Saturday, 12 October 2013 12:13

መፍትሔ የታጣለት የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ችግር

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)
  • ሁለት ዓመት የሚፈጀው የባቡር ፕሮጀክት ችግሩን በከፊል ይፈታል ተብሏል 
  • የመንግስት ሠራተኞች በቅርቡ ሰርቪስ ይመደብላቸዋል

በመስቀል አደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ የተከለከለው በቅርቡ ነው፡፡ የትራንስፖርት ተገልጋዩ ግን በየቀኑ እየተሰለፈበት ነው - ታክሲ ጥበቃ፡፡ አንደኛው ረጅም ሠልፍ ውስጥ የታክሲ ወረፋ ይዞ ያገኘሁት ወጣት ዳንኤል መዝገቡ፤ ከቃሊቲ መኖርያ ቤቱ 4 ኪሎ ወደሚገኘው መስሪያ ቤቱ ለመድረስ ከ3 ሠአት በላይ እንደሚፈጅበት ይናገራል፡፡
“ጠዋት ጠዋት ሁሌ ስለማረፍድ ከአለቆቼ ጋር ጭቅጭቅ ነው፣ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያም ደርሶኛል” የሚለው ዳንኤል፤ “ሠአታትን በሚወስደው የጠዋት ጉዞ አካሌ ተዳክሞና ዝሎ ቢሮ ስለምደርስ ስራዬን በአግባቡ መወጣት አልችልም” ይላል - በትራንስፖርት እጥረት የደረሰበትን ሲናገር።
ጠዋት እና ማታ ታክሲዎች ሆን ብለው ከመስመራቸው ይጠፋሉ ያለኝ ደግሞ ሌላው የትራንስፖርት ተጠቃሚ ተመስገን ይህደጐ ነው፡፡ “ሠልፍ ሲያዩም የዋጋ ጭማሪ ያደርጋሉ፤ አማራጭ አጥቶ የቆየው ተጠቃሚም ያለማንገራገር የተጠየቀውን ከፍሎ ይጓዛል” ብሏል ተመስገን፡፡
የትራንስፖርት ቁጥጥር ሠራተኞች ይሄን እያዩ በቸልታ ያልፉታል የሚለው ተመስገን፤ ህብረተሰቡ በዚህ መሃል እየተበዘበዘ መሆኑን ይናገራል፡፡ ከጦር ሃይሎች ሃያ ሁለት እየተመላለሰ እንደሚሠራ የነገረኝ አንድ ወጣት በበኩሉ፤ በመስመሩ ላይ የተመደቡ ታክሲዎች እያቆራረጡ ስለሚጭኑ ከገንዘብ፣ ከጊዜ አጠቃቀምና ከጉልበት አንፃር በርካታ ኪሣራዎች እንደሚያጋጥሙት ይገልፃል፡፡
ተገልጋዮች የትራንስፖርት ዘርፉ ችግር በማለት የሚጠቅሷቸው ጥቂት አይደሉም፡፡ የታክሲዎች እያቆራረጡ መጫን፣ ከታሪፍ ውጪ ማስከፈል፣ በቀጠናቸዉ አለመስራት፣ የመንገድ መዘጋጋት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በተለይ ከባቡር ግንባታው ጋር በተያያዘ መንገዶች በሚዘጋጉባቸው መስመሮች አላግባብ የታሪፍ ጭማሪ ይደረጋል፡፡ ለምሣሌ ከስታዲየም እስከ ቃሊቲ መነሐሪያ 7 ብር ከ50 የነበረው ታሪፍ፤ አሁን እስከ 10 ብር እየተጠየቀ ነው፡፡ አልከፍልም ያለ ተሣፋሪ ከመውረድ ውጭ አማራጭ የለውም፡፡
በመገናኛ ዞን ፀሃይ የባለታክሲዎች ማህበራት ሊቀመንበር አቶ አበባው ካሣ፤ በአሁን ሠአት ተገልጋዩም አገልጋዩም በእኩል እየተጐዱና ብዙ ተግዳሮቶች እየተጋፈጡ መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአራቱም የከተማይቱ ማዕዘናት እየተገነባ ካለው የባቡር መንገድ ጋር ተያይዞ የመንገዶች መዘጋጋት ዋና ችግር እንደሆነ ያሠምሩበታል፡፡
በዚህ ሳቢያ የታክሲያችን ምልልስ መጠን እንዲቀንስ አድርጓል የሚሉት አቶ አበባው፤ ቀድሞውኑ ያሉት ተሽከርካሪዎች ውስን ሆነው ሣለ የምልልስ መጠናቸው እንዲቀንስ መገደዱ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኗል ይላሉ፡፡
