቶች ለደንበኞች አስረክባችኋል? በአመት ስንት ለማስረከብስ አቅዳችኋል?
እስካሁን ብዙ ቤት ለደንበኞች አስረክበናል። ገብተው መኖር የጀመሩ ብዙ ናቸው፡፡ እንዲሁ ተረክበው መንገድ እስኪስተካከል ብለው የቆዩ ደንበኞችም አሉን፡፡ በየአመቱ ከ40-50 ቤቶች እናስረክባለን፡፡ ህዳር መጨረሻ ላይም ከአርባ የሚበልጡ ቤቶች ለደንበኞች እናስረክባለን፡፡
የወደፊት እቅዳችሁ ምንድነው?
ወደፊት ለህብረተሰቡ አቅሙን ያማከለ አፓርትመንት ሰርተን ለማስረከብ እቅድ አለን። በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እየታገዝን እስከ ዛሬ ከሰራናቸው ትምህርት ወስደን የተሻሉ ቤቶችን እንገነባለን ብለን እናስባለን፡፡

Read 1747 times