Print this page
Saturday, 12 October 2013 12:50

ልማት በሥነ - ምግባር ፍልስፍና ሲፈተሽ

Written by  ደረጀ ኅብስቱ
Rate this item
(0 votes)

ሰው፤ ከነዳጅም-- ከወርቅም-- ከማእድናትም-- በላይ የከበረ ፍጡር ነው!

ልማት የሚባለው መርሃ ግብር በአብዛኛው አሳሳች መልክ ያለው ነገር ነው፡፡ በዓለማችን በየዘመናቱ የተከሰቱ መንግስታት ለአገዛዝ ይመቻቸው ዘንድ በተስረቀረቀ ድምጽና በመሰንቆ ምት የዘመሩለት ርዕሰ ጉዳይ ልማት ይመስለኛል፡፡
በአማላይ መልኳና በሚያዘናጋው መዝሙሯ ኃይል፤ ልማት ለረጅም ዓመታት ከሥነ ምግባር ፈላስፎች እይታ ለመሰወር ችላለች፡፡ በልማት ሰበብ የሚደርሱ በደሎችና ጭቆናዎች በመብዛታቸው ምክንያት ግን በዘመናችን ትልቅ ትኩረት ከሚሰጣቸው የግብረገብ ፍልስፍና ክፍሎች ውስጥ አንዱ ልማት ለመሆን በቅቷል፡፡ የህክምና ስነ ምግባር፣ የጥናትና ምርምር ስነ ምግባር፣ የአካባቢ (ጥበቃ) ስነ ምግባር፣ የማስተማር ስነ ምግባር ወዘተ የምንላቸው ጉዳዮች የአፕላይድ ኤቲክስ ውላጆች ናቸው፡፡ ከነዚህም ውስጥ የልማት ስነ ምግባር በተለያዩ የግብረገብ ፈላስፋዎች በታዳጊ ሀገራት ላይ ስለሚተገበሩ የእድገት መመሪያዎች አግባብነት ጥያቄዎችን በማንሳት ይታወቃል፡፡
አንድ ሀገር በምን አቅጣጫ እና በምን መንገድ ማደግ ይሻላታል? ያደጉት ሃገራት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን የመርዳት የሞራል ግዴታ አለባቸው ወይ? በእርዳታ ለውጦችን ለማምጣት ኃላፊነቱ የማነው? መልካም ልማት ማለት ምን ዓይነት ነው? የልማት ስነምግባር ለታዳጊ ሀገራት ብቻ ወይስ ያደጉት ሃገራትንም ይመለከታል? ባደጉት ሀገራት ውስጥ ያሉ ዜጐች ለሚሰማቸው ከፖለቲካ መገለል፣ ያልተመጣጠነ የሃብት ክፍፍል እና ከራስ መነጠል (ባይተዋርነት) ተጠያቂው ማን ነው? ለነዚህና መሰል የግብረገብ ጥያቄዎች ትንታኔ እና መልስ በመስጠት ረገድ የስነ ምግባር ፈላስፋዎች ተፍተፍ ይላሉ፤ ልማትን በሥነምግባር ሊያለሟት፡፡
የመጀመሪያዎቹ የልማት ስነምግባር ተሟጋቾች ከአፍሪካ እነ ፋነንን፣ ከህንድ እነ ጋንዲን፣ ከላቲን አሜሪካ ደግሞ እነራውልን ያካትታል፡፡ የዚያ ዘመን ዋና አንገብጋቢ የታዳጊ ሃገራት ጥያቄ ኮሎኒያሊዝም ነበርና በልማት ማስፋፋት ሽፋን ሉአላዊ አገራትን በኃይል መቆጣጠር ኢ-ስነምግባራዊ መሆኑን እና እድገት ማለት የኮሎኒያሊስቶችን ሀገር መምሰል እንዳልሆነ ይሞግታሉ፡፡ በዛሬው ዘመን በረሃ የታገሉት ዘመዶቻችን “ነጻ አውጭዎች ነን” እንደሚሉን ሁሉ፤ በኮሎኒያሊዝም ዘመንም አውሮፓያዊያን “የስልጣኔ መልእክተኞች ነን” እያሉ ነበር ታዳጊ ሃገራትን በጉልበት የገዟቸው፡፡ እራሳቸውን የሁሉም ነገር ወሰን መለኪያ አድርገው ይቆጥሩ ነበር አውሮፓውያን፡፡ ስለሆነም ቀሪው ዓለም የሚሰለጥነው የነርሱን መንገድ በመከተል ነው ማለት ነው ፤ እንደ ኮሎኒያሊስቶቹ፡፡
