Saturday, 19 October 2013 11:32

የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ‹‹በወረዳ ባለሥልጣናት ተጽዕኖ እየተደረገብኝ ነው›› ስትል መንግሥትን ወቀሰች

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ዓለም አቀፍ ጉባኤው፤ ሲኖዶሱ የመንፈሳዊ ኮሌጁን ችግር እንዲፈታ አሳሰበ
የክልል መንግሥታት የወረዳ ባለሥልጣናት÷ የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ እንዳይታነፅ፣ የመካነ መቃብር፣ የልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች እንዳይፈቀዱ፣ የቦታ ይዞታ ባለቤትነት በሕግ እንዳይረጋገጥ፣ ምእመናን ሥርዐተ አምልኮአቸውን በሰላምና በነጻነት እንዳይፈጽሙ፣ መብታቸውን ሲጠይቁም አፋጣኝና አግባብነት ያለው ፍትሕ እንዳያገኙ በማድረግ ተጽዕኖና በደል እያደረሱብኝ ነው ስትል የኦርቶዶክስ ቤ/ክርስትያን ወቀሰች፤ አቤቱታዋም በጥንቃቄ ታይቶ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣት አሳሰበች።
ቤተ ክርስቲያኒቱ ከጥቅምት 4 ቀን ጀምሮ በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ስታካሂድ በቆየችውና በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ በሚጠበቀው ዓለም አቀፍ የመንበረ ፓትርያርክ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ፣ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ተወካዮች ‹‹የብዝኃነት አያያዝ፣ አክራሪነት/ጽንፈኝነት ዝንባሌዎቹና መፍትሔዎቹ›› በሚል ርእስ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ ‹‹የሃይማኖት መቻቻል›› በሚለው የአጠቃላይ ጉባኤው መርሐ ግብር ላይ በቀረበው በዚህ ጽሑፍ÷ ሌሎች አገሮች ብዝኃነትን ይዞና አቻችሎ አንድነትን ለማስቀጠል ተግዳሮት እንደኾነባቸው፣ የብዝኃነት ተምሳሌትና መገለጫ በኾነችው ኢትዮጵያ ግን በየጊዜው ወደ አገሪቱ የገቡ ሃይማኖቶች፣ በሰላም የተቀባበሉበትና በመገናዘብ የኖሩበት ጥልቅ ትርጓሜና ታሪክ እንዳለው ተገልጧል፡፡
ጽሑፉን ተከትሎ በነበረው ውይይት በሰሜን ወሎ፣ በምዕራብ ወለጋ ሦስት ዞኖች፣ በጋሞጎፋ ሦስት ወረዳዎች፣ በሶማሌ ዘጠኝ ዞኖች፣ በደቡብ ጎንደርና በወላይታ ኮንታ በዴሳ ወረዳ የሌላ እምነት ተከታይ በኾኑ የመንግሥት ባለሥልጣናት በቤተክርስቲያኒቱ ላይ ይፈጸማሉ የተባሉ የመብት መደፈሮች፣ የአስተዳደር፣ የፍትሕና የጸጥታ አካላት አድልዎች በሀገረ ስብከቶቹ ሊቃነ ጳጳሳት በዝርዝር ተሰምተዋል፡፡
ሊቃነ ጳጳሳቱ እንዳስረዱት÷ ለዞን መስተዳድር አካላት ውሳኔና መመሪያ የማይገዙ፣ የሌላ እምነት ተከታይ የኾኑና ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ቤተ ክርስቲያኒቱን በፊውዳልነትና ነፍጠኛነት እየከሰሱ፣ ይዞታዋ እንዲነጠቅ ሕዝብን በበቀል ስሜት የሚያነሣሱ፣ በአማኞች ላይ አካላዊ ሥቃይና ሥነ ልቦናዊ ጫና በማድረስ ለመፈናቀልና ለሞት የሚዳርጉ፣ የሕዝቡን፣ የአገልጋዮችንና የሃይማኖት አባቶችን ጩኸት የማይሰሙ የወረዳ ባለሥልጣናት ጥቂቶች አይደሉም፡፡
በት/ቤት በአንገታቸው ማተብና መስቀል ያሠሩ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ተማሪዎች፣ ‹‹ከበላይ የመንግሥት አካል መምሪያ ተላልፎልናል፤ በሸሪዓ ሕግ ሴቶች ራሳቸውን እንዳይከናነቡ፣ ክርስቲያኖች ማተብና መስቀል እንዳያስሩ ተከልክሏል›› በሚሉ መምህራንና የፖሊስ አባላት ማተባቸው ከአንገታቸው ይበጠሳል፤ በጸሎተ ቅዳሴ ላይ ያሉ ምእመናን ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ በማስወጣት፣ ጸሎተ ቅዳሴው እንዲስተጓጎልና በበዓላት ቀን ሥራ እንዲሠሩም ይገደዳሉ፡፡ በሞትም በሕይወትም መደጋገፍ በሚታይባቸው ዕድሮችና በሕዝብ መጓጓዣዎች ሕዝቡ እንዳይረዳዳና እንዳይገለገል የወረዳ ዳኛ፣ ‹‹ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር አንድነት የለንም›› በማለት እስከ 80 ዓመት የቆየ ዕድር እንዲፈርስና ማኅበራዊ ግንኙነቶች እንዲታወኩ ምክንያት መሆኑ በስብሰባው ላይ በምሬት ተነግሯል፡፡
