Saturday, 12 October 2013 12:57

“የብርሃን ፈለጐች”ን ተከትለን ስንጓዝ “የብርሃን ፈለጐች”ን ስንጀምር

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“የብርሃን ፈለጐች” ከቀደሙት ሁለት የደራሲው ሥራዎች (አጥቢያና ቅበላ) በገፁ ብዛት ዳጐስ ብሎ የቀረበ ከመሆኑ አንፃር፣ በበቂ የተለፋበትና የተደከመበት ሥራ እንድንጠብቅ የሚያደርገን ነው፡፡ በተለይም ደራሲው “አጥቢያ” እና “ቅበላ”ን አከታትሎ ለአንባቢ ካደረሰባቸው ከሁለት ዓመታት ያነሰ ጊዜ አንፃር “የብርሃን ፈለጐች” ከአራት ዓመታት በኋላ ሲመጣ፣ ከቀደሙት ሥራዎቹ ከአንባቢ ያገኘውን አስተያየት እንዲሁም የራሱን ስህተትና ክፍተት ሞልቶና አርሞ በተሻለ መገለጥ እንደመጣ መገመት የሚከብድ አልነበረም፡፡ በእርግጥም “የብርሃን ፈለጐች” የፈጠራ ድርሰት የመገምገሚያ መሠረታዊ አላባውያን በሆኑት በታሪክ ፈጠራ፣ በዘይቤ፣ በግጭት፣ በተዓማኒነት፣ በልብ ሰቀላና በአተራረክ ቴክኒክ እንዲሁም በሌሎች መመዘኛዎች የተሳካ ሥራ ለመሥራቱ የያዝኩትን ቅድመ ግምት ያጠናከረልኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
ይሁንና ከላይ የጠቀስኳቸውን መሠረታዊ የመገምገምያ ነጥቦች ተጠቅሜ በ“የብርሃን ፈለጐች” ዙሪያ ቅኝት ከማድረግ ይልቅ ለዛሬ የመጽሐፉን ታሪክ ከዋናው ገፀ-ባህርይ አንፃር ለመፈተሽና በዚሁ ላይ ተመስርቼም የደራሲውን የአፃፃፍ ፈለግ በመመርመር፣ አንዳንድ በወጉ መረዳት የሚገቡንን ነጥቦች ማስቀመጥን መርጫለሁ፡፡
ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ ለዚህ መጽሐፉ መግቢያ የሚሆን ነገር አላበጀለትም፡፡ ከዚያ ይልቅ ሃያሲ አብደላ ዕዝራ ከሕትመት በፊት በእጁ የገባውን ረቂቅ ተመልክቶ በተረዳውና በገባው መጠን የሰጠውን አስተያየት በመጀመሪያው ገጽ እና ከእዚያው ውስጥ የተቀነጨበውን ደግሞ በመጽሐፉ የኋላ ሽፋን ላይ እንዲሰፍር አድርጓል፡፡ እርግጥ ነው ደራሲው ሥራው ለአንባቢ ከመድረሱ በፊት ለእንደ አብደላ ዕዝራ ዓይነቱ በኢትዮጵያ የስነ ጽሑፍ ሂስ ታሪክ አንድ ሥፍራ ለሚይዝ ባለሙያ አስተያየት አስቀድሞ ማቅረቡ ለአንባቢ ያለውን አክብሮትና ግምት እንዲሁም በሥራው ላይ ያለውን ትጋት የሚያሳይ ነው፡፡ ይሁንና በመግቢያ መልክ የተሰጠውን አስተያየት ቀንሶ በኋላ የመጽሐፉ ሽፋን ላይ መድገሙ ለምን አስፈላጊ እንደሆነ ግልጽ አልሆነልኝም፡፡
“አንባቢያን መጽሐፉ ከዚያ የላቀም ይሁን ያነሰ ታሪክ በውስጡ አልያዘምና አዲስ ነገርን በመፈለግ አትድከሙ” በማለት ሊያቆም ፈልጐም ከሆነ “blurb” ሆኖ የሰፈረልን ማሳሰቢያ በቂ በሆነን ነበር፡፡ ከዚያ ይልቅ (ግዴታም ባይሆን) ደራሲው በራሱ ብዕር የመግቢያውን ሥፍራ በመሰለው የግሉ እምነትና አስተሳሰብ ቢይዘው ኖሮ፣ ቢያንስ በአንባቢያን ዘንድ ስለመጽሐፉ ልዩ ምልከታና አስተያየት ሊፈጠር የሚችልበት የተሻለ አጋጣሚ በተፈጠረ ነበር እላለሁ፡፡
የዘመን ጉዳይ
