Saturday, 12 October 2013 13:08

ሳውዝ ስታር ኢንተርናሽናል ሆቴል-የሀዋሳ ፈርጥ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(6 votes)
  • ለግንባታው 246 ሚ. ብር ወጥቷል 
  • የኦሎምክፒክ ደረጃ ያለው መዋኛ፣ ሲኒማ ቤቶች፣ ናይት ክለብ … ይገነባሉ 
  • 8 ሰዎች የሚይዘው ጃኩዚ ውሃ የማያበላሸው LCD ቲቪ አለው

ሳውዝ ስታር ኢንተርናሽናል ሆቴል በደቡብ ኢትዮጵያ ከአዲስ አበባ 275 ኪ.ሜ ላይ በሀዋሳ ከተማ ተገንብቶ በቅርቡ ሥራ የጀመረ አዲስ ዘመናዊ ሆቴል ነው፡፡ “ሀዋሳ፣ የቱሪስት መዳረሻ እየሆነች ነው፡፡ የውጭ አገርና የአገር ውስጥ ቱሪስቶች፣ በግል፣ በቡድን፣ በቤተሰብ የሚመጡባት ከተማ ሆናለች፡፡ እንግዶቻችን ሲመጡ የሚያርፉበት ብቻ ሳይሆን፣ በቆይታቸው የሚዝናኑበትና የተሟላ ምቾት የሚያገኙበት ዘመናዊ ሆቴል አዘጋጅተን እየጠበቅናቸው ነው” ይላሉ፤ የሳውዝ ስታር ኢንተርናሽናል ሆቴል ባለቤት ተወካይ አቶ መኳንንት አሰፋ፡፡
“በአካባቢያችን ከሚገኙ ሆቴሎች የምንለይበት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ 4 ባር እና 4 ሬስቶራንቶች የተለያየ መጠቀሚያ ዕቃዎችና (ፋሲሊቲ) ዋጋ ያላቸው 5 ዓይነት መኝታ ክፍሎች፣ … አሉን፡፡

ስለዚህ እንግዳው ሳውዝ ስታር ኢንተርናሽናል ሆቴል ገባ ማለት፣ በፈለገው ቦታ፣ በፈለገው ሁኔታ መዝናናት፣ በፈለገው ደረጃና ዋጋ ክፍሎችን መያዝ ይችላል፡፡
“ለምሳሌ ስታንዳርድ፣ ትዊን፣ ፋሚሊ፣ ዴሉክስ፣ ኤግዚኩቲቭ ዴሉክስ ሱት ቤድሩም፣ የተሰኙ ክፍሎች አሉን፡፡ እንግዳው እንደአቅሙ መከራየት እንዲችል አማራጮች ቀርበውለታል፡፡ ከቁርስ እስከ እራት የሚስተናገድበት ኦል ዴይ ሬስቶራንት አለ፡፡ በቡድን (ግሩፕ) የሚመጡ ሰዎች እየተወያዩ ምሳም ሆነ እራት የሚበሉበት ፕራይቬት ዳይንግ ሩም፣ ቡና ለመጀመሪያ ጊዜ በተገኘባት ስፍራ ማንኪራ የተሰየመ ማንኪራ ጋርደን ካፌ፣ አናት (ቴራስ) ላይ እስከ 200 ሰዎች መያዝ የሚችል ሬስቶራንት አለን፡፡
“አራተኛ ፎቅ ላይ ታቦር ተራራን፣ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን፣ ሀዋሳ ሐይቅንና በአጠቃላይ ከተማዋን እየቃኙ የሚዝናኑበት ታቦር ላውንጅ ባር፣ ሁለተኛ ፎቅ ላይ ጢያ ፑል ባር፣ ሎቢ ባር፣ ትኩስ ነገር፣ ቢራ፣ ድራፍት፣ … የሚስተናዱበት ማንኪራ ጋርደን ካፌ አለ፡፡ ደንበኛው ብዙ አማራጮች ስላሉት በፈለገው ቦታ ይዝናናል ማለት ነው፡፡

