Print this page
Saturday, 19 October 2013 11:36

ከ31 ዓመት በላይ የሆነው የአስክሬን ምርመራ ክፍል

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(2 votes)

ለ15 ዓመታት ምርመራውን የሚያካሂዱት የኩባ ሃኪሞች ብቻ ናቸው
ሦስት ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ራሳቸውን አጥፍተዋል

በአድዋ ጦርነት የተጎዱ ወታደሮች እንዲታከሙና እንዲያገግሙ በማሰብ ነው አፄ ምኒልክ በአገሪቱ የመጀመሪያውን ሆስፒታል የመሰረቱት፡፡ ዛሬ ዳግማዊ ምኒልክ ሪፈራል ሆስፒታል የቀዶ ጥገና፣ የውስጥ ደዌ እና የአጥንት ህክምና አገልግሎቶችን የሚሰጥ ቢሆንም ግማሽ ያህሉ ህመምተኞች ለአይን ህክምና የሚመጡ ናቸው፡፡ ባለፈው አመት ተኝተው የሚታከሙትንና ቀዶ ህክምና የሚያስፈልጋቸውን 82ሺህ ተመላላሽ ታካሚዎችን አስተናግዷል፡፡
ዋነኛ የህክምና አገልግሎቶችን ወደ አራት ለማሳደግ ህንፃ እያስገነባ መሆኑን የገለፁት የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ሞገስ መስፍን፤ ግንባታው ሲጠናቀቅ የእናቶችና ህፃናት ህክምናን እንደሚጀምር ገልፀዋል፡፡
ብዙውን ጊዜ የምኒልክ ሆስፒታል ስም የሚነሳው ግን በአስከሬን ምርመራ አገልግሎት ነው፡፡ በ1965 ዓ.ም የተቋቋመው የአገሪቱ ብቸኛ የአስክሬን ምርመራ ክፍል፣ በቀን በአማካይ ሰላሳ አስከሬኖችን ይመረምራል፡፡ በመጀመሪያዎቹ 15 ዓመታት የአስክሬን ምርመራው ላይ ሦስት ኢትዮጵያውያን የህክምና ባለሙያዎች መስራታቸው የሚታወስ ቢሆንም፣ ሶስቱም እራሳቸውን አጥፍተው መሞታቸውን በተመለከተ ስራ አስኪያጁ ማረጋገጫ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ከዚያ ወዲህ በአስከሬን ምርመራ ክፍል ውስጥ የሚሰራ ኢትዮጵያዊ ባለሙያ አለመገኘቱ ግን እውነት ነው። ሆስፒታሉ የኩባ ሃኪሞችን ስድስት ዓመት የስራ ውል እያስፈረመ ማስመጣት የጀመረውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ አሁን እየሰሩ ያሉት የአስክሬን ምርመራ ብቸኛ ኩባዊት ባለሙያ ግን የሁለት አመት ውል ነው የፈረሙት፡፡ ኩባዊቷ ሃኪም በአዲሱ አመት መግቢያ ላይ የጤና እክል ሲገጥማቸው የአስክሬን ምርመራ ለሦስት ቀናት ከመስተጓጎሉም በተጨማሪ፣ ባለፈው ሳምንት የስራ ውላቸውን በማጠናቀቃቸው፣ የአስክሬን ምርመራ ክፍል ተዘግቶ ነበር፡፡ የሆስፒታሉ ምንጮች እንደሚሉት፤ ኩባዊቷ ሃኪም በ6000 ብር የወር ደሞዝ ነው ሲሰሩ የቆዩት። ከ400 ዶላር በታች መሆኑ ነው፡፡ አሁን ሌሎች ሃኪሞች ከኩባ እስኪመጡ ድረስ ሃኪሟ በ800 ዶላር ክፍያ ለአንድ ወር በስራቸው ላይ እንዲቆዩ ተደርጓል፡፡
