Print this page
Saturday, 05 October 2013 10:34

ኢትዮጵያዊው ምሁር በሩሲያ ፕሮፌሰር ዘነበ ክንፉ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

“በህይወት እስካለህ ደግ መስራት ጥሩ ነው”
በሆለታ ተወልደው ያደጉት አቶ ዘነበ ክንፉ ታፈሰ፣ ለትምህርት ወደ ራሽያ የሄዱት የዛሬ 22 ዓመት ገደማ ነው፡፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ የፅሁፍ ፍቅር ነበራቸው፡፡ ነፃ የትምህርት እድል አግኝተው ወደ ሩሲያ የሄዱትም ኢንተርናሽናል ጆርናሊዝም
(ዓለም አቀፍ ጋዜጠኝነት) ለመማር ነበር፡፡
ትምህርታቸውን እስከ ዶክትሬት ደረጃ የተማሩት ፕሮፌሰር ዘነበ፤ በራሽያ ዩኒቨርስቲ ውስጥ እያስተማሩ ይገኛሉ፡፡ “ቢዝነስ አፍሪካ” የተሰኘ መፅሄት መስራችና ባለቤትም ናቸው፡፡ ጋዜጠኛ ግሩም ሠይፉ ለ14ኛው የዓለም ኦሎምፒክ ሻምፒዮን ሩሲያ በሄደ ጊዜ በሞስኮ ከተማ አግኝቶ አነጋግሯቸዋል፡፡ ስለሆለታ ትዝታቸው፣ ስለ ፅሁፍ ፍቅራቸው፣ ስለትምህርታቸውና ሙያቸው በስፋት አውግተዋል፡፡ እነሆ፡-


ጋዜጠኝነትን የተማሩት ራሽያ ቢሆንም ለጋዜጣ መፃፍ የጀመሩት ሆለታ እያሉ ነበር ሲባል ሰምቻለሁ…
እውነት ነው፡፡ ገና ታዳጊ ሳለሁ ጀምሮ እፅፍ ነበር፡፡ ስልክ አምባ እና ዜኒት የሚሉ የብዕር ስሞች ነበሩኝ፡፡ በእነዚህ ስሞች ፅሁፎቼን ለተለያዩ ጋዜጦችና የሬድዮ ፕሮግራሞች እልክ ነበር፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ፅሁፍ የወጣልኝ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ነው፡፡ በኋላ ለሬድዮ ፕሮግራሞችና ለ“ሰርቶ አደር” ጋዜጣ ሁሉ መፃፍ ጀመርኩ፡፡ ፅሁፎቼ በማህበራዊ ችግሮች ዙርያ የሚያተኩሩ ነበሩ። አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የወጣውን የመጀመሪያ ፅሁፌን አራተኛ ክፍል ሆኜ ነው የፃፍኩት፡፡
ስለ እድገትዎ ይንገሩኝ…
የተወለድኩትና ያደግሁት ከአዲስ አበባ ወጣ ብላ በምትገኘው ሆለታ ከተማ ነው፡፡ በ1968 አካባቢ በከተማዋ ድርቅ ተከሰተ፡፡ የከተማው ነዋሪ ውሃ ፍለጋ አራትና አምስት ኪሎ ሜትር ይጓዝ ነበር፡፡ እኔም ከእናቴ ጋር ሄጄ ይህን ችግር አየሁ፡፡ የፃፍኩት ነገር … ለምንድነው ባለስልጣኖች የውሃ ጉድጓድ የማያስቆፍሩት የሚል ሃሳብ ይዟል፡፡ በጣም አጭር ፅሁፍ ነው፡፡ ግማሽ ገፅም አይሆንም፡፡ “የውሃ እጥረትን ለመፍታት የአካባቢው አስተዳደር መንቀሳቀስ አለበት” በሚል ነው የሚቋጨው፡፡ ፅሁፉን በጋዜጣው አድራሻ በፖስታ ቤት ላክሁት፡፡ ብዙም ሳይቆይ ነበር ጋዜጣው ላይ የወጣው፡፡
