Saturday, 19 October 2013 10:54

የጐንደር ዩኒቨርስቲ የ“ልማትና አካባቢ እንክብካቤ” “የተመረቃችሁበት የትምህርት መስክ አይታወቅም” - ቀጣሪዎች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)
  • “በስራ አጥነት ተመዝግባችሁ ተደራጁ” ተብለዋል
  • ዩኒቨርሲቲው በዘረፉ ማስተማሩን ቀጥሏል
  • ተመራቂዎች የሚቀጥረን አጣን አሉ

ከጐንደር ዩኒቨርስቲ በ“ልማትና የአካባቢ እንክብካቤ ጥናት” የተመረቁ ተማሪዎች በመንግስትም ይሁን በግል መስሪያ ቤቶች የስራ መደብ ዝርዝር ውስጥ ባልተካተተ የትምህርት ዘርፍ በመመረቃችን ስራ አጥ ሆነናል ሲሉ አማረሩ። የትምህርት ክፍሉ ሃላፊዎች በበኩላቸው፤ ከፌደራልና ከክልል ሲቪል ሠርቪስ መስሪያ ቤቶች ጋር ተነጋግረን ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረግን ነው፤ ጥቂት የማይባሉ ተመራቂዎችም ስራ ማግኘት ጀምረዋል ብለዋል፡፡
በ2003 ዓ.ም ከትምህርት ክፍሉ በመጀመሪያ ዲግሪ መመረቃቸውን የሚገልፁት ክብሮም ሃጐስና ጓደኞቹ፤ በትምህርት ክፍሉ ሲመደቡ ጀምሮ ስራ የመቀጠር ዕድል እንደሌላቸው እያወቁ ምርጫ በማጣት ትምህርቱን ለመማር መገደዳቸውን ያስታውሳሉ፡፡ በሶስት አመታት ቆይታቸው ዲፓርትመንቱ በግለሠቦች ይሁንታ መጀመሩን በሚገልፅ መልኩ “የሙሉቀን ልጆች” እየተባሉ ይጠሩ እንደነበር የገለፁት እነ ክብሮም፤ በትምህርት አሠጣጡ ላይ ቅሬታ ያለው ተማሪ ባይኖርም ለአመታት በደከሙበት የትምህርት መስክ ከተመረቁ በኋላ ስራ ማጣታቸው በርካቶችን ተስፋ እንዳስቆረጠ ተናግረዋል፡፡ “በግሌም ሆነ የተማሪዎቹን ጥያቄ ይዤ ለበርካታ ጊዜያት የፌደራል ሲቪል ሠርቪስ ሚኒስቴር ድረስ በመመላለስ በትምህርት መስኩ የስራ እድሎች እንዲፈጠሩ ለመጠየቅ ሞክሬያለሁ” የሚለው ክብሮም፤ እስከዛሬ ግን ምላሽ አለማግኘቱን ገልጿል፡፡
በሃገሪቱ በሚወጡ የስራ ማስታወቂያዎች “በልማትና የአካባቢ እንክብካቤ የትምህርት ዘርፍ የተመረቀ” የሚል የስራ መደብ ማስታወቂያ እስከዛሬ ወጥቶ አያውቅም ያለው ተማሪው፤ በ2004 ዓ.ም የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር በ“ዴቨሎፕመንታል ስተዲስ” የትምህርት መስክ ማስታወቂያ ሲያወጣ ተያያዥነት አለው በሚል ለመመዝገብ ሄደው እንደነበር አስታውሶ፣ “የተመረቃችሁበት የትምህርት መስክ አይታወቅም” ተብለው ማስረጃቸው እንደተመለሰላቸው ገልጿል።
የስራ እድሉን ለማግኘት በአዲስ አበባ ከተማ 114 ወረዳዎች እየዞረ ከቀጣሪ አካላት ጋር መነጋገሩን የሚገልፀው ክብሮም፤ ሁሉም ግን ለትምህርት መስኩ የሚሆን የስራ መደብ እንደሌላቸው መረዳቱን ተናግሯል፡፡ እንደውም በሚኖርበት የካ ክፍለ ከተማ፣ የክፍለ ከተማውን አስተዳደር ባነጋገረበት ወቅት “ለምን በስራ አጥነት ተመዝግባችሁ አትደራጁም” የሚል ምላሽ እንደተሠጠው ገልጿል።
“ከተመረቅንበት ጊዜ ጀምሮ በየእለቱ የሚወጡ የስራ ማስታወቂያዎችን ከጓደኞቼ ጋር ሆነን አንድም ቀን ሣናሣልፍ ስንከታተል ቆይተናል” የሚለው ተማሪው፤ “ተያያዥ ለሆኑ የስራ መስኮች የትምህርት ማስረጃ ስናስገባ በመጀመሪያ አካባቢ ‘ይሄ የትምህርት መስክ አይታወቅም’ እየተባልን ማመልከቻችን ተመላሽ ይደረግ ነበር፤ እየቆየ ግን ማመልከቻችንን ይቀበሉንና በኋላ ያስወጡናል” ብሏል፡፡ በዚህም ምክንያት “የቤተሠቦቻችንን ሃብት አባክነን፣ ተምረን እንዳልተማርን ሆነን መና ቀርተናል” የሚለው ክብሮም፤ በግለሠቦች በጐ ፈቃድ እንደተጀመረ የሚነገርለት የትምህርት ክፍሉ ግን ዛሬም ተማሪዎችን እየተቀበለ ማስተማሩንና ማስመረቁን እንደቀጠለ ገልጿል፡፡
“ልማትና የአካባቢ እንክብካቤ ጥናት” የተባለው የትምህርት መስክ በጐንደር ዩኒቨርስቲ ብቻ እንደሚሠጥና በ1999 ዓ.ም እንደተጀመረ የሚናገሩት ተማሪዎቹ፤ ከ2003 ቀደም ብሎ የተመረቁትም ሆኑ ከዚያ በኋላ የተመረቁት አብዛኞቹ ተማሪዎች ስራ አጥ እንደሆኑ ይገልፃሉ፡፡ አንዳንዶቹም ከትምህርት መስኩ ውጭ ባሉ ስራዎች መሠማራታቸውን ተናግረዋል፡፡
ወደ ትምህርት ክፍሉ ተመድበው በገቡበት ወቅት በተሠጣቸው ማብራሪያ ላይ ከሴቶችና ህፃናት ጉዳይ፣ ከቱሪዝም፣ ከአካባቢ ጥበቃ፣ ከስርአተ ፆታ እንዲሁም ከፖሊሲ ቀረፃ ጋር በተገናኙ የስራ መስኮች ሠፊ የስራ እድል አላችሁ ተብሎ ተነግሮናል ያሉት ተመራቂዎቹ፤ ሆኖም የተባሉት የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት ጀርባቸውን እንደሰጧቸው ይናገራሉ፡፡
የትምህርት ክፍሉ ተጠሪ የነበሩትን አቶ ሲሣይ ምስጋናውን ስለ ጉዳዩ ጠየቀናቸው በሰጡት ምላሽ፤ ችግሩ መኖሩን አምነው፤ ከፌደራል እስከ ክልል ካሉ የሲቪል ሠርቪስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ችግሩን ለመፍታትና ተመራቂዎች በተማሩበት መስክ የስራ እድል እንዲያገኙ ጥረት መደረጉንና አሁንም ጥረቱ እንደቀጠለ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ “ችግሩ ጐልቶ የሚታየው አዲስ አበባ ባሉ የ2003 ተመራቂዎች ላይ ሲሆን በተቀሩት አመታት የተመረቁ በርካታ ተማሪዎች የትምህት ክፍሉ ባደረገው ጥረት በአማራ፣ በትግራይና በደቡብ ክልሎች የስራ መደብ ተፈጥሮላቸው ተቀጥረው እየሠሩ ነው፤ በአዲስ አበባና በተቀሩት ክልሎች ግን እስካሁንም ለትምህርት መስኩ እውቅና ለመስጠት ማንገራገሮች አሉ” ብለዋል-አቶ ሲሳይ፡፡ በ2002 ዓ.ም የፌደራል ሲቪል ሠርቪስ ሚኒስቴር በሁሉም የክልል መስተዳድሮች በሚገኙ ወረዳዎች ሣይቀር በዚህ የትምህርት መስክ የተመረቁ ስራ ፈላጊዎች የሚሣተፉበት የስራ መደብ ተፈጥሮ ቅጥሮች እንዲከናወኑ የሚያዝ መመሪያ መተላለፉን ያስታወሡት አቶ ሲሣይ፤ መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ ግን ቸልተኝነት መስተዋሉን ገልፀዋል፡፡ ይሁን እንጂ የትምህርት ክፍሉ አሁንም ቢሆን ሠፊ የስራ እድል ያለው በመሆኑ አመለካከቱን ለመቀየርና ሁሉም ተመራቂዎች ስራ እንዲያገኙ ለማድረግ ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር በሠፊው እየተነጋገሩበት እንደሆነ አቶ ሲሣይ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የትምህርት ክፍሉ በግለሰቦች በጐ ፈቃድ ነው የተከፈተው የሚባለው ግን አቶ ሲሳይ አይቀበሉትም፡፡ “ዲፓርትመንቱ በዩኒቨርስቲው የተከፈተው ህጋዊ ሆኖ ነው፤ መጀመሪያ የፍላጐት ጥናት (need assesment)፣ ከዚያም የተለያዩ ወርክሾፖች ተካሂደው ነው ወደ ስራ የተገባው” ሲሉም አስረድተዋል፡፡

Read 2031 times