Saturday, 12 October 2013 13:01

የኩዌትና ኢትዮጵያ ግንኙነት

Written by  ኤልሳቤት እቁባይ
Rate this item
(1 Vote)

ኢትዮጵያና ኩዌት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት የዛሬ 60 ዓመት ገደማ ሲሆን ኤምባሲዎቻቸውን የከፈቱት ደግሞ በ1997 ዓ.ም ነው፡፡
በሁለቱ አገሮች ግንኙነት፣ በኩዌት ስላሉ ኢትዮጵያውያንና ኩዌት በመጪው ህዳር ወር በምታስተናግደው የአፍሪካ - አረብ ጉባኤ ዙርያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ኤልሳቤት እቁባይ በኢትዮጵያ የኩዌት አምባሳደር ከሆኑት ራሺድ አል ሀጅሪ ጋር ያደረገችው አጭር ቃለ ምልልስ እንዲህ ተጠናቅሮ ቀርቧል፡፡

ኩዌት ከኢትዮጵያ ጋር ስላላት ግንኙነት …
ሁለቱ አገሮች ረጅም እድሜ ያስቆጠረ እና ታሪካዊ ግንኙነት አላቸው፡፡ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በጣም ጠንካራ ነው፡፡ በሁለቱ አገሮች ባለስልጣኖች መካከል የሚደረጉ የስራ ጉብኝቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ግንኙነቱ ከፍ እያለ እንደሆነ ያሳያል። የተከበሩ የኩዌት አሚር ሼክ ሱባህ አልአህመድ አልሱባህ፤ የአፍሪካ ህብረት እና የኢትጵያ የክብር እንግዳ ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝም ባለፈው ግንቦት በኩዌት የስራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በቆይታቸውም የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ወደተለያዩ ዘርፎች እንዲያተኩር እና ተግባራዊ እንዲሆን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል፡፡ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት በቃላት መግለፅ ይከብደኛል፡፡ እኔ የኩዌት አምባሳደር ብቻ ሳልሆን ለኢትዮጵያም ራሴን እንደ አምባሳደር ነው የማየው፡፡
ኩዌት ለኢትዮጵያ ስለምታደርገው ድጋፍ …
በሁለቱ አገሮች መሀል ያለው የትብብር ግንኙነት ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው፡፡ የኩዌት የልማት ፈንድ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረጉ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ያግዛል፡፡ ከዚህ በፊት ኩዌት ለረጅም ጊዜ በሚከፈል ብድር ለኢትዮጵያ የአውሮፕላን ነዳጅ ታቀርብ ነበር፡፡ የኩዌት የልማት ፈንድ ማናጀር፣ ከኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ ሶፊያን አህመድ ጋር ተወያይተው፣ የአክሱም የውሀ ፕሮጀክት ድጋፍ በሚያገኝባት ሁኔታ ላይ ተስማምተዋል፡፡ የመንገድ ስራ እና ሌሎች ፕሮጀክቶችንም ይደግፋል፡፡ ሌላው የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ነው፡፡ እንደሚታወቀው አዲሱ የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የተሠራው ከኩዌት በተገኘ ገንዘብ ነው፡፡
አውሮፕላን ማረፊያው ብዙ መንገደኞችን የሚያስተናግድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ነው፡፡ ለዚህ ስራ ድጋፍ በማድረጋችን እጅግ ደስተኞች ነን። ወደ አገሪቱ የሚገባ ሠው መጀመሪያ የሚያገኘው የሁለቱን አገራት ወዳጅነት በሚያሳየው አውሮፕላን ማረፊያ መሆኑ ያኮራናል፡፡
በኩዌት ስለሚገኙ ኢትዮጵያውያን …
የኢትዮጵያና የኩዌት ግንኙነት አንዱ ዘርፍ የሚባለው ስራና ሠራተኞችን የሚመለከት ነው። በኛ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ 93 ሺ ይደርሳሉ ብዬ ነው የማስበው፡፡ ጥሩ የሆነ ተሳትፎ ያደርጋሉ፡፡ መልካም እንቅስቃሴ አላቸው፡፡ ወደ እኛ አገር የሚደረገው እንቅስቅሴ በተስተካከለ መልኩ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ የሚመጡት ሠዎች የስራ ልምድ ያላቸው፣ የተማሩ፣ ስልጠና የተሰጣቸው እንዲሆኑ እንፈልጋለን፡፡ ምክንያቱም በኛ አገር ለሚኖራቸው እንቅስቃሴ የተመቻቸ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው ያደርጋል፡፡ ከኩዌት ህዝብ ጋርም ለመግባባት የተሻለ እድል ይሠጣቸዋል። የኢትዮጵያውያን ሚና ከፍተኛ ነው፣በኛ በኩል ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የሌበር ስምምነት ተፈራርመናል፡፡ የሚመጡት ሠዎች አቅማቸው ከፍ ያለ እንዲሆን ተገቢውን ጥረት እናደርጋለን፡፡
ኩዌት ከአፍሪካ ጋር …
ኩዌት ከአፍሪካ አህጉር ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመጀመር ቀዳሚ ናት፡፡ የኩዌት የልማት ፈንድ አፍሪካ ውስጥ ከፍተኛ ተሳተፎ ያደርጋል። የልማት ፕሮጀክቶችን ይደግፋል፡፡ የተከበሩ የኩዌት አሚር፤ የአፍሪካ ህብረት የክብር እንግዳ መሆናቸው፣ የግንኙነቱን ጥንካሬ የሚያሳይ ነው። የኩዌት የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አፍሪካ ውስጥ ገብተው የተለያዩ ስራዎችን ለመስራት ከተለያዩ አገራት ጋር ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ በአፍሪካ ህብረት የጤና ማዕከል ለማቋቋምም እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡
ስለ አፍሪካ አረብ ጉባኤ …
በኩዌት አስተናጋጅነት የሚካሄደው ጉባኤ በመጪው ህዳር ወር ይካሄዳል፡፡ ከአፍሪካ አገሮች ጋር ያለውን ግንኙነት ከፍ ለማድረግ ያለመ ነው። የበፊቶቹ ጉባኤዎች ፖለቲካዊ ይዘት ነበራቸው፡፡ የአሁኑ ግን በልማት እና ትብብር ላይ የሚያተኩር ይሆናል፡፡ በኢኮኖሚው ዘርፍ የሚታቀዱ ዕቅዶች ተግባራዊ እንዲሆኑ መከናወን ስላለባቸው ስራዎች ይወያያል፡፡ በአፍሪካ በኩል ሠፊ ተሳትፎ ይጠበቃል።

Read 1896 times