ከቤታችን ደጃፍ አንድ ባለሱቅ ነበር፡፡ መሃመድ ነው ስሙ፡፡ ስኳር ለመግዛት ወደሱ ሱቅ ስሄድ “ያንተ ስም ነው እንዴ እዚህ ጋዜጣ ላይ የወጣው?” ብሎ አሳየኝ፡፡ ለማንም እንዳትናገር ብሎ ፅሁፌ ያለበትን የጋዜጣውን ገፅ በ10 ሳንቲም ሸጠልኝ፡፡ አየህ የሆለታ እርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት ከቤታችን አቅራቢያ ነበር፡፡ በዚያ አትክልት በሚያፈሉበት ስፍራ የውሃ ጉድጓድ ቆፍረው ውሃ በማውጣት ይጠቀሙ ነበር። እዚያ ግቢ ውስጥ ውሃ አለ፡፡ እናቴ እና የከተማው ህዝብ ግን ረጅም ርቀት እየተጓዙ ውሃ ይቀዱ ነበር። የሚገርምህ ፅሁፉ ወጥቶ ብዙም ሳይቆይ ለሆለታ ከተማ ነዋሪ ውሃ ለማሰራጨት የጉድጓድ ቁፋሮ እንዲሰራ ባለስልጣኖች አዘዙ፡፡ ጉድጓድ ተቆፍሮ ውሃ ከወጣ በኋላ፣ ባንቧ ተሰርቶ ከተማው መሃል ውሃ ተገኘ፡፡ እኔም በዚሁ የውሃ ጉድጓድ፣ ውሃ ሻጭ ሆኜ መስራት ቻልኩ፡፡
ከልጅነትዎ አንስቶ ፀሐፊ የመሆን ፍላጐት ያሳደረብዎ ምንድነው?
እንደነገርኩህ ያኔ ገና አራተኛ ክፍል ብሆንም ብዙ አነብ ነበር፡፡ እቤታችን የተለያዩ ጋዜጦች ይመጣሉ፡፡ ጀርመናውያን ጐረቤቶች ስለነበሩን የእንግሊዝኛ ህትመቶችንም የማንበብ ዕድል ነበረኝ፡፡ የስነፅሁፍ ዝንባሌዬ ከፍተኛ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ በአንድ ምሽት ባለ16 ገፅ ደብተር ሙሉ ግጥም ፅፌ ለአማርኛ አስተማሪያችን አሳየኋት፡፡ “ይሄ ግጥም የሚሆን አይደለም” ብላ አሳፈረችኝ። ግጥሙ ስለ ምን እንደሆነ ትዝ አይለኝም፡፡ የሆኖ ሆኖ ግጥሙን ትቼ ጋዜጠኛ ለመሆን አስብ ጀመር። ያኔ በጣም ከምወዳቸው ጋዜጦች አንዱ “ፖሊስ እና ርምጃው” ነበር፡፡ በጣም ቆንጆ ጋዜጣ ነው፡፡ አብዮት የተጀመረበት ጊዜ ስለነበር ብዙ ጋዜጦች እና መፅሄቶች ይወጡ ነበር፡፡ ሆለታ ከተማ ውስጥ የእጩ መኮንኖች ማሰልጠኛ፣ የእርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት እና ሌሎችም ተቋማት ነበሩ፡፡ በርካታ የውጭ አገር ዜጎችም ነበሩ፡፡ በዚህ ምክንያት ለመረጃ ቅርብ ነበርን፡፡ አባቴም አልፎ አልፎ ጋዜጦችን፣ መፅሃፍት እና መፅሄቶችን ያመጣልኛል። ሬድዮ እከታተላለሁ። ከተፈጥሮ ተሰጥኦዬ ጋር ይህ ሁሉ ሲጨመር ፀሃፊ ለመሆን ያነሳሳኝ ይመስለኛል፡፡
በወጣትነት ዘመንዎ ሆለታ ምን ትመስል ነበር?