የዚያ ዘመን የልማት ስነምግባር ተሟጋቾች ይሉት የነበረው “ከዓለም ተወዳዳሪ የሆነውን ሸራተንን የጭርንቁስ ነዋሪዎች አለቃ በሆነችው መዲናችን መሃል መደንቀር ልማት ነው ወይ?” እንደማለት ነው፤ ወደ ዘመናችን ስናመጣው፡፡ ለቅኝ ገዥዎች መንቀባረሪያ ካልሆነ በስተቀር ለኔ ቢጤ ድሃው ምን ፋይዳ አለው፡፡ አብዛኛው ታዳጊ ሃገር የገዛ መሬቱን በግፍ በአውሮፓ ኮሎኒያሊስቶች ተነጥቆ ነበር፤ በልማት ሰበብ፡፡ ባቡር እንዘረጋለን፣ መንገድ እንገነባለን የሚባለው ፈሊጥ፣ የዜጐችን መብት ለመደፍጠጥና መኖሪያ ለማሳጣት የሚያስችል እሴት አይደለም፡፡ እንዲህ አይነት ጥያቄዎች የመጀመሪያው ትውልድ ሙግቶች ነበሩ፡፡ የሰው ልጅ ነጻነት፤ የሰው ልጅ የመኖር መብት ከሁሉም ይበልጣል፡፡
እኛ ሰልጠነናል፤ስልጣኔ ላልደረሳቸው ሀገራት እናዳርሳለን የሚሉት ኮሎኒያሊቶች የለሙበት መንገድ ለሁሉም ሃገራት ብቸኛ የልማት መንገድ አድርገው ይወስዱታል፡፡ አኗኗርን፣ የትምህርት ስርዓትን፣ አመጋገብን፣ የቤት አያያዝን ወዘተ-- አውሮፓዊ ማስመሰል ዋናው የልማት መገለጫ ተደርጐ ይቆጠር ነበር (የኤርትራ ክፍለ ሀገር ወንድሞቻችን “ለኢትዮጵያዊያን ሹካና ማንኪያ አያያዝ ያስተማርናቸው እኛ ነን” ይሉን ነበር የዛሬውን አድርገውና) “እናሰልጥናችሁ፤ የኛን ፈለግ ተከተሉ” እያሉ ኮሎኒያሊስቶች ለሚያነሱት የስልጣኔ መከራከሪያ ነጥብ፤ “ጥያቄው የወረራና የእኛን ምሰሉ ጉዳይ እንጂ የመሰልጠን ወይም የመልማት ጉዳይ አይደለም” ነበር፤ የስነምግባር ተሟጋቾቹ እነ ፋነን እና እነ ጋንዲ የሚያሰሙት ሙግት፡፡ በእርግጥም ኮሎኒያሊስቶች የራሳቸውን ባህልና ቋንቋ በህዝብ ላይ በመጫን ብዙ አገርኛ ቋንቋዎችን ድራሻቸውን አጥፍተዋቸዋል፡፡ ይህንን ቀኖናዊ የልማት እሳቤ በመሞገትና ፀረ - ኮሎኒያሊዝም እንቅስቃሴዎችን በመምራት የመጀመርያዎቹ የእድገት ስነምግባር ተሟጋቾች አልፈዋል፡፡
ከሁለተኛው ትውልድ የልማት ስነ ምግባር ተሟጋቾች ውስጥ ደግሞ አሜሪካዊው ዴኒስ ጉሌት ጐልቶ ይጠቀሳል፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተነሳው የጉሌት አስተምህሮ፤ የልማት መመሪያዎች ስነምግባርን እና እሴትን ግምት ውስጥ ያስገቡ መሆን ይገባቸዋል ይለናል፡፡ የልማት መመሪያዎች/ፖሊሲዎች፤ ልማቱ በምን ዓይነት የስነምግባር ማእቀፍ ውስጥ መተግበር እንዳለበት በግልጽ ማስቀመጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ልማት የምንለው እንቅስቃሴ ወይም ተግባር በእነማን እሳቤ ሲታሰብ ነው ልማት የተባለው፡፡ በእነማን የአተረጓጐም መንገድ ነው አንድ ድርጊት ልማታዊ ድርጊት የሚባለው ይለናል፤ ጉሌት፡፡ የደርግ የመንደር ምስረታ የገጠሪቱን ኢትዮጵያ አለማት ወይስ ነባር ማህበራዊ ስሪቷን መነጋግሎ ጣለው? እንደ ማለት ነው ጥያቄው፡፡ ህንዶችና አረቦች የሚቀራመቱት የምዕራብ ኢትዮጵያ መሬት የአካባቢው ነዋሪዎችን ብልጽግና ወይስ ቁርቁዝና ያላብሳል? ይሆናል፤ ሙግቱን ወደኛ ዘመን ስናመጣው፡፡ እውነት ግን የሸንኮራ መሬት ኢትዮጵያ አጥታ ነው ዋልድባ አፍንጫ ስር የምናርስ? ዋልድባ እንኳን ለእርሻ ለምነና አይርቅም እንዴ?