“የብርሃን ፈለጐች” የሁለት ዘመን ትውልዶች የሚገለጡበት ልብ - ወለድ ነው፡፡ ይኸን ለማለት ያስገደደኝ በእኛ ሀገር የዘመንም ሆነ ትውልድ ሽግግርና ለውጥ በዓመታት ቀመር የሚሰላ ሳይሆን ዙፋን ላይ በተቀመጠው መንግሥት ምንነትና የአገዛዝ ባህርይ የሚወሰን ሆኖ ስለሚሰማኝ ነው፡፡ የአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ትውልድ ከደርግ፣ የደርጉ ደግሞ ከኢህአዴግ የሚለይበት የየራሱ መገለጫ ባህርይ እንደተሸከመው ማለት ነው፡፡ እርግጥ ነው በመጽሐፉ ውስጥ የምናገኘው ታሪክ የተፈፀመበትን ዘመን ደራሲው እንድንረዳ የሚያደርገን በገፀ ባህርያቱ አለባበስ፣ አኳኋንና አልፎም ንግግር ነው፡፡
“የግንፍሌ ማለዶች” በመጽሐፉ ውስጥ በቅድሚያ የምናገኘው የታሪክ ክፍል ሲሆን ዘመኑን ለመገመት ለሚነሳ አንባቢ ግን የራሱን ፈተና ከፊቱ ማስቀመጡ የሚቀር አልሆነም፡፡ የታሪኩ ዋና ገፀባህርይ የሆነው መክብብ፤ የልጅነት ዕድሜውን ያሳለፈባትን ግንፍሌን ከቤተሰቡ፣ ከጓደኞቹ፣ ከጐረቤቶቹና ከሠፈሩ ሰዎች ጋር ባለው ተራክቦ በሚገባ እንድናያት ደራሲው ማድረጉን ሳንክድ ነገር ግን የዘመን ጥያቄ ሲነሳ በአፄው ዘመነ መንግሥት ለመሆኑ ከግምት እንዳናልፍ የሚያደርጉን ሁለት ጉዳዮች እናገኛለን። የመጀመሪያው “ገዳማይ” የሚለው ዘፈን ተደጋግሞ መምጣት ሲሆን (ዘፈኑ በኋላ በደርግ ዘመን በሙሉቀን የተቀነቀነ ቢሆንም ከዐፄው ዘመን የወረሰው በመሆኑ) እና ሁለተኛው የአባቱ የፀጉር አቆራረጥ ከ“ፕሪስሊ” ጋር መገናኘቱ ነው፡፡ ዘፈኑም ሆነ የኤልቪስ ፕሪስሊ የፀጉር ፋሽን በሀገራችን ሰፊ ተቀባይነት የነበራቸው በ60ዎቹ መጀመሪያ ከመሆኑ ጋር በተገናኘ ግንፍሌን የምንመለከትበት መነጽርም የአፄው ዘመን እንዲሆን ብንወስን እንኳን ሌላ ፈተና ደግሞ መምጣቱ አልቀረም፡፡ ይኸውም ዘፈኑ የሚቀርብልን በመክብብ አባት የትዝታ እንጉርጉሮ በመሆኑ፣ ዘመኑን ወደ ደርግ የሚጐትተው ሲሆን የፀጉር አቆራረጥ ዘይቤውም ቢሆን አባቱ በውስጡ ለዓመታት ከተቆራኘው የሙዚቃ ፍቅር ማምለጥ አለመቻሉን የሚያስረግጥ ማሳያ እንጂ የሚገኝበትን ትውልድ የዘመን ፋሽን የመግለጥ አቅሙ ደካማ ከመሆኑ ላይ ነው፡፡ ምናልባት በዚሁ ዘይቤ ሌላ ገፀ ባህርይ ተስሎልን ቢሆን ወይም ተጨማሪ ገለፃ ከመቼት አንፃር ሰፍሮልን ቢሆን በግንፍሌ የታሪክ ዘመን ላይ ጥያቄ ባልኖረንም ነበር፡፡
ወደሁለተኛውና የመጽሐፉ ሰፊ የታሪክ መሽከርከሪያ ወደሆነችው ሞጆ ስንሻገር፣ የዘመን ጥያቄ በደራሲው በቂ ምላሽ የተሰጠበት ሆኗል። ቢያንስ በሁለት ገፀ ባህርያት አማካይነት ሞጆ የተገለፀችበት ዘመን የአብዮቱ ዓመታት እንደነበሩ ግልጽ ነው፡፡ የናፍቆት አባት ተደጋጋሚ “የአብዮታዊት ኢትዮጵያ” ስብከትና የመምህርቱ ሙና ያለፈ የኢህአፓ ትዝታ ሞጆ በየትኛው ዘመንና ትውልድ ተስላ እንደቀረበችልን በቂ ማሳያ ናቸው፡፡
እዚህ ላይ የዘመን ጉዳይ በፈጠራ ድርሰት ውስጥ ቀዳሚውን ሥፍራ ሊያገኝ የሚገባበትን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥቼ ማስቀመጤ ምክንያቱ ግልጽ ይመሥለኛል፡፡ ይኸውም ማንኛውም የልብ ወለድ መጽሐፍ ለንባብ ሲበቃ፣ ደራሲው በውል የሚያውቀውን ዘመንና ሥፍራ የሚያሳይ መስታወት በአንባቢው ፊት የማቆሙን ግዴታ ከግምት በመክተት ነው፡፡ ድርሰት የቱንም ያህል የደራሲ የፈጠራ ውጤት ቢሆን ፍፁም ውሸት ተደርጐ የማይወሰደውም ከዚህ በመነሳት ነው፡፡ የፈጠራነቱ ባህርይ ውሸት ቢያደርገውም የሚፈጠሩት ገፀ ባህርያት፣ ጊዜያት (ዘመን)፣ ሥፍራዎች፣ ድርጊቶች … ወዘተ የገሃዱ ዓለም ነፀብራቅ በመሆናቸው ደግሞ “እውነት” ሊሆኑ የሚችሉ አድርገን መቀበላችን አይቀሬ ነውና፡፡
