Saturday, 12 October 2013 11:51

በአረብ አገራት፣ ኢትዮጵያውያን ቦንድ ለመግዛት እንደተገደዱ ገለፁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

            በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች እና በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ የኤምባሲና የቆንፅላ ፅ/ቤት አገልግሎቶችን ለማግኘት የሕዳሴ ግድብ ቦንድ እንድንገዛ እየተገደድን ነው አሉ፡፡ “ሁሉም ስደተኛ ተሰብስቦ ያሳለፈው ውሳኔ ስለሆነ የግድ ቦንድ መግዛት አለባችሁ” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ስደተኞቹ ተናግረዋል፡፡ በአባይ ወንዝ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የተስማማበት ፕሮጀክት እንደመሆኑ፣ እኛም ድጋፋችንን በተለያየ መንገድ በመስጠት ላይ ነን የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ የገንዘብ መዋጮውና የቦንድ ግዢው የግዴታ መሆኑን ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡

የቦንድ ግዢም ሆነ መዋጮ በዜጎች ፈቃደኝነት የሚፈፀም እንደሆነ መንግስት በተደጋጋሚ እየገለፀ መመሪያ ሲያስተላልፍ እንደነበር ያስታወሡት ቅሬታ አቅራቢዎች፣ ይሁን እንጂ በዱባይ እና በሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲዎች ወይም የቆንፅላ ፅ/ቤቶች ግን ፓስፖርት ለማሣደስና ሌሎች አገልግሎቶች ለማግኘት ስንሄድ፣ ቦንድ እንድንገዛ እንገደዳለን ብለዋል፡፡ ለ10 አመታት ከሚኖርበት ከሳዑዲ አረቢያ ባለፈው ሣምንት ለእረፍት ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን የሚናገረው ጀማል አረቦ ኢስማኤል፤ ቢያንስ በ500 ሪያል (ወደ 3ሺ ብር ገደማ) ቦንድ መግዛት አለብህ እንደተባለ ገልጿል፡፡ ቅሬታቸውን ለኤምባሲዎችና ለቆንስላ ፅ/ቤቶቹ አቅርበው እንደሆነ ተጠይቆ ጀማል ሲመልስ፤ ብዙ ስደተኞች በተደጋጋሚ ቅሬታቸውን ማቅረባቸውን ጠቅሶ፣ መፍትሄ ግን አልተሰጠንም ብሏል፡፡

“ቃል ስለገባችሁ በቃላችሁ መሠረት የቦንድ ግዢውን ፈፅሙ” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው አቶ ጀማል ገልጿል፡፡ የቦንድ ግዢ በእያንዳንዱ ሰው ፈቃደኝነትና ውሳኔ እንጂ፣ የተወሰኑ ሰዎች ተሰብስበው ወስነዋል ተብሎ በሁሉም ሰው ላይ ግዴት የሚጫን መሆን የለበትም ብሏል - ጀማል፡፡ “ስንቸገር ዞር ብሎ ያላየንና በችግራችን ጊዜ ያልደረሠልን ኤምባሲ፤ የዜጐችን የላብ ውጤት በአስገዳጅ ሁኔታ መቀማቱ ተገቢ አይደለም” የሚለው ጀማል፤ ሁሉም ነገር በፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት ይላል፡፡ በሳዑዲ አረቢያ ለ6 አመት የኖረው ሌላው ወጣት በበኩሉ፣ በርካቶች ለቦንድ ግዢ የሚጠየቁትን ክፍያ በመሸሽ ወደ ኤምባሲው አገልግሎት ለማግኘት መሄድ እንደማይፈልጉ ተናግሯል፡፡

“እያንዳንዱ ዜጋ ቦንድ ግዢውን በፍቃደኝነት ብቻ ነው የሚሣተፈው፤ በምንም ሁኔታ አይገደድም” የሚለውን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊን ቃል አስታውሶ፣ አሁን ግን ተግባራዊ እየተደረገ አይደለም ብሏል፡፡ በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ በዱባይ የምትኖር ሌላዋ አንዲት ወጣት፤ ፓስፖርት ለማሣደስ ወደ ቆንፃላ ፅ/ቤቱ ብታመራም 1000 ድርሃም ካልከፈልሽ አገልግሎት ማግኘት አትችይም መባሏን ገልፃለች። 500 ድርሃም ለቦንድ ግዢ ሲከፈል ቀሪው 500 ደግሞ ይህን ጉዳይ ለማስፈፀም ለተቋቋመው ኮሚቴ ተብሎ ይከፈላል የምትለው ኢትዮጵያዊቷ፤ ክፍያው ካልተፈፀመ ከማንኛውም የቆንስላ ፅ/ቤት አገልግሎት ማግኘት አይቻልም ብላለች፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ በስልክ አግኝተን ያነጋገርናቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሣደር ዲና ሙፍቲ፤ “ይሄ ስለመፈፀሙ የተጨበጠ መረጃ የለንም፣ ነገር ግን ማስገደድ ተቀባይነት የሌለውና ፈፅሞ የተከለከለ ነው፡፡ ተገቢ እንዳልሆነ ከዚህ በፊትም ተነግሯል” ብለዋል፡፡ አክለውም “ይሄ ድርጊት ተፈፀመብን የሚሉም ጥቆማውን ለመስሪያ ቤታችን ማሣወቅ ይችላሉ” ብለዋል፡፡

Read 1884 times