ልማትን እንደገና በመበየን እና በመተርጎም የግብረገብ ጥያቄዎች በውስጧ እንዲነሱ ቦታ መፍጠር ይኖርብናል ይላል፤ጉሌት፡፡ ልማት የሰውን ልጅ እንግልት የምታስከትል ከሆነና ለህይወት ትርጉም የምትጨምረው ነገር ከሌላት ውድቀት ትሆናለች ማለት ነው፡፡ መኪና እንደልብ በዜጎቻቸው ቁጥር ያላቸው ሃገራት የሚቀይሱትን ለመኪና ተስማሚ የሆነ መንገድ፤ በእግረኛ እስከ አፍንጫዋ ለተጥለቀለቀች እንደ ኢትዮጵያ ያለች ሃገር አምጥቶ መደንቀር ምን ይባላል፡፡ የመንገድ ቅየሳዎች ለመኪና እንዲስማሙ እንደሚደረገው ሁሉ ለእግረኛ ሃገራትም ለእግረኛ ተስማሚ ቅየሳዎች ሊተገበሩ ይገባል፡፡ ግቢውን በጭራሮና በስሚዛ (ሰንሰል) እያጠረ፣ ትዳሩን ልጆቹን ግቢውንም እያስከበረ ማንነቱን ላዋቀረ ማህበረሰብ፣ የፈረንጆቹ የጋራ ቤት (ኮንዶሚኒየም) የኑሮ ዘዬ ሊያስከትል የሚችለውን ቀውስ በአንዳንድ መንደሮች (ጆሞ፣ ጎተራና ገርጅ ኮንዶሚኒየም) እያየነው ነው፡፡ ልማት ውድቀትን ልታስከትል ትችላለች ማለት ይሄው ነው፡፡
ሦስተኛው የልማት ስነ ምግባር ሙግት ደግሞ ከግብረገብ ፈላስፎች እንደ ኒጌል፣ ኦኔል፣ እና ጀሮም ከመሳሰሉት ይመነጫል፡፡ አብይ ትኩረታቸውን የእርዳታ ፋይዳ ላይ አድርገው፣ ዝም ብሎ የእርዳታ ስነ-ምግባር ስነ ምግባር ማለት ሳይሆን የሚያስፈልገው ሁሉ አቀፍ የሆነ፣ በተግባር የተፈተሸ፣ ለልማት መመሪያ አግባብነት ያለው የሦስተኛው ዓለም እድገት ስነ ምግባር ያስፈልገናል ይላሉ፡፡ የሰሜኑ እና የደቡቡ የዓለም ክፍል ግንኙነት በመልካም ልማት ላይ እንዲመሰረት ጥሪ ያቀርባሉ። ባለ ጸጋ ነን የሚሉት በሰሜኑ የዓለም ንፍቅ ውስጥ ያሉት በደቡቡ የዓለም ንፍቀ ክበብ ውስጥ ላሉት ታዳጊ ሃገራት የሚሰጡት እርዳታ በትክክል ለውጥ አምጥቷል ወይ? ወይስ ሁለቱንም ሃገራት ደሃ አደረጋቸው?
የምግብ እርዳታ ማድረግ እና ምንም ምግብ አለመርዳት የክርክር ርእስ ነበር በዚህኛው ዘመን። እርዳታ የኃላፊነት (የውዴታ) ግዴታ ነው ወይስ ልግስና ነው? አወዛጋቢ ጉዳይ ነበር፡፡ ለጋሽ ሃገራት የሚባሉት በሙሉ የየራሳቸውን የእርዳታ መርሃግብር በመቅረጽ፣ በአውቅልሃለሁ መንፈስ ወደ ታዳጊ ሃገራት እርዳታቸውን አፈሰሱት፤ ውጤቱ ግን ረጅውን እና ተረጅውን ደሃ የሚያደርግ ሆነ። ስለሆነም በተረጅ ሃገራት ውስጥ በእርዳታ አማካኝነት ለውጥ እንዲመጣ ካስፈለገ፣ እኛ እናውቅልሃለንን እንተወውና የተረጅ ሃገራትን እቅድና ግብ አስቀድመን መገንዘብ ያስፈልገናል ይላሉ፤ ፈላስፎቹ፡፡
አራተኛው የልማት ስነ ምግባር ሙግት የሚነሳው በእነጳውሎስ ስትሪተን እና አማርቲያ ሴን ነው፡፡ እነዚህ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ደግሞ የዓለም ኋላ ቀርነትን፣ ርሃብን፣ እና የሃብት ልዩነት ምክንያቶችን በማንሳት የልማት ስነምግባር እሳቤዎችን በመጠቀም ትንታኔ ይሰጣሉ፡፡ ልማት ማለት የምጣኔ ሃብት እድገት ማለት አይደለም፤ ኢንዱስትሪ ማስፋፋትም አይደለም፡፡ ይልቁንም ልማት የሰዎች ክህሎትና ምርታማነት መስፋፋት ነው፤ ሰዎች ማድረግ የሚችሉትና ማድረግ የተሳናቸው ምንድነው መሆን አለበት የልማት ጥያቄ፡፡ ለምሳሌ ረጅም እድሜ መኖር ችለዋል ወይ? ተመጣጣኝ ምግብ ማግኘት ችለዋል ወይ? ማንበብ መጻፍ መግባባት ችለዋል ወይ? ድንቁርና ተወግዷል ወይ? በትምህርት እና በሳይንሳዊ ፈለጎች ላይ መሳተፍ ችለዋል ወይ? ለሚሉ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ማለት ነው፤ ልማት ማለት ይሉናል፡፡
የአማርቲያ ሴን ሙግት የሚያላውስ አልነበረምና እነ አለም ባንክ የሚያካክሉ ግዙፍ አለም አቀፍ ድርጅቶች ለልማት ያላቸውን መለኪያ ሚዛን እንዲያስተካክሉ አስገድዷቸዋል። እንግዲህ ይህንን ሙግት ወደ ሃገራችን ነባራዊ/ወቅታዊ ሁኔታ ስናመጣው ነው አይናችን የሚፈጥጥ፡፡ ጭንቅ ጥብብ ያለ ነገር ነው፡፡ በእውኑ ግን ማንን እያነገሥን ነው? ኢትዮጵያዊ የቁስ አካላት ባሪያ እየሆነ ነው ወይስ በቁስ አካላት ላይ እየሰለጠነባቸው፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ከመኪና፣ ከህንጻ፣ ከባቡር፣ ከመንገድ፣ ከግድብም በላይ ናት፤ እነዚህ ሁሉ ከኢትዮጵያና ከህዝቧ ሊበልጡ ከቶ አይችሉም፡፡ ከነዚህም በላይ ኢትዮጵያና ህዝቧ ይገባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያና ህዝቧ የትልቅ ታሪክና የጥንት ስልጣኔ ባለቤት ናቸውና፡፡ ቁም ነገሩ ግን ቅድሚያ የሰጠነው ለማነው ነው፡፡
ልማት ማለት ግሳንግስ ማጠረቃቀም ሳይሆን የሰው ልጅ መስፋፋት፣ ምልአተ ክህሎት፣ የችሎታ መንሰራፋትና ሰው በራሱ ላይ መሰልጠን ማለት ነው፡፡ ይህንን የመሆን ጸጋውን እንዲቀዳጅ ሲሆን ብቻ ነው ቁስ አካላት ለሰው አጋዥ ረዳት ሆነው መቅረብ ያለባቸው፡፡
የዚህ ዓለም ንጉሡ፣ ሰው እንጂ ቁሳቁሶች አይደሉም፡፡ በጣም ቀላል ማሳያ የሚሆነን የአረብ አገራት ነባራዊ ሁኔታ ነው፡፡ በየትኛውም የዓለም ክፍል ካሉት ዘመዶቻችን በከፋ ሁኔታ በአረብ አገራት በሥራ ላይ ባሉ እህቶቻችን የሚደርሰው እንግልት እና የመብት ረገጣ ለዘመናችን የሰው ልጅ ስልጣኔ የሚዘገንን ነው፡፡ ሰው በጭንቅላት ሃብቱ ከቁስ አካላት ሃብቱ ካልበለጠ ሊከሰት የሚችለው ቀውስ በመጠኑም ቢሆን በአረብ አገራት ውስጥ ይንጸባረቃል፡፡ አሰሪዎቻቸውን እንደዚያ ሊያስጨክናቸው የሚችለው ዋናው ምክንያት ሃብትና ገንዘብ ተትረፍርፎ ጭንቅላት ግን ባዶ መሆኑ ነው፡፡ ገንዘብና ቁሳቁስ በሰው ላይ ሲነግሡ የሚከሰተው ይሄው ነው፤ በወርቅ የተሽሞነሞነ አረመኔ፡፡
ሃገር ማለት ትውልድ ነው፤ ጅረት - የዛሬ ማንነቱ ከተቋረጠ የእሾህ አሜከላ ማበቢያ ለም መሬት የሚሆን፡፡ ዛሬ ሰውን እያቃለልን የቁስ ልማትን ብናፋጥን፣ ነገ ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን እራሳቸውን መሆን የማይችሉ፣ በገዛ ሃገራቸው ባይተዋሮች ይሆናሉ፡፡ የአንድ ሃገር ሃብቷ ሰው ነው። ሰው ከነዳጅም ከወርቅም ከማእድናትም በላይ የከበረ ፍጡር ነውና፡፡

Read 3267 times