‹‹አንድ ሰው እግሩን እሳት እየበላው ቻል ይባላል? መቻቻል እስከ ምን ድረስ ነው?›› ሲሉ የጠየቁት የሰሜን ወሎ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ ‹‹እንድንቻቻል አድርጉን፤ እንችላለን›› ሲሉ የሚኒስቴሩን ተወካዮቹ አሳስበዋል፡፡
የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ተወካዮች በውይይቱ ላይ ክርስትና በአራተኛው መቶ ክ/ዘመን ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን የተናገሩ ሲሆን ሊቃነ ጳጳሳቱ መረጃው የተሳሳተ መሆኑን ጠቁመው ማስተካከያ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ከቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮና ከመጽሐፍ ቅዱሱ ምስክርነት ጋር የሚጣረስ ነው፤ ክርስትናን የተቀበልነው ክርስቶስ ዐርጎ ዓመት ሳይሞላው፣ ሐዋርያትም ከኢየሩሳሌም ሳይወጡ በ34 ዓ.ም በጃንደረባው አማካይነት ከእግዚአብሔር ነው፤›› በማለት በቀጣይ የሚኒስቴሩ ተወካዮች በተመሳሳይ ርእሰ ጉዳይ በቤተ ክርስቲያኒቱ መድረኮች ተገኝተው ገለጻ ሲሰጡም፤ ክርስትና በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደገባ የሚጠቅሱትን አርመው እንዲቀርቡ መክረዋቸዋል፡፡
‹‹ክርስትና በአራተኛው መ/ክ/ዘ ወደ ኢትዮጵያ ስለመግባቱ የተናገሩት ዐፄ ኢዛና ክርስትናን በኦፊሴል ተቀብለው ያስፋፉበት ወቅት በመኾኑ ነው›› ሲሉ የተናገሩት የሚኒስቴሩ ከፍተኛ አማካሪ፤ በ34 ዓ.ም. ጃንደረባው እንደ ግለሰብ መቀበሉ ኢትዮጵያን ሊወክል ይችላል ተብሎ ከታመነ፣ ‹‹እኛ እናንተ ባላችሁት ለማስተካከል ችግር የለብንም፤ የተስማማችኹ ከኾነ በታሪክ መጻሕፍትም ሳይቀር እንዲስተካከል እናደርጋለን፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 27/2 ማንኛውም ሃይማኖት እምነቱን ለማስፋፋት ተቋማትን መመሥረት እንደሚችል፣ ለዚህም የቁጥር ገደብ እንዳልተቀመጠ ተወካዮቹ አውስተዋል፡፡
የተጠቀሱት በደሎችና ጥፋቶች በተጨበጠ ማስረጃ ተጠናክረው እንዲሰጧቸውና እነርሱን በተግባር በመፍታት በሂደት እንዲፈትኗቸው ያመለከቱት የሚኒስቴሩ ተወካዮች፣ ስሕተት በመንግሥትም በሃይማኖት አባቶችም ዘንድ እንዳለ፣ በታሪክ አጋጣሚ ወደ ኋላ በቀሩትና የመሠረተ ልማት ዝርጋታና ትስስር በሌላቸው ክልሎች ደግሞ ስሕተቱ እንደሚጎላ፣ ወቀሳውም እያንዳንዱ ቤተ እምነት በሁሉ ላይ የሚያሰማው እንደኾነ ጠቁመዋል፡፡
በሊቃነ ጳጳሳቱ ያልተነገሩ በየወረዳው ያሉ በርካታ ቅሬታዎችን መከታተሉን የሚኒስቴሩ ተወካዮች ገልጸዋል፡፡ እንደ ጥፋት ደረጃውም ርምጃ የተወሰደበት ሁኔታና ተቀጥተው የተለቀቁ አካላት ስላሉ፣ በሕግ የተያዙት ጉዳዮች በሕግ እንዲያልቁ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጠንክረው እንዲከታተሉ ጠይቀዋል፡፡
በሌላ በኩል ‹‹ኮሽ ባለ ቁጥር ወደ ቃሊቲ መፍትሔ ስለማይሆን›› ሚኒስቴሩ ግንዛቤ ላይ መሥራትን እንደሚያስቀድም፣ በሃይማኖት ተቋማቱም ዘንድ አስተምህሮውን ጠንቅቀው ያወቁ ሰባክያን ብቻ መሰማራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ ‹‹እዚህ ተገኝታሁ ያቀረባችሁት ሐሳብ በጣም ጠቃሚ ነው›› በማለት ተወካዮቹን ያመሰገኑት ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ‹‹በየጊዜው መነጋገር ለሃይማኖትም ለጸጥታም የሚጠቅም ስለሆነ መማማሩ በአንድ ጊዜ የሚያበቃ ባይኾን ጥሩ ነው›› ሲሉ ውይይቱ እንዲቀጥል ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል፡፡
በሌላ ዜና ዓለም አቀፍ ጉባኤው በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎችና በአስተዳደሩ መካከል በተማሪዎች አቀባበልና የምዝገባ ቀን፣ መምህራን ከኮሌጁ መኖርያ ቤቶች እንዲለቁ ከተላለፈው የአስተዳደሩ ትእዛዝና ከኮሌጁ ሌሎች የአሠራር ችግሮች ጋር ተያይዞ ሰሞኑን ዳግመኛ ላገረሸው ውዝግብ፤ በቅርቡ የሚካሄደው ቅ/ሲኖዶስ ኹነኛ መፍትሔ እንዲሰጠው መጠየቁ ተዘግቧል፡፡

Read 3036 times