የአፃፃፍ ፈለግ
የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ ጉዳይ ወደሆነው በ “የብርሃን ፈለጐች” ውስጥ ወደተስተዋለው የአፃፃፍ ፈለግ ደግሞ እናምራና መጠነኛ ፍተሻ እናድርግ። እንግዲህ አንድ ደራሲ እንደሚገኝበት ዘመንና በዘመኑ እንደነገሰውም አስተሳሰብ፣ የራሱን የአፃፃፍ ፈለግ የመከተል ነፃነት እንደተጠበቀ የመሆኑ ጉዳይ ተሰምሮበት ነገር ግን የማኅበረሰቡን ልማድ፣ ወግ፣ ንቃተ ህሊና፣ መሻትና ፍላጐት ደግሞ ከግምት የከተተ መሆኑ ተመራጭ ያደርገዋል፡፡
እርግጥ ነው ደራሲ ከማኅበረሰቡ የተለየ ዓይንና ማስተዋል የታደለ እንደመሆኑ መጠን የተመለከተውንና የታዘበውን ወይም ያስደነቀውን እውነት በመሰለውና ባመነበት መንገድ የማስቀመጡ ነፃነት ለእሱ የተተወ ነው፡፡ ለምሳሌ በአፃፃፍ ስልቱ (Style) ዙሪያ አንድም በምርጫ ወይም በግላዊነት ላይ ተመስርቶ ድርሰቱን ለመፃፍ ይችላል፡፡ በምርጫ ስንል ለምሳሌ የቀለም ምርጫ የግሉ ነው፡፡ ውበትን ለመግለፅ ቀይ ቀለምን ምርጫው ያደረገ ደራሲ “ለምን?” የሚል ክርክር ሊነሳበት አይችልም፡፡ ከግላዊነትም አንፃር ለምሳሌ ረዥም ወይም አጭር ዐረፍተ ነገርን መርጦ መጠቀሙ፣ ተረትና ምሳሌ ማብዛቱ፣ የዘይቤ ምርጫው ሁሉ ከዚሁ የግላዊነት ነፃነቱ የሚመነጩ ናቸው፡፡
ይህ እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ ደራሲ አለማየሁ በ “የብርሃን ፈለጐች” ውስጥ ገንኖ የወጣበት የአፃፃፍ ፈለግ በዘመናችን በርካታ አለም አቀፍና አንዳንድ ጥቂት የሀገራችን ደራስያን (አዳም ረታ ተጠቃሽ ነው) በሥራዎቻቸው በስፋት የሚጠቀሙበት የ“Postmodernism” የአፃፃፍ ፈለግ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር የደራሲውን ሥራ ከመቃኘቴ በፊት ይኼ የአፃፃፍ ፈለግ ዋነኛ አትኩሮቱ ምን እንደሆነ በቀላል ማብራሪያ አንባብያንን ግንዛቤ ማስጨበጥ ያሻል፡፡
የ“Postmodemism” እሳቤ በኪነጥበብ ዘርፍ ለማቆጥቆጥ መነሻ የሆነው በኪነ-ሕንፃ (architecture) ጥበብ ላይ የተነሳው አዲስ አስተሳሰብ እንደነበር ይታመናል፡፡ ይኼ ፈለግ ሁለት መሠረታዊ ደረጃዎችን ተሻግሮ፣ በተለይ በ1950ዎቹና 60ዎቹ ያቆጠቆጠ ሲሆን ከእሱ በፊት ቀዳሚ የነበሩት ሁለት ፈለጐች የመጀመሪያው “Premodernism” ሲሆን በመቀጠል ደግሞ “modernism” በመባል ይታወቃሉ፡፡ በ “Premodernism” ማንኛውም የጥበብ ሰው የአስተሳሰቡ መሠረት አድርጐ በሥራው እንዲያንፀባርቅ የሚጠበቅበት መንገድ ከባህሉና ወጉ ወይም እምነቱ የመነጨ ሊሆን ይገባል የሚል ነበር፡፡ በተለይ ይኼን አስተሳሰብ በማራመድ ተጠቃሽ የሆነችው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ስትሆን