አንዳንድ የታክሲ አሽከርካሪዎችም በማህበራቱ የሚነሱትን ችግሮች ይጋሩታል፡፡ ስሙ እንዲገለጽ ያልፈቀደ ከጦር ሃይሎች 22 መስመር የሚሠራ አንድ ታክሲ አሽከርካሪ፤ የሚነዳት ታክሲ በናፍጣ ስለምትሰራ ለባለቤቶቹ በቀን 350 ብር ገቢ ማድረግ የሚጠበቅበት ቢሆንም በመንገዶች መዘጋጋት የተነሳ ያን ያህል ገቢ ለማግኘት እንደሚቸገርና ከባለንብረቶች ጋር ሁሌ እንደሚነታረክ ይገልፃል። ባሳለፍነው ዓመት የመጨረሻ አራት ወራት ውስጥ ብቻ አራት ሚኒባስ ታክሲዎችን ቀያይሯል - ከባለቤቶቹ ጋር ባለመግባባት፡፡
በሐምሌ ወር አጋማሽ በቤንዚን የምትሠራ ሚኒባስ ማሽከርከር ጀምሬ ነበር የሚለው ወጣቱ፤ ለባለቤቶቹ በቀን 290 ብር ገቢ ማድረግ የሚጠበቅበት ቢሆንም አንዳንዴ በመንገድ መዘጋጋት የቢያጆ (ምልልስ) መጠን ስለሚቀንስ በገቢ ጉዳይ ላይ አለመግባባቶች ይፈጠሩ ነበር ይላል፡፡ በአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የትራንስፖርት ኮርፖሬሽን ዋና የስራ ሂደት መሪ አቶ ወጋየሁ አሰፋ፤ በከተማዋ ለተፈጠረው የትራንስፖርት ችግር በግንባታ ላይ ያለውን የባቡር ፕሮጀክት የመጀመሪያ ተጠያቂ ያደርጋሉ። የአስፓልት መንገድ ግንባታዎች በ2006 ዓ.ም በየአካባቢው ተጠናክረው መቀጠላቸውም የችግሩ መንስኤዎች ናቸው - እንደ ኃላፊው፡፡ እነዚህ እስከሚጠናቀቁ ለሁለት አመታት ችግሩ ሊቀጥል የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ ሃላፊው ይገልፃሉ፡፡
ሃላፊው እንደሚሉት፤ በ2007 ይጠናቀቃል ተብሎ ከሚጠበቀው የባቡር መስመር በተጨማሪ የፈጣን አውቶቡስ አገልግሎት የሚጀምርበት ሁኔታ በጥናት ላይ ነው፡፡ ባቡሩ ሙሉ ለሙሉ ወደ አገልግሎት ሲገባ የከተማዋን 25 በመቶ የትራንስፖርት ችግር የሚያቃልል ሲሆን ሌላው በሚኒባስ፣ በአውቶቡስ እና በሌሎች አማራጮች የሚሸፈን ይሆናል፡፡ የባቡር ፕሮጀክቱ እስኪጠናቀቅ ግን በአጭር መፍትሔነት የተያዙ አማራጮች አሉ፡፡ አንደኛው በ2006 ዓ.ም የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት አገልግሎትን አጠናክሮ ማስቀጠል ነው፡፡ ለዚህም ሲባል 150 አዳዲስ የአንበሳ አውቶቡሶች በያዝነው አመት ወደ ዘርፉ እንዲቀላቀሉ የሚደረግ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 50 የሚሆኑት በሚቀጥለው ሣምንት ስራ ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአዲስ አበባ ለሚገኙ የመንግስት ሠራተኞች በስራ መግቢያና መውጫ ሰአት ሠርቪስ የሚሰጡ 410 የሚሆኑ አውቶቡሶች ለመግዛት ታስቧል የሚሉት አቶ ወጋየሁ፤ እነዚህ የአመቱ አጋማሽ ላይ ወደ ስራ የሚገቡ ከሆነ የመንግስት ሠራተኛውን ከማመላለስ ባሻገር ለህዝቡም በተመጣጣኝ ዋጋ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡
ህብረተሰቡ በስፋት ቅሬታ የሚያቀርብባቸው የሚኒባሶች አቆራርጦ መጫን፣ መስመር ላይ አለመገኘት እና ከታሪፍ በላይ ማስከፈል የመሳሰሉትን ለማስቀረትም በየክፍለ ከተማው የተለያዩ ኮማንድ ፖስቶችን በማቋቋም ጠንከር ያለ ቁጥጥር ለማድረግ መታሰቡን ሃላፊው ገልፀዋል፡፡
የችግሩ የመጨረሻ መፍትሔ፤ በየደረጃው የሚወሰዱ የማቃለያ የመፍትሔ እርምጃዎችን መጠባበቅ እና ሰፊ ተስፋ የተጣለባቸውን በአማካይ ሁለት አመት የሚፈጀውን የባቡር ፕሮጀክት ጨምሮ አዳዲስ መንገዶች እስኪጠናቀቁ መጠባበቅ መሆኑን ከሃላፊው ገለፃ መረዳት ይቻላል፡፡

Read 2702 times