Saturday, 12 October 2013 12:51

የአዳማ ጉዞ ማስታወሻ!

Written by  ነቢይ መኰንን
Rate this item
(3 votes)

ዝርጓ፣ ውቧና ለምለሟ አዋሳ
“ዛሬ ቀባሪ አታሳጣኝ ሳይሆን እንጀራ አታሳጣኝ ነው መባል ያለበት”
ዕሮብ መስከረም 8, 2006 ዓ.ም ነው ከሞጆ ወደ አዋሳ መጓዝ የጀመርነው። ቆቃ፣ ዓለምጤና መቂ…ጤፍ፣ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ቲማቲም፣ ፓፓያ…የቁልቋል አጥር እያለፍን ወደ ዝዋይ ስንጠጋ ሽንኩርት፣ ጐመን በሽበሽ ሆኖ አየን፡፡ አዳሚ ቱሉ፣ ቡልቡላ፣ አርሲ ነገሌ …በአህያ የሚሳብ ጋሪ፣ በጐማ የሚበር እንደፌንጣ የሚዘል አይሱዙ፣ …መልካ አዳ፣ ኩይራ…የእህል አገር … የድንገተኛ ዝናብ አገር … በስተግራ ዶዶላ፣ አርሲ አሰላ፣ አዋሽ መልካ ሰዲ፣ አዋሽ ጐርጐ፣ ናዝሬት … ትተን ወደ ጃማይካዎቹ ሠፈር ወደ ሻሸመኔ ተጠጋን…ሻሸመኔ ቡና ከጠጣን በኋላ የአላሙዲ ነው የተባለውን ረዥምና አርበ ሰፊ የበቆሎ እርሻ በግራ እያየን ቀኝ ቀኙን ወደ ዝርጓ ውቧና ለምለሟ አዋሳ ገባን፡፡ አዋሳን በልጅነቴ የማውቃት በመልካሙ ተበጀ ዘፈን በኩል ነበር “አዋሳ ላንጋኖ ለሽርሽር ሄጄ (በቆሎ እርሻ ውስጥ) ያየሁሽ የሲዳማ ቆንጆ እንዴት ነሽ” አድጌ አዋሳን ያገኘኋት ግን አንድ ባለታክሲ በነገረኝ ቀልድ በኩል ነው፡፡ የአዋሳ ሴቶች ብስክሌት ይነዳሉ፡፡ ከወደኋላ ደልደል ሰፋ ያለ ሰውነት ያላቸው ናቸው፡፡
ባለባጃጁ ሹፌር ሲገልፃቸው “ከኋላ ስታያቸው ‘አፈር-ልብላ’ ትላለህ…ከፊት ስታያቸው ‘አፈር ብይ’ ትላለህ” አለኝ፡፡
የአዋሳ ቅርንጫፍ የእየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ማስረሻ፤ ከአንድ አጭር፣ ጠይም፣ ጥብቅ የሚመስሉ፣ አንደበተ ቀናና ሲናገሩ የሃሳብ ፍሰታቸው የሚያስገርም ሰው ጋር አስተዋወቁኝ፡፡ እኒህ ሰው የአዋሳ አካባቢ 128 ዕድሮች ሰብሳቢ ናቸው፡፡
“ቀደም ሲል ሠራዊቱ ቤት የነበርኩና ፌዝ - አውት ስናደርግ ወደ ማህበረሰቡ የመጣሁ ነኝ” አሉኝ፡፡ “ማህበረሰቡን በማገልገል የድርሻዬን እየተወጣሁ ነኝ፡፡ ዛሬ ማንም ሰው ወንደላጤም ሳይቀር የዕድር አባል መሆን አለበት፡፡ ክፉ አለ ደግ አለ፤ ሰው የሚያጋጥመው አይታወቅም፡፡
የድርሻውን ለመወጣት የእድሩ አባል መሆን አለበት። ዕድል የማይሻር ተቋም ነው! ይልቁንም ከወቅቱ ጋር እየጐለበተ ነው የሚሄደው። ዕድር ላይ value (እሴት) ካልጨመርክ ቤተሰብ ራሱ ይዳከማል፤ ዕድርና ቤተሰብ የተሳሰሩ ናቸው፡፡ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ቤተሰብ የዕድር ተጠቃሚ ነውና ቤተሰቤን ትቼ መጣሁ አልልም፡፡ ደሞ ወድጄ ነው የገባሁት - በጐ ፈቃደኛ ነኝ፡፡ አገለግላለሁ!”
“በጐ - ፈቃደኝነት በአገራችን የተሰመደ አይመስለኝም” አልኳቸው፡፡
