Saturday, 05 October 2013 11:09

የማራቶን ሪከርድ በኬንያዊ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

ድጋሚ ተሰበረ፤ ከ2 ሰዓት በታች ይሮጣል ክርክሩ ቀጥሏል

      ከሳምንት በፊት በተደረገው የበርሊን ማራቶን በ31 ዓመቱ ኬንያዊ አትሌት ዊልሰን ኪፕሳንግ የዓለም ማራቶን ሪከርድ ተሰበረ፡፡ አዲሱ የማራቶን ሪከርድ 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ23 ሰኮንዶች ነው፡፡ ዊልሰን ኪፕሳንግ የዓለም ማራቶን ክብረወሰን ያሻሻለው ከሁለት ዓመት በፊት በሌላው ኬንያዊ አትሌት ፓትሪክ ተመዝግቦ ከነበረው 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ38 ሰኮንዶች የሆነ ጊዜ በ15 ሰኮንዶች ፈጥኖ በመግባቱ ነው፡፡ አዲሱን የዓለም ማራቶን ሪከርድ ካስመዘገበ በኋላ እንደ ኃይሌ ገብረስለሴ ክብረወሰኑን በድጋሚ ለማሻሻል የምችል አይመስለኝም ያለው ዊልሰን ኪፕሳንግ፤ ከእንግዲህ ትኩረቱ በኦሎምፒክ እና በዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያዎችን ማግኘት እንደሆነ ተናግሯል፡፡ በበርሊን ማራቶን ለሁለት ጊዜያት የማራቶን ሪከርዶችን ያስመዘገበውና አራት ጊዜ ያሸነፈው ኃይሌ ገብረስላሴ ዘንድሮው ውድድሩን በማስጀመር ተሳታፊ ነበር፡፡ ዊልሰን ኪፕሳንግ አዲሱን የዓለም ማራቶን ሪከርድ ባስመዘገበ በማግስቱ በዓለም የአትሌቲክስ ማህበረሰብ እና መገናኛ ብዙሃናት ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ይገባል አይገባም የሚለው ክርክር በከፍተኛ ደረጃ አገርሽቷል፡፡

ባለፉት 15 ዓመታት የዓለም ማራቶን ሪከርድ በበርሊን ሲሰበር የዘንድሮው ለስምንተኛ ጊዜ ነው በመሮጫው ጎዳና አመቺነታቸው የበርሊንና ለንደን ማራቶኖች ከ2 ሰዓት በታች የሚገባዎች መወዳዳርባቸው እንደሆነ ይገለፃል፡፡ የአትሌቲክስ ባለሙያዎች እና እውቅ የማራቶን አትሌቶች በማራቶን ከ2 ሰዓት በታች የሚገባበትን ግዜ በአማካይ ከ20 እና ከ25 አመታት በኋላ የሚፈፀም ታሪክ መሆኑን እየገለፁ ቆይተዋል፡፡ ከሰሞኑ ግን በቅርብ አመታት የመሳካት እድል እንደሚኖረው ተዘግቧል፡፡ አዲሱን የዓለም ማራቶን ክብረወሰን የጨበጠው ኬንያዊ አትሌት ኪፕሳንግ የማራቶን ርቀትን ከ2 ሰዓት በታች መግባት እንደሚቻል ቢናገርም ለዚሁ ታሪካዊ ስኬት ራሱን በእጩነት ከማቅረብ ተቆጥቧል፡፡ ዘ ሳይንስ ኦፍ ስፖርት ከዓለም የማራቶን ፈጣን ሰዓቶች 80 በመቶው በሁለቱ የአፍሪካ አገራት ኬንያ እና ኢትዮጵያ በሚገኙ አትሌቶች የተመዘገበ መሆኑን በመጥቀስ ከ2 ሰዓት ሊገባ የሚችል አትሌትን የምናገኘው ከሁለቱ አገራት ነው በሚል ትንታኔ ሰርቷል፡፡