ይኼ ለየት ከሚያደርጉን ነገሮች አንዱ ነው፡፡
“ሌላው ደግሞ ለእንግዶቻችን ደህንነት የምናደርገው ጥንቃቄ (ሴፍቲ ኤንድ ሴኩሪቲ) ነው። እኛ ጋ ያረፈ እንግዳ ደህንነቱ በ68 ካሜራዎች ይጠበቃል፡፡ ካሜራዎቹ የቀረፁትን ምስል እስከ 6 ወር ማቆየት ይችላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቃጠሎ መነሳቱን የሚጠቁም ፋየር አላርም ሲስተም፣ ጪስ ጠቋሚ (ስሞክ ዲተክተር)፣ … በአጠቃላይ፣ እንግዶቻችን የደህንነት ስጋት እንዳይገባቸው ከፍተኛ ጥረት አድርገናል፡፡ ዋነኛው ለየት የሚያደርገን ነገር፣ የሆቴላችን የጥራት (ኳሊቲ) ደረጃ ነው፡፡ ከግንባታ ጀምሮ የተሠራበት ማቴሪያል፣ ፈርኒቸርስና ለሆቴል መገልገያ የምንጠቀምባቸው ዕቃዎች (ሆቴል ዩቲሊቲስ) የዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃን የጠበቁ ናቸው፡፡” ይላሉ አቶ መኳንንት፡፡
ብዙ ጊዜ የሚያምር ውብ የሆቴል ሕንፃ ተሠርቶ፣ የጥራት ደረጃቸው ከፍተኛ በሆኑ ዕቃዎች ተሟልቶ ሠራተኞቹ ስልጠና ስለማይሰጣቸው ከፍተኛ የመስተንግዶ ችግር ያጋጥማል፡፡ የዚህ ዓይነት ችግር እንዳያጋጥም፣ ሳውዝ ስታር አስቀድሞ ተዘጋጅቶበታል፡፡ ከዚህ አንፃር፣ ግንባታውን፣ የቁሳቁስ መረጣና ግዢውን፣ የሰው ኃይል ምልመላና ቅጥሩን … ባለቤቱ ብቻቸውን አልፈፀሙትም። በአገራችን ባልተለመደ ሁኔታ አማካሪ ድርጅት ቀጥረው ነው ያሠሩት፡፡
“ምንም ዓይነት ሆቴል ቢሠራ፣ የመጨረሻ ግቡ፣ ደንበኛውን ማስደሰትና ማዝናናት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር፣ ከሕንፃው ግንባታ ጀምሮ “ኤሌመንት ሆስፒታሊቲ ኮንሰልታንሲ” ከሚባል አማካሪ ድርጅት ጋር ተፈራርመን፣ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ እየተከታተለ ነበር፡፡ ይህ ድርጅት ሆቴሎች ሲገነቡ ማማከርና በቀጣይም ማደራጀት ነው ሥራው። ሠራተኛ የመቅጠር፣ የማሠልጠንና የመከታተል ኃላፊነት አለበት፡፡ ስለዚህ፣ ሠራተኞች ኢንተርቪው ተደርገው፣ ተመልምለውና ተቀጥረው ወደ ሥልጠና የገቡት በአማካሪ ድርጅቱ በኩል ነው። ከዚህ በኋላ ነው ሆቴሉ የተከፈተው፡፡ የሆቴሉ ማኔጅመንት አባላት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች ከፍተኛ የሙያ ብቃትና ልምድ እንዲሁም ኃላፊነት በነበራቸው ፕሮፌሽናሎች ነው የተዋቀረው፡፡” በማለት አቶ መኳንንት አስረድተዋል፡፡