ማንኛውም የፈጠራ ሥራ በባህልና እምነት ተፅዕኖ ሥራ መውደቅ እንዳለበት ቀዳሚ ተከራካሪ ሆና ለዘመናት ዘልቃ ነበር፡፡ ከዚያ በመቀጠል የመጣው የ“modernism” ፈለግ ደግሞ የሰው ልጅ አብርሆ መቃኘት ያለበት አዲስ ነገርን በማሰብና በተፈጥሮ ሳይንስ ሊሆን ይገባል እንጂ በባህልና ህግ እንዲሁም በእምነት መሪዎች አስተሳሰብ ሥር መውደቅ የለበትም የሚል ነው፡፡ የዚህ አስተሳሰብ መሠረቱ የሕይወት ትርጉምም ሆነ እውነት የሚመነጨው ከግለሰቡ አመለካከትና አቋም እንጂ በላዩ ከተጫነበት እምነትና ባህል ሊሆን አይገባም የሚል ነበር፡፡ እናም የዚህ ፈለግ አራማጆች ማንኛውም የፈጠራ ሥራ የቀደመውን ባህልና ወግ እንዲሁም አስተሳሰብ ወደ ጐን አስቀምጦ አዲስና ቀልብን የሚማርክ ነገር በመፍጠር ላይ ያተኮረ ሊሆን ይገባል ባይ ናቸው፡፡
የዚህ ፈለግ ተቃዋሚ ሆነው ብቅ ያሉት ደግሞ በተለይ በስነጽሑፍ ዘርፍ በ1970ዎቹ እ.ኤ.አ ገንነው የወጡት “Postmodernist” ናቸው፡፡ “Postmodernist” በዋነኛነት የሚያራምዱት አስተሳሰብ በቀላል አገላለፅ ሲቀመጥ የ“modernism” አስተሳሰብ የሆነውን አዲስና ማራኪ የፈጠራ ሥራ መከወንን ተቀብለው፣ ነገር ግን መሠረቱ ሊያደርገው የሚገባው የቀደመውን ወይም ነባሩን ባህልና ወግ እንዲሁም እምነት ሊሆን ይገባል የሚል ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የ “Postmodernist” የአፃፃፍ ፈለግ በዋነኛነት ለመመለስ የሚሻው ጥያቄ “የሰው ልጅ ማንነት (ሕልውና) በተፈጥሮ ውስጥ ያለው ሥፍራ ምን እንደሆነ” ፈልጐ ማግኘትን ነው። ለምን ተፈጠርኩ? ማነው የፈጠረኝ? የመፈጠርስ ዓላማ በፈጣሪ ወይስ በየግል የአስተሳሰብ አቋም የሚገለፅና የሚወሰን ነው? ከተፈጠርን በኋላስ በምድራዊ ሕይወታችን ለሚገጥመን ክፉም ሆነ በጐ አጋጣሚ ተጠያቂው የማኅበረሰቡ እምነትና ባህል? አካባቢያችንና ቤተሰባችን? ፈጣሪያችን? ወይስ ማን? የሚሉና መሰል ከውስጣዊ ማንነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን መንደርደሪያው ያደርጋል፡፡ ይሁንና የጥያቄዎቹ ምላሽ ሊፈለግ የሚገባው ደግሞ ግለሰቡም ሆነ ማኅበረሰቡ በተቃኘበት እምነት፣ ባህል፣ አስተሳሰብና ወግ ላይ ተመስርቶ ሊሆን እንደሚገባ “Postmodernist” ያሰምሩበታል፡፡
እንግዲህ ወደ “የብርሃን ፈለጐች” ስንመለስ፣ በአመዛኙ ይኸው የማንነት (የሕልውና) ጥያቄን መሠረቱ አድርጐ ከመቆሙ ባሻገር ለጥያቄው ምላሽ የሚያፈላልገው ደግሞ ከማኅበረሰቡ ባህልና ወግ ከዚያም ሲያልፍ በፈጣሪው ላይ ከገነባው እምነት የለሽ የመሆኑ እውነታ ነው፡፡ ለዚህ በቂ ማሳያ የሚሆነን ደራሲው በዋናው ገፀ ባህርይ መክብብ አማካይነት ደጋግሞ የሚያነሳውን የማንነት ጥያቄና ከቤተሰቡ እስከ ማኅበረሰቡ እንዲሁም ባህልና ወጉን አልፎም ፈጣሪውን የሚሞግትበት ስልት ይሆናል፡፡
ደራሲው ከመነሻው እንዲህ ዓይነቱን ጥያቄ የሚያነሳልን በመክብብ መፈንከት ይሆናል፡፡ መክብብ በጓደኛው ጋንጩር ተፈንክቶ በጓደኞቹ ሸክም ወደቤቱ ሲወሰድ ከመፈንከቱ በላይ ጥያቄ ፈጥሮበት ከራሱ ጋር ሙግት የሚያስገጥመውና ግርምት የሚፈጥርበት ከውስጡ የሚፈልቀው ደም ነበር፡፡
