Saturday, 12 October 2013 12:36

ኮንዶም እየሸጡ ህይወታቸውን የለወጡ ወጣቶች

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

“ኮንዶም ለእኔ ሕይወቴ ነው፤ ዝናብና ፀሃይ ሳይበግረኝ እሸጣለሁ”
“ኅብረተሰቡ ስለኮንዶም ያለው ግንዛቤ አነስተኛ በነበረበት ወቅት ኮንዶም ገዝቶ ሊጠቀም ቀርቶ እያዞርኩ ስሸጥ ያፍር ነበር፡፡
‹ምነው ቢቀርብሽ? እንዴት ይህን የብልግና ነገር ትሸጪያለሽ?...› ይሉኝ ነበር፡፡ ደቻቱ አካባቢ በሌሊት እያዞርኩ ስሸጥ ‹የኮንዶሙን ዋጋ ልክፈልሽና ከእኔ ጋር ተኚ› ይሉኝ ነበር፡፡ አሁን ኅብረተሰቡ ለኮንዶም ያለው ግንዛቤ ቢያንስ 50 በመቶ ጨምሯል” ያለችው ህይወት ከበደ ናት፡፡
ህይወትን ያገኘኋት ዲኬቲ ኢትዮጵያ በሀዋሳ ከተማ 4ኛው ብሄራዊ የ“ያንግ ማርኬተርስ ኮንፈረንስ” ተሳታፊ ሆና ነው፡፡
ዲኬቲ እያንዳንዳቸው 192 አባላት ያላቸው ሶስት ክለቦች አሉት፡፡
ሕይወት የድሬደዋ ነዋሪ ስትሆን፣ቀደም ሲል ደጋፊ ስላልነበራት ኑሮዋ መጥፎ ነበር፡፡ ሴት ልጇን ያሳደገችው በሴተኛ አዳሪነት በምታገኘው አነስተኛ ገቢ ነው፡፡ ልጇን ጥሩ ት/ቤት ማስተማርም አትችልም ነበር፡፡ አሁን ግን ሁኔታዎች ተለውጠዋል ትላለች፤ ሕይወት፡፡ እንዴት?
ሕይወት አሁን በምትኖርበት ከተማ “የበርቲ ሴቶች ንብረት ስራ ማኅበር ሊቀመንበር ናት። ከዚህም በተጨማሪ የዲኬቲ ኢትዮጵያ “ያንግ ማርኬተርስ” ናት፡፡ “እንዴት ከዚያ አስቀያሚ ሕይወት ወጥታ ለዚህ ኋላፊነት በቃች?” ማለታችሁ አይቀርም። ዲኬቲ፣በማህበር በክለብ የተደራጁ ወጣቶችንና ሴተኛ አዳሪዎችን በኮንዶም ሽያጭ ወይም ስርጭት እንደሚያሳትፍ ሰማች፡፡ እሷና ጓደኞቿ የገቡበት ሕይወት ምርርና ስልችት ብሏቸው ነበር፡፡ 25 ሆነው ተደራጁና የ“በርቲ ሴቶች ኅብረት ስራ ማህበር” በመመስረት የዲኬቲ ያንግ ማርኬተርስ አባል ሆኑ።
የዲኬቲ ዓላማ ህብረተሰብ ኮንዶም በቅርበት አግኝቶ በመጠቀም ራሱን ከኤች አይቪ/ኤድስ እንዲጠብቅ ማድረግ ነው፡፡