በትላልቅ ድርጅቶችና ሆቴሎች ሳይቀር ማኔጅመንቱና ሠራተኛው አይስማሙም፤ ፍ/ቤት የሚቆሙበት ጊዜም አለ፡፡ ሳውዝ ስታር ይህ ችግር እንዳከሰት ምን እያደረገ ይሆን? ለዚህ አቶ መኳንንት ምላሽ ሲሰጡ፤ ሆቴሉ ሁለት ዓይነት እንግዶች እንዳሉት ገልጸዋል፡፡ “አንደኛው ሠራተኛው ሲሆን ሁለተኛው ወደ ሆቴሉ የሚመጣው ደንበኛ ነው። ሠራተኞቹን በደንብ ስትይዛቸው፣ እነሱ ደግሞ ደንበኛውን በደንብ ያስተናግዳሉ፤ ለማኔጅመንቱ ሁለቱም እንግዶች ስለሆኑ በሚገባ እየተንከባከብን እንይዛቸዋለን፡፡ ሠራተኞቹ ባላቸው የሥራ ተነሳሽነትና ቅልጥፍና ምንም ዓይነት ቅሬታ እንደሌለ እያየን ነው፡፡ ሠራተኞቹ ፕሮቪደንድ ፈንድ ይቆረጥላቸዋል፣ የትራንስፖርትና የሕክምና አገልግሎት ያገኛሉ፤ ምግብና ንጽህናም ከሆቴሉ ያገኛሉ…” ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሆቴሉ 200 ቋሚ ሠራተኞች አሉት፡፡ ግንባታው አራት የፈጀ ሲሆን በየዓመቱ ለ200 ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥሮ እንደነበር አቶ መኳንንት ገለፀዋል፡፡ በሆቴል ኢንዱስትሪ ሳውዝ ስታር ለግንባታ የወሰደው አራት ዓመት አጭር ጊዜ ነው ያሉት አቶ መኳንንት፤ የክልሉ መንግሥት በሰጣቸው 12ሺህ ካ.ሜ የማስፋፊያ ቦታ ላይ ሀዋሳን በጣም ጥሩና ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻና መዝናኛ ከተማ ለማድረግ የሚጐድሏትን ነገሮች በአጭር ጊዜ እንደሚያሟሉ ገልፀዋል፡፡
የሕፃናት መጫወቻ፣ በሁሉም ወቅት የሚያገለግል የኦሎምፒክ ደረጃ ያለው መዋኛ፣ ሲኒማ ቤቶች፣ የተለያዩ የስፖርት መጫወቻዎች፣ ትልቅ አዳራሽ፣ አሁን ካለውና 200 መኪኖች ከሚይዘው ተጨማሪ የመኪና ማቆሚያ፣ ትልቅ ሞል፣ ናይት ክለብ፣ ጂምናዚየም፣ … በማስፋፊያው ለመሥራት ከታቀዱት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ሳውዝ ስታር ኢንተርናሽናል ሆቴል 114 ክፍሎች አሉት፡፡ 96 ስታንዳርድ፣ 4 ትውንስ፣ 7 ፋሚሊ፣ 4 ኤግዚኩቲቭ ዴሉክስና 3 ዴሉክስ ሱት ክፍሎች ሲኖሩት ለግንባታው 246 ሚሊዮን ብር ወጥቷል። ሆቴሉ ስፓ (የሴቶች መዋቢያ)፣ ጃኩዚ ስቲም፣ ሳውና ባዝና ማሳጅ (መታሻ) ክፍሎች አሉት፡፡ “በሪሞት ኮንትሮል የሚገባና የሚወጣ፣ ውሃ የማያበላሸው LCD ቲቪ ያለው፣ 3ሜ ከ20 ሳ.ሜ ስፋትና 8 ሰዎች ማስተናገድ የሚችል ጃኩዚ መያዛችን ልዩ ያደርገናል፡፡ ዓላማችን በሀዋሳም ሆነ በአዲስ አበባ ምርጥ ከተባሉ ሆቴሎች አንዱ መሆን ነው” ብለዋል ተወካዩ፡፡