“አካላችን ውስጥ እንዳልነበር፣ የእኛ እንዳልሆነ በባዕድነት ዝም ብሎ መንዠቅዠቁ አስረገመኝ” (ገፅ 6)
ደራሲው በዋናው ገፀ ባህርይ ውስጥ ከጅምሩ የፈጠረው በራስ ላይ የሚነሳ የማንነት ጥያቄ፣ በቤተሰቡ ውስጥም የሚንፀባረቀው ብዙም ሳንጓዝ በእናቱ አማካይነት ይሆናል፡፡ የመክብብን እናት ማንነት የዘመን ወካይነቷን መነፅር አጥልቀን እንድናይ የምንጋበዘው በቤታቸዉ በሰፈነው ድባብ አማካኝነት ሲሆን ከግድግዳው መገርጣት፣ ከብርሃን ማጣቱ፣ እንደጐሬ ከመክበዱ … ወዘተ ጋር በተገናኘ ለእሱ ጭንቅ የሚፈጥርበት ክስተት በእናቱ ዘንድ ግን ተቃራኒ ስሜት የያዘና ከዚያ ያለፈ የመለወጥ ምኞትም የሚፈጥር አልሆነም፡፡ ለመክብብ የቤታቸው መገለጫ ከሆኑት “ብርሃን የሚውጡ” ቁሳቁሶችም ሆነ ስሜት ከሚያጨልመው ጣራና ግድግዳዉ መካከል ዓይን ሳቢ የነበረው የሚካኤል ስዕል ቢሆንም እሱም እንክብካቤ ተነፍጐና በጢስ ጠቁሮ በቤቱ መንፈስ የተዋጠ ሆኗል፡፡ ሕይወት ዕጣ-ፈንታው አድርጋ የለገሰችውን ድህነት፣ ቤተሰቡ በፀጋ ተቀብሎ መኖሩ ከልጅነቱ አልዋጥልህ ብሎ ጭንቁን የሚተነፍሰው መክብብ፤ ቢያንስ የእምነት መገለጫ የተደረገውን ስዕል እንኳን የመለወጥ ፍላጐት ከእናቱ ዘንድ ማጣቱ፣ እንደ ኑሮው እምነቱም በወደቀ ቤተሰብ ውስጥ ለመኖሩ ማንፀሪያ አድርጐታል፡፡
“ይሄ ምስል በአዲስ ይቀየር ብትባል እናቴ በጀ የምትል አይመስለኝም” (ገፅ 9) በማለት ድህነት ቤተሰቡ ላይ የፈጠረው የኑሮ ብቻ ሳይሆን የእምነት ዝንጋታ በመክብብ በኩል ሲነገረን፣ ደራሲውን የነበረው ባህል፣ ወግ፣ እምነት ላይ የተመሠረተ አዲስ ለውጥና መሻሻል ናፋቂ ሆኖ እናገኘዋለን። የ“Postmodernism” ፈለግ ይኸው ነው፡፡ የገፀ-ባህሪያቱን አስተሳሰብ፣ ስነ-ልቦና፣ እምነት፣ ምልከታ … ዘልቆ በመፈተሽ ከገሃዱ ዓለም እውነታ ጋር በንፅፅር የማቅረብና በአዲስ መንገድ የማስታረቅ ዓላማን አንግቦ የሚጓዝ፡፡
ደራሲው የማንነትን ጥያቄ ከገፀባህርያቱ ስነልቦና እየፈተሸ ምላሽ ሲያፈላልግ ከምናገኝበት ክስተቶች አንዱ በቤተሰብ ዙሪያ የሚያጠነጥን በተለይም በባልና ሚስት መካከል የሰፈነው ግንኙነት ምን መምስል እንደሚገባው የሚመለከት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ከእናቱ ይልቅ ወደ አባቱ የሚያደላ ፍቅር የምናይበት ዋናው ገፀ-ባህርይ መክብብ፤ በልጅነቱ የተቀረፀበትን “የወላጆቹ ትዳር በእናቱ የበላይነት መመራት” ከባህሉና ከወጉ ጋር የሚጣላ ብቻ ሳይሆን ፍፃሜው መፈራረስ መሆኑን የሚያሳየን በብዙ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውጥንቅጥ የተሞላው የጐረቤቶቻቸው ትዳር እንደነበር ሲቀጥል፣ የወላጆቹ መጨረሻ ግን መለያየት እንደጠቀለለው በመተረክ ነበር፡፡ ቤተሰብ የማኅበረሰብ መሠረት እንደሆነና ድህነት የሚፈጥረው ፈተና እንኳን በቀላሉ እንደማይሰብረው ደራሲው ከግንፍሌ ነዋሪዎች ሕይወት እግረ-መንገድ እያነሳልን ካስጓዘን በኋላ ወደ ዋናው ገፀ ባህርይ ወላጆች ሲያደርሰን ግን የዘመኑን የትዳር መንፈስ ከኋለኛው የሚያነፃፅርበት ሰበዝ አድርጐ ይመዘዋል፡፡ እናም በራስ ላይ ለሚነሳ የ“ለምን አገባሁ?” ጥያቄና ለትዳር መፍረስ ምላሽ በማድረግ የሚያስቀምጠው ትዳር፤ በነባሩ የባህልና ወግ ሥርዓት መሠረት ወንዱ የሚገባውን የበላይነት ሥፍራ በቅድሚያ መልሶ ሲያገኝ እንደሆነ በመሞገት ነው፡፡