የሆለታ ህዝብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ነው። ልዩነቱ ሁሉም አይነት ብሄረሰብ የተሰባሰቡባት ከተማ መሆኗ ነው፡፡ ቅድም እንደነገርኩህ ሆለታ የእጩ መኮንኖች ማሰልጠኛ፣ የእርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት፤ የመሳሪያ ግምጃ ቤት፤ የሙሉጌታ ቡሊ ቴክኒክ ትምህርት ቤት፤ የሱባ ደን ልማት፣ የወተት ሃብት ልማት… እነዚህ ሁሉ የመንግስት ድርጅቶች ነበሩባት፡፡ በኋላም እነ ሙገር በሆለታ መንገድ ላይ ተሰርተዋል፡፡ በእነዚህ የመንግስት ተቋማት ይሰሩ የነበሩት ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተሰባሰቡ ናቸው፡፡ ኦሮሞው፣ አማራው፣ ትግሬው… ሁሉም ብሄር ብሄረሰብ ነበር፡፡ አትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ የተለያዩ አገራት የውጭ ዜጎች እንዲሁም በርካታ አፍሪካውያን ነበሩ፡፡
ስራ የጀመርኩት እዚያው ሆለታ ውስጥ ነው፡፡ የመጀመሪያው ስራዬ የተለያዩ ሸቀጦችን መነገድ ነበር፡፡ 9ኛ ክፍል ሆኜ ነው የጀመርኩት። ለወታደሮችም እላላክ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ውትድርና ገባሁና ለአራት አመታት በአየር ወለድነት ሰለጠንኩ፡፡ በሰሜን እና በሰሜን ምዕራብ ዘምቼ፣ ብዙ ግዳጆችን ፈፅሜአለሁ፡፡ በውትድርና ዘመኔም መፃፉን አልተውኩትም፡፡ የሚገርምህ አንጋፋው ደራሲ በዓሉ ግርማ አለቃዬ ነበር። አስመራ ለሰራዊቱ በሚዘጋጅ “የጀግናው ገድል” የተባለ ጋዜጣ ላይ ፊደል ለቀማ (Proof reading) ስሰራ ማለቴ ነው። ያኔ እንግዲህ 19 አመቴ ነበር፡፡ በሰራዊቱ አባልነቴ ጋዜጣ በማቋቋምና የኪነት ቡድን በመመስረት ፈርቀዳጅ ሚና ተጫውቻለሁ፡፡ የኢትዮጵያ አየር ወለድ በኃይለስላሴ ጊዜ ፈርሶ በደርግ ዘመን በድጋሚ በሁርሶ ተቋቋመ፡፡ ከውትድርና የወጣሁት ወሎ አካባቢ በፓራሹት ስወርድ (ዝናብ ስለነበር) ወድቄ በመጐዳቴ ነው፡፡
ከውትድርና ወጥተው የት ገቡ?
ደቡብ ውስጥ ድርቅ ስለነበር በሻሸመኔ መልሶ ማቋቋም ተቋም ውስጥ ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩ። አሁንም መፃፌን አልተውኩም፡፡ ባለኝ ትርፍ ጊዜ ሁሉ እየፃፍኩ በተለያዩ ህትመቶች ላይ ይወጣልኝ ነበር፡፡ በሬድዮም ይነበቡልኛል፡፡ የምፅፋቸው በአብዛኛው ትችቶች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ “የባህር ዛፍ አጨዳ እና ሽያጭ” በሚል መሃል ሸዋ አካባቢ የሚካሄደውን የደን ጭፍጨፋ የሚመለከት መጣጥፍ ፅፌ ነበር፡፡ የባህር ዛፍ ጭፍጨፋው አደገኛ ችግሮች እንደሚያመጣ፤ የድርቅም ምክንያት እንደሆነ በመግለፅ የፃፍኩት ፅሁፍ፤ በ“ሰርቶ አደር” ጋዜጣ ላይ እንደታተመልኝ ትዝ ይለኛል፡፡
እንዴት ነው በራሽያ ነፃ የትምህርት እድል ያገኙት?
በሁለተኛ ደረጃ ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና 3.4 አመጣሁ፡፡ ውጭ ሄጄ መማር አለብኝ ብዬ አስብ ነበር፡፡ አሁን እንዴት እንደሆነ ባላውቅም ድሮ ስኮላርሺፕ የሚሰጡ አገራት ምርጫ ይቀርብልሃል። በውድድር ነው፡፡ የሦስት አገራት ምርጫ ተሰጠኝ። ከልጅነቴ ጀምሮ የምመኘውን የጋዜጠኝነት ሙያ ለመማር መረጥኩ፡፡ ለኢንተርናሽናል ጆርናሊዚም ነፃ የትምህርት እድል የነበራቸው አገራት ደግሞ ራሽያ፣ ቻይናና ሃንጋሪ ነበሩ፡፡ ሶስቱንም ሞላሁ፡፡ በመጀመርያ ቻይና ደረሰኝ፡፡ ሳይታሰብ ግን በዚያ አገር ብጥብጥ ተነሳ፡፡ ቻይናን የመረጥኩት ትልቅ አገር ነች በሚል ነበር፡፡ ከዚያ ራሽያ ደረሰኝና ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ለፈተና ተቀመጥን፡፡ ፓትሪስ ሉምቡባ ዩኒቨርስቲ ነበር የተመደብነው፡፡ ሰባ ተማሪዎች ተወዳድረን ሁለት ልጆች ፈተናውን በማለፍ እድሉን አገኘን፡፡
ከ22 ዓመታት በፊት ሞስኮ ሲገቡ የአገሪቱ ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?