አሁን ካሉት የዓለማችን ታላላቅ የማራቶን ሯጮች ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ይገባሉ በሚል ከፍተኛ ግምት ባይሰጣቸውም የኬንያዎቹ ሞሰስ ሞሰፕ እና ኤልውድ ኪፕቾጌ፤ የኢትዮጵያዎቹ ቀነኒሳ በቀለ፣ አየለ አብሽሮ እና ፀጋዬ ከበደ እንዲሁም የእንግሊዙ ሞፋራህ በሚቀጥለው ዓመት አዲሱን የዊልሰን ኪፕሳንግ የማራቶን ክብረወሰን ለማሻሻል እንደሚችሉ እየተነገረላቸው ነው፡፡ ሞፋራህ በቀጣይ ዓመት ከትራክ ውድድር ወደ ማራቶን ሲሻገር ካሉት እቅዶች ዋንኛው ሪከርድ መስበር እንደሆነ ነው፡፡ የማራቶን ርቀትን ከ2 ሰዓት በታች ይገባል ቢልም እኔ አደርገዋለሁ ግን አላለም፡፡ ሞ ፋራህ ወደ ማራቶን ውድድር መግባቱን ለመደገፍ ታዋቂው የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ ናይኪ በዓይነቱ የተለየ የመሮጫ ጫማ እየሰራለት እንደሆነ ታውቋል፡፡ ከሞ ፋራህ አሰልጣኝ አልበርቶ ሳልዛር ጋር በተደረገ ትብብር የሚዘጋጀው የናይኪ የመሮጫ ጫማ ከማራቶን ሰዓት እስከ 2 ደቂቃዎች ሊያተርፍ እንደሚችል ጥናት የተሰራበት ነው፡፡

አንዳንድ የአትሌቲክስ ባለሙያዎች ግን በትራክ የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ውድድሮች የዓለም እና የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው ሞፋራህ በሁለቱ ርቀቶች ያሉት ፈጣን ሰዓቶች በኢትዮጵያዊው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከተያዙት ክብረወሰኖች በ15 ሰኮንዶች የዘገዩ መሆናቸውን በመግለፅ የእንግሊዛዊውን አትሌት ሪከርድ የመስበር እድል አጣጥለውታል፡፡ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ሞ ፋራህ ስኬታማ ከሆነበት የትራክ ውድድር ያለጥናት ወደ የማራቶን ውድድር ለመቀየር የገባውን ጥድፊያ ውጤታማ አያደርግህም ብሎታል፡፡ ከሞ ፋራህ ይልቅ የማራቶን ክብረወሰንን ለመስበር እድል ያለው ቀነኒሳ በቀለ እንደሆነም ዘገባዎች ጎን ለጎን ይመሰክራሉ፡፡ ከሳምንታት በፊት በቡፓ ግሬት ኖርዝ ራን አትሌቅ ቀነኒሳ በቀለ ሲያሸንፍ በመጨረሻዎቹ ሜትሮች ሞ ፋራህን ቀድሞ በመግባት ነበር፡፡ ይህ ውድድር ካለቀ በኋላ ሁለተኛ የወጣው ሞ ፋራህ “ለንደን እንገናኝ” ብሎ ቀነኒሳን ሲያናግረው “የሚጋብዙኝ ከሆነ ለመሳተፍ ዝግጁ ነኝ” ብሎ ምላሽ ሰጥቶታል፡፡ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በ2014 ወደ ማራቶን ሙሉ ለሙሉ ለመግባት እቅድ እንዳለው መናገሩ የሚታወስ ነው፡፡ በተለይ በ2016 በሪዮዲጄነሮ በሚካሄደው ኦሎምፒክ አገሩን በማራቶን ወክሎ በመወዳደር የወርቅ ሜዳልያ የማግኘት ሃሳብ እንዳለው ገልጿል፡፡ አሁን በዊልሰን ኪፕሳንግ 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ23 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ከተያዘው ሪከርድ ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት 204 ሰኮንዶች ይቀላሉ፡፡ ባለፉት አምስት አመታት ክብረወሰኖች በአማካይ 27 ሰኮንዶች ብቻ እየተሻሻሉ መቆየታቸው ታሪካዊውን ስኬት ለማግኘት እስከ 20 ዓመታት መጠበቁን ግድ ያደርገዋል፡፡ እንደስፖርት ሳይንቲስቶች ጥናት የሰው ልጅ የማራቶንን ርቀት ለመጨረስ በተፈጥሮ ብቃቱ ያለው የሰዓት ገደብ 1 ሰዓት ከ57 ደቂቃ ከ58 ሰኮንዶች ነው፡፡

Read 2886 times