ደራሲው በዋናው ገፀ-ባህርይ መክብብ በኩል ይህንኑ የትዳር መሠረታዊ ችግር የሚያሳየን ከእናቱ አስተሳሰብ በመነሣት ነው፡፡
“እናቴ አባቴን ከጫካ አጥምዳ፣ የሚበላው እየሰጠች የገራችው የግሏ አውሬ ይመስለኛል” (ገፅ 14) ይላል፡፡
ደራሲው በመክብብ በኩል ከሚያነሳቸዉ የማንነት ጥያቄዎች አንዱ እንግዲህ ከሕልውና መሠረቶች አንዱ የሆነውን የቤተሰብን አወቃቀር እንዲህ የሚፈትሽና ምላሽ የሚያፈላልግ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የማኅበረሰብ መገለጫው በውስጡ እንደሚገኙ ቤተሰቦች (ትዳር) ጥንካሬና ድክመት የሚወሰን ሲሆን የሀገሩ ባህልም ሆነ እምነት በአወቃቀሩ ከማይደግፈው ከዚያ ቤተሰብ የተገኘው መክብብ ደግሞ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚመለከተውን በወንዱ የበላይነት የሚመራ ትዳር፤ ለወላጆቹ ከመሻቱ የተነሣ የፍቅራቸውን ሰዓት እንኳን የሚመለከተው በቅናት መንፈስ ተሞልቶ ነበር፡፡ ዘወትር የአባቱ በእናቱ ተሸናፊነትና ዝቅ ተደርጐ መመልከት፣ እንዲሁም የአባቱ የማያሰልስ ታዛዥነትና ትዳር የለገሰችውን ሥጋዊ ስሜቱን በነፃነት የማርካት መብት ሳይቀር በልምምጥ ለማግኘት በየምሽቱ መታተርን መታዘቡ፣ ለአባቱ በማዘን ብቻ ሳይሆን በመቆርቆርም እንዲያድግ አድርጐታል። ለዚህ ቀላል ማሳያ የምትሆነን የመክብብ እናት ወደ ሞጆ ለመሄድ ስትነሣ የተፈጠረውን ትዕይንት እንመልከት፡-
“እናቴ ወደ ሞጆ ስትሄድ አባቴ በሎሌነት ዘንቢሏን አዝሎ ይከተላታል፡፡ ዘንቢሉ የተሞላው በጆንያ፣ በከረጢት፣ በማዳበሪያና በስልቻ ነው። በዚህ ትዕይንት ትክክል ያልሆነ ነገር እንዳለ ይሰማኛል፡፡ እናቴ ጥቁር ከፋይ ካፖርት በነጠላ ክንንብ ላይ ደርባለች፡፡ ሦስት ማእዘን ቅርፅ ያላትን ቦርሳ ክንዷ ላይ አንጠልጥላለች፡፡ አባቴ ፕሪስሊውን እንደደፋ ኋላ ኋላዋ ቱስ ቱስ ይላል …
“ትክክል ያልሆነ ነገር እንዳለ ይሰማኛል፡፡ እናቴ የአባቴን ፍፁም ታዛዥነት ለመንደርተኛው የምታስመዘግብበት ትዕይንቷ ነው …” (ገፅ.36)
ከትዳር ትርጉም በላይ ደራሲው በመክብብ አማካኝነት የሚያነሳልን ሌላ የማንነት ጥያቄ ደግሞ አባቱ ምኞቱንና ሕልሙን በእናቱ ፍርሃት ሥር ጥሎ እንዲኖር ያስገደደውን የሙዚቃ ፍቅር ነበር። የዚህ ምኞትና ሕልሙ ማስተንፈሻ የነበረችው ጊታር፣ ከአልጋቸው ሥር ተጠቅልላ ስትወረወር፣ አባቱ በምድር ላይ የተፈጠረበትን ምስጢርና ዓላማ እንኳን ፈልጐ እንዳይደርስበት በሚስቱ ፍርሃት ተሸብቦ በዘበኝነት ለመኖር ምርጫው ማድረጉ፣ ለራሱ አስገራሚ ጥያቄ የሚፈጥርበት ነበር፡፡ ከአልጋ ሥር የተጣለችው የመክብብ አባት ጊታር ወደ ማኅበረሰቡ ሕይወት ወርዳ ስትመነዘር፣ ከእያንዳንዱ ሰው የመፈጠር ምክንያት ጋር የተገናኘ ምኞትና መሻትን እንዲሁም መክሊትን የምትወክል ሆና እናገኛታለን፡፡ መሆን የምናስበውንም ሆነ የምንችለውን እንድንሆን መንገዱን በቅድሚያ የሚሰጠን የምናድግበት ቤተሰብና አልፎም ማኅበረሰብ ቢሆንም በመንገዱ ላይ ለመጓዝ ግን ቤተሰብና ማኅበረሰብ የተመሠረተበትን ባህልና ወግ እንዲሁም እምነት መለስ ብሎ መፈተሽ እንደሚገባ ደራሲው የሚሞግት ይመስላል፡፡ ለዚህም ነው የአባቱን ሕልምና ምኞት ለጊዜውም ቢሆን በእናቱ የሞጆ ጉዞ ባገኙት ነፃነት ላይ መስርቶ ከወደቀበት ለማንሳት መክብብ የሚንደፋደፈው፡፡
ይኼን የአባቱ ሕልምና ምኞት ወኪል የሆነ ጊታር የተጣለው ደግሞ የምድሪቷን ድንጋይና አፈር እንዲሁም ቆሻሻ ሲረግጡ ኖረው ከተጣሉ አሮጌ ጫማዎች ሥር እንደነበር ስንመለከት፣ ደራሲው በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ ሊፈጥር የፈለገው ስነ-ልቦናዊ ጥያቄ ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ ለመገመት ያስችለናል፡፡ የመክብብ ልጅነት ለአባቱ አዲስ ማንነት (እንደእናቱ) ለመፍጠር የሚውገረገር ዓይነት ሳይሆን የተደበቀውንና የተሸነፈ የሚመስለውን የቀድሞ ሕልምና ምኞቱን እንደ አዲስ ነፍስ ሲዘራበት ለመመልከት የሚጓጓ ማንነትን የተላበሰ ነው፡፡ ከቆሻሻና ከተጣለ የእግር መሸፈኛ ሥር የአባቱን “ራዕይ” ሲጐትት ግን ስለዚያ የአባቱ ራዕይ የሚያውቀው አልነበረም ወይም ዘንግቶታል። ለአባቱ ደግሞ “ራዕዩ” የፍርሃትና የስጋቱ ምንጭ ነበር፡፡ (ገፅ 39-40)
ያለፈው ትውልድና ዘመን በኑሮ ጥያቄም ይሁን በባህልና እምነት ወግ ተሸንፎ የጣለውን የማንነት ፈለግ የአዲሱ ዘመንና ትውልድ ወኪል ሆኖ የቀረበልን መክብብ፤ በፍለጋው መሰማራት ብቻ ሳይሆን ለራሱ ማንነትም ፈለጉን ተከትሎ በመጓዝ ምላሽ እንዲሰጥ ጥያቄውን አሸክሞ ደራሲው ወደ አዲስ መንደር፣ ማኅበረሰብና ሕይወት ይከተዋል፡፡
መክብብ የማንነቱን ስነ ልቦና የቀረፁት ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብና በተለይም አብሮ አደግ ጓደኞቹ በአዲሱ የሞጆ ሕይወቱ እንደ ቀላል የሚረሱና የሚጣሉ እንዳልሆኑ ስንመለከት ከላይ አስቀድመን የጠቀስነውን የ“Postmodernism” የአፃፃፍ ፈለግ ደራሲው በሚገባ እንደተከተለ የሚያስረግጥልን ይሆናል፡፡ ከግንፍሌው የቤተሰቡ የድህነትና የመከራ ሕይወት በመነሣት፣ በሞጆ የምቾትና የደስታ ኑሮ በአክስቱ ቤት የተቀበለው መክብብ የምናይበት ለውጥ የስነ-ልቦና ወይም የአስተሳሰብ ሳይሆን የሥጋ ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡ በ“Postmodernism” የአፃፃፍ ፈለግ አንዱ የደራሲ ትልቁ አቅም ሆኖ የሚቆጠረው በገፀ-ባህርያቱ እምነት፣ ፍልስፍና፣ አስተሳሰብ፣ አቋም … ውስጥ ዘልቆ በመግባት ማሳየት እንጂ ድህነት በሀብት፣ ክህደት በእምነት፣ ጥላቻ በፍቅር … የሚሸነፍበትን ውጫዊ ዓለም መፍጠር አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ ደራሲው የተዋጣ ሥራዉን ለአንባቢ ማቅረቡን መመስከር የሚያስችሉ በርካታ ማስረጃዎች ማምጣት ይቻላል፡፡