መንግስት የአስክሬን ምርመራ ክፍሉን ያቋቋመው፣ በደል የደረሰባቸው ዜጎች ፍትህ እንዲያገኙ በማሰብ ነው የሚሉት የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ሞገስ፤ ወንጀል የተፈፀመበትንና ያልተፈፀመበትን በሳይንሳዊ ምርመራ እየለየን የፍትህ አካላትን እናግዛለን ብለዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ የአስክሬን ምርመራ ክፍል በየጊዜው በርካታ ትችቶች እንደሚሰነዘሩበት ይታወቃል፡፡ በአስተዳደር ችግሮችና በአሰራር ጉድለቶች የተነሳ እንግልት እንደሚደርስባቸው ተገልጋዮቹ ይናገራሉ፡፡ የሟች ቤተሰቦች አስከሬን ለመውሰድ ሲመጡ፣ የሌላ ሰው አስከሬን ተቀይሮ ይሰጣቸዋል የሚል ቅሬታም በተደጋጋሚ ይሰማል፡፡ ኩላሊት ይሰርቃሉ የሚል ውንጀላም አልፎ አልፎ ይሰነዘራል፡፡
ኩላሊት ተሰርቆ ይወሰዳል የሚለው ውንጀላ፣ መሰረት የሌለው አሉባልታ ነው የሚሉት አቶ ሞገስ፤ “ፈፅሞ አይደረግም፤ ሊደረግም አይችልም” ብለዋል።
በእርግጥ፣ የኩላሊት ስርቆት ከፍተኛ ወንጀል ስለሆነ፣ እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ ቀርቶ ሌሎች አገራት ውስጥም በቀላሉ የሚፈፀም ወንጀል አይደለም፡፡ ነገር ግን ህገ ወጥ በመሆኑ ብቻ አይደለም ኩላሊት የማይሰረቀው፤ የሰውነት አካል ወስዶ ወደ ሌላ ሰው ለማስተላለፍ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ያፈራቸው የረቀቁ መሳሪያዎች እንደሚያስፈልጉት አቶ ሞገስ ገልፀው፣ ለኩላሊት ስርቆት የሚሆን ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ብለው እንደማያምኑ ይናገራሉ። ከአስክሬን ምርመራ ጋር ተያይዞ የኩላሊት ስርቆት በጭራሽ ሊፈፀም እንደማይችል በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል የሚሉት አቶ ሞገስ፤ አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ለህክምና የሚያገለግል የአካል ክፍል ይኖረዋል ወይ ብለን መጠየቅ አለብን ብለዋል፡፡ አቶ ሞገስ እንደሚሉት፤ ከአስክሬን ተሰርቆ የሚወሰድ ኩላሊት ሊኖር አይችልም፡፡ ለነገሩ፣ ከአረብ አገራት በተለያዩ ምክንያቶች ሞተው የሚመጡ አስከሬኖች ላይም አንዳችም የአካል ክፍል ስርቆት አጋጥሞ እንደማያውቅ ባለሙያዎች ይመሰክራሉ፡፡ እንዲያም ሆኖ አከራካሪ ነገሮች መፈጠራቸው አልቀረም። ለምሳሌ የአይን ብሌን ከሟቾች አካል መውሰድ እንደሚቻል እና እንደሚወሰድ ይታወቃል፡፡ በአንድ በኩል በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የአካል ክፍል “ልገሳ” መልካም ነው፡፡ ያለ ፈቃደኝነት የሚከናወን የአይን ብሌን “ልገሳ” ሲኖር ግን ያሳስባል። የሆነ ሆኖ፣ አስከሬን ወደ ሆስፒታሉ የሚመጣው በፖሊስ ፍቃድ ብቻ እንደሆነና ያለ ፖሊስ ፍቃድ ሆስፒታሉም አስከሬን እንደማይቀበል አቶ ሞገስ ይገልፃሉ፡፡ መንገድ ላይ ሞቶ ሲገኝ፣ በሰው እጅ ተገድሏል ተብሎ ሲጠረጠር፣ ቤተሰብ በጥርጣሬ እንዲመረመርለት ሲጠይቅ፣ በማረሚያ ቤት ህይወቱ ካለፈ፣ ከአረብ አገር አስክሬን ሲመጣ ምርመራ ይካሄዳል፡፡ የሆስፒታሉ የአስክሬን ምርመራ ለፖሊስ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ የወንጀል ድርጊት መፈፀሙንና አለመፈፀሙን ለማወቅ ብቻ ሳይሆን፣ የወንጀል አፈፃፀሙንና የወንጀለኛውን ማንነት ለማወቅ ይጠቅማል፤ የአስከሬን ምርመራ፡፡
የአስከሬን ምርመራ ወንጀለኞችን ለመያዝ የመጥቀሙን ያህል፣ የተሳሳቱ ጥርጣሬዎችን ለመከላከል እንደሚረዳ አቶ ሞገስ ሲገልፁ፤ አንድ ገጠመኝን ይጠቅሳሉ፡፡ የመኪና አደጋ የደረሰበት አንድ ወጣት በህክምና ድኖ ስራውን ይጀምራል። ጉዳት ያደረሰውም አሽከርካሪ፣ ከተጎጂ ቤተሰብ ጋር በመስማማቱ ክስ አልተመሰረተበትም፡፡ ተጎጂው ወጣት ታክሟል፡፡ ከአንድ አመት በኋላ ግን ህይወቱ አለፈ፡፡ የሟቹ ቤተሰብም ለፖሊስ አመለከቱ፤ ልጃችን የሞተው ከአመት በፊት በደረሰበት ግጭት ነው አሉ፡፡ ፖሊስ አስከሬኑን አምጥቶ አስመረመረ። ወጣቱ በመኪና አደጋ ሳይሆን በሳንባ ምች እንደሞተ በአስክሬን ምርመራ ስለተረጋገጠ፣ የተሳሳተ ጥርጣሬና ውንጀላን ለማስወገድ ተችሏል።
በሌላ በኩል ደግሞ ወንጀለኞች ማምለጫ እንዳያገኙ ለመከላከል የአስከሬን ምርመራ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው፡፡ እራሱን አጥፍቷል የተባለ ሰው፣ አስከሬኑ ሲመረመር በሌላ ሰው እጅ እንደሞተ የሚረጋገጥበት አጋጣሚ አለ፡፡ ያኔ ፖሊስ ወንጀለኛውን አድኖ ይይዘዋል፡፡
የአስከሬን ምርመራ በአንድ ሆስፒታል ውስጥ ብቻ መሰጠቱ ችግሮችን ይፈጥራል ያሉት አቶ ሞገስ፤ ተገልጋዮችንም የሚያጉላላ እክል በየጊዜው ሊፈጠር ይችላል ይላሉ፡፡ በአንድ ወይም በሁለት ባለሙያዎች ብቻ የሚካሄድ የአስከሬን ምርመራ፣ ባለሙያዎቹ የግል ችግር ሲገጥማቸው ስለሚስተጓጎል ተገልጋይ ይጉላላል። በተለይ አስክሬን ለመውሰድ መኪና ተከራይተው ከክልሎች የሚመጡ ቤተሰቦች ከፍተኛ የገንዘብና የህሊና ጉዳት ይደርስባቸዋል፡፡
የአስክሬን ምርመራ ባለሙያዎች በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አማካኝነት ከኩባ ብቻ የሚመጡት በክፍያቸውም ተመጣጣኝነት ሊሆን ይችላል የሚሉት አቶ ሞገስ፤ በባለሙያዎች እጥረት አገልግሎት የተስተጓጎለው ለሁለት ቀናት ብቻ ነው ብለዋል፡፡ የአገልግሎቱ መስተጓጎል ተጋኖ የወጣው ህብረተሰቡ የጉዳዩን አሳሳቢነት ስለተገነዘበ ይመስለኛል ሲሉም አቶ ሞገስ ተናግረዋል፡፡

 

Read 2205 times