ሆቴሉ ባለስንት ኮከብ ነው ማለታችሁ አይቀርም፡፡ አቶ መኳንንት እንደሚሉት፤ እስካሁን ባለው ባለ 5 ኮከብ ሆቴል የሚያሰኘውን መመዘኛ አሟልተዋል፡፡ “የሚጐድል ነገር አለ ከተባለም እናሟላና በእርግጠኝነት 5 ኮከብ እንወስዳለን” ብለዋል፡፡
የምግብ ቤቱ ሼፎች ከፍተኛ ሙያና ልምድ ያላቸው፣ በትላልቅ ሆቴሎች የሰሩ ናቸው፡፡ “ለምሳሌ፣ ዋናው ሼፍ በሸራተን አዲስ ሆቴል ለ15 ዓመት የሠራ ሲሆን፣ ምክትሉም በዚያው ሆቴል ለብዙ ዓመት የሠራ፣ ከፍተኛ ልምድና እውቀት ያለው ነው፡፡ የመጠጥ (ቤቬሬጅ) ማናጀሩም በሼራተንና በሌሎች ከፍተኛ ሆቴሎች የሠራ ነው፡፡

በሌሎች ደረጃ ያሉት ሠራተኞቻችንም ከፍተኛ ልምድና ሙያ ያላቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ሙያተኞች ጥሩ ውጤት እንደምናገኝ እንተማመናለን” በማለት ሠራተኞቻቸውን አሞካሽተዋል፡፡
እንዲህ ከሆነ ዋጋው አይቀመስም ብላችሁ ይሆናል፡፡ አቶ መኳንንት ግን በዚህ ሐሳብ አይስማሙም፡፡ “ሆቴሉ ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟላ ቢሆንም፣ የተሰራው ለኅብረተሰቡ ስለሆነ ማንኛውም ካፌና ሬስቶራንት ገብተው በሚበሉበትና በሚጠጡበት ዋጋ እዚህም ገብተው መጠቀም ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ፣ ቡና 10 ብር፣ ድራፍት 15 ብር፣ የረዥም ዓመት ልምድ ባላቸው ፕሮፌሽናሎች የተሠራውና ትክክለኛ የፒዛ ጣዕም ያለው ፒዛችን 65 ብር ሲሆን ሌላ ጋ የሚሸጠው ግን ከመቶ ብር በላይ ነው፡፡ ስለዚህ ዋጋችን ተመጣጣኝና የኅብረተሰቡን አቅም ያገናዘበ ነው ብለን እናምናለን፡፡” በማለት ገልጸዋል፡፡
አሁን ደግሞ አለፍ አለፍ እያልን ክፍሎቹን እንቃኝ፡፡ ለሥራም ሆነ ለመዝናናት ሀዋሳ ሄደው ሳውዝ ስታር ኢንተርናሽናል ሆቴል ሲያርፉ፣ ወደ ክፍል የሚሄዱት መስተዋት በተገጠመለት (ፓናሮሚክ) ሊፍት የአካባቢውን ውበት እየቃኙ ነው፡፡ ከሊፍቱ እንደወረዱ፣ ወለሉና ኮሪደሩ ከጥግ እስከ ጥግ በሚያምር ምንጣፍ ተውቦ ያገኙታል። በየፎቁ፣ አረፍ የሚሉበት ወይም ከቤተሰብና ከጓደኛ ጋር የሚጫወቱበት ወይም ስለ ቢዝነስ የሚነጋገሩበት ሰፊ ማረፊያ አለ፡፡ ወደ ክፍል ሲሄዱ በሩ የሚከፈተው በካርድ ነው፡፡ ካርዱን ወደ በሩ ጠጋ አድርገው እጀታውን ጫን ሲሉት በሩ ይከፈታል፡፡ በሩ ብቻ ሳይሆን የክፍሉ ኤሌክትሪክም የሚሠራው በካርድ ሲስተም ነው፡፡ ካርዱን ግድግዳ ላይ ባለው ማስቀመጫ ውስጥ ሲከቱት መብራት ይመጣል፡፡ መፀዳጃ ክፍሉን ወደ ጐን ትተው ወደ ዋናው ክፍል ሲዘልቁ በግራና በቀኝ የራስጌ መብራት ያለው ያማረ ሰፊ ኩዊን ሳይዝ አልጋ ያገኛሉ፡፡