ለምሳሌ በግንፍሌ ያለፈበት የድህነት ሕይወት መክብብን በሞጆ አልጠበቀውም፡፡ ነገር ግን የተቀማጠለ ኑሮው የማንነት ፍለጋውን የማስረሳት አቅም ደግሞ አላገኘም፡፡ በልጅነቱ ደሀና ድህነትን አስመልክቶ የነበረው አስተሳሰብና ጥያቄን በሞጆም ተሸክሞት ይዞራል፡፡ በልጅነቱ ከአባቱ የወረሰው ድብድብ ያለመፍራት ወኔና ድፍረቱን በግንፍሌ ሜዳ በጋሙዳ ላይ እንዳስመሰከረው፣ በሞጆ ደግሞ በረት ገልባጭ ላይ አሳይቶናል፡፡ የኑሮ ለውጡ በመክብብ ስነ-ልቦና ላይ የፈጠረው ይኼ ነው የሚባል ለውጥ በቀላሉ አናገኝም፡፡ በግንፍሌ የምናውቀው መክብብ፤ ፍቅር የሚፈራና የሚያርበተብተው ነበር፡፡ በግንፍሌዋ ንፁህ ላይ ያሳየን የፍቅር ፍርሃት ሞጆ ሲገባ ደግሞ በናፍቆት ሲደግመው እናያለን፡፡ ለመክብብ የኑሮ ምቾት፣ ትምህርት፣ አዲስ መንደርና ጓደኛ የማንነትን ጥያቄ የሚመልሱ ወይም የሚሽሩ አልሆኑለትም፡፡ ለእሱ ከሕይወት የተቀበለው የመፈጠሩ ምክንያት የተጣለውና የወደቀው የአባቱ ምቾትና ሕልም የተዘረጋበትን ፈለግ ተከትሎ መጓዝ ነው፡፡ የመፈጠሩን ሕልም ለትዳሩ መስዋዕት ያደረገው አባቱ፤ በምላሹ ውርደትን ሲቀበል ተመልክቷል። ፍቅርን በመፍራት የተያዘ ስነ-ልቦና ብናይበት አንደነቅም፡፡ መማር ሰርቶ ገንዘብ ከማግኘት ባለፈ ራዕይን ለመፈፀም እንደማያበቃ አሁንም ከአባቱ ማንነት የተረዳው በመሆኑ፣ በትምህርት የራሱን ማንነት እንደማያገኝ ተስፋ የቆረጠ ስነ-ልቦና ቢላበስ የሚገርም አይሆንም፡፡
ራዕይና መክሊትን ለአባቱ ሰጥቶ ደሀ ያደረገውን አምላክም ሕልውናውን ለመቀበል ሲቸገር ብንመለከት በማን-ፈለግ እየተጓዘ እንደሆነ ለመገመት አያስቸግረንም፡፡ በድህነት ሕይወቱ ከአባቱ የወረሰውን የማንነት ፍለጋ በተሻለ የምቾት ሕይወት ውስጥ ራሱን ሲያገኝ አለመዘንጋቱ እንዲሁ የሚጓዝበትን ፈለግ አመላካች ሆኗል፡፡ ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ በ “ብርሃን ፈለጐች” ሥራው እነዚህንና ሌሎች የአንድ ዘመንና ትውልድ አባል የሆነ እንደመክብብ ዓይነቱ ሰው የሚያነሳቸውንና የሚያስጨንቁትን ስነ-ልቦናዊ ጥያቄዎች እስከ አእምሮው ጓዳ አብረነው ገብተን እንድንበረብር አድርጐናልና አድናቆታችንን ልንቸረው ይገባል፡፡
ማጠቃለያ
“የብርሃን ፈለጐች” በዓመቱ ከቀረቡልን የስነ-ጽሑፍ ትሩፋቶች ግንባር ቀደሙ ተደርጐ ቢወሰድ የምስማማበት ዋነኛው ምክንያት በአፃፃፍ ፈለጉ (“Postmodernism”) መሠረታዊውን የማኅበረሰብ ባህል፣ እምነት፣ አስተሳሰብ፣ ወግ ሳይለቅ ነገር ግን የትውልዱን መሻት፣ ሕልምና ፍላጐት ከሥጋዊ ስኬት ባሻገር ወደ ልቦናው ጠልቀን እንድንመለከት የመጋበዙ ጉዳይ ነው፡፡ መክብብ ያለፈው ትውልድና ዘመን ወኪል አድርገን በትዝታ የምናስበው ሳይሆን በዛሬው ትውልድ ስነ-ልቦና ውስጥ የተቀበረውን የማንነት ጥያቄ እንድንፈትሽና መልሱን እንደመረዳታችን መጠን እንድንደርስበት ምሳሌአችን ሆኖ የቆመ ሰባኪ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በእሱ “የብርሃን ፈለጐች” አብረን ስንጓዝ የምንደርስበት እውነትም ወደራስ ማንነት ከመመለስ በላይ ታላቅ ስኬት አለመኖሩን መረዳት ይሆናል፡፡

Read 1500 times