ገና አብዮቱ ባይጀመርም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የለውጥ ንቅናቄዎች እየተስተዋሉ ነበር፡፡ ፕሮስትሬይካና ግላሽኖስት (ግልፅነትና ተጠያቂነት) …የጎርባቾቭ የተሃድሶ እቅድ ተጀምሯል፡፡ ትርምሱ ታዲያ ለጋዜጠኛ ሰርግና ምላሽ ነበር፡፡ እኛ በወቅቱ ቋንቋ እየተማርን ቢሆንም እዚያው በገዛሁት ካሜራ ግርግሮችን ፎቶ እያነሳሁ እሰበስብ ጀመር፡፡ በኋላም ቪድዮ ካሜራ ገዝቼ በከተማዋ የሚታዩ የለውጥ ንቅናቄዎችን እቀርጽ ነበር፡፡ ይሄን የማደርገው ለሚዲያ ለመዘገብ ሳይሆን የራሴን የጋዜጠኝነት ስሜት ለማርካትና መረጃ መሰብሰብ ስለምወድ ነው፡፡ እንደስራ ልምምድም መሆኑ ነው፡፡ በኋላ ላይ “ሞስኮ ታይምስ” ለተባለ ጋዜጣ ሁላችንም መስራት ጀመርን፡፡ በነፃ ሳይሆን እየተከፈለን፡፡ ሞስኮ ውስጥ በአማርኛ ቋንቋ የሚሰራጭ ሬድዮ ጣቢያ ስለነበር እዚያም እሰራ ነበር፡፡ ዜና ማንበብ፤ ደብዳቤዎችን አንብቦ ምላሽ መስጠት ነበር ስራዬ፡፡ በ“ሞስኮ ታይምስ” ጋዜጣ ላይ ደግሞ በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ እፅፍ ነበር፡፡ የመጀመርያው ፅሁፌ ትዝ ይለኛል፡፡ የአፍሪካ ችግሮች ላይ የሚያተኩር ነበር፡፡ ከዚያም ኢትዮጵያን ማስተዋወቅ ጀመርኩ… ስለ ኢትዮጵያ በዓላትና፤ ስለ ባህል ብዙ ፅፌአለሁ፡፡ አብዛኞቹን በራሽያ ቋንቋ የፃፍኳቸው ቢሆንም በእንግሊዝኛም እየፃፍን ክፍያ እናገኝ ነበር፡፡
የትምህርቱስ ነገር?
ኢንተርናሽናል ጆርናሊዝም ለአምስት አመት ተምሬ በባችለር ዲግሪ ተመርቄአለሁ፡፡ ለዲግሪ ማሟያ የፃፍኩት የጥናት ወረቀት በኢትዮጵያ ፕሬስ አጀማመር እና ህጎች ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ በአጠቃላይ የሶሻል ሳይንስ ባለሙያ ነኝ፡፡ ማስትሬቴን በራሽያ ታሪክ፣ ፒኤችዲዬን ደግሞ በዓለም አቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ላይ ነው የሠራሁት፡፡ በኢንተርናሽናል ፊልም ሁለተኛ ማስትሬት ዲግሪም አግኝቻለሁ፡፡
መቼ ነው የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያገኙት?
