Saturday, 19 October 2013 11:16

መዐሕድ “የአማራ ተወላጅ ተማሪዎች መፈናቀል” እንዲቆም ጠየቀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

          በ15 ቀን ውስጥ ከወልቃይት  ጠገዴ ሁለት ሺ ተማሪዎች ተፈናቅለዋል”

            የመላው አማራ ህዝብ (መዐህድ) በአማራ ተወላጅ ተማሪዎች ላይ እየደረሰ ያለው መፈናቀል በአስቸኳይ እንዲቆም ጠየቀ፡፡ መአህድ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የአማራ ተወላጆችን መፈናቀል በተመለከተ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ማሳወቁንና መፈናቀሉ እንዲቆም መጠየቁን ጠቁሞ፤ ጉዳዩ እስካሁን እልባት አለማግኘቱን ገልጿል፡፡
መፈናቀሉ ሊቆም ቀርቶ ተጠናክሮ መቀጠሉንና በቅርቡም ከጉራፈርዳ፣ ከቤኒሻንጉል እና ከወልቃይት ጠገዴ የአማራ ተወላጅ ተማሪዎች መፈናቀላቸውን የጠቆመው መዐህድ፤ ድርጊቱ በአገሪቱ ስርዓት አልበኝነት መንሰራፋቱን ያሳያል ብሏል፡፡
ከተማሪዎች በተጨማሪ የአማራ ተወላጅ አርሶ አደሮችንም ለይቶ ማፈናቀሉ ለመሪር ሀዘን እንደዳረገው መአህድ ገልፆ፤ አንድን ብሄር ማዕከል ያደረገ ማፈናቀል እንዲቆም ጠይቋል፡፡
ባለፉት 15 ቀናት ብቻ “አካባቢያችሁ አይደለም” በሚል ከወልቃይት ጠገዴ ሁለት ሺህ ተማሪዎች መፈናቀላቸውን የገለፁት የመአህድ ፕሬዚዳንት አቶ ሸዋንግዛው ገብረስላሴ፤ ከጉራፈርዳም ተማሪዎች ተፈናቅለው ከትምህርት መስተጓጐላቸውንና ለጊዜው ቁጥራቸው በውል አለመታወቁን ፕሬዚዳንቱ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ “ከጉራፈረዳ ምን ያህል ተማሪዎች እንደተፈናቀሉና በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ የሚያጣራ ቡድን ልከናል” ያሉት አቶ ሸዋንግዛው፤ አጣሪ ቡድኑ ሁኔታውን አጣርቶ ሲመለስ መዐህድ በድጋሚ የአቋም መግለጫ እንደሚያወጣም ተናግረዋል፡፡
“ተማሪዎች የወደፊት አገር ተረካቢ ሲሆኑ አርሶ አደሮችም የአገር ህልውና ምሰሶ ስለሆኑ በአገራቸው የትኛውም ቦታ የመማርና የመስራት መብታቸው ተከብሮ፤ ተማሪዎችም ወደ ትምህርት፣ አርሶ አደሮችም ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ እንጠይቃለን” ብለዋል፤ ፕሬዚዳንቱ፡፡
የአማራ ተወላጆችን ከተለያዩ አካባቢዎች ከማፈናቀል በተጨማሪ የአማራውን ክልል ለማጥበብ ወደ አጐራባች ክልሎች የሚደረገው የመሬት ሽንሸና ዘመቻ በአስቸኳይ እንዲቆም መዐህድ በመግለጫው የጠየቀ ሲሆን በአማራ ህልውና ላይ በተደጋጋሚ እየደረሰ ያለው ስልታዊ እንቅስቃሴ እና ትንኮሳ ሊገታ ይገባል ሲል አሳስቧል፡፡ ሌሎች ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪል ማህበራትም ይህንን ኢ-ሰብአዊ ድርጊትና መብት ረገጣ እንዲያወግዙ ጠይቋል፡፡

Read 2939 times