እነ ሕይወት ልቅ የግብረ ስጋ ግንኙነት በሚፈፀምባቸው አካባቢዎች ኮንዶም እንዲጠቀሙ ሲሰብኩ ከፍተኛ ችግር ነበረባቸው፡፡ በሴተኛ አዳሪነት የተሰማሩትን ሴቶች በአቻ ለአቻ ትምህርት ስለ ኤች አይቪ/ኤድስ አደገኝነት አስተምረው ኮንዶም እንዲጠቀሙ ይመክሯቸዋል፡፡ ሴቶቹ ምክራቸውን ተቀብለው ተግባዊ ለማድረግ ሲሞክሩ ወንዶች ግን ከተስማሙበት ዋጋ በተጨማሪ “ይህን ያህል እጨምርሻለሁ፣ያለ ኮንዶም እናድርግ” እያሉ ያስቸግሯቸው ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ጥያቄውን ተቀብለው ያለ ኮንዶም የሚያደርጉ ቢኖሩም ፣በአቋማቸው ፀንተው አይሆንም ብለው የሚሸለሙም ነበሩ፡፡
አሁን ግን የዚያን ጊዜ ሁኔታ ተለውጧል። በሰጠነው ያለሰለሰ ትምህርት ኅብረተሰቡ ስለኮንዶም ጥቅም ያለው ግንዛቤ ቢያስ 50 በመቶ ጨምሯል ትላለች - ሕይወት፡፡
የዲኬቲ ያንግ ማርኬተርስ ሆና ኮንዶም በመሸጧ ሕይወቷ መለወጡን ትናገራለች፡፡ በፊት ገቢዋ ከእጅ ወደ አፍ በነበረበት ጊዜ ልጇን የምታስተምረው ደካማ ት/ቤት ነበር፡፡ አሁን ግን ገቢዋ ጨምሮ በወር እስከ 1,200 ብር ታገኛለች። ስለዚህ ልጇን ከቀድሞው ት/ቤት አስወጥታ ለት/ቤት 200 ብር፣ ለሚያመላልስላት ባጃጅ ደግሞ 200 ብር፣ በአጠቃላይ 400 ብር መድባ ልጇን የተሻለ ት/ቤት እያስተማረች ነው፡፡ ኑሮዋም ተሻሽሏል። “ኮንዶም ለእኔ ሕይወቴ ነው፤ ዝናብና ፀሃይ ሳይበግረኝ በሁሉም ቦታ ተዘዋውሬ እሸጣለሁ” ብላለች፤ ሕይወት፡፡
ኮንዶም ሸጦ ዩኒቨርስቲ መማር
ዓለምአንተ ወርቁ በጋምቤላ ክልል መዠንገር ዞን ነዋሪ ነው፡፡ እሱና ወላጁና ደጋፊ የሌላቸው ወጣቶች “ሕይወት ለልማት” የተባለ ማህበር መስርተው ከዲኬቲ ኢትዮጵያ ጋር መስራት የጀመሩት በ2002 ዓ.ም ነበር፡፡
በዚያን ጊዜ ኅብረተሰቡ ስለኮንዶም ያለው ግንዛቤ አነስተኛ ስለነበር በወር አንድ ካርቶን ኮንዶም እንኳ አይሸጡም ነበር፡፡ አሁን የኅብረተሰቡ ግንዛቤ ስለጨመረ በወር እስከ አራት ካርቶን ኮንዶም ስለሚሸጡ ሕይወታቸው ተለውጧል፡፡
“እኔን ጨምሮ የማኅበሩ አባላት በኮንዶም ሽያጭ እየተጠቀምን ነው፡፡ በኮንዶም ሽያጭ በወር ከ400-700 ብር እናገኛለን፤ በዚህ ገንዘብ ዩኒቨርሲቲና ኮሌጅ የሚማሩ ልጆች አሉ፤አንዱ ደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ፤ ሌላው ደግሞ አላጌ ግብርና ኮሌጅ ይማራል፤ እኔም ተምሬ በአሁኑ ወቅት በመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ በሪፖርተርነት እየሰራሁ ነው፡፡ ስለዚህ ዲኬቲ ሕይወታችንን ለመለወጥ ምክንያት ሆኖናል፡፡” ብሏል፤ ዓለምአንተ ወርቁ፡፡

Read 2752 times