በ2001 እ.ኤ.አ ላይ ነው ሙሉ ፕሮፌሰር የሆንኩት፡፡ በዋናነት የማስተምረው በራሽያ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ዓለምአቀፍ ጋዜጠኝነትና በአገራት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዎች ውስጥ እንዴት መስራት እንደሚቻል አስተምራለሁ፡፡ በተለያዩ አገራት እየተጋበዝኩም ሌክቸር እሰጣለሁ፡፡ በአጠቃላይ በ59 የዓለም አገራት ተዟዙሬ ሠርቼአለሁ፡፡ በባንግላዲሽ መገናኛ ብዙሐን ላይ አንድ መጽሐፍ አሳትሜያለሁ፡፡ አምና “የአፍሪካና የአረብ አብዮት” በሚል ርዕስ ሌላ መፅሃፍ ፅፌአለሁ፡፡ ባለፉት 5 ዓመታት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ችግሮች ላይ ያተኮሩ፣ ከተለያዩ ምሁራን ጋር በትብብር የተዘጋጁ ከ49 በላይ መጽሐፍትና የጥናት ፅሁፎች ለህትመት በቅተውልኛል፡፡
“ቢዝነስ አፍሪካ” የተባለ መጽሔት እንደሚያሳትሙ ሰምቻለሁ፡፡ ስለዚህ ዓለም አቀፍ መፅሄት ይንገሩኝ…
መጽሔቱ የፖለቲካ ነው፡፡ በሦስት ቋንቋ ነው የምንጽፈው፡፡ በዋናነት የቻይና-አፍሪካንና የራሽያ-አፍሪካን ግንኙነትን ይዳሰሳል፡፡ ከፍተኛ አንባቢ ያለው ድረገጽም አለው፡፡ ለመጽሔቱ ቃለምልልስ የምናደርገው ከትላልቅ ኩባንያ ዳሬክተሮች፣ ሚኒስትሮች፣ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሃላፊዎች ጋር ነው፡፡ የመጽሔቱ ስርጭት ብዙ ባይሆንም በሞስኮ፣ በኬፕታውንና በሻንጋይ ከተሞች ለገበያ ይቀርባል፡፡ ከተመሠረተ 4 ዓመት ሆኖታል፡፡ እኔ በፕሬዚዳንትነት እየመራሁት ነው። በዓለም ዙሪያ እየከፈልናቸው የሚሰሩልን ከ200 በላይ ጋዜጠኞች አሉን፡፡ በራሽያ፣ በቻይና እና በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ለሚገኙ ኩባንያዎች የኢኮኖሚ ትንታኔዎችን እንሠራለን፡፡
በኢትዮጵያ እየተሰሩ ስላሉት የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ምን ይላሉ?
ኢትዮጵያ በዓለም በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ከሚገኙ አገራት አንዷ መሆኗ እውነት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ስትመለከተው ግዙፍ የመሠረተ ልማት እንቅስቃሴዎች መኖራቸው ተገቢ ነው፡፡ በቂ ነው ለማለት ግን አልደፍርም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት እኮ ከፍተኛ ነው፡፡ እስከ 100 ሚሊዮን መድረሱ አይቀርም፡፡ ከዚህ የህዝብ ብዛት አንጻር በብዙ ነገሮች ገና ነን፡፡ በቂ አይደሉም፡፡
የህይወት ፍልስፍናዎ ምንድነው?
ትልቁ ነገር ደግነት ነው፡፡ የተቸገረውን መርዳት፣ የወደቀውን ማንሳት፣ የሞተውን መቅበር። በህይወት እስካለህ ድረስ ደግ መስራት ጥሩ ነው፡፡ እውቀት ያለው እውቀቱን፣ ገንዘብ ያለው ገንዘቡን፣ ጉልበት ያለው ጉልበቱን ለሌላው ማካፈል አለበት። ኢትዮጵያ ከዓለም ሁሉ የምትለየው በዚህ ነው፡፡
ወደ አገር ቤት የመመለስ ሃሳብ አለዎት?
ከአገር ቤት ከጠፋሁ 5 ዓመት ሆኖኛል፡፡ ጊዜ አልነበረኝም፡፡ በተለያዩ የራሽያ ጐረቤት አገሮች ብዙ ስራዎች ነበሩኝ፡፡ በሞስኮ ስኖር ከአገሬ ውጭ እንደሆንኩ አልቆጥረውም፡፡ ሁልጊዜ ከአገር ቤት እንግዶች ይመጣሉ፡፡ ከኤምባሲው ጋር የኢትዮጵያን ጉዳዮች አብረን ነው የምንሰራው፡፡ ለ12 ዓመታት በሞስኮ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ፕሬዝዳንት በመሆን አገለግያለሁ፡፡ አሁን ደግሞ በሞስኮ ውስጥ የአፍሪካ ማህበረሰብ እየሰራሁ ነው፡፡

Read 4842 times
Administrator

Latest from Administrator