Saturday, 05 October 2013 10:44

የብርሃን ስጦታ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

                ፖላንዳዊው ሚስተር ስታሽኬ በአገራቸው እጅግ የታወቁ ነጋዴ ናቸው፡፡ የፕላስቲክ ምርቶችን እያመረተ ለመላው አውሮፓ ገበያ የሚያቀርብ ግዙፍ ፋብሪካም ባለቤት ናቸው፡፡ በዚህ ግዙፍ ፋብሪካ እየተመረተ ለገበያ ከሚቀርበው የፕላስቲክ ምርቶች ከሚያገኙት ትርፍ በላይ ከፍተኛ ደስታና የህሊና እርካታ የሚሰጣቸው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በትራኮማና ካታራክት ሳቢያ የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ ሰዎች ብርሃናቸውን መልሰው እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡ ይህንን ተግባር ለመፈፀምም ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የአሁኑ አራተኛ ጊዜያቸው ነው፡፡ በዚህ የአራት ዙር ምልልስም በአማራ ክልል ላሊበላ፣ ደሴ፣ አለም ከተማና ዙሪያዎቹ፤ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ፍቼ ከተማ ውስጥ የሚኖሩና ከ660 በላይ የሚሆኑ የችግሩ ተጠቂዎች ከገጠማቸው የማየት ችግር ተላቀው የአይን ብርሃናቸው መልሰው አግኝተዋል፡፡

ሚ/ር ስታሽኬ፤ ይህንን የበጐ ፈቃድ ተግባር የሚያከናውኑት ጓደኞቻቸውን በማስተባበርና ዓላማውን ደግፈው በዘመቻ መልክ ለተግባር እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ነው፡፡ በሚ/ር ስታሽኬ ተነሳሽነትና በእሣቸው አስተባባሪነት የሚንቀሳቀሰው የህክምና ቡድን ሙሉ ወጪው የሚሸፈነው በእሣቸውና በጓደኞቻቸው ነው፡፡ ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊት ችግሩ ጐልቶ በሚታይባቸው አካባቢዎች የሚኖሩና ህክምናውን ለማግኘት በቂ ገንዘብ የሌላቸው ሰዎችን በጤና ጥበቃ በኩል እንዲመዘገቡ በማድረግ ህክምናውን ይሰጣል፡፡ በዚህ የበጐ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ተሳታፊ ለሚሆኑ የህክምና ባለሙያዎች ሊከፈል የሚገባው ክፍያ ሁሉ በእነ ሚ/ር ስታሽኬ የተከፈለ በመሆኑ ህመምተኛው አገልግሎቱን የሚያገኘው በነፃ ነው፡፡ ቡድኑ ከአይን ሞራ ገፈፋ ህክምና በተጨማሪ መድሃኒትና መነጽርም በመስጠት በዓይን ሞራ ግርዶሽ ሳቢያ ብርሃናቸውን ያጡ ሰዎች መልሰው ለማየት እንዲችሉ ያደርጋል፡፡ ቡድኑ ከመስከረም 20 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ በፍቼ ከተማ ውስጥ ይህንኑ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቶ ከትናንት በስቲያ ሥራውን በማጠናቀቅ ወደ አገሩ ተመልሷል፡፡ በዚህ ዙር ከ80 በላይ የችግሩ ሰለባዎች ከችግራቸው ተላቀው የዓይን ብርሃናቸውን መልሰው እንዲያገኙ አድርገዋል፡፡ በቀጣይም በሌሎች የአገሪቱ ክልሎች ይህንኑ አገልግሎት እንደሚሰጡም ታውቋል፡፡

Read 1954 times