“ዕውነት ነው፡፡ እንደእየሩሣሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት (እህማልድ-JECCDO) ያሉ ተቋማት ናቸው ያስፋፉት፡፡ እህማልድ - jeccdo) ሰፊ ሥራ ሠርቷል፡፡ ግንዛቤ ሰጥቷል፡፡ በበጐ ፈቃደኝነት ላይ አስተምሯል፡፡ የበጐ ፈቃደኝነት ስራ ውስጡ ስትገባ የመንፈስ እርካታ ታገኝበታለህ፡፡ በጐ ፈቃደኝነት ከገንዘብ የበለጠ ነው፡፡
በበጐ ፈቃደኝነት ምን ምን ሥራ ሠራችሁ ታዲያ? እስቲ ታሪካችሁን አጫውቱኝ፡፡
“በመሠረቱ ዕድር የችግር ጊዜ ደራሽ ነው። አሁን ጊዜ ተለወጠ፡፡ ዓለም ግሎባላይዝድ ሆነና ከቀብር ወደ ልማት ተገባ … ዛሬ ቀባሪ አታሳጣ ሳይሆን እንጀራ አታሳጣኝ ነው መባል ያለበት!
ሰው ትልቅ ሀብት ነው፡፡ ካንቀሳቀስነው፤ አይደለም ለዕድር ለመንግሥት ራሱ ትልቅ Input (ግብዐት) ነው፡፡ መንግሥትን መንግሥት የሚያደርገው የእያንዳንዱ ሰው አስተዋጽኦ (Contribution) ነው
“ልማት ለርሶ ምንድን ነው” አልኳቸው ንግግራቸውን በደቋረጤ ቅር እያለኝ፡፡
“መጀመሪያ ራስህን ለውጥ፤ ከዚያ ሠፈርህን ለውጥ ማለት ነዋ” (ልበ - ሙሉነታቸው ይገርማል)
“ህፃናቶች ናቸው የልማት \ትኩረቶቻችሁ?”
ከእየሩሳሌም ጋር ያገናኘንም የህፃናት ጉዳይ ነው፡፡ በአረጋውያን ላይ፣ በኤችአይቪ ዙሪያ፣ ማህበረሰብን መሠረት ያደረገ ነው ሥራችን፡፡
ይሄ አዳራሽ አሁን ተጨባጭ ነገር ነው። ይከራያል፤ ገቢ ነው፡፡ ለአቅመ ደካሞች ይውላል ገቢው፡፡
ዕድራችን ሰኔ 16 1993 ነው የተቋቋመው፡፡ በተናጠል ከምንንቀሳቀስ ለምን በአንድ የዕድሮች ዣንጥላ ሥር አንሆንም? አልን፡፡ አገራችንን ለማልማት የምንችለው በተናጠል ሳይሆን በጋራ ነው፤ ዕድሮች ብዙ ካፒታል አላቸው፤ ሰብሰብ አድርገን ለመንቀሳቀስ ነው፡፡ በደርግ ጊዜ የ66ቱ አብዮት ሲፈነዳ ድንኳንና ቁሳቁሶች ተወስደው ስለነበር “እባብ ያየ በልጥ በረየ” ሆነና መጀመሪያ ላይ ያለመቻቻል ችግሮች ነበሩ፡፡ ኋላ ግን ከብት ማርባቱ፣ በግ አደልቦ መሸጡ፣ ባጃጅም አለን፣ ለአሳዳጊዎች ሥራ በመፍጠር … ምኑ ቅጡ! የእየሩሳሌም (ጄክዶ) የአዋሳ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ Positive thinker (ቅን አሳቢ) በመሆናቸው ትልቅ እገዛ ተደርጐልናል። የልምድ ልውውጥ እናደርጋለን፤ አገር አራጭ፡፡ ለመሪዎች፣ ለአሳዳጊዎች፣ ለወጣቶች ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ ክህሎት አግኝተናል-ያ ገንዘብ ማለት ነው!
“ጄክዶ በሚሄድ ጊዜ ምን ትሆናላችሁ?”
“እሱማ ሥራውን ሠራ’ኮ! መሠረት ተጥሎልናል፤ ሲስተሙ ተዘርግቷል፡፡ ሜዳውም ያው ፈረሱም ያው፡፡ ራሳችን የገቢ ምንጭ እንፈጥራለን፤ ፕሮጄክት ቀርፀን ሥራ እንሠራለን፤ በራሳችን ኃይል እንንቀሳቀሳለን፤ በህብረተሰቡ መሠረታዊ ዕድሮች ላይ ዘመናዊነት መጨመር ማለትኮ በራስህ መቆም ነው!”
(ጉዞዬ ይቀጥላል)

Read 2916 times