ስልክ፣ ቲቪ መቀመጫ ሶፋና ጠረጴዛ፣ ድሬሲንግ ቴብል፣ ቁምሳጥን፣ ሚኒባር፣ …ያገኛሉ፡፡ ቁም ሳጥኑ ውስጥ የሌሊት ልብስ (ጋዋን)፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የልብስ መስቀያዎች፣ እንግዳው ውድ ዕቃዎቹን በራሱ ኮድ የሚቆልፍበት ካዝና (ሴፍቲ ቦክስ)፣ ልብስዎን ማሳጠብ ቢፈልጉ የሚከቱበት የላውንደሪ ከረጢት …ያገኛሉ፡፡ ሁሉም ክፍሎች በረንዳ ወይም ባልኮኒ አላቸው፡፡ እንግዳው በመስኮት በኩል አካባቢውን እየቃኘ ሊዝናና ይችላል፡፡ ሆቴሉ፣ ከሀዋሳ መስቀል አደባባይ ፊት ለፊት መንገድ ዳር የተሰራ ቢሆንም ክፍል ውስጥ ሆነው የውጪ ድምፅ አይሰማም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ መስኮቱ ድርብ መስተዋት (ደብል ግሌዝድ) ስለሆነ ነው፡፡ የመስተዋቱ መጋረጃ ብል የማይበላው ወይም የሲጋራ ቁራጭ በቀላሉ ከማያቃጥለው ማቴሪያል የተሠራ ነው፡፡
4ኛ ፎቅ ላይ ያሉት ኢግዚኩቲቭ ዴሉክስ ክፍሎች ለአገር መሪዎች፣ ለአምባሳደሮች፣ ለትላልቅ የቢዝነስ ሰዎች … የተዘጋጁ ናቸው፡፡ እነዚህ ክፍሎች በተለያዩ የአገራችን የቦታ ስሞች፣ ማለትም በአክሱም፣ በጣና፣ በኤርታሌና በባቢሌ የተሰየሙ ሲሆን ስታንዳርዱ ክፍል ካለው መገልገያ በተጨማሪ የሻይ ወይም ቡና ማፍያ፣ ካውያ፣ ሳሎን አላቸው። አልጋው ሁለት በሁለት ሜትር በመሆኑ በጣም ሰፊ ነው፡፡ 2ኛ ፎቅ ላይ ደግሞ አልጋ የያዙ ሰዎች ብቻ በነፃ የሚቀጠሙበት መዋኛ አለ፡፡ ዴሉክስ ሱት ክፍሎች ስቲም ባዝ አላቸው፣ እንግዳ ቢመጣባቸው የሚጠቀሙበት ከዋናው መፀዳጃ ቤት የተለየ ሌላ መፀዳጃ ቤትም አላቸው፡፡
በብዙ ሆቴሎች መፀዳጃ ቤት የሚገኙትን የቆሻሻ መጣያዎች የሚጠቀሙት፣ በእጅ ወይም በእግር በመክፈት ነው፡፡ እዚህ ግን አጠቃቀሙ ይለያል፡፡ ቆሻሻ መጣያዎቹ ሴንሰር የተገጠመላቸው ስለሆኑ፣ እንግዳው እጁን ሲያስጠጋ ይከፈቱና ከተጣለባቸው በኋላ ይዘጋሉ፡፡ ስለዚህ እንግዳው ከቆሻሻ መጣያው ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ ሳይፈጥር ደረቅ ቆሻሻ ያስወግዳል ማለት ነው